የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብርሃኑ በሻህ (ዶ/ር) ከኃላፊነታቸው ለቀቁ፡፡ በውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር፣ ኢንጂነር) የሚመራው የኮርፖሬሽኑ ሥራ አመራር ቦርድ፣ ሰኞ መስከረም 21 ቀን 2011 ዓ.ም. በመሰብሰብ የዋና ሥራ አስፈጻሚውን ከሥልጣን የመልቀቅ ጥያቄ መቀበሉ ታውቋል፡፡
የሥራ አመራር ቦርዱ በእሳቸው ምትክ ተወካይ ሆነው እንዲሠሩ አቶ የኋላሸት ጀመረ (ኢንጂነር) ሰይሟል፡፡
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ብርሃኑ (ዶ/ር) ከኃላፊነታቸው የለቀቁት በራሳቸው ጥያቄ ነው፡፡
በኮርፖሬሽኑ በተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉት ተሰናባቹ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ ከግንቦት 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የቀድሞውን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌታቸው በትሩ (ዶ/ር፣ ኢንጂነር) ተክተው እስከ ሰኞ መስከረም 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ በኃላፊነት ቆይተዋል፡፡
ተሰናባቹን ዋና ሥራ አስፈጻሚ በውክልና የተኩት ወጣቱ አቶ የኋላሸት (ኢንጂነር)፣ በአሁኑ ወቅት በኮርፖሬሽኑ የባቡር ኔትወርክ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ ይህንኑ ኃላፊነት ደርበው የዋና ሥራ አስፈጻሚ ወኪል ሆነው እንደሚሠሩም ታውቋል፡፡
አቶ የኋላሸት (ኢንጂነር) የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ምሕንድስና፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ሆላንድ ከሚገኘው ከዴልፋት ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ በስትራክቸራል ምሕንድስና ማግኘታቸው ታውቋል፡፡
በ2003 ዓ.ም. ኮርፖሬሽን ከተቀላቀሉ በኋላ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ መሥራታቸው ገጸ ታሪካቸው ይናገራል፡፡
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በኅዳር 2000 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 141 የተቋቋመ ግዙፍ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው፡፡
ኮርፖሬሽኑ በቢሊዮኖች በሚቆጠሩ ዶላሮች በርካታ ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍኑ፣ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ የባቡር ትራንስፖርት አውታሮችን የገነባና እየገነባ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡