Friday, August 19, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  ‘እሳት ቢያንቀላፋ ገለባ ጎበኘው…’

  ሰላም! ሰላም! የሰው ጠላቱ ‘ትናንትና ዛሬው ነው’ ሲሉ ሰማሁ። ለመስማትና ለማየት ፈጥሮኝ መቼ ነገር ያልፈኛል። እንደኔ ለድለላና ለነገር ከተፈጠራችሁ ታክሲ፣ አውቶብስ፣ ባቡር፣ ሀብት፣ ንብረት፣ መሬት ያመልጣችሁ እንደሆነ እንጂ የተባለውና የሚባለው አያልፋችሁም። እናም ሰው ነው አሉ በትዝታና በተስፋ መሀል ተጠልፎ ያላለቀ ወስከንባይ ሲሉ ሰማኋቸው። መሶቡ ኑሮ መሆኑ ነው። አቤት ክዳን ያጣ መሶብ ዘንድሮ መብዛቱ። ደግሞ ከሁሉ ከሁሉ መሶቡ ሲኖር እንጀራው መጉደሉ፣ እንጀራው ሲገኝ አንድም ሻግቶ አንድም ኮምጥጦ አልታኘክ ማለቱ። ያገኙትን ይዘው ከዚያ ብልጥ ልጅ የያዙትን ይዞ እሪ ማለትን ተክነን ስንጮህ እንዳልኳችሁ ተጠልፈን፣ ቀልመን ያላለቅን ወስከንባይ ነንና ሌማቱም ጎጆውም ክፍት ውሎ ያድራል። ክፍት ይዋል ክፍት ይደር ብለው ሲመርቁ ቤቱም ክፍት አደረ ሰዎቹም አለቁ አለ ያገሬ ሰው እያሉ ባሻዬ በዚህ ሰሞን ሲተክዙ ነበር።

  እሳቸውም አንዱ የትናንት ተጠቂ መሆናቸው ነው። ደግና ክፉን አሳልፈው፣ ያለአቻ ያለ ብጤ ብቻቸውንም ቀርተው በትዝታ ወዲያ በርቀት እየተሰደዱ ያለቁ ዘመዶቻቸውን ይቆጥሩና ይተክዛሉ። የሚገርመው አንድ የሃያ ዓመት ወጣትና እሳቸው እኩል ወደ ትናንት አፍጠው ትካዜያቸው ሲመጣጠን ማየት ነው። ይገርማል ልበል እንጂ ሌላ ምን እላለሁ? ታዲያ በመገረም ደጅ የሰው ሰው ትካዜና ትዝታ እያያችሁ ስታልፉ በተቃራኒው ዘመንና ዘመነኞች ቆመው ትታዘባላችሁ። ዘመኑ ያው የገንዘብ ነውና የመረጃ ነው። ሰውም የዚህ ዘይቤ ጀሌ ሆኗል። የገባውም ያልገባውም መሆኑን ታልፉትና ትካዜውን ስታጠኑ፣ የዚህኛው ጭንቅ ነገ መሆኑን ትታዘባላችሁ። ነገ ይህን ቋጥሬ ያንን ፈትቼ፣ ያቺን አገንትሬ ያንን ፈልጬ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅቼ፣ አምታትቼ፣ ተምታትቼ … በቃ ነገና የነገ ትካዜ። በተስፋና በትዝታ መሀል የፈዘዝን አበባዎች። ዋ ሰው መሆን!

  ምን ልላችሁ ነው መሰላችሁ? አሁንና አሁንን የሚኖር ሰው ጠፍቶብኝ ተቸግሬያለሁ። አንድ ደላላ ወዳጄን እንዲህ ብለው፣ ‹‹ማናት አሁን?›› ብሎኝ አረፈው። ‹‹አሁን ናታ አሁን አሁን…››፣ ስለው አሁን አሁንን እየተካው እኔ ራሴ አሁንን መጨበጥ አቃተኝ። በል ተወው ብዬ የቤቷን ቁሳቁሶች እንዳሻሽጥላት ፈልጋ የደወለችልኝ ገር ቢጤ ደንበኛዬ ዘንድ ደወልኩ። ና ስትለኝ በጥቆማ ቤቷ ደረስኩ። ገባሁ። ቤቱ ያምራል። የቁሳቁሱ አቀማመጥ፣ የሶፋው እጥር ምጥን ብሎ ግርማ መድፋት፣ ፅዳቷና አያያዟ አስገርሞኝ ‘ለምን ዕቃ መሸጥ ተፈለገ?’ ብዬ ራሴን ጠየቅኩ። ያው እንደምታውቁት የዘንድሮ ኑሮና ሰው ግድ ሆኖበት በሳንባው ይተነፍሳል እንጂ ዋናው መተንፈሻው አንጀቱ ሆኗል።

  የሆነ ነገር እርር ድብን እንዳደረጋት ከገጿ መጠቋቆር ገብቶኛል። ሳልጠይቃት ጀመረችልኛ። እኔ እኮ አንዳንዴ ከድለላዬ ጎን ለጎን ጆሮዬን ማከራየት ብጀምር ራሱ ሳይጠቅመኝ አይቀርም። “ይኼውልህ ባሌን ጊዜ ለወጠው። ልንስማማ አልቻልንም። ሳገባው እኮ እንዴት ያለ ሸጋ፣ ጨዋ፣ መካሪ፣ ለሰው ደራሽ ነበር መሰለህ? ታዲያ ምን ያደርጋል ይኼን ቅጠል መብላት ለመደልህና አመሉ እያደር ተቀያየረ። ጭራሽማ አንድ ቀን ማታ ሲገባ ጃኬቱ ጥንብ ጥንብ ይላል፡፡ ሲጋራም ያጨስልሃል ለካ? ተው አልኩ… እሺ አለ። ይሰበሰባሉ … አሉት መድረሻ ያጡ ጓደኞች፡፡ ተሰብስበው ይኼን ቅጠል ሲበሉ መዋል ነው። መርካቶ ሱቅ ነበረው። ሲከስር ነው እንዲህ መሆን የጀመረው። እኔም ትዕግሥቴ አለቀልህና ሴቶች ጉዳይ ሄጄ ከሰስኩት፤” ስትለኝ ልቤ ቀጥ። ለካ ባለትዳሮች እንድሸመግላቸው መደወል ያቆሙት እዚህ ተደርሶ ነው። ‘ምንድነው ቀለበት ምንድነው መሀላ…’ ያለው ለካ ወዶ አይደለም ያ ዘፋኝ እናንተ!

  - Advertisement -

  “እሺ?!” እያልኩ እኔም ጆሮዬን ጣል። “ምን እሺ አለው? ይኼ መለማመጥ፣ መርመጥመጥ ድሮ በእናቶቻችን ዘመን ቀረ እኮ። መጥሪያዬን ይዤ መጣሁና ጎረቤት ሰብስቤ ስሰጠው፣ አፈር ልብላለት ቀኑን ሙሉ ቁጭ ብሎ ሲያለቅስ ዋለ። ይኼን ጫት፣ ሲጋራና መጠጥ ካልተውክ እፈታሃለሁ አልኩት። ዝም ብሎ ማልቀስ። ምን ያስለቅስሃል? ስለው ምን እንዳለኝ ታውቃለህ ጫት መብላት ተው የምትይኝ ሥጋዬን በልቼ እንዳልቅልሽ ነው ወይ አይለኝ መሰለህ? ይኼው ድፍት ያርገኝ ስልህ። ለካ ለሱሱ ኖሯል ያለቅስ የነበረው። ይኼው ዛሬ ካጠገቡ አገኘው። በልማ ይህቺን ቀማምስና ይኼን የምታየውን ዕቃ በሙሉ ጠቅልሎ የሚገዛ ሰው ካገኘህ ፈልገህ አገናኘኝ፤›› አለችኝ።

  የጎረስኩት ጉሮሮዬ ላይ ወገቡን ይዞ ቆሞ ትን ቢለኝ ተንደርድራ ሄዳ ውኃ ቀድታ አመጣች። ውኃ አቀዳዷን ሳየው ባሏን አሰብኩና አዘንኩ። መብትና መብተኞች የጠለዙት የፉከራ ኳስ ሜዳውን አልፎ የት እንደወደቀ አየሁ። አመመኝ ስላችሁ፣ አታምኑኝም አመመኝ። ማንጠግቦሽን እያሰብኩ ዝም ብሎ መተከዝ። በልዩነት የመቻቻል ዘመን ለካ በእኛ ጫንቃ ላይ የተንጠላጠለች የፕሮፓጋንዳ ቃጭል ናት አልኩኝ። ኪል ለማድረግ አንዴ መብት ጽሕፈት ቤት ሄደን ገፋ ማድረግ ነው። በቃ! በረባ ባልረባው ቅድሚያ የሚሰጠውን በማጓተት፣ ወልደን ከብደን፣ በልተን ጠጥተን፣ ኖረን ኖረን እንዲሁ ቻው ቻው ሆነና ቀረ የእኛ ነገር። የሚቻለኝን አደርጋለሁ ብዬ ስወጣ የመጨረሻ ልጇ ከመኝታ ክፍሏ ብቅ ስትል አየኋት። እንግዲህ ወልዷል ካሉ ይመስላል አይገድም ነውና ‘ቁርጥ አንቺን’ ብዬ ሄድኩ። ጣምራ አጣሹ ጎጆ በቅዳጅ ወረቀት እንዴት መልከስከሱን እንደቀጠለ ታዘቡልኝማ። እም ነው አሉ!

  ይህ በእንዲህ እንዳለ ብዬ ከጉድ ጉድ መዝለሌን ልቀጥል እንጂ ምን አደርጋለሁ? ‘ንፋሱ ይነፍሳል እኔም እነፍሳለሁ፣ አልጠገብኩምና ስስታም ነኝና እንደ እውር ዝንጀሮ ዛፍ ላይ ተንጠልጥዬ እወዘወዛለሁ’ ያለው ማን ነበር? ንፋሱ ነገር ዛፉ ኑሮዬ መሆኑ ነው። ሰምና ወርቁን ለምን ነገርከን ለምትሉ እኔም እላለሁ፡፡ እግሊዝኛ ፈተና ብቻ ነው እንዴ የሚሰረቀው? ታዲያስ! እናላችሁ ያ ያልኳችሁ ደላላ ወዳጄ ደወለልኝ። ምነው ስለው ጣቢያ ነኝና ድረስልኝ አለኝ። ደግሞ ምን ውስጥ ገባ ብዬ በዋስ የመውጣት መብት ካለው የማስይዘው ገንዘብ ይዞልኝ እንዲቀድመኝ ለባሻዬ ልጅ ደወልኩ። ስደርስ ጉዱን ሰማሁ። ሰዎቹ ቤቱን ተከራይተውት ኖሯል። የሐሰት ካርታ አሠርተው በአየር ላይ ሲሸጡት ወዳጄ አሻሻጩ ሆኖ ተውኗል። ባለቤቱ የመኖሪያ ፈቃዱን ለማደስ አሜሪካ ነበር አሉ።

  ዕድሜ ለግሎባላይዜሽን ሸገር ላይ እየበላን እየጠጣን የመኖሪያ ፈቃድ የምናድሰው ስቴት ሄደን ሆኗል። ይኼንንስ ማን አየብን? አይደለም ነው? ኧረ ነው በሉ ተዉ ኋላ ‘በኮምፕሌክሳምነት’ ተጠርጥራችሁ ቪዛ እንዳትከለከሉ። ቂቂቂ! ልሳቅ እንጂ በገዛ ጥርሴ። አሉ አይደል ፎርጅድ ሳቅ አስለምደውን ነገር ያበላሹብን። ሳቋ ላይ ብንቀጣ ኖሮ፣ ብንማማር ኖሮ የሐሰት የይዞታ ካርታ ማዘጋጀት ላይ አንደርስም ነበር እኮ ጎበዝ። ሳይቃጠል በቅጠል እንዲል ተረቱ ብንል ዳሩ ማን ሰማን። የአንድ አካባቢ ተረትና ፍልስፍና አገር አይወክልም መባባል ጀምረን አልደማመጥ አልን። እናማ ደላላው ወዳጄ ምንም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ በምርመራ ተረጋግጦ ዋስ ሆኜ አስወጣሁት። ወዳጄ በሆነው ነገር እጅግ አዝኖ ስለነበር የቤቱን ሕጋዊ ባለቤት አግኝቼ እግራቸው ሥር ሳልወድቅ አልተኛም አለ። ብዙ አይደለም እንጂ አንዳንዴ እንዲህ ያለም አለ እሺ?! አዎ አንዳንድ አለን አይዟችሁ!

  በሉ እንሰነባበት። እኔ፣ የባሻዬ ልጅና ደላላው ወዳጄ ሆነን ሰውዬውን ስናፈላልግ ስኳራቸው ሰማይ ነክቶ ሆስፒታል መተኛታቸውን ሰማን። ተኝተውበታል ወደተባለው ሆስፒታል ለመጓዝ ታክሲ ተሳፈርን። ታክሲ ውስጥ የሚወራው ደግሞ ተሰርቋል ተብሎ ስለተቋረጠው የዘንድሮ ማትሪክ ፈተና ነው። ‹‹ምን ያልተሰረቅነው ነገር አለ ዘንድሮ?›› አለ የባሻዬ ልጅ። ወዳጄ ምነው ግን እንዲህ ዓይን ያወጣ ሌብነት ወረሰን? ያልነበረብንን? እያለ ሆስፒታል ደረስን። ከስንት ጥበቃና አደብ መግዛት በኋላ ገብተን ሰውዬውን አየናቸው። ትንሽ ቢበሳጩበትም ትህትናውና ሥርዓቱን አይተው ወዳጄን፣ ‹‹ይቅር ብዬሃለሁ፤›› አሉት። ‹‹አሁን ደህና ነዎት?›› ስላቸው፣ ‹‹ነኝ ልበል እንጂ ልጄ። በገዛ ርስቴ በገዛ ቤቴ፣ ፈጣሪ ባልተረሳበት አገር፣ ይሻላል በሚባል አማኝ ወገኔ እንዲህ ስደረግ ድርቅ ብዬ መቅረት አልነበረብኝም? እኔ እኮ አሜሪካ አገር አርባ ዓመት ኖሬያለሁ። ሃያ ስምንቱን ተወው አትቁጠረው። እንደ አትላስ ምድርን ከእነምናምኗ ተሸክሜ የኖርኩበት ነው። መትረፌን ሳይ ዕድሜ መቀጠሉን፣ ብርታቴን ሳይ እግዜር አገርህ ግባና የላብህን ፍሬ በልተህ ደስ ብሎህ ሙት ብሎኝ ነው ብዬ አገሬ መጣሁ። ይኼው ስመጣ! ይኼው አልጋ ላይ! ያን ሁሉ ዘመን ቀን ከሌት ስባትል የማላውቀው የጤና ቀውስ፣ ጉንፋን የማያውቀው ሰውነቴ ይኼው!›› ብለው ሲቃ ያዛቸው።

  ምን ይባላል? እግዜር ይማርዎት ብለን ወጣን። ቋንቋ ገለባ ነው የተባለው ያኔ ታወቀኝ። ‹‹ይኼው ነው አገሬ…›› እያለ የባሻዬ ልጅ እንደ እብድ ሲያደርገው ዛሬ ካላነጋ አይገባም ብዬ በጊዜ ወደቤቴ ተሰበሰብኩ። እስኪ ራሳችሁን እየጠበቃችሁ ጎበዝ። ቤቱ፣ ፈተናው፣ የተፈጥሮ ሀብቱ፣ የሕዝብ ሀብትና ንብረት ተበዝብዞ ያለቀ እንደሆነ እኮ የለመደ አርፎ አይቀመጥም። ምን ይታወቃል በቁም የሚሸጠን ይመጣ ይሆናል። ‘ትናንትን እንዳላይ ትዝታው ጋርዶኛል፣ ነገን እንዳልጨብጥ አልነጋ ይለኛል፣ አሁንም አሁንም አሁን የት ይገኛል’ የሚለውን ግጥም በለሆሳስ ተወጣሁት፡፡ በለሆሳስ ውስጥ ሆነን አንዳንድ ነገሮችን ስናወጣ ስናወርድ የአገር ጉዳይ፣ የትውልዱ ዕጣ ፈንታ፣ ከትናንትናና ከዛሬ ይልቅ ነገ፣ ምናለፋችሁ ሁሉም ነገር ያሳስባል፡፡ በደላላነት ዘመኔ እንደዚህ ዘመን የሚያስፈራ አጋጠሞኝ አያውቅም፡፡ ራስን መውደድና ለራስ ሁሉን ጥሩ ነገር መመኘት እንዳለ ሆኖ፣ ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነት ውስጥ መዘፈቅ ግን ያስጠላል፡፡ መንገዱ ላይ በፍጥነት በመንቀዥቀዥ በአቋራጭ የመበልፀግ ሱስ የተፀናወታቸውን ስታዩ፣ በአጭር መቅረትም አለ የሚባለውን ምክር ንፋስ እንደ ገለባ ይበትነዋል፡፡ አቋራጭ ናፋቂና ገለባ አንድ መሆናቸውን ማን ይንገርልን? ገለባን እሳት አጭር እንደሚያደርገው በአቋራጭ የሚበለፅገውንም የሚያበራየው አለ፡፡ ‘እሳት ቢያንቀላፋ ገለባ ጎበኘው…’ እንበል እንዴ? መልካም ሰንበት!  

  Latest Posts

  - Advertisement -

  ወቅታዊ ፅሑፎች

  ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት