[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ዘመዳቸው ቢሮአቸው ሄዶ እያነጋገሩት ነው]
- አንተ ከየት ተገኘህ እባክህ?
- አለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ዛሬ ምን እግር ጣለህ?
- አንድ አሳሳቢ ጉዳይ አለ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ማለትህን ትተህ ጉዳዩን ንገረኝ፡፡
- ምን መሰለህ ጋሼ?
- ምንድነው እሱ?
- የእነዚህ ሁለት ልጆችህ ጉዳይ አሳስቦኛል፡፡
- እነሱ ደግሞ ምን ሆኑ?
- ኧረ ጋሼ በጊዜ መላ መፈለግ አለብህ፡፡
- ምን ሆነዋል?
- ወንዱ ልጅ ለይቶለታል ጋሼ፡፡
- ምንድነው የምትለው?
- እኔ ነኝ ያለ ኢንቨስተር እንኳን እንደሱ አይደለም፡፡
- ኢንቨስተር?
- አዎ ጋሼ፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- በየቀኑ የሚመነዝረው ገንዘብ ያስደነግጣል፡፡
- ምን?
- ረብጣ ተሸክሞ እኮ ነው የሚዞረው ጋሼ፡፡
- እና?
- እኔ ነኝ ያለ አፓርታማ ከጓደኞቹ ጋር ተከራይቶ. . .
- እሺ እባክህ?
- ጋሼ ጫት ትላለህ፣ ሺሻ ትላለህ፣ መጠጥ. . .
- አንተ ሰው አብደሃል?
- ኧረ ጤነኛ ነኝ ጋሼ፡፡
- እሺ?
- ሲመሽ ደግሞ ከኮረዶች ጋር የከተማዋን ክለቦች ይቀውጣል ጋሼ፡፡
- ኧረ ዝም ብለህ አታውራ፡፡
- ጋሼ አሉባልታ ላወራ አይደለም የመጣሁት፡፡
- በል ቀጥል፡፡
- ልጁ በዚህ ከቀጠለ. . .
- ምን?
- ጣጣ ውስጥ ይከትሃል፡፡
- ለዚህም ደርሶ?
- ምን ይኼ ብቻ ጋሼ?
- ሌላ ምን?
- ያገኘውን ሁሉ ማንጓጠጥ፣ መሳደብ፣ መደባደብ፣. . .
- ኧረ አንተ ሰውዬ በፈጠረህ?
- ጋሼ እህ ብለህ ስማኝ፡፡
- እንዴት ነው የምሰማህ?
- ይኼ ልጅ የአንተን ስም እየጠራ ሰዎች ያስፈራራል ጋሼ፡፡
- ምን እያለ እባክህ?
- አሳያችኋለሁ እያለ ነዋ፡፡
- ምንድነው የሚያሳየው?
- የአንተን ሥልጣን ይሆናላ ጋሼ፡፡
- ከዚህ ሌላስ?
- ሌላማ እያስፈራራ ከሰዎች ገንዘብ ይቀበላል ጋሼ?
- ከማን?
- አንተ ዘንድ ጉዳይ ካላቸው ጋሼ፡፡
- ሌላስ?
- ድራግ ይጠቀማል ጋሼ፡፡
- ምን?
- እሱን ሲወስድማ ዕብደቱ ይነሳል ጋሼ፡፡
- እንዴት ያደርገዋል እባክህ?
- ላዩ ላይ ልብሱን ይቀዳድዳል ጋሼ፡፡
- እንዴ?
- ጓደኞቹ ላይ ጠርሙስ ቮድካ ወይም ውስኪ እያንቆረቆረ እየፈሰሰ በሺዎች የሚቆጠሩ ብሮችን መክፈል ልማዱ ነው ጋሼ፡፡
- ወይ ጉድ?
- ለመናገር የሚያዳግቱ በርካታ ነገሮችን ይፈጽማል፡፡
- ይህንን ሁሉ ጉድ እንዴት አልሰማሁም?
- ሰዎች እየፈሩህ እንዴት ይንገሩህ ጋሼ?
- ልጅህን ተቆጣ ማለት ምን ያስፈራል?
- ወይ ጋሼ?
- ምነው?
- ሰዎች እኮ ባለሥልጣናትን አያምኑም ጋሼ፡፡
- ለምን?
- ጥቃት ይደርስብናል ብለው ይፈራሉ ጋሼ፡፡
- አንተ ይህንን ሁሉ ጉድ እንዴት አወቅክ?
- አንድ የተማረረ ጓደኛዬ ነግሮኝ ስከታተል ነው የቆየሁት፡፡
- የሴቷስ ጉድ ምን ይሆን?
- የእሷ ችግር መጠጥ ነው ጋሼ፡፡
- ትጠጣለች እያልከኝ ነው?
- ዶልፊን በላት ጋሼ፡፡
- ምን ማለት ነው?
- ታንቆረቁረዋለች ጋሼ፡፡
- ለመሆኑ ምንድነው የምትጠጣው?
- ምን ይተርፋታል ጋሼ?
- ምን ማለት ነው?
- ጋሼ ከድራፍት እስከ ኮኛክ ምንም አይተርፋትም፡፡
- ይኼንን ሁሉ እንዴት ትችለዋለች?
- እሷ እኮ ቅጽል ስም ወጥቶላታል ጋሼ?
- ማን አሏት እባክህ?
- ስፖንጅ ይሏታል ጋሼ፡፡
- ለምን ስፖንጅ አሏት?
- ምጥጥ ነዋ የምታደርገው፡፡
- ወይ ጣጣ?
- ጋሼ?
- አቤት?
- ይኼ ሁሉ የአንተ ጥፋት ነው፡፡
- ለምን እንዲህ አልክ?
- ልጆቹን ከአቅማቸው በላይ ገንዘብ እያሸከምክ ነዋ ጋሼ፡፡
- ችግሩ እሱ ነው ብለህ ነው?
- ይኼ ችግር እኮ በአገር ላይ ጦስ አለው ጋሼ፡፡
- ምን ዓይነት ጦስ?
- አንዳንድ ባለሥልጣናትና ሀብታሞች ልጆቻችሁን ገንዘብ ካቅማቸው በላይ እየሰጣችሁ እኮ ሕዝቡ. . .
- ሕዝቡ ደግሞ ምን ሆነ?
- በዋጋ ግሽበት እየተመታ ነው ጋሼ?
- ይኼ ደግሞ ምን የሚሉት ወሬ ነው?
- ምንጩ የማይታወቅ ገንዘብ ገበያውን እየወረረ ሕዝብ እያደኸየ ነው ማለት ነው!
[ክቡር ሚኒስትሩ በፍጥነት ሚስታቸው ዘንድ ደወሉ]
- የት ነው ያለሽው?
- ከጓደኞቼ ጋር ፉት እያልን ነው፡፡
- ምን አለብሽ አንቺ?
- ምን ሆኑ ደግሞ ክቡር ሚኒስትር!
- የልጆቹን መባለግ ታውቂ ነበር?
- ምን አልከኝ?
- እነዚህ ሁለት ልጆች ምን እንደሚሠሩ ታውቂያለሽ?
- ትልቁ ዩኒቨርሲቲ ይማራል፣ ትንሿ ደግሞ ሃይስኩል ናት፡፡
- እሱን አልጠየቅኩሽም፡፡
- ታዲያ ምንድነው የምትለው?
- ልጆቹ ሐሺሽና መጠጥ እንደሚያዘወትሩ ታውቂያለሽ? ወይስ አታውቂም?
- አንተ ያምሃል እንዴ?
- እኔ ጤነኛ ነኝ መልሽልኝ፡፡
- እኔ የማውቀው ተማሪ መሆናቸውን ብቻ ነው፡፡
- የምትደብቂው ነገር እንዳለ ይታወቀኛል፡፡
- አይ አንተ?
- ምነው?
- ወሬ እየሰማህ ጭንቅላትህን ትበጠብጣለህ አይደል?
- አንቺ የምታውቂው እንዳለ አሁን ገባኝ፡፡
- ምኑ ነው የገባህ?
- ልጆቹ መበላሸታቸውን ነዋ፡፡
- ኧረ ይኼንን ወሬ ተወኝ ክቡር ሚኒስትር?
- እኔማ አልተውም ገባሽ?
- ብትተወው ይሻልሃል፡፡
- ለምን?
- ይኼ እኮ. . .
- ምን አልሽ?
- የምቀኛ ወሬ ነው፡፡
- ምን?
- የጠላት ወሬ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ተጠራጥረው አንድ የቀድሞ ጓደኛቸው ዘንድ ደወሉ]
- አንድ ጉዳይ ላማክርህ ነበር?
- ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
- ልጆቼን ታውቃቸው የለ?
- ድሮማ አውቃቸው ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አሁንስ?
- አሁንማ ሥልጣንም ሀብቱም ለያይቶናል፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- የዘንድሮ ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች ልጆች ጉዳይ ተከድኖ ይብሰል፡፡
- እንዴት ነው ሁሉንም አጠቃለህ እንዲህ የምትለው እባክህ?
- በእርግጥ ሁሉንም አይመለከትም፣ አሁን ግን በዛ. . .
- ምኑ ነው የበዛው?
- ጥጋቡ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ሆነሃል?
- እርስዎ ምን ሆነዋል?
- አንተ ንገረኛ?
- ይሰማሉ ክቡር ሚኒስትር?
- አዎ እሰማለሁ፡፡
- ልጆችዎን ቶሎ ከገቡበት ማጥ ውስጥ ያውጡ፡፡
- ለምን እንዲህ አልክ?
- እንደ ዓይን ጠፍተዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምሳሌ?
- ወንዱ ልጅዎ የከተማው ዋና ጥጋበኛ ከመሆኑ የተነሳ ሰው ሁሉ ይፈራዋል፡፡
- ምን?
- ሰው ፊት ላይ መጠጥ ይደፋል. . .
- እ?
- ጠርሙስ ወርውሮ ይፈናከታል. . .
- እንዴ?
- አንዳንዴማ ጩቤ ይመዛል. . .
- ምን አልክ?
- አንድ ቀን የምፈራው. . .
- እ?
- የእርስዎን ሽጉጥ. . .
- ሽጉጤን ምን?
- ተኩሶ ሰው እንዳይፈጅ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይኼን ያህል?
- በዚህ ተግባሩ እኮ ቅጽል ስም ወጥቶለታል?
- ማን አሉት እባክህ?
- እንደልቡ፡፡
- ሴቷስ?
- እሷ እኮ ጉበቷ ጤነኛ መሆኑን እጠራጠራለሁ፡፡
- በምን ምክንያት?
- አጠጣጧ አደገኛ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ዓይነት አጠጣጥ?
- አጥፍቶ መጥፋት ይሉታል!
- ምንድነው የምትለው?
- ሱሳይድ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮአቸው ውስጥ ተክዘው እንደተቀመጡ አማካሪያቸው ገባ]
- ክቡር ሚኒስትር ምን ሆነዋል?
- ምንም፡፡
- የሆኑት ነገርማ አለ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አንድ ነገር ልጠይቅህ?
- እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስለባለሥልጣናትና ባለሀብቶች ልጆች የሚወራው እውነት ነው?
- የሁሉም ባይሆንም የአንዳንዶቹ ያስፈራል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እስኪ ንገረኝ?
- ከየት ልጅምር ክቡር ሚኒስትር?
- ከፈለግከው፡፡
- ቁጥጥር የማይደረግባቸው ልጆች በዝተዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ልጆቹ ምን ያደርጋሉ?
- አንደኛ ካቅማቸው በላይ ገንዘብ ይይዛሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ማለት ነው?
- ከዕድሜያቸው ጋር የማይመጣጠን ገንዘብ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እሺ?
- ሁለተኛ ገንዘቡን ዝም ብለው ይበትኑታል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ማለት?
- የተጠየቁትን ያለክርክር ስለሚከፍሉ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እሺ?
- ሦስተኛ ከመጠጥ እስከ ድራግ ሰፍረውበታል፡፡
- ሌላስ?
- በዚህ ላይ ነውጠኛ ናቸው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይኼ ሁሉ ችግር ይመለከተኝ ይሆን?
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ምነው?
- የእርስዎ ስም ከእንትኑ ቀጥሎ በልጆችዎ አይደል እንዴ የሚነሳው ክቡር ሚኒስትር?
- ከምኑ ቀጥሎ?
- ያውቁታል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምኑን ነው የማውቀው እባክህ?
- ሙስናውን ነዋ!