የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች ሲያካሂድ የቆየውን የመሬት ኦዲት አጠናቀቀ፡፡ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የኦዲት ግኝቱ በቅርቡ ለሕዝቡ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡
በኦዲት ግኝቱ መነሻነት ታግደው የቆዩ የመሬት ዘርፍ አገልግሎቶች ከመስከረም 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲጀመሩ፣ ምክትል ከንቲባው ለክፍላተ ከተሞች ሥራ አስፈጻሚዎች መመርያ ሰጥተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሪፎርም ያስፈልጋቸዋል ካላቸው ዘርፎች መካከል መሬትና መሬት ነክ ዘርፍ ግንባር ቀደሙ ነው፡፡
በዚህ መሠረት ቀደም ሲል ለኢንቨስተሮች በተለይም ለሪል ስቴት፣ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ፣ ለመኖሪያ ቤት፣ ለንግድ ሕንፃዎች ግንባታ በሊዝ ጨረታና በድርድር የተሰጡና ታጥረው ያለ ሥራ የተቀመጡ ቦታዎች ኦዲት ተደርገዋል፡፡
በኦዲቱ መሠረት ከሕግና ከመመርያ ውጪ ቦታ አስፋፍተው የያዙ፣ በጥቅም ትስስር በሕገወጥ መንገድ መሬት የያዙ፣ ያለ ፈቃድ ግንባታ ያካሄዱና ለዓመታት አጥረው በያዙ ባለሀብቶች ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ምክትል ከንቲባ ታከለ የመሬት ኦዲት ከመካሄዱ በፊት አገልግሎት እንዳይሰጡ ያገዷቸው አራት ዓይነት መስተንግዶዎች ናቸው፡፡
እነዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት መጨረሻ የወጣው 30ኛው የመሬት ሊዝ ጨረታ፣ የኢንዱስትሪ አልሚዎች የመሬት ጥያቄ፣ የሰነድ አልባና አግባብ ባለው አካል ሳይፈቀድ በወረራ የተያዙ ቦታዎች መስተንግዶና መሬት ያልተረከቡ የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት መስተንግዶ አገልግሎቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በከተማው ውስጥ ለዓመታት ታጥረው ለዓመታት በተቀመጡ 186 ሔክታር የመልሶ ማልማት ቦታዎች ላይ አስተዳደሩ ሲከተል የቆየውን አሠራር እንደሚለውጥ፣ ተነሺዎችን ከግምት ያስገባ አዲስ አሠራር እንደሚከተል ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
ምክትል ከንቲባው የኦዲት ግኝቱ ውጤት ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል ብለው፣ የቆሙ አገልግሎቶችን በድጋሚ መጀመር የሚያስችሉ ሥራዎችም የተጠናቀቁ ስለሆኑ መስከረም 13 ቀን 2011 ዓ.ም. አገልግሎቶች በይፋ እንደሚጀመሩ አስታውቀዋል፡፡