Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  የእኛ ነገርማ ገና ብዙ አለበት!

  እነሆ ጉዞ። ከትውልድ ትውልድ እየተቀባበልን ባቀናነው፣ ባፈረስነው፣ ባሳመርነውና በቆፈርነው ጎዳና ዛሬም በ’ኧረ መላ መላ’ ዜማ ጉዟችንን ጀምረናል። ‹‹አለመጠጋጋት የጠባብነትና የትምክህተኝነት አስተሳሰብ ማሳያ ነው። ሄይ . . . ጠጋ. . . ጠጋ. . .›› እያለ ወያላው ትርፍ ያግበሰብሳል። ‹‹ምን አስገለበጠኝ ወተቱን በጋን፣ ችዬ እገፋዋለሁ የማልለውን?›› ስትል መላ የጠፋት መላ የጠፋበት በበኩሉ፣ ‹‹ከቶ አንቺ አይደለሽም ጥፋቱ የእኔ ነው፣ እንደማይሆን ሳውቀው የምመላለሰው፤›› ይላታል። ችለው የማይገፉትን ወተታቸውን በጋን የገለበጡና እንደማይሆን እያወቁ በሞትና በሕይወት ጎዳና የሚመላለሱት፣ ‘እምጵ’ አፈር ልብላልህ’ እያሉ ከከተማ መኮንን እኩል ያቀነቅናሉ። እኛ መጨረሻ ወንበር የተሰየምን ወጣቶች ከቅኔውም፣ ከዋርካውም፣ ከመብቱም፣ ከወተቱም ስለሌለንበት፣ ‹‹አቦ ዲጄው ሊጀምር ነው ጣቢያውን ቀይርልን፤›› እያልን ሾፌሩ ላይ እንጮኸለን። “መቃሚያ ቤት መሰላችሁ?” በማለት ወያላው ተኮሳትሮ ወደ እኛ ዞረ። ‹‹የት ታውቀናለህ? አንተ ነህ ውሎና አዳራችንን የምትነግረን? ጣቢያ ቀይሩ ማለት እዚህ ያዳርሳል?›› አለው አንደኛው ከመሀላችን ቱግ ብሎ።

  ነፍሱን ይማረውና ከተማ መኮንን ‘ኧረ መላ መላውን’ ቀጥሏል። ‹‹ፀብ አብርዱ በቃ። ምናለባት ይኼንንስ ብንሰማ? የቸገረን እኮ በአገር ልጅ ለአገር ልጆች የሚበሰር መላ ነው። እስከ ዛሬ ያጣነውም እሱን ነው። እስኪ በኑሮ እስኪያድለን በዘፈን እንፅናና፤›› አለው ፊታችን የተሰየመ ቀጠን ረዘም ያለ ጎልማሳ። አጠገቤ የተሰየሙት ወጣቶች ሰከን አሉ። ሾፌሩ ይኼኔ፣ ‹‹ሰው ዘንድሮ ምን ነክቶት ነው ጣቢያዎችና ሥርጭቶቻቸው ላይ መግባባት ያቃተው?›› ሲል አጠገቡ የተሰየሙ ብርቱ አዛውንት፣ ‹‹እየተደናበረ ነዋ። ሁሉ ተሳዳቢ፣ ሁሉ ተቺ፣ ሁሉ ተንታኝ፣ ሁሉ ጽንፈኛ. . . ሆነ። የማሰብና የመናገር መብታችን ተጣሰ እያሉ በሌላ ጥግ ከእነሱ ጋር ቆሞ ያልተሳደበና ያልጮኸ ሁሉ ጠላት ይደረጋል፤›› አሉት። ይኼኔ ሾፌሩ፣ ‹‹ጋሼ እኔ እኮ ስለሬዲዮ ዘፈኖቻችን ነው ያወራሁት፤›› ሲላቸው፣ “እኔስ ታዲያ ስለምን አወራሁ?” ብለው አስፈገጉን። እውነት አይደል? ዘፈንና ጫጫታ አልበዛባችሁም?!

  ጥቂት እንደሄድን ደግሞ ከአዛውንቱ አጠገብ የተሰየመ ተሳፋሪ፣ ‹‹እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋልና አንድ ጨዋታ ላጫውታችሁ፤›› ሲሉ አዛውንቱ፣ ‹‹ማን ተጫወተ? ሳንነጋገር?›› አሉት። ‹‹እንዴ? ጋሼ ዝምታም እኮ ጨዋታ ነው። አሁን የማጫውታችሁም ተድበስብሶ በዝምታ ስለፀና እኩልነት ነው፤›› አላቸው። “እስኪ ቀጥል. . .” ተባለ። ጨዋታው እነ አያ አንበሳ መንደር ነው። ቀበሮ፣ በግና አያ አንበሳ ከዕለታት አንድ ቀን ከየማዕዳቸው ጠግበው እንደተነሱ መንገድ ላይ ተገናኙ። ጥጋብ ላይ ናቸውና በጥሞና የእግዜር ሰላምታ እየተሰጣጡ ተሳሳሙ፣ ተጨባበጡ። ቀበሮ ‘አያ አንበሳ ሰሞኑን ስፈልግህ ነበር’ ብላ ወሬ ጀመረች። ‘በደህና?’ አለ አያ አንበሳ የማረፊያ ቦታ እየመረጠ። በአካባቢያችን ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ የመጣው ሁከትና ሰላም ማጣት በእጅጉ እያሳሰበኝ ነው። እርስዎ ደግሞ ከእኔ በላይ እንደሚያሳስብዎ አልጠራጠርም። ‘አይደለም እንዴ እሜቴ?’ አለች ወደ በግ ዞራ።

  ‹‹ልክ ነው። መቼም የዚህ ሁሉ አለመረጋጋትና ሰላም ማጣት መንስዔው የሁላችንም የአመጋገብ፣ የቋንቋና የአፈጣጠር ልዩነት ነው። ልዩነታችንን ብናቻችል ይኼ ሁሉ ነገር አይመጣም፤›› ስትል አንበሳ ቀበል አድርጎ፣ ‘ድንቅ ንግግር ነው። ደግሞ እንዴት ነው ሁለታችሁም ያማረባችሁ?’ እያለ በአንክሮ ማዳመጡን ቀጠለ። ቀበሮም የአንበሳን ከልክ በላይ መጥገብና የምትለውን ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ዓይታ፣ ‹‹ታዲያ አያ አንበሳ ከዛሬው ቀን ጀምሮ ሁላችንም ሳር በል ብንሆን ምን ይመስልሃል? የሆዳችንን ነገር ከተቆጣጠርን በሌላ በሌላው መቻቻል አይከብደንም’ አለች። አያ አንበሳ በቀረበው ሐሳብ ተስማማ፤›› እያለ ሰውየው ተረቱን ሲቀጥል፣ ‹‹ኧረ አሳጥረው በፈጠረህ የፖለቲካ ፓርቲ መግለጫ አስመሰልከው እኮ?›› ብሎ አንዱ ከመሀል መቀመጫ ጮኸበት። ነገሩ፣ ተረቱ፣ ፀቡ፣ ኩርፊያው፣ መግለጫውና ሠልፉ ስለሚረዝምብን ይሆን ትዕግሥት ያጣነው?

  - Advertisement -

  ታክሲያችን ጉዞዋን ቀጥላለች። ባለተረቱ ተናዶ፣ ‹‹ምናለበት ብታስጨርሱኝ? ፌስቡክ ላይ ካልሆነ በቃ ንግግራችንን ጀምረን መጨረስ አንችልም ማለት ነው?›› ብሎ ተቆጣ። ‹‹ታዲያ በየት አገር ነው አንበሳ ሳር ለመጋጥ የሚደራደረው?›› አለች ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየመች ወይዘሮ። “ሁሉንም ስጨርሰው ታውቁት የለ?” ብሎ አፈጠጠ። የሰውየውን ሁኔታ ዓይታ ደግሞ አንዷ፣ ‹‹ሁልጊዜ ሰዎች የእኛን አስተሳሰብ ለምን አልተቀበሉም? ወይም ለምን እንደ እኛ አላሰቡም ብለን ሰዎችን አንቃወማቸው እባካችሁ። ከተሳሳቱ ሊመለሱ ወይም ምናልባት ‘ካፈርኩ አይመልሰኝ’ ብለው በእዚያው ሊቀጥሉ ይችላሉ። አካሄዳችውን ጊዜ ሰጥቶ ማየት መልካም ነው፤›› ብላ ስታበረታታው ጉሮሮውን ይጠራርግ ነበር። “እሺ በል ቶሎ ንገረን!” ጮኸ አጠገቤ የተቀመጠው፡፡

  ‹‹ኋላማ ሁሉም ሆዳቸው ጎደለና ሳር ሊግጡ ሜዳ ተገናኙ። እሜቴ በግ አጨድ አጨድ፣ ሽርክት ሽርክት እያደረገች ሳሩን ስታላምጠው ቀበሮ የቱን ግጣ የቱን እንደምትተወው ጨነቃት። ይኼኔ ወደ በግ ጠጋ ብላ ድንገት ሳይታሰብ ሆድ ዕቃዋን ዝርግፍ አደረገችው። በዚያው ቅፅፈት አያ አንበሳ ከተፍ ማለት። ‘ምነው ቀበሮ ምን ተባብለን ነበር?’ ቢላት ‘ምን ላድርግ እሜቴ በግ በእኩልነት አታምንም። ልምድና ተሞክሮዋን በመጠቀም በደቂቃዎች ውስጥ የጋጠችው ሳር የወር ይሆናል’ አለችው። ‘እንዲያማ ከሆነ ደግ አድርገሻል’ ብሎ ተራውን አያ አንበሳ ቀበሮ ላይ ጉብ ብሎ ሲገነጣጥላት፣ ‘ምነው አያ አንበሳ ምን ተባብለን ነበር?’ አለች ቀበሮ ተራዋን ውጪ ነፍስ ግቢ ነፍስ ሆና፡፡ ‘እኩልነት ያለ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እኮ አይሠራም’ አላታ! ምን ለማለት ፈልጌ ነው መሰላችሁ. . . ሲል፣ “በቃ! በቃ! በቃ!” እያሉ ሁሉም ጮኹበት፡፡ ደግሞ እንደገና በምፀት ሳቅ አሽካኩ፡፡ ‹‹ምነው? የሰው ዘፈን ደጋግመው እየዘፈኑ የሰው ቀልድ ደግመው እየቀለዱ ታዲያ እስከ መቼ? ሥራ መፍጠር ቢያቅተን ተረት ለምን አንፈጥርም ብዬ እኮ ነው፤›› እያለ አሁንም ተራቹ ሰቅዞ ሲይዘን  እንገላገለው ብለን ከዳር እስከ ዳር አጨበጨብንለት፡፡ ለማጨብጨብ ደግሞ ማን ብሎን፡፡ እንገላገል እያልን እያጨበጨብን በገዛ እጃችን አናታችን ላይ የሚወጡብን በዙ እንጂ፣ የማጨብጨብስ ችግር አልነበረብንም!

  ወያላችን ሒሳብ እየሰበሰበ ነው፡፡ በዚህ መሀል አንድ ተሳፋሪ፣ ‹‹የት ነበር ያደረኩት? የት ነበር?›› እያለ ይርበተበታል። ወያላው በአፅንኦት ሲያጤነው ቆይቶ፣ “ከሌለህ ውረድ!” አለው። ‹‹ገንዘቡ አይደለም የጠፋብኝ ጓንቱ ነው፤›› አለው። “የምን ጓንት?” አለ ከጎኔ። “የእጅ ነዋ። ታዲያ እናንተን አምኜ ደግሞ ቫይረስ ይጫወትብኝ?” ሲል የታክሲው ተሳፋሪዎች አጉረመረሙ። ‹‹ለምንድነው ግን የአሸባሪዎችና የአንዳንድ በሽታዎች ስም እጥር ቅጥን የሚለው?›› ትላለች ከፊት የተሰየመች ወጣት። “እኛ ምኑን አውቀን ቆንጂት?” ይላታል ተረት የነገረን። ‹‹ነውር አይደለም እንዴ? እንዳመጣልህ ሰውን ቆሻሻ ብለህ ትሳደባለህ? ዘረኝነት፣ ጠባብነትና ትምክህተኝት እኮ ከዚህ ነው የሚጀምረው፤›› አለው አንዱ። ‹‹እኔ ምለው እንዴት እስካሁን ስለእነዚህ አስከፊ ነገሮች ዶክመንተሪ ሳይሠራ ቀረ?›› ብላ ወይዘሮዋ ጠየቀች።

  ‹‹ኧረ ስላላየሽ ነው ተሠርቶ ከተላለፈ ቆይቷል። እኛ እኮ ሲፈርስ እንጂ ሲሠራ ለማየት አንጓጓም፤›› ሲላት ወጣቱ፣ ‹‹ይኼ የቱርክ ፊልም እንዴት ሥራ እንዳስፈታኝ አትጠይቁኝ፤›› አለቻቸው በኃፍረት። ‹‹ምንም እንኳ ቴሌቪዥን መከታተል ራሱን የቻለ ሥራ መሆኑን ብናምንም፣ ይኼ ይኼ ጉዳይ የሞት የሽረት ስለሆነ ሁላችንም ባያመልጠን ጥሩ ነው፤›› መሀል መቀመጫ ላይ የተሰየመ ጎልማሳ ነው፡፡ ‹‹አንተን እኮ ነው የምጠብቀው፤›› ብሎ ወያላው ሲጮኽ ነው ያ ተሳፋሪ ጓንቱን ፍለጋ ላይ እንደነበር ያስታወስነው፡፡ የግዱን ከኪሱ አውጥቶ በእጁ አሥር ብር ሰጠው። ወያላው ዘርዝሮ መልስ መለሰ። ወያላው ተረጋግቶ ደገፍ ብሎ፣ ‹‹እናንተ እኮ በዚህ አያያዛችሁ ታክሲ ውስጥ የእጅ መታጠቢያ አዘጋጁልን ትሉ ይሆናል፤›› ቢል አዛውንቱ ቀበል አድርገው፣ ‹‹እናንተ እኮ አታፍሩም ይኼንንም ዘረኝነት፣ ጠባብነትና ትምክህተኝነት ትሉት ይሆናል?›› ብለው አሳጡት። ትምክህተኝነት የእምነት ስብከት ላይ ጭምር ባይወገዝ ኖሮ በዶክመንተሪ ብቻ የምንማማር አንመስልም ዘንድሮ!       

  ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። መንገዱ እርጥበታማ ነው፡፡ አቀማመጣችን ቁዘማዊ ነው። ሥጋትና ግራ መጋባት በእያንዳንዱ ተሳፋሪ ላይ ጎልቶና ደብዝዞ ይስተዋላል። ‹‹የዘንድሮው ደግሞ የተለየ ነው፤›› ትላለች ቆንጂት። “ምኑ?” ይላታል ጎልማሳው። ‹‹ፈውሱም ሕመሙም አንድ ላይ ሆኗል። ጥፋትና ልማት መሳ ለመሳ ቆመዋል። ወዴት እየሄድን ነው?›› ስትል ከጎኔ የተሰየመ ወጣት፣ “ወደ ሜክሲኮ ነዋ!” አላት እየሳቀ። ‹‹ይኼን እኮ ነው የምለው። ቁም ነገር ሲወራ እንቀልዳለን። ቀልድ ሲወራ ተጠምዝዞ ፖለቲካ ይሆናል። ይኼንን የተምታታ ሰብዕና ከየት ነው የወረስነው?›› ብላ ከመጠየቋ፣ ‹‹ምናልባት ከዶናልድ ትራምፕ ይሆናላ። እውነቴን ነው። እንደ እኔ አስተያየት ‘ኢትዮጵያዊ ትራምፖች’ እየበዙ ነው። አንዱ ‘ኑ ግድግዳ እናፍርስ’ ብሎ ይገጥማል፣ ሌላው ‘ኑ አጥር እንጠር’ ብሎ መግለጫ ያወጣል። ደግሞ አንዳንዱ ሳንወክለው ተወካያችሁ ነኝ እያለ ‘ስታርባክስ’ ቁጭ ብሎ ‘ዛሬም በሕይወት አላችሁ? ሙቱ አላልኳችሁም? አትጫረሱም?’ እያለ ቁም ስቅላችንን ያሳየናል፤›› አለቻት ወይዘሮዋ።

        ‹‹ታዲያ ጥፋቱ የማን ነው? ዕውቅና የሰጠናቸው እኛ፤›› ጎልማሳው መለሰ። ‹‹ጎበዝ መውጫ መግቢያ ካሳጣን የአካባቢና የግል ንፅህና ጉድለት በላይ የአስተሳሰብ ቫይረስ ሊያሰጋን ይገባል፤›› ሲል ተረተኛው አዛውንቱ ዝም ብለው ቆይተው፣ ‹‹እኮ ይኼ ቫይረስ በሐተታ ነው በተግባር የሚሽረው?›› ብለው ጠየቁት። ጥያቄው ሳይመለስ ወያላው “መጨረሻ” ብሎ በሩን በረገደው። ከሚያዩትና ከሚሰሙት ይልቅ የሚጠብቁ ብፁአን ናቸው ብለናል። ‘ቫይረስ በተግባር ፈውስ እንጂ በሐተታ ብቻ አይሽርም’ ያለም ነበረ ከተሳፋሪዎች መሀል። ‘አልሽር ያለ ደዌን በምን ያክሙታል?’ ያለው ማን ቢሉት እኔ እንጃ ያለው ማን ነበር? ይኼን ጊዜ ነው እንግዲህ አቤቱ ፈጣሪያችን ምሕረት ካንተ እንጂ ከቶ ከየት ይገኛል ማለት ያለብን፡፡ እንዲህ እያልን ሰብዓዊነት ካልተላበስን ዘፋኙ እንዳለው የእኛ ነገርማ ገና ብዙ አለበት፡፡ መልካም ጉዞ!

  Latest Posts

  - Advertisement -

  ወቅታዊ ፅሑፎች

  ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት