[የክቡር ሚኒስትሩ ሹፌር ከቤታቸው ወደ ቢሯቸው ሊወስዳቸው መጣ]
- ምን ሆነሃል ዛሬ?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ሰላምታም የለም እንዴ?
- እዚህ አገር ምን ሰላም አለ ብለው?
- ይህቺ አገርማ ወፍ ራሱ የማይጮህባት ሰላማዊ አገር አይደለች እንዴ?
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር ሰላምማ ከጠፋ ቆየ፡፡
- መቼም አንተ ሁሌም መዓት ነው የምታወራው?
- ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ መንግሥት ለሕዝቡ አባት ነበር የሚመስለኝ፡፡
- አባት ብቻ አይደለም፤ እናትም፣ እህትም፣ ወንድምም፣ አክስትም፣ አጐትም፣ ብቻ በአጠቃላይ ዘመድ ነው፡፡
- ለእኔ ግን ዘመድ ሳይሆን ጠላት ነው፡፡
- አንተ አፍራሽ እንደሆንክ አውቃለሁ፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ይኸው መንግሥት አባት ስለሆነ አይደል ኮንዶሚኒየም ቤት የሚገነባው?
- እ…
- አባት ስለሆነ አይደል ባቡር የሚገነባው?
- ወይ ባቡር?
- አባት ስለሆነ አይደል ግድብ የሚገነባው?
- እኔ መቼ ግድብ ናፈቀኝ?
- አፍራሽ ነሃ፡፡
- አባት ስለሆነ አይደል መንገድ የሚገነባው?
- ክቡር ሚኒስትር አልገባዎትም፡፡
- ምኑ ነው ያልገባኝ?
- እኔን መንግሥት እያማረረኝ ነው፡፡
- እኮ ምን አድርጐ?
- ይኸው የገቢ ግብር ይስተካከላል ብዬ ብዙ ገንዘብ ተበድሬ ነበር፡፡
- እና ምን ሆነ?
- መንግሥት ቀለደብኝ፡፡
- የገቢ ግብሩ አልተስተካከለም?
- እሱማ ተስተካክሏል፡፡
- ይኸው አባት ማለት እንዲህ ነው፡፡
- ኧረ እኔ ቢቀርብኝ ይሻለኝ ነበር፡፡
- ወርቅ ሲያቀርቡልህ ፋንድያ የምትል ሰውዬ?
- መቼ ገባዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ምኑ ነው ያልገባኝ?
- ይኸው አከራዬ የገቢ ግብሩ ይስተካከላል የሚለውን ወሬ ሰምቶ፣ በወር 300 ብር ጨምሮብኛል፡፡
- ስጥ ይሰጥሃል አይደል እንዴ የሚለው?
- ትናንትና አስቤዛ አድርጌ የ500 ብር ጭማሪ መጥቶብኛል፡፡
- እና መንግሥት የጨመረልህ እኮ ለሌላው ፈሰስ እንድታደርግ ነው፡፡
- ምን አሉኝ?
- ስማ የተጨመረልህን ገቢ እንደ ግድብ መገደብ ነው የምትፈልገው?
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር እኔንማ ከህዳሴ ግድቡ ጋር ባያነፃፅሩኝ ጥሩ ነው፡፡
- ለመሆኑ ምንድን ነው እንደዚህ የምታማርረው?
- ክቡር ሚኒስትር መንግሥት ቀለደብኝ አልኩዎት፡፡
- እኮ እንዴት ሆኖ?
- ይኼ ሁሉ ጭማሪ መጥቶብኝ ለእኔ ግን በገቢ ግብሩ ጭማሪ የተደረገልኝ መቶ ምናምን ብር ነው፡፡
- ትቀልዳለህ?
- ምን እኔ እቀልዳለሁ? መንግሥት ግን ቀለደብኝ፡፡
- ባክህ አትቀልድ፡፡
- እኔማ ስም አውጥቼላችኋለሁ፡፡
- ማን አልከን?
- ቻርሊ ቻፕሊን!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሯቸው ሲገቡ አማካሪያቸውን አገኙት]
- ምነው ተቆጡ ክቡር ሚኒስትር?
- አቃጣይ ሁላ ተሰብስቦ ምን ላድርግ?
- ማን ነው ያቃጠልዎት?
- ይኼ ሹፌሬ ነጅሶኝ ነዋ፡፡
- ምን አልዎት?
- እኛ ስንት ዓመት ፈጅቶብን ያዘጋጀነውን የገቢ ግብር ቀልድ ነው አለን፡፡
- እውነት?
- እንዲያውም ቻርሊ ቻፕሊን ነው ያለን?
- ሚስተር ቢን ማለቱ ነው?
- አንተም መቀለድ ጀመርክ?
- ኧረ ቀልዴን አይደለም እውነቴን ነው፡፡
- እንዴት ማለት?
- ሹፌርዎት እውነቱን ነው፡፡
- ምኑ ነው እውነቱ?
- የገቢ ግብሩ እኮ በጃንሆይ ዘመን የወጣ ነው፡፡
- አየህ? ደርግ ምንም ሳያሻሽለው እኛ ግን አሻሻልነው፡፡
- ወይ ማሻሻል?
- ደርግ አንዴ እንኳን ሳያሻሽለው ይኸው እኛ በ25 ዓመታችን ማሻሻል ችለናል፡፡
- ለመሆኑ 25 ዓመት ሙሉ ምን ስትሠሩ ነበር?
- ምን ያልሠራነው ነገር አለ?
- እኮ ምን?
- አሁን በደርግ ጊዜ መንገድ ነበር?
- እ…
- እኔ የማውቀው መንገድ የማርያም መንገድ ብቻ ነበር፡፡
- አይ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አሁን በደርግ ጊዜ ግድብ ነበረ?
- እ…
- ደርግ ሐሳብን ከመገደብ ውጪ ምን ያውቃል?
- ሌላስ?
- ይኸው በዚህ ዘመን አይደል ሚዲያዎች እንደ አሸን የፈሉት?
- ምን አሉኝ?
- ሚዲያ እንደ አሸን የፈላው?
- ታዲያ ተዘጉ እኮ፡፡
- በአግባቡ አልሠራም ሲሉ ምን እናድርጋቸው?
- አዬዬ፡፡
- ባቡርስ ብትል በዚህ ዘመን አይደል የተሠራው?
- እኔ እንዲያውም በደርግ ዘመን ድሬዳዋ በባቡር ነበር የምሄደው፣ አሁን ግን በቅጥቅጥ አውቶብስ ነው የምሄደው፡፡
- ባቡሩ በቅርቡ ያልቃል ስልህ?
- እኔ ግን ክቡር ሚኒስትር በዚህ ዘመን ብዙ ችግሮችን አይቻለሁ፡፡
- እኮ ምን?
- ሙስና፡፡
- እ…
- ኪራይ ሰብሳቢነት፡፡
- እ…
- የመልካም አስተዳደር ችግር፡፡
- እ…
- የሰብዓዊ መብት ጥሰት፡፡
- በእሱ እንኳን ከደርግ እንሻላለን፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ከደርግ ጋር መወዳደር ለምን አታቆሙም?
- ከማን ጋር እንወዳደር ታዲያ?
- ከራሳችሁ ጋር!
[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ቢሯቸው ገባች]
- እንግዳ ሊያናግርዎት ይፈልጋል?
- የምን እንግዳ ነው?
- የመሥሪያ ቤታችን ሠራተኛ ነው፡፡
- እኮ ማን ነው?
- የጥበቃ ሠራተኛ ነው፡፡
- እኔ የጥበቃ ሠራተኛ ላናግር?
- ክቡር ሚኒስትር ምን አለበት?
- ስሚ ሌላ ሰው ያናግር፣ እኔ ጊዜ የለኝም፡፡
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር ለጥቂት ደቂቃ ነው የሚያናግርዎት?
- ሌላ ሰው ለምን አያናግርም?
- ችግሩን እርስዎ እንዲፈቱለት ፈልጐ ነው፡፡
- እሺ አስገቢው፡፡
[የጥበቃ ሠራተኛው ቢሯቸው ገባ]
- ለቅሶህን አቁምና ንገረኝ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በልማታዊ መንግሥት ይዤዎታለሁ፡፡
- ለቅሶውን አቁም አልኩህ እኮ፡፡
- በቃ በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ስም ነፃ ያውጡኝ፡፡
- ምን ሆነህ ነው?
- አፈረሱብኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሕንፃህን ነው?
- ኧረ ሕንፃ የለኝም፡፡
- ቪላ ነው ያለህ?
- ኧረ እኔ ደሳሳ ጐጆ ነው ያለኝ፡፡
- ወፍ ነህ እንዴ አንተ ጐጆ ቤት ውስጥ የምትኖረው?
- ይኸው ክቡር ሚኒስትር አሞራዎች ጐጆዬን አፈረሱብኝ፡፡
- ማን ነው ያፈረሰብህ?
- ግብረ ኃይሉ፡፡
- እንዴ አሸባሪ ነህ እንዴ አንተ?
- አይ ክቡር ሚኒስትር እሱኛውን ግብረ ኃይል አይደለም የምልዎት?
- ታዲያ የትኛው ግብረ ኃይል ነው?
- የወረዳው ግብረ ኃይል፡፡
- ለምን አፈረሱብህ?
- በሕገወጥ መሬት ወርሬ ነበር፡፡
- እሺ የእኔ ጉንዳን፣ የራስህን አገር ትወራለህ?
- ምን አሉኝ?
- እንዴት የራስህን አገር ትወራለህ?
- ክቡር ሚኒስትር የቤት ኪራዩ ግራ ሲያጋባኝ ምን ላድርግ?
- ቤት ኪራይ ቢያስቸግርህ ሕገወጥ መሆን አለብህ?
- ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር
- አንተማ ማስተማሪያ መሆን አለብህ፡፡
- አሁን እኮ ቤት የለኝም፡፡
- በቃ ኮንዶሚኒየም ቤት መጠበቅ ነዋ፡፡
- እሱንማ ቤት አለህ ብለውኝ አልመዘገቡኝም፡፡
- አሁን በቃ ይመዘግቡሃል፡፡
- ለምን ብለው?
- ቤትህን ስላፈረሱት ነዋ፡፡
- መቼ ይመዘግቡኛል?
- የሚቀጥለው ዙር ላይ!
[የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ስልክ ደወሉላቸው]
- እንኳን ደስ አለህ፡፡
- ምን ተገኘ?
- ዛሬ ፓርቲ ነው የምናደርገው?
- ፓርቲ ነው የምናቋቁመው?
- የለም ድግስ እንደግሳለን፡፡
- እኮ ምን ተገኘ?
- ደብዳቤው ተጻፈ፡፡
- የሹመቱ ነው?
- የምን ሹመት?
- የፍቅር ነው ታዲያ?
- ሕጋዊ ሆንን፡፡
- እኔ ሕገወጥ ሆኜ አውቃለሁ?
- የዛሬ አሥር ዓመት አካባቢ የእህል ውኃዬ ሊያበቃለት ይችላል ብለህ የወረርከው መሬት ትዝ አለህ?
- አሥር ሺሕ ካሬ ሜትሩ?
- እህሳ፡፡
- እና ካርታ ሊሰጠን ነው?
- በሚገባ፡፡
- ምንድን ነው የምንሠራበት ታዲያ?
- ሪል ስቴት መንደር እንገንባበት እንዴ?
- እሱንማ ሁሉም ሰው እየሠራበት ነው፡፡
- ታዲያ ምን ተሻለ?
- ለምን ስታዲየም አንገነባበትም?
- እሱንማ ለመንግሥት ብንተወው አይሻልም?
- እኛ ምንድን ነን? መንግሥት አይደለን እንዴ?
- እሱማ ነን ግን ሁሉንም ሥራ ከመንግሥት ነጥቀን አንዘልቀውም፡፡
- እሱስ ልክ ነሽ፡፡
- ታዲያ ምን እንገንባበት?
- ፓርክ ለምን አንገነባበትም?
- ምን ዓይነት ፓርክ?
- የሚኒስትሩ ኢንዱስትሪያል ፓርክ!