Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  እስኪ ዱብ ዱብ!

  ሰላም! እንዴት ይዟችኋል? ያው እኔም እንዳቅሚቲ ሮጥ ሮጥ እያልኩ ፑሽ አፕ እየሠራሁ ጤንነቴን ስንከባከብ ነበር፡፡ ይህንን የሰሞኑ ተግባሬን የታዘበችው ውዷ ማንጠግቦሽ በአሽሙር፣ ‹‹ደግሞ ምን አስበህ ነው ላይ ታች የምትለው?›› ስትለኝ ባላየ ባልሰማ በዝምታ አለፍኳት፡፡ ዘንድሮ እኮ አንዳንዱ ነገራችን ዝም ጭጭ ያሰኛል፡፡ አይደለም እንዴ? መቼም ተስፋን በውስጣችን የመለኮስ ባለሙሉ ሥልጣን ስለሆንን፣ ማናችንም በአጠቃላይ ሁኔታችን ሒሳብ መዛባት መባዘን እንደማይገባን ሳስብ ነበር የሰነበትኩት፡፡ ለማሰቤ ምክንያቱ ደግሞ አንድ ከብዙ ዓመታት በፊት የተለየኝን የቀድሞ ወዳጄን ማግኘቴ ነው፡፡  ‹‹ሰው ካልሞተ በስተቀር መገናኘቱ የማይቀር ነው›› የሚባለው አባባል በሕይወቴ የሠራው ለብዙ ጊዜ ነው፡፡ ደላላ አይደለሁም? ያከራየኋቸውን ሰዎች ሳስለቅቅ፣ መልሼ ሳከራይ፣ ያሻሻጥኩትን መልሼ ሳሻሽጥ ከስንት ሰዎችና አጋጣሚዎች ጋር በተደጋጋሚ እገናኛለሁ መሰላችሁ? ይህ ዓይነቱ ግንኙነት በድለላ ኑሮውን ለሚገፋው አምበርብር ምንተስኖት እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ተመጥኖ የተሰጠን ዕድሜ በአስተማማኝ እንዲቀጥል በተደጋጋሚ መገናኘቱ አይከፋም፡፡  ደጋግመን ስንገናኝ ግን ጥንቃቄ ያሻናል፡፡ ሳናስበው ከበባ ውስጥ እንገባለንና፡፡

  ‹‹መኖር ደግ ነው እንደ መሰንበት ያለ ሸጋ ነገር የለም፤›› አለኝ እንደኔ ከብዙ ዓመታት መለያየት በኋላ ዓይኔን ያየው ወዳጄ፡፡

  ‹‹ሁሉንም ያገኛል ሰው በሕይወት ካለ፣

  የሞተ ተጎዳ መቃብር ውስጥ ያለ፤›› ተብሏል አሉ፡፡ ስለመልሶ መገናኘት ምን ያልተባለ ነገር አለ? ‹‹እንገናኛለን እኔ አልቆርጥም ተስፋ. . .›› የሚለውን ዘፈን ስንቶች ተቀባብለው እንደ ዘፈኑት ሳስብ፣ መልሶ መገናኘት ሁሌም ይኖራል ብቻ ሳይሆን የኑሮ አካል ነው፡፡ ይህ የቀድሞው ወዳጄ የእኔ ቢጤ ደላላ ነው፡፡ ከረዥም ጊዜ በኋላ እንደ መገናኘታችን መጠን አንዳችን ስለአንዳችን የማወቅ ጉጉታችን ጨምሮ ኖሮ፣ በአንድ ጊዜ ሁለታችንም ለመናገር ስንደነቃቀፍ ቆየንና ስለሥራ፣ ስለቤተሰብ በአጠቃላይ ስለሕይወት ማውጋት ጀመርን፡፡

  - Advertisement -

  ‹‹ምን እባክህ የዘንድሮን ነገር ለመርሳት መሞከር ከማሰቡ የከበደ ቢሆንም፣ የተቻለንን ያህል ብንጥር ነው የሚሻለን፡፡ ከኑሮ መክፋትና እንደ እቶን መንደድ አኳያ ቤተሰብ መምራት እስከ ማልችልበት ደረጃ ደርሻለሁ፡፡ መቼም አንድ አንተ ለራስህ አታንስም፡፡ ምናልባት ግን ለአንድ ለራስህ የምታንስበት ቀን ሊመጣም ይችል ይሆናል፡፡ ለብዙ ስትሆን ግን አቅልህን ትስታለህ፡፡ እናም ይኼውልህ ይኼን ብለን እኔና ባለቤቴ ተማክረን ተለያየን፡፡ ቤተሰብ ከማስተዳደር ራስን ብቻ ለማስተዳደር መሞከር የሚል መፈክር አንግበን ተለያየን፡፡ ሳንለያይ ተለያየን፤›› አለኝ፡፡ በጣም ተገርሜ በአንድ በኩል ስለሰላማዊ ፍቺ የሰማሁበትን ቀን ለመዘከር እያውጠነጠንኩ፣ በሌላ በኩል ችግር ብልኃትን ይወልዳል እንዲሉ የሰው ልጅ ለመኖር የሚፈነቅላቸውን ደንቃራ መሰናክሎች በምናቤ ለመሳል ተጣጣርኩ፡፡ ምን ዋጋ አለው የደላላ እንጂ የሠዓሊ ተሰጥኦ ስለሌለኝ ተውኩት፡፡ ስንቱን ትተን እንችለዋለን ግን? እንደ ሰሞኑ ጉድ በፑሽ አፕ አንገላገለው ነገር፡፡

  ታዲያ ከዚህ የረዥም ጊዜ ወዳጄ ጋር የመጨዋወት ጉጉቴ ጨምሮ ቀልቤን ሰብስቤ አዳምጠው ቀጠልኩ፡፡ እሱም ስለሥራው ሁኔታ አጫወተኝ፣ ‹‹የሥራን ነገር አታንሳብኝ፡፡ ደላላ ማለት በተለይ አሁንማ ሙልጭ ያለ ሌባ የሚመስላቸው ሰዎች ብዙ ሆነዋል፡፡ እስኪ ይታይህ በጥቂት ገብጋባ ደላሎች ምክንያት ለሁሉም አንድ ዓይነት ስያሜ መሰጠት አለበት? በሩጫዬ መካከል አንድ ተጨማሪ ሥራ የሆነብኝ ደግሞ የደላላ ትርጉም ለተጣመመባቸው የማስተካከያ ስብከት ማስደመጥ ነው፤›› አለ፡፡ ‹‹ምን እያልክ ነው የምትሰብከው?›› አልኩት፣ መልከ መልካምነቱን የዋጠውን የዕድሜ መግፋት  እየታዘብኩ፡፡ ኑሮ ስንቱን አጎሳቅሎ አስረጀው እናንተዬ?

  ‹‹ደላላ ከስም አንፃር እንኳ በአማርኛ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ስም አለው እያልኩ ነው፡፡ ደላላ ዓለም አቀፋዊ ነው፡፡ ደላላ የአገርና የዓለም ገበያ መኩሪያ ነው፡፡ ከፈለጋችሁ የየአገሩን ገበያ መርምሩ፡፡ ደላላ በእንግሊዝኛ ‘ብሮከር’ ይባላል፡፡ አሜሪካ የወደደችውንና ያመነችውን፣ እናንተ እነማናችሁ የምትጠሉትና የምትጠረጥሩት እያልኩ እሰብካለሁ፤›› ሲለኝ በፈገግታ ቅኝት የቅኔውን ፍቺ እየፈለቀቅኩ ጨዋታውን አጣጣምኩለት፡፡ ይህንን ቅኔ በፑሽ አፕ ብናወራርደውስ?

  እንዲህ እንዲህ እያልን በመካከል ገዝፈው ያለያዩንን ረዥም የልዩነት ጊዜያት በአንድ ጊዜ የሚሞሉ ይመስል ለመሙላት በብዙ የሐሳብ ሽርሽር ደከምን፡፡ ‹‹እንዲያው ይህን ያህል ጊዜ ስንለያይ ትዝ ብዬህ አውቃለሁ?›› ብዬ በትዝብት ዓይን ጠየቅኩት፡፡ ‹‹አይ አንተ ሰው ከራሱ ጋር ተረሳስቷል እንኳን ከቀድሞ ወዳጁ፡፡ ትዝ ብትለኝም አፍታ ከውስጤ ሳትቆይ በኑሮ ኮተት ሐሳቦች ተጠርገህ ትጠፋለህ፡፡ የሆነው ሆኖ ፍቅርንና መተሳሰብን የሚያቀዘቅዝ ዘመን በአፍንጫችን ይውጣ፡፡ ለነገሩ እኛ ነን ፊት የሰጠነው፡፡ አየህ መሸ ነጋ ስለሆድ አስበን፣ ስለኑሮ ተጨንቀን፣ ስለምቾት አውርተን አናታችን ላይ አወጣነው፡፡ አኅጉር ከአገር እንደሚሰፋው ሁሉ ፍቅርና መተሳሰብም ከሆድ ይበልጣሉ፡፡ ይህ አልገባን ብሎ ነው መሰለኝ የዳዴያችን ዙሩ የበዛው፡፡ . . .ለምሳሌ ወታደርን ተመልከት፣ ውትድርናን ሲያስብ አብሮ ፈንጂ መርገጥንና በጦር ሜዳ መውደቅን ያስባል፡፡ ለነገሩ የዘመኑ ወታደር ቤተ መንግሥት ገብቶ ከበላይ አዛዥ ጋር ፑሽ አፕ ሠርቶ ራቱን በልቶ ይሸኛል. . .›› እያለ ሲስቅ እኔም ሳቄን መቆጣጠር አቃተኝ፡፡

  በእውነት የዚህ ጓዴ የንግግር ዘዬ አስገረመኝ፡፡ በእሱ ለውጥ ውስጥ የእኔን ለውጥ አሰላሁት፡፡ ሒሳቡ ጨመረብኝ፡፡ መለየት የሚሉት ብሂል ግን ምንድነው? ከወደድነው ጋር አብሮ መኖር ለምን አቃተን? ትካዜ ትውስታዎቼን በረቂቅ ዳሰሳው፣ በረበራቸው፡፡ ትዝታ በጓዴ ፊት ከዓይኖቼ እንባ ከማመንጨቱ በፊት ተሰናብቼው ሰሞኑን ከገጠር የመጡትን ባሻዬን ጥየቃ ወደ ቤታቸው ሄድኩ፡፡ ባሻዬ በቅርቡ ገጠር ሄደው ዘመዶቻቸውን ጠያይቀው ተመልሰዋል፡፡ መቼም የድሮ ሰውና ብዙ ውጣ ውረድን አብሮ ስላሳለፈ ዘመድም ባይሆን ይጠያየቃል፡፡ የባሻዬን ለየት የሚያደርገው አንድ ከተማ ተቀምጦ ሰው መጠያየቅ በተረሳበት ዘመን

  ‹‹ዘመን ደህና ሰንብት መንገድ ጉድ ያግኝህ፣

  ብድርም የለብኝ እኔም አልሸኝህ፤›› ብለው እሳቸው ገጠር ድረስ ሄደው መጠየቃቸው እጅግ ያስደምማል፡፡ እርጅና የተጫጫናቸው ባሻዬ ግን ገጠር ደርሰው ተመለሱ፡፡ ታዲያ ስለጉዟቸውና ስለዘመዶቻቸው ልጠይቃቸው ቤታቸው ጎራ ስል፣ ያለ ወትሮአቸው ሰላምታዬ እስከ ማይሰማቸው ድረስ ጮክ ብለው ዳዊታቸውን ሲያነቡ ነበር፡፡ ከስንት ትዕግሥትና መጠበቅ በኋላ ሲጨርሱ ዓይቼ በሰላም ደርሰው መምጣታቸውን ጠየቅኩዋቸው፡፡ ‹‹ኧረ ተወው የዘንድሮውንስ ነገር? ከሥርና ከላይ እንደ ገና ዳቦ ሆነ እኮ የእኛ ነገር አቤቱ ማረን፣ አቤቱ ይቅር በለን፣ ቱ… ቱ… ቱ…›› አሉ ወደ መሬት አቀርቅረው፡፡ ጨነቀኝ፡፡ ሁሌም ቢሆን ነገራቸው እንደዚህ ሲረዝምብኝ ይጨንቀኛል፡፡ ምን እንዳዩ ወይ እንዳጋጠማቸው እንዲነግሩኝ ትዕግሥቴን ጨርሼ በጉጉት ስጠይቃቸው፣ ‹‹ግጭት ነዋ! ግጭት ሰውን ፈጀው፡፡ ገባህ አይደል? ድንገት ሳይታሰብ ሕዝብ ሲያልቅ ምን ይባላል? ለእኔ ከላይ ይሁን ከታች ግራ ይገባኛል፡፡ ወይ ፈጣሪዬ. . .›› ብለው ሲነግሩኝ፣ እኔ ራሴ ሰሞኑን የበረገግኩባቸውን ቀናት ጥቂት አለመሆናቸውን ጨምሬ አስቤ እንዴት ነው ዘንድሮ መሬቱ መብረቅ፣ ሰማዩ መብረቅ ሆነ አልኩ፡፡ ‹‹የዘንድሮን ጉዳይ የላይኛው ጌታ ካልሆነ በስተቀር ማንም አይመልሰውም፤›› ብለው ወደ ዳዊታቸው ሲመለሱ እኔም አንገቴን ደፍቼ ተመለስኩ፡፡

  ይህን የባሻዬን ነገር ለውቧ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ባጫውታት እሷም በፍርኃት ተርበደበደች፡፡ በዚህ ምክንያት ታዲያ በደላላነቴ ላይ ሌላ ሥራ ተጨምሮብኝ አረፈው፡፡ የማፅናናትና የመምከር ብሎም አለሁልሽ የማለት ነገር ተጨምሮበት፣ የሰው አፍ ባምባረቀ ቁጥር እሷን እንደ ሕፃን ማቀፍ ሆኗል ሥራዬ፡፡ ይኼኔ ነበር ያ የቀድሞው ወዳጄ የነገረኝ የፍቺ ብልኃት እንደማይሠራ የገባኝ፡፡ ለካ ‹‹ሰው ለሰው መድኃኒቱ ነው›› የሚባለው እውነት ኖሯል? የአገራችን ሰው መቼም መተረት ያውቅበታል፡፡ ታዲያ በስንት ምክርና ማባበል ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ከፍርኃቷ ብትላቀቅም፣ አልፎ አልፎ የወሬ መብረቅ ሲባርቅ ልቧ ብርግግ ይላል፡፡ ፍርኃቱ ነው መሰል ቅኔም ያስቀኛታል፡፡

  ‹‹መብረቁ በረቀ ልቤ በረገገ፣

  በኑሮና በሞት አሾፈና ሳቀ፣

  ስቆም አለቀሰ. . .›› ስትል እሰማለሁ፡፡

  ቀድመን እንዳልነው ሰው ከሰነበተ መገናኘቱ ባይቀርም የመለየት ጊዜው ይኼው እንዳሁኑ እንደኛ ድንገት ነው፡፡ ብቻ ነገ እንዳሰብናትና እንዳለምናት ስለማትጠብቀን ስለትናንት በመተከዝ በትዝታ መኖር አይጠቅመንም፡፡ ዛሬን በምንሰማው ነገር አንደበታችንን ለጉመን በፍርኃት መራድ ትርፉ ውድቀትና ጉስቁልናን ያስከትላል፡፡ ‘አኅጉር ከአገር ትሠፋለች’ እንዳለው ወዳጄ፣ ነገን በሰፊ የተስፋ ብርሃን ብናስባት ሳይሻለን የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ‘በትዝታ ከመኖር በተስፋ መኖር ይሻላል’ ያለውን ሰው ብናውቀው ኖሮ ይመቸን ነበር፡፡ ስለትናንት እያሰቡ ‹‹ድሮ ቀረ›› ከሚሉ ይልቅ፣ ‹‹ነገን ነው መናፈቅ›› የሚሉ ልሂቃን ቢኖሩን ሳይሻል አይቀርም፡፡ እኔማ ሌሊቱ ነግቶ ነገን እስከማይ ድረስ ጊዜው ስለሚረዝምብኝ፣ በህልሜ ሳይቀር የነገዋን ቀን ለማየት እፈልጋለሁ፡፡ ኪሳራን ማወራረድ አይጠቅምም፡፡ ኪሳራን በኪሳራ እያባዙ ከመንጎድ አዋጪውንና ቀናውን መንገድ መምረጥ የእኛ ፋንታ መሰለኝ፡፡ በትንሽ በትልቁ ነገር እየተፈላለግን ካገኘነው ጋር ከመላተም፣ ነገን ለማሳመር የሚረዱ ጉዳዮች ላይ ብናተኩር የበለጠ እናተርፋለን፡፡ ከውዥንብር ወደ ትርምስ አንንደርደር፡፡ ይልቁንስ ውጥረቱን በፑሽ አፕ እናርግብ! እስኪ ዱብ ዱብ! ሰላም ሁኑ! መልካም ሰንበት! 

  Latest Posts

  - Advertisement -

  ወቅታዊ ፅሑፎች

  ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት