Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ​ከልጅ ልጅ ቢለዩ…?!

  ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ሥልጣን ከተቆናጠጠ ሩብ ምዕተ ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን፣ በእነዚህ ዓመታት በተለያዩ ጊዜያት በርካታ አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች በመንግሥት ሲወሰድ ቆይቷል፡፡ መንግሥት በወሰዳቸውም የተለያዩ አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች ላይም ወጥ ያልሆኑ መሥፈርቶች የሚታዩ በመሆኑ፣ ከተለያዩ አካላት የሰላ ትችት ሲሰነዘርበት ሰንብቷል፡፡ መንግሥት ተመሳሳይ ለሆኑ ጉዳዮች ወጥነት የሌለውን መሥፈርት እየተጠቀመ ያሳለፋቸው አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች፣ በሕዝቡ ዘንድ ቁርሾ አየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡

  በቅርቡ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ቦሌ ቡልቡላ ወረገኑ በመባል በሚታወቀውና በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በሚገኙበት ሥፍራ፣ ሕገወጥ የተባሉ ቤቶችን መንግሥት የማፍረስ ዘመቻ ጀምሯል፡፡ የአዲስ አበባ የከተማ አስተዳደር የከፋ የመሬት ወረራ ተፈጽሞበታል ባለው በዚህ መንደር፣ በፀጥታ ኃይሎች የታጀበው የወረዳው አፍራሽ ግብረ ኃይል ሕገወጥ ቤቶች ናቸው ያላቸውን አፈራርሷል፡፡ በአካባቢው ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ ያለምሪት ቤት የሠሩ በርካታ ነዋሪዎች የሚገኙ ሲሆን፣ የከተማ አስተዳደሩ በወሰደው ዕርምጃም በርካታ ዜጐች ቤት አልባ ሆነዋል፡፡

  በሌላ በኩል ደግሞ ሰሞኑን እንደሰማነው፣ ከምርጫ 97 በኋላ በአገሪቱ በተፈጠረው ቀውስ ሳቢያ በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መንገድ የተያዙ በርካታ ይዞታዎች ሕጋዊ ሆነዋል፡፡ በወቅቱ በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና በተለይ በቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (ቅንጅት) መካከል በተፈጠረው አለመረጋጋት፣ በአዲስ አበባ በርካታ መሬቶች ያለመንግሥት ዕውቅና ተይዘዋል፡፡ በተለይ ከ1996 እስከ 1998 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት ውስጥ በከተማዋ መጠነ ሰፊ የሆነ የመሬት ወረራ ተካሂዷል፡፡ የከተማ አስተዳደሩም በወቅቱ በሕገወጥነት የሰፈረው ሕዝብ ብዛት ከፍተኛ በመሆኑና የተገነቡት ቤቶች ቁጥር በርካታ በመሆናቸው ምክንያት እንዲሁም በኅብረተሰቡና በኢኮኖሚው ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት እነዚህ ሕገወጥ ይዞታዎች ሕጋዊ እንዲሆኑ ወስኗል፡፡ በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ ከ1988 ዓ.ም. እስከ 1998 ዓ.ም. ግንቦት ወር ድረስ፣ በሕገወጥ መንገድ ቤት ለሠሩ ሰነድ አልባ ቦታዎች ካርታ ሠርቶ በመስጠት ሕጋዊ አድርጓቸዋል፡፡

  በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 ላይ የሰፈረው የእኩልነት መብት፣ ሁሉም ዜጐች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ በመካከላቸውም ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል ይላል፡፡ በዚህም ረገድ በዘር፣ በብሔር ብሔረሰብ፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት እንዳላቸው ተደንግጓል፡፡

  መንግሥት ሕጐችን፣ መመርያዎችንና ደንቦችን በማውጣት ሕዝቡን ያስተዳድራል፡፡ በዚህም መሠረት ዜጐች ምን እንደተፈቀደና ምን እንደተከለከለ በማወቅ ሕይወታቸውን ይመራሉ፡፡ ሆኖም ግን ሕጐች፣ መመርያዎችና ደንቦች በዘፈቀደ የሚተገበሩ ከሆነ በአገር ላይ ከፍተኛ ቀውስና ኪሣራ ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ ከመንግሥት መሠረታዊ ኃላፊነቶች መካከል ሕጐችን፣ መመርያዎችንና ደንቦችን በተገቢው ሁኔታ በማውጣት ወጥ የሆኑ አሠራሮችን መተግበር ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ግን በዘፈቀደ የሚኬድ ከሆነ፣ የምንሄድበትን መንገድ ወልጋዳ ከማድረጉም ባሻገር አገርን ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል፡፡

  ሰሞኑን በወረገኑ አካባቢ የፈረሱት ሕገወጥ ግንባታዎች በቦታው ላይ ከሦስት ዓመትና ከዚያ በላይ የቆዩ ናቸው፡፡ አሁን ቤቶች የፈረሰባቸው ዜጐች በይዞታቸው ላይ ትላልቅ የሆኑ ግንባታዎችን የገነቡ ናቸው፡፡ እነዚህ ይዞታዎች በሕገወጥ መንገድ የተያዙ መሆናቸው እየታወቀና መፍረሳቸው አይቀሬ መሆኑ እየታወቀ፣ ግንባታዎቹ ሲገነቡ ዝም መባሉ ያስተዛዝባል፡፡ በየወረዳው የሚገኙ የልማት ኮሚቴዎችና ደንብ አስከባሪዎች ለወትሮው ሚስማር ሲመታ ከደጃፍ የማይጠፉ ሲሆን፣ በዚህ አካባቢ ግን እንደዚህ ዓይነት ታላላቅ ግንባታዎች ሲገነቡ እንዳላየ መሆናቸው ያጠያይቃል፡፡ መንግሥት ለእነዚህ ሕገወጥ ግንባታዎች ውኃ፣ መብራት እንዲሁም መንገድ ሲሠራ ፀጥ ማለቱም ለባለይዞታዎቹ የልብ የልብ መስጠቱ ግልጽ ነው፡፡ እንዲህ መሆኑም በሕገወጥ መንገድ የተያዙት ይዞታዎች ኋላ ላይ ሕጋዊ ይሆናሉ የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ እዚህ ላይ እንዲሰመርበት የምንፈልገው ነገር ሕገወጦች ትክክል ናቸው እያልን ሳይሆን፣ በአንድም በሌላም ቢሆን ግን እንዲበረታቱ ተደርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ በሕግ ሥርዓቱና አፈጻጸሙ ላይ ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ ያሳያል፡፡

  ሌላው ነጥብ ደግሞ በሰሞኑ ሕገወጥ ቤቶችን የማፍረስ ዘመቻ ግዙፍ የአገር ንብረት ለብክነት ተዳርጓል፡፡ ምንም እንኳን ሕገወጦች እንዳይንሰራፉ ሕግ የማስከበር ድርጊቱ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ፣ ሕግን ለማስከበር ግን ይኼን ያህል መቆየቱ ግዙፍ የአገር ንብረት እንዲባክን አድርጓል፡፡ ከአገርና ሕዝብ ንብረት ባለፈ በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት አስከትሏል፡፡ መንግሥትም ጉዳት ከደረሰ በኋላ ሕግን ለማስከበር ከሚሯሯጥ፣ መጀመሪያውኑ ሕገወጦችን አደብ ማስገዛት ነበረበት፡፡

  መንግሥት እንደ መንግሥት ባለራዕይና የሩቁን ማየት ስለሚገባው፣ በየጊዜው ለሚፈጠሩ ችግሮች የአንቡላንስ አገልግሎት መስጠት ማቆም አለበት፡፡ በመሆኑም ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ችግሮች ሥር ሰደው ከፍተኛ ጉዳት በአገር ላይ ከድረሳቸው በፊት አስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

  ሕግን ማስከበር በተመለከተ ሰሞኑን የከተማው አስተዳደር ዕርምጃ በመውሰድ የ250 ይዞታዎችን ካርታ አምክኗል፡፡ ይኼ ዕርምጃ የተወሰደው በወቅቱ ግንባታ ባላካሄዱ አልሚዎች ላይ ሲሆን፣ ይህ በራሱ በጣም አበረታች ነው፡፡ መንግሥት ለልማት የሚሰጣቸውን ቦታዎች ሳያለሙ የአገርና የሕዝብ ሀብት ላይ የሚቀልዱ ባለሀብቶች ላይ እንዲህ ዓይነት ዕርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል፡፡ ሆኖም ግን አሁንም አንዳንድ ባለሀብቶች ለበርካታ ዓመታት ያለምንም ልማት ሰፋፊ ቦታዎችን እያጠሩ ሲያስቀምጡ የአስተዳደሩ ምላሽ ዝምታ ሆኗል፡፡ ስለዚህ መንግሥት በአንዳንድ ግለሰቦች ላይ ዕርምጃ እየሰወሰደ በሌሎች ላይ ደግሞ ዝም ማለቱ ወጥ የሌለው አሠራር መኖሩን ያመለክታል፡፡ ይህ ችግር በዜጐች መካከል ቅራኔ የሚፈጥር ሲሆን፣ መንግሥት የእንጀራ ልጅና የቤት ልጅ አለው ወይ? የሚል አስተሳሰብ ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ መንግሥት እንደዚህ ዓይነቱን የዘፈቀ አካሄድ ልጓም አበጅቶለት፣ ወጥ የሆነ አሠራር መዘርጋት አለበት፡፡ አለበለዚያ ‹‹የልጅ ልጅ ቢለዩ…›› የሚለውን ቢህል ሊያስከትል ይችላል፡፡           

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  ለኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸጥበት ታሪፍ ማሻሻያ ተደረገበት

  በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ስምምነቱ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያና የኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል...

  አዲስ አበባ እንዳይገቡ በተከለከሉ ዜጎች ጉዳይ የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ተወያይተው ችግሩ እንዲፈታ አደረጉ

  ለሳምንታት በርካታ ቅሬታ ሲነሳበት የነበረውና ከአማራ ክልል በደብረ ብርሃን...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...

  ለኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸጥበት ታሪፍ ማሻሻያ ተደረገበት

  በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ስምምነቱ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያና የኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ሁለተኛው ተርባይን ሥራ መጀመሩ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈጠረው ደስታ ቃላት ከሚገልጹት...

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን ነፃነትም ተምሳሌት ናት፡፡ የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የሚያኮራ ተግባር ፈጽመው ያለፉት፣ ከአገራቸው በፊት የሚቀድም...