Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  ወይ ነዶ?

  እነሆ ጉዞ ከኮተቤ ወደ መገናኛ። ምን እንደገጠማቸው ያልታወቀ ሁለት ሴቶች ፊት ለፊት ተላተሙ። “አንችዬ! ምነው ዓይንሽ ቢያይ?” ብላ ግንባሯን እያሸች አንደኛዋ ቆመች። አንዱ ከአንዱ እያረፈደ ታክሲያችን ውስጥ የሚሞላው ተሳፋሪ ገሚሱ ሲስቅ ገሚሱ እንዳፈጠጠ ነው። “ምነው አንቺ ያላየሽኝ?” አለች ሌላዋ ጥያቄን በጥያቄ መሆኑ ነው። “ይገርማል! የመኪና ግጭትና አደጋ ባሰለቹበት አገር እንዴት ሰውና ሰው ይጋጫል?” ብሎ ወያላው ወደ ሥራው ተመለሰ። “አዬ! ምን ብርሃን ቢሆን ምን አገር ቢለማ፣ የልቦና ዓይን ጨልሞ ሰው ማስተዋል ከተሳነው እኮ አበቃ!” ይላሉ ነጠላ አዘቅዝቀው ከለቅሶ የሚመለሱ አዛውንት ሴት። “ጀመረ እንግዲህ ይኼ አሽሙር!” ይላል መሀል ወንበር ላይ አብሮኝ የተቀመጠ ተሳፋሪ። የሰዎቹ ምልልስ እያዝናናኝ ዓይኔ በሚያየው ስገረም ጥቂት ደቂቃዎች አለፉ። ከትርምስምሱ መሀል ምሕረት የሞላባት የፀሐይ ብርሃን ፍንትው ብላ በርታለች። መንገዱ የጠበበውና የገዛ ጉዳዩ አዕምሮውን የወጠረው እንዲህ ላለው መገረም ጊዜ ያለው አይመስልም።

  “ትቀልዳለህ ዘመኑ ‘የቻፓ’ ነው፤” የሚል አባባል ድንገት ሐሳቤ መሀል ድንቅር አለ። ሦስተኛ ወንበር ላይ ከተቀመጡት ወጣቶች አንደኛው ነው። “ታዲያስ! ያለሱ ምን አለ ወንድሜ? ብታለቅስ አያምርብህ ብትስቅ ብቻህን! ከመኪና እስከ መኖሪያ ቤት ሁሉም የሚገኘው በገንዘብ ብቻ ነው፡፡ ቆነጃጅቱም ልባቸው ገንዘብ ላይ ነው፤” እያለ ፀጉሩን ያካል። “ሥነ ሥርዓት! ሴት በወለደች፣ እህት በሆነች እንዲህ ተፈርጃ የመጠራቷ ሚስጥር ለምንድነው?” ቱግ ያለች ቆንጆ ከኋላ ወንበር ጮኸችበት። ለመብቱ ተቆርቋሪና ለስሙ ተሟጋች እየበዛ ነው። “ኧረ ተረጋጊ እህቴ ጨዋታ ነው እኮ!” ይመልስላታል ክሱ የሚመለከተው ወጣት። ቆንጆይቱም አጉረምርማ ዝም። ዝምታዋ የንዴት ነው፡፡ ነገር ከቆሰቆሱ በኋላ ‹‹ተረጋጉ›› ማለት በሕዝብ መብት ላይ እያሴሩ ከደሙ ንፁህ ነን ማለትን እንኳን ለእሷ ለቀሪዎቻችንም የተዋጠልን አንመስልም። ታክሲውም በዝምታ ዋግ ተመትቶ በአንዴ እረጭ አለ፡፡

  ወያላው ሲያሰኘው ፎክሮ፣ ወይም ለምኖ፣ አልሆን ሲለው ደግሞ ተለማምጦ እንደ ምንም የመጀመሪያ ተልኮውን ተወጥቶታል። ተልዕኮው ታክሲዋን መሙላት መሆኑ ነው። ሁሉም ከቢጤው ጋር የጨዋታ አንድ ሁለት ይላል። አዛውንቷና አጠገባቸው ያለ ወጣት ይጠያየቃሉ። “. . . አይ ጉድ ሰው አለቀ!” ይላሉ አዛውንቷ። “ትልቅ ሰው ነበሩ?” ይጠይቃል ከቀብር መመለሳቸውን አስተውሎ ስለተሸኙት ሰው። አዛውንቷ ኮስተር ብለው፣ “ምነው ልጄ የሰው ትንሽ አለው? ምንም ቢሆን ሰው እኩል መሆኑን ዕድሜ አስተምሮኛል እኮ?” ይሉታል ቆፍጠን ብለው፡፡ ወጣቱ ደንግጧል። ፈጣን፣ ከእሱ በላይ አዋቂ፣ ከእሱ በላይ ያለ የማይመስለው የዚህ ዘመን ወጣት ተወካይ የሆነው ይኼው ልጅ መልሳቸው እንደ ብራ መብረቅ ልቡን ተርክኮ ጣለው። “እንደዚያ ማለቴ ሳይሆን . . .” ሲላቸው፣ “እህ ምን ማለት ነው ታዲያ?” ሲሉት፣ “በቃ እሺ ይተውት ይቅር. . . ” አለ የሚናገረው ጠፋው።

  “አይዞህ ተናገረው ካሰኘህም በአሜሪካኛ (እንግሊዝኛ ማለታቸው ነው) በለው። መቼም የዛሬ ልጆች በአሜሪካ ናላችሁ ዞሮ ቋንቋውን ረስታችሁታል። ምናለበት ግን ግራ ገብቷችሁ ግራ ባታጋቡን?” ይሉታል። ወጣቱ አባባላቸውና ሁኔታቸው እያሳቀው፣ “ቋንቋ ማወቅ እኮ ክፋት የለውም እማማ! አይደለም ዓለም እንዲህ በተቀራረበችበት ወቅት ቀርቶ ድሮም ቋንቋ ማወቅ ወንዝ ያሻግራል ይባላል እኮ?” ብሏቸው፣ “ግን እርስዎ ይህችን አሜሪካ የምትባል አገር ለማየት ተመኝተው አያውቁም?” በማለት ጠየቃቸው። ለእሳቸው መልስ የሁላችንም ጆሮ ቆመ። መልሳቸው ግን አጭር ነበረ። “የማያውቁት አገር ሲናፍቅ እኮ ነው?” አሉት። አጠገቤ የተቀመጠው፣ “ምነው ግን ዘንድሮ አባባሉ፣ ተረቱ፣ ንትርኩ፣ አሽሙሩ፣ ሽርደዳው በዛሳ?” ይለኛል። ወራጅ አይባል ጉዞው ገና ነው፡፡

  - Advertisement -

  ወያላው ከተሳፋሪዎች የሚቀበላቸውን ብሮች መልሶ መላልሶ ሲቆጥራቸው ላስተዋለ፣ በምርቃና ዓለም ውስጥ የት እንዳለ ለማሰብ ይቸግራል። በስሱ ማላመጡንም ዘግይተን እያየን ነው። “እየው ይኼን ወያላ! ከዓለም ባንክ ካዝና የተዘረገፈለት ይመስል ብሮቹ ላይ እንዴት ነው የሚያፈጠው?” ይላል አንዱ ከኋላ መቀመጫ። “ወዶ መሰለህ? ገንዘቡን ደጋግመን ካላየን የሥራ ሞተራችን መቼ በቀላሉ ይነሳል? እንዲሁም አልቻልነው እንኳን ባዶአችንን፤” ትለዋለች ከጎኑ የተቀመጠች። “ይቅርታ ይኼንን በመጠየቄ፡፡ ለመሆኑ አንቺ ከዚህ ቅጠላ ቅጠል ሞክረሽ ታውቂያለሽ?” በማለት የማይጠየቅ ጥያቄ በይቅርታ ሽፋን ሲጠይቅ እንሰማዋለን። እኛም ታክሲ ውስጥ የማይወራ የለም ብለን ሁሉን ችለን እንሰማለን፣ የማይቻል የለምና። “ከማምረቻ ፋብሪካዎች ይልቅ የጫት መሸጫዎች ቁጥር ባሻቀበበት አገርና ዘመን እየኖርኩ እንዴት ብዬ ላመልጥ ወንድሜ?” ብላ ምፀት አዘል መልስ ወረወረችለት። በተናገረችው ሀቅ ምክንያት አብዛኛዎቹ ተሳፋሪዎች በዓይናቸው ተጠቃቀሱባት።

  አንዳንዱ ገልመጥ እያለ ያያትና ድፍረትና ግልጽነቷን ያዳንቃል። “እውነትም ይህች አገር እያደገች ነው። እንዲህ በአደባባይ ለንስሐ ቅርብ የሆኑ ገመናዎቻችንን ማጋለጥ ከጀመርን ምን እንፈልጋለን? ብራቮ! ብራቮ!” ብሎ አጠገቤ የተቀመጠው ይቦጭቃታል። ከወደ ጋቢና ገልመጥ ብለው ‘ማነች እንዲህ የምታወራው?’ ዓይነት ያዩዋት ተሳፋሪዎች፣ ‘እንዲያው ትንሽ አታፍርም?! እርባና ቢስ ትውልድ!’ ሲባባሉ መሀል ሰፋሪዎቹ እናዳምጣለን። እንተራረም፣ እንማማር ብለን የሕይወታችንን ሀቅ ከላይ እስከ ታች ከመንግሥት እስከ ግለሰብ እያጥፋፋን፣ አገርን እንዴት ብለን ልንለውጥ እንደምናስብ ለማሰብ ይከብዳል። በአደባባይ የሚታየውን ችግራችንን እንደሌለ ወይም እንደማናውቀው  ሆነን ስንኮፈስ፣ ሁላችንንም በሚመለከተን ጉዳይ አያገባንም በሚል መንፈስ ስንሸሽ፣ ሀቁን ፍርጥ አድርገው የሚያወጡትን ስናወግዝ፣ በአጠቃላይ ከእውነት ጋር ተኳርፈን የምንኖር መብዛታችንን የታክሲው ሁኔታ ይገልጸዋል፡፡

  መንገድ በክስተት የተሞላ ነውና ታክሲያችን መካከለኛ ፍጥነቱ ተገትቶ መሀል መንገድ ላይ ቀጥ ብሎ ሲቆም ሁላችንም ወደ መንገዱ አሰገግን። በእግረኞች መሻገሪያ ዜብራ ላይ አንድ ሰው ተዝናንቶ ይጓዛል። ለካስ ልንገጨው ኖሯል። “ደግሞ ይዝናናል እንዴ?” ይላል ሾፌራችን ድንጋጤው ሳይለቀው። ወያላው መስኮቱን ከፍቶ፣ “ፍሬንድ ለምን አንደኛህን ዜብራውን ይዘኸው አትሄድም?” ሲለው ፈገግ ብለን እርስ በርሳችን ተያየን። አዛውንቷ በአንክሮ ሁኔታውን ሲከታተሉ ቆይተው፣ “የዘንድሮ ሰው የሚፈራው ነገር ምን ይሆን?” ብለው በነጠላቸው አፍንጫቸውን አበሱ። “እንዴት?” አላቸው አጠገባቸው ያለው ወጣት። “መኪና አይፈራ፣ ሕግ አይፈራ፣ ታላላቆቹን አያከብር፣ ይሉኝታ የለው፣ ፈጣሪን አይፈራ፣ ህርራሔ አጥቶ የገዛ ወገኑን ለመግደል ምን የልብ ልብ እንደሰጠው እንጃለቱ?” ብለው አሁንም በነጠላቸው ዓይናቸውን አሻሹ። የወዳጃቸው ሐዘን ቶሎ ከልባቸው የወጣ አይመስልም።

  ከጎኔ ያለው ጎልማሳ ደግሞ፣ “ምን የልብ ልብ የሚሰጥ ነገር አለ ልብ የሚያዝል ሁሉ ተሰብስቦ፤”  ብሎ ወደ እኔ ያፈጣል። ጉዟችን እንደ ቀጠለ ነው። ወያላውና ሾፌሩ የበኩላቸውን እንዲህ ይጨዋወታሉ። “አስበኸዋል በዚህ ዕዳችን ላይ ሰው ገጭተን?” ሾፌሩ ነው የሚጠይቀው። “ኧረ በጣም! ሰው እንደሆነ ኑሮ ከሚገጨው መኪና ቢገጨው የመረጠ ይመስላል፤” ይላል ወያላው። “እንዲህ ከሆነስ በቁም ከመሞት ይሻለው ነበር። እኛን ያውጣን እንጂ!” ሲል ጨከን ባለ አነጋገር ሾፌሩ ያጉረመርማል። ኑሮን ካስመረረንና ካስወገዘን ካለንበት ውጥንቅጥ የቱ ጀግና ሲገላግለን እናይ ይሆን? ኧረ ከቶ ማን? 

  ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ታክሲ ጥበቃ ሌላ ረጃጅም ሠልፎች ይታዩናል። “ወዴት ነው ይኼ ሠልፍ?” ትጠይቃለች ከኋላ መቀመጫ። “ወደ ኮተቤ!” ወያላው ፈጠን ብሎ መለሰላት። “ምነው ዘንድሮ በየአቅጣጫው ሠልፍ በዛሳ? ሠልፍ ፋሽን ሊሆን ነው? ወይስ ምን ገጠመን?” ይላል አንዱ፡፡ “እርግማን! የእሱ ቁጣ! መቼም ፊደል ለቆጠረ የማይዋጥ ቢመስልም ሌላ ሰበብ የለውም፤” ይላሉ አዛውንቷ። የተቀናቀናቸው አልነበረም። የሚታየውን ከማይታየው ለማጣመድ ማስተዋል የሚጠይቅ ይመስላል። ምድራዊ ምክንያቶች መፍትሔ መውለድ ካልቻሉ ለበላይ አካል እንዲህ ነገርን እርግፍ አድርጎ መተው አማራጭ የሌለው ዘዴ ከሆነ ሰነባብቷል።

  ሦስተኛው መቀመጫ ላይ የተቀመጡት ሰዎች ስለአዲሱ ዓመት ወጪ ማውጋት ሲጀምሩ ቀልባችን ወደነሱ አዘነበለ። “ከየት ይመጣ ይሆን?” ይላል አንደኛው። “እንጃለት! አሁንስ ወዴት እንድረስ ነው ጥያቄው?” ያስተካክልለታል። “አሁን በእኛ ገቢ ለቤት ቆጥበን፣ ለቤት ኪራይ ከፍለን፣ ለልጆች ትምህርት ቤት ክፍያና ለመማሪያ ቁሳቁሶች፣ ለዕለት ጉርስና ለመሳሰሉት የተደራረበ ወጪ ሲኖርብን ምን ትላለህ?” ይላል የፊተኛው። “አይ ወንድሜ! በቀትር ከሕዝብ ኪስ የሞጨለፈው ሌባ ሙሰኛ ሁሌም በዓሉ ነው፡፡ በየቀኑ እየደገሰ ይበላል፣ ያበላል። እኛ ነን ምስኪኖቹ! አሉልህ እንጂ በውሻቸው ስም ሳይቀር ተቀማጭ ያላቸው ማፊያዎች፤” ብሎት እልህ ተናንቆት ዝም አለ። አዛውንቷ ከመስማት አልፈው ሁኔታቸውንም በንቃት ነበር የሚከታተሉት። ወያላው “መጨረሻ!” ብሎን ከወረድን በኋላ አዛውንቷ ‘ጠብቁኝ’ ብለው ወደ ወጣቶቹ ሄዱ። ሁለቱንም አቅፈው፣ “አሁን አሮጌው ዓመት አልፏል። ዓመቱም አዲስ ተብሎ ተጀምሯል። ሁሌም ወደፊት ስትራመዱ ነገሮች አዲስ ናቸው። ብቻ እናንተ እጅ አትስጡ!” ብለዋቸው ጉዞአቸውን ቀጠሉ፡፡ አጠገቤ የነበረው ከጎኔ እየተራመደ፣ “በአዲሱ ዓመት ቃል ሊገባላቸው የሚያስፈልጉ ጉዳዮቻችንን ምነው ችላ አልናቸው?” ይለኛል። “እነዚህ ጉዳዮች ምን ይሆኑ?” ስለው፣ “ሲንከባለሉ የመጡት ናቸዋ፡፡ እነሱም ጭቅጭቅና ብሽሽቅ ያጀባቸው የፖለቲካ ሽኩቻዎች መሆናቸውን አታውቅም?” አለኝ፡፡ በአዲስ ዓመት አጋማሽ ላይ ሆነን እነዚህን ስናስብ ቀኑ መንገዱን ቀጥሏል፡፡ ወይ ነዶ እንበል እንጂ ሌላ ምን ይባላል? መልካም ጉዞ!  

  Latest Posts

  - Advertisement -

  ወቅታዊ ፅሑፎች

  ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት