በየዓመቱ የመስከረም ሦስተኛ እሑድ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል መስከረም 20 ቀን 2011 ዓ.ም. በርካታ ሕዝብ በተገኘበት በቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሰዲ ለተከበረው። ኢሬቻ ወርኃ ክረምት አልፎ ወደ መፀው ብርሃን የሚደረገው ሽግግር የሚከበርበትና ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት በዓል ነው። በበዓሉ ላይ በተለይ ከሲዳማ፣ ቡርጂ፣ ሀላባ፣ ኮንሶና ጋሞ ብሄረሰቦች የመጡ ሽማግሌዎችና ወጣቶች ተገኝተዋል። ‹‹ኢሬቻ ለፍቅርና ለአንድነት›› በሚል መሪ ቃል በተከበረው የወቅት ሽግግር የምስጋና በዓል አጋጣሚም ሙሽሮች ሠርጋቸውንም በሥፍራው አክብረዋል፡፡ በዋዜማው በቢሾፍቱ ከተማ በተዘጋጀው መሰናዶ የቀድሞው የቱላማ ኦሮሞ አባገዳ በየነ ሰንበቶ ለአዲሱ አባገዳ ጎበና ሆላ ኢሬሶ ሥልጣኑን አስረክበዋል፡፡ በገዳ ሥርዓት አጠራር ‹‹የአለንጋ ርክክብ›› ተብሎ የሚታወቀው ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል። ክብረ በዓሉን አስመልቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፣ ‹‹ኦሮሞ የዘመናዊ ዴሞክራሲ ሥርዓት ባለቤት ነው ስንል፣ በየስምንት ዓመቱ ከአንድ አባገዳ ወደሌላ አባገዳ የሚተላለፈው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ተምሳሌትነትን ልናስተምርበት ነው!›› ብለዋል፡፡ የኢሬቻ ክብረ በዓል በሰላም መከበሩን አስመልክቶ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በሰጡት መግለጫ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱት አባ ገዳዎች ምክር ቤት፣ ለወጣቶች፣ ለኦሮሚያ ክልል ፖሊስ፣ ለፌዴራል ፖሊስና ለመከላከያ ሠራዊት አባላት እንዲሁም ለቢሾፍቱ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎችም ምስጋና አቅርበዋል። ፎቶዎቹ የክብረ በዓሉን ከፊል ገጽታና በዋዜማ የነበረውን የአባ ገዳዎች ሥልጣን ርክክብ ያሳያሉ፡፡
- Advertisement -
ፌርማታ ፅሁፎች
ትኩስ ፅሁፎች
- Advertisement -