[ክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊያቸውን ቢሮ አስጠሯት]
- ፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
- እስኪ ተቀመጭ፡፡
- ምን ልታዘዝ?
- አሁን ካለው ለውጥ ጋር መጓዝ የሚችል አሠራር መቅረፅ አለብን፡፡
- ትክክል ነዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለውጡ ከላይ የጀመረ ስለሆነ እኛም ይህንኑ ወደታች ማውረድ አለብን፡፡
- እስማማለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስለዚህ የመሥሪያ ቤታችንን አሠራር በዚሁ መሠረት ማድረግ አለብን፡፡
- ምን ይደረግ ታዲያ?
- አሁን ስብሰባ ይቅር ተብሏል፣ ከተቻለ ስብሰባዎቻችን እዚህ ባይሆኑ ጥሩ ነው፡፡
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- አየሽ የድሮ ሥርዓት መፈራረስ ስላለበት አካሄዳችን መስተካከል አለበት፡፡
- የድሮውን ሥርዓት እንዴት ነው የምናፈርሰው?
- ለምሳሌ ስብሰባ ይቅር ተብሏል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር የእርስዎ ዋና ሥራ እኮ ስብሰባ ነው፡፡
- እሱንማ አውቃለሁ፡፡
- ታዲያ ስብሰባ ካስቀረን እርስዎ ምን ሊሠሩ ነው?
- ስብሰባውን ሳይሆን የምናስቀረው፣ የስብሰባውን ፎርማት ነው የምንቀይረው፡፡
- ትንሽ ቢያብራሩልኝ ክቡር ሚኒስትር?
- አንቺ ለመሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ይህን ጉዳይ አስመልክተሽ ደብዳቤ ትጽፊልኛለሽ፡፡
- ምን ዓይነት ደብዳቤ?
- አሁን የምንከተለው የሥራ አካሄዳችን ለበርካታ መሥሪያ ቤቶች እንደ አርዓያ የሚቆጠር መሆን ይኖርበታል፡፡
- ምን ዓይነት የሥራ አካሄድ ነው?
- አገሪቱ የጀመረችውን ለውጥ ተቀብለን ለማስቀጠል ስለቆረጥን አዲስ የስብሰባ አካሄድ እንከተላለን፡፡
- ምን ዓይነት አካሄድ ነው?
- ይህንን አካሄድም ሌሎች መሥሪያ ቤቶች እንዲከተሉን ስብሰባችን የተለየ ነው የሚሆነው፡፡
- ስለዚህ ምን ዓይነት ደብዳቤ ነው የምጽፈው?
- ምን ዓይነት ስብሰባ እንደምናካሂድ፣ ለስብሰባ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችና ስብሰባው የት መካሄድ እንዳለበት በደብዳቤው መሥፈር አለበት፡፡
- መልካም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አሁን ስብሰባ ለማድረግ ከተማችን ውስጥ ያለውን ሙቀት ተመልከቺ፣ አየሽ በዚህ ሙቀት ስብሰባ ብትቀመጪ እንኳን ሐሳብ ልታመነጪ ቀርቶ ያለሽ ራሱ ይጠፋብሻል፡፡
- ባለፈው ለስብሰባ አዳራሹ በመቶ ሺሕ ብሮች እኮ ነው ኤሲ የተገጠመላቸው፡፡
- ነገርኩሽ እኮ እንደዚህ በታፈነ ክፍል ውስጥ የሚመጣ ሐሳብ ራሱ የታፈነ ስለሚሆን፣ አሁን ስብሰባችንን ማድረግ ያለብን አውትዶር ነው፡፡
- አውትዶር ሲሉኝ?
- በቃ ተፈጥሮን እያደነቅሽና እያጣጣምሽ ደጅ ላይ ስብሰባ ብታደርጊ የሐሳብ ጎርፍ ነው የሚመታሽ፡፡
- መቼም ያን ሐሳብ ሊያመጡት እንዳይሆን?
- የቱን ሐሳብ?
- በመመርያ የተከለከለውንና በየሪዞርቱ ስብሰባ እናድርግ የሚለውን ነዋ፡፡
- አሁን ሪፎርም እናድርግ ስለተባለ ከዚያም ላቅ ያለ ሐሳብ ነው ያለኝ፡፡ እኔ ከአዳራሽ ውጪ ስብሰባ እንዲካሄድ ነው የምፈልገው፡፡
- ከአዳራሽ ውጪ ታዲያ ከሆነ ጫካ ገብተን ስብሰባ ልናካሂድ?
- ጫካ መግባት ያለፈበት ፋሽን ስለሆነ እኔ ያለኝ ሐሳብ በጣም የተለየ ነው፡፡
- ምን ዓይነት ሐሳብ?
- ከዚህ በኋላ ስብሰባችን መደረግ ያለበት ቦታ ለየት ያለና ተሰብሳቢዎችን ማዝናናት የሚችል ነው፡፡
- ምን ዓይነት ቦታ ነው?
- ቦታው በአገር ውስጥ ስለሌለ በአስቸኳይ ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣት አለብን፡፡
- የምን ጨረታ?
- የስብሰባ ቦታችንን እንዲገነቡልን ለማድረግ ነዋ፡፡
- ምን ልናስገነባ ነው?
- መርከብ!
[የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ቢሯቸውን በርግደው ይገባሉ]
- ከየት መጣሽ?
- ጉድ ሆነናል፣ ጉድ ሆነናል፡፡
- የምን ጉድ ነው?
- ለመሆኑ መንግሥት አለ?
- እኔ አይደለሁ እንዴ መንግሥት?
- ብትሆንማ ይኼ ሁሉ ነገር ሊፈጸም አይችልም፡፡
- ምን ተፈጸመ?
- ጥረን ግረን ያፈራነውን ንብረት ተወሰደ፡፡
- ሴትዮ ተረጋግተሽ እስኪ ንገሪኝ?
- ስማ ከተማ መሀል ከልጆቻችን ጉሮሮ እየነጠቅን የሠራነውን ሕንፃ ተነጠቅን እኮ ነው የምልህ?
- የትኛውን ሕንፃ ብዙ እኮ ነው ያለን፡፡
- መሀል አዲስ አበባ ላይ መቶ ሚሊዮን ብር አውጥተን የገነባነው G+7 ሕንፃ ነዋ፡፡
- ማን ነው የነጠቀን?
- ወዳጄ ነው የምትለው ውክልና የሰጠኸው ደላላ ነዋ፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- ይኸው ዛሬ የሕንፃውን ኪራይ ላክልኝ ብዬ ደውዬለት ነበር፡፡
- አላከልሽም ታዲያ?
- ‹የምን የሕንፃ ኪራይ?› ብሎ ጠየቀኝ፡፡
- የሕንፃውን ነዋ፡፡
- ‹ሕንፃውን የእናንተ ማን አደረገው?› አይለኝ መሰለህ፡፡
- ታዲያ የሕዝብ ሕንፃ ነው ሊል ነው እንዴ?
- እኔ ምን አውቅልሃለሁ?
- ቆይ እስኪ ተረጋጊ?
- ስማ እንዴት ነው የምረጋጋው?
- ምን ተፈጠረ?
- ‹ሕንፃው የእኔ ነው› እያለ ነው፡፡
- መጀመርያ ተረጋጊ፡፡
- ሰውዬ አሁኑኑ እንዲህ ዓይነት ክህደት የፈጸመው ደላላ ላይ ዕርምጃ መውሰድ አለብህ፡፡
- ምን ዓይነት ዕርምጃ?
- አብዮታዊ ዕርምጃ ነዋ፡፡
- አንቺ መግደል መሸነፍ ነው፣ እንዲህ ዓይነት ሐሳብ አይኑርሽ፡፡
- ብቻ ሌላም ዕርምጃም ቢሆን ውሰድበት፡፡
- ስሚ ዘመኑ የምን ዘመን እንደሆነ ረሳሽው?
- የምን ዘመን ነው?
- የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የመደመር ዘመን ነው፡፡
- እኔ ከእንዲህ ዓይነቱ ከሃዲ ጋር መደመር አልፈልግም፡፡
- ስሚ ይህን ሰውዬ እኮ ማስገረፍም ሆነ ማስገደል እንችላለን፣ ግን መግደል መሸነፍ መሆኑን መቀበል አለብሽ፡፡
- ይኼ የፖለቲካ ዲስኩርህ እኔ ዘንድ አይሠራም፡፡ ቢያንስ አሁን ሰውዬውን አሳስርልኝ፡፡
- ምን ነካሽ? እኛ አስረን አናጣራም፣ አጣርተን ነው የምናስረው፡፡
- ለዚያ ነው የአዲስ አበባን ልጆች ያጎራችኋቸው?
- ይኸውልሽ አዲስ አበባ ነዋሪ እንጂ ልጆች የሏትም፡፡
- ቀስ ብለህ አንተ ከተማዋ መሀን ናት ትለኛለህ፡፡
- እንደዚያ አልወጣኝም፡፡
- ሰውዬ አሁን እኔ የምፈልገው ይኼ ከሃዲ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ነው፡፡
- ለእሱ አታስቢ ተገቢውን ቅጣት እኔ እሰጠዋለሁ፡፡
- ሰውዬው እኮ የጊዜው ሰው ነኝ ብሎ ነው የሚደነፋው፡፡
- ነገርኩሽ እኮ ለጊዜው እኔ የጊዜውን ቅጣት እሰጠዋለሁ፡፡
- ምንድነው የጊዜው ቅጣት?
- ፑሽአፕ!
[በአዲሱ የሚኒስትሮች ሹመት እካተታለሁ ብሎ የሚያስብ ባለሥልጣን ከሚኒስትሩ ጋር እያወራ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር በአዲሱ የሚኒስትሮች ሹመት እንደምካተት ተነግሮኛል፡፡
- በእሱ እርግጠኛ አትሁን፡፡
- ለምን?
- እኛንም ድሮ እንደዚሁ ተስፋ ይሰጡንና በመጨረሻ ያንሳፍፉን ነበር፣ ስለዚህ ብዙ ተስፋ አታድርግ፡፡
- ቢሆንም እኔ ራሴን ለሚኒስትርነት እያዘጋጀሁ ብጠብቅ ይሻላል፡፡
- ምን ልርዳህ ታዲያ?
- ከአንድ ሚኒስትር የሚጠበቁ የሥራ ሥነ ምግባራትን እንዲነግሩኝ ነው፡፡
- ሚኒስትርነት ትልቅ የአገር ኃላፊነት መሆኑን ማወቅ አለብህ፡፡
- ልክ ነዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ቢሆንም መጀመርያ አገልግሎት የሚጀምረው ከራስ ነው፡፡
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- መጀመርያ ራስህን ከጠቀምክ በኋላ ነው ቀጥሎ ሕዝቡን መጥቀም የምትችለው፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ሆድህንና ኪስህን ከሞላህ በኋላ የሕዝቡን ሆድና ኪስ መሙላት ትችላለህ፡፡ የአንተ ሆድና ኪስ ባዶ ሆኖ የሕዝቡን እንዴት ልትሞላ ትችላለህ?
- ልክ ብለዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስለዚህ በመጀመርያ ማሰብ ያለብህ እንዴት ታታሪ ዘራፊ መሆን እችላለሁ የሚለውን ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ትልቅ ትምህርት እየሰጡኝ ስለሆነ እኔም ኖት እየያዝኩ ነው፡፡
- ሁልጊዜ መሬትና ኮሚሽን የሚሉትን ነገሮች ከጭንቅላትህ ማውጣት የለብህም፡፡
- እ. . .
- ምንም ሥራ ስታስብ ኮሚሽኔ ምንድነው የሚለውን አብረህ ማሰብ አለብህ፡፡
- ጥሩ ነጥብ ናት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አንዳንዱ ኮሚሽን ገንዘብ ነው ብሎ ያስባል፣ አንዳንዱ ደግሞ የሕዝብ ፍቅር ነው ብሎ ያስባል፡፡
- አሁን ገባኝ፡፡
- ስለዚህ አንተ ከየትኛው ጎራ መሆን እንደምትፈልግ ዕወቅ፡፡
- እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንደ እኔ እንደ እኔ ቅድም እንዳልኩህ ራስህን መጥቀም አለብህ፡፡
- እሱ በደንብ ያግባባናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሌላው በተቻለህ መጠን በርካታ ደላላ ጓደኞች ሊኖሩህ ይገባል፡፡
- ጥሩ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አየህ ከአንድ ደላላ ይልቅ በዘርፍ በዘርፍ ደላላ ጓደኞች ቢኖሩህ ጥሩ ነው፡፡
- ምንድነው የሚደልሉት?
- በቃ እነሱ እንደ አንተ ሆነው ቢዝነስህን ያጣጡፉልሃል፡፡
- ዋናው ጉዳይ እሱ አይደል እንዴ?
- በዚህ አካሄድ እነሱም ይሠራሉ አንተም ትሠራለህ፡፡
- በሚገባ እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንግዲህ ይኼን አካሄድ ነው ሠርቶ ማሠራት የምንለው፡፡
- ይኼማ ሌላ ስም ነው ያለው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን?
- ሰርቆ ማሰረቅ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር አዲስ መሥሪያ ቤት እንዲቋቋም ስለተወሰነ እርስዎ ምን ዓይነት አዲስ መሥሪያ ቤት ይቋቋም ይላሉ?
- ብዙ ጊዜ የአገሪቱን ችግር ሊፈታ የሚችል መሥሪያ ቤት እንዲቋቋም ጠቁሜ እኮ ሰሚ አጥቼ ነው የተውኩት፡፡
- ዛሬ ላናግርዎት የመጣሁት እኮ ለዚያ ነው፡፡
- እንደነገርኩህ በቀድሞው ሥርዓትም ሆነ አሁንም አገሪቱ የጎደላት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አንድ ነው፡፡
- ምንድነው የጎደለው?
- ሕዝቡ ስትመለከተው በጣም ያዝናል፣ ይጨነቃል፡፡ ስለዚህ ይህንን የሕዝብ ችግር የሚፈታ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መቋቋም አለበት፡፡
- ምን ዓይነት መሥሪያ ቤት? የሰላም ነው?
- ይኸውልህ ከሰላም በፊት መቅደም ያለበት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አለ፡፡
- ታዲያ የፍቅር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ነው?
- ምን መሰለህ ከፍቅርና ከሰላም በፊት ሊኖረን የሚገባ መሥሪያ ቤት አለ፡፡
- ምንድነው እሱ?
- የፈንጠዝያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት፡፡
- ይቀጥሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይህ የፈንጠዝያ ሚኒስቴር ዋናው ሥራው በየሳምንቱ ቅዳሜ ሕዝቡ በየሥጋ ቤቱ እስኪጠግብ በልቶ የተከሸነውን እንዲጋት ያደርጋል፡፡
- ኖት እየያዝኩ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ወደ አመሻሽ ላይ ደግሞ በየፓርኮቹ አሉ የተባሉ ዲጄዎች በሙዚቃ ድግስ ሌሊቱን ሙሉ ሕዝቡን ያስፈነድቁታል፡፡
- በጣም ጥሩ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እሑድ ደግሞ ሕዝቡ ሲኒማ እየኮመኮመ እንዲዝናና ይደረጋል፡፡
- እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በአዘቦት ቀን ሕዝቡ ጥሩ ጥሩ ምግብ ቤቶች እየገባ እንዲዝናና ማድረግ ሌላኛው ሥራው ነው፡፡
- መልካም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስለዚህ በከተሞቻችን ያሉትን የምግብ ቤቶችና የሆቴሎች አቅም በመገንባት ቢቻል ደግሞ፣ የውጭ ብራንዶችን እያስገባን የሕዝቡን የደስታ መጠን መጨመር አለብን፡፡
- ይህን ሐሳብ ለሚመለከተው አካል እናቀርባለን፡፡
- እንዲህ በማድረግ ሕዝቡን በማስፈንጠዝ ከችግር ማላቀቅ እንችላለን፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ግን ይኼንን ትልቅ ተቋም ማን ሊመራው ይችላል?
- እውነት ለመናገር እኔ እንኳን ይህንን ተቋም መምራት ይከብደኛል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እንደነገሩኝ ከሆነ ይኼ መሥሪያ ቤት ከተቋቋመ የአገሪቱ ችግር ሙሉ ለሙሉ ጠፋ ማለት ነው፡፡
- ምን ነካህ? 11 በመቶ የሚያድገው ኢኮኖሚ ራሱ 111 በመቶ ማደግ ይጀምራል፡፡
- እሱን እኮ ነው የምልዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ዋናው ጥያቄ ማን ይምራው የሚለው ነው?
- ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሰሞኑን እንዳየኸው ሚኒስትሮቻችን ዶክተሮች፣ ኢንጂነሮች፣ ኮሚሽነሮች፣ ዶክተር ኢንጂነሮችና ከፍተኛ ማዕረግ ያላቸው ናቸው፡፡
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስለዚህ ይህን ተቋም ሊመራው የሚገባው ሰው ሁሉንም ማዕረግ የያዘ መሆን አለበት፡፡
- ምን ዓይነት ማዕረግ ያለው?
- ብርጋዴር ኮሚሽነር ጄኔራል ዶክተር ኢንጂነር!