Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ አንድ ወር ሲቀረው ጨፌ ኦሮሚያ 1.6 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ...

  የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ አንድ ወር ሲቀረው ጨፌ ኦሮሚያ 1.6 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አፀደቀ

  ቀን:

  ሰሞኑን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) የ2008 በጀት ዓመት ሊጠናቀቅ አንድ ወር እየቀረው 1.6 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አፀደቀ፡፡

  ጨፌ ኦሮሚያ ሰኔ 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ባካሄደው ጉባዔ ከተመለከታቸው ጉዳዮች መካከል የተጨማሪ በጀት ጥያቄ ይገኝበታል፡፡ የክልሉ መንግሥት የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ አንድ ወር ሲቀረው 1.6 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት እንዲፀድቅለት መጠየቁ ያልተለመደ እንደሆነ ለበጀት ስሌት ቅርብ የሆኑ ባለሙያዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

  የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ተሰማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የጨፌ ኦሮሚያ አባላትም ይህን ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡

  የጨፌ ኦሮሚያ አባላት የበጀት ዓመቱ አንድ ወር እየቀረው ይህን ያህል ገንዘብ መጠየቁ ለምንድነው? ሥራውንስ ልታከናውኑ የምትችሉበት ጊዜ አላችሁ ወይ? ብለው መጠየቃቸውን አቶ ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡

  አቶ ፈቃዱ እንዳብራሩት፣ በእርግጥ የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ አንድ ወር ብቻ ቢቀረውም፣ ክልሉ በአጭር ጊዜ ሊያከናውናቸው የሚገቡ ፕሮጀክቶች በማጋጠማቸው በጀቱ ሊፀድቅ ችሏል፡፡

  አስቸኳይ ከተባሉት ፕሮጀክቶች መካከል ኦሮሚያን ጨምሮ በመላ አገሪቱ ለተከሰተው በታሪክ ትልቅ የቆዳ ሽፋን ያለው ድርቅን ለመመከት የተዘጋጀው ተጠቃሽ ነው፡፡ የክልሉ መንግሥት በድርቁ የተጎዱ ወገኖችን በመደገፍ ላይ እያለም ከወትሮ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ መጣል በመጀመሩ፣ የክልሉን ሕዝብ ለተጨማሪ ጉዳት ስለዳረገው ምላሽ መስጠቱ አስቸኳይ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም በሕዝብ ተሳትፎ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች፣ ኅብረተሰቡ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት አስተዋጽኦ ማበርከት ባለመቻሉ፣ የግድ መንግሥት ፕሮጀክቶቹን አጠናቆ ሥራ ማስጀመር ይኖርበታል በማለት አቶ ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡

  አቶ ፈቃዱ ጨምረው እንደገለጹት፣ የተጀመሩ የግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል የዋጋ ለውጥ የታየባቸው በመኖራቸው ክፍያ መፈጸም አስፈላጊ በመሆኑ ተጨማሪ በጀት ፀድቋል፡፡

  የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የበጀት ሕግጋት የበጀት ዓመቱ ከመጠናቀቁ አንድ ወር እስኪቀር ድረስ ተጨማሪ በጀት ለጨፌ ኦሮሚያ ቀርቦ ሊፀድቅ እንደሚችል እንደሚደነግጉ አቶ ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡

  የክልሉ መንግሥት ይህንን ተጨማሪ በጀት የሚሸፍነው የክልሉ በተለይ ትላልቆቹ ከተሞች ከዕቅዶቻቸው በላይ ከሰበሰቡት ገቢ መሆኑ ታውቋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ቀጣዩን የ2009 ዓ.ም. በጀት በማዘጋጀት ላይ ሲሆን፣ ጨፌ ኦሮሚያ በቅርቡ ይህንን በጀት ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...