Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  ብንተሳሰብስ?

  ሰላም! ሰላም! እነሆ ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም ስል ጨዋታዬን ልጀምር ነው። ጠቅሞ ስለመጠቀም ካነሳን ዛሬ የምንለያይ አይመስለኝም። እንዴት ይዟችኋል? ሕዝብና ስፋት አብሮ ሲጠመድ ለወግና ለፖለቲካ እንደሚመች ምን ሌላ ነገር ሲመች አይታችኋል? ምንም! ደላላ ነኝና ይህችን ይህችን ለእኔ መተው ያዋጣል! ታዲያ ይኼ የመጠቃቀም ፖለቲካ ለመዘወር የመመቸቱን ያህል አያይዞ ገደል የከተተ ጊዜ አይጣል ነው። አንድ ብልህ ወዳጄ፣ ‹‹ከዓለማችን ሕዝብ 95 በመቶ የሚሆነው ሁሌም እንደተሳሳተ ነው፤›› አለኝ። አንዳንዱ ሰው አለ አይደል የማይላችሁ ነገር የለውም። ‹‹እንዴት?›› ስለው፣ ‹‹ከሚመሩት የሚከተሉት ነፍሶች ቁጥር ቀላል ስላልሆነ ነው፤›› የሚል ነበር መልሱ። ያስደነግጣል። ‹‹መጠቃቀም ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የኖረና ወደ ፊትም የሚኖር የሕዝብና የመንግሥት ወግ ነው። በሌላውም መሀል የሚሠራ የተፈጥሮ ሕግ ነው። ነገር ግን ይህ ወግ አቅጣጫውን እየሳተ ሌላ ጣጣ እያመጣ መሆኑን በትጥቅ ማስፈታት ዘመቻው እያየን ነው፡፡ የደላላ ነገር የት ውስጥ ገባሁ ደግሞ፡፡

  ዳሩ የሰው ልጅ በምድር ላይ ኖሮ የማያውቀውን ፍፁምነት ፍለጋ ሲማስን ራሱን ያባክናል። አያሳዝንም? ‹‹ከአንፃራዊነት ሕግ ርቀን ፍትሕና ፍፁምነትን ፍለጋ ባጠፋንባቸው ክፍለ ዘመናት ያስቆጠርነው ዕድሜ፣ እነ ማቱሳላ ዘመናቸው እንዲረዝም የጠጡትን ወይም ያጤሱትን ዕፀ ፋሪስ ፍለጋ ብንደክም ኖሮ የተሻለ ውጤት ነበረው፤›› የሚለኝ ደግሞ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው። መኖር ነው ዋናው ሊል ፈልጎ እኮ ነው። ለነገሩ እውነቱን ነው መሰንበትን የመሰለ ነገር የለም። ይኼው ሳይታወቀን ብሶት ከወለደው ኢሕአዴግ ጋር ከ27 ዓመታት በላይ ኖርን አይደል እንዴ? አይገርምም ግን? ጊዜ ራሱ ከቁብ አልቆጥረን ብሎ እንደምታዩት ይገሰግሳል። እኛም ብልጥነት አንሶንና ማስተዋላችን ቀንሶ ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬ ደግሞ ነገ እንደሚሻል ማሰብ አንገፍግፎን እዚህ ደርሰናል። ‘የሰው ልጅ ሰይጣን በሌለበት የራሱ ሰይጣን፣ እግዚአብሔር በሌለበት የራሱ እግዚአብሔር ነው’ ያለው ፈላስፋ ማን ነበር? ባውቀው ኖሮ ያለኝን በሙሉ እሸልመው ነበር፡፡

  ካለፉት ዕለታት በአንዱ ገና ካልጋ ሳልወርድ ውዷ ማንጠግቦሽ ቀኑን በትዝታ ጀመረችው። ‹‹አቤት ያኔ…›› አለች እየተሽኮረመመች። ‘ለካስ ጦረኛ ነህ ታነጣጥራለህ፣ በርቀት ተኩሰህ ልብ ትመታለህ’ የሚሉት የትዝታ ጨዋታ መጀመሩ እንደሆነ ገብቶኝ ‹‹መቼ?›› አልኳት። ‹‹ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ነዋ!›› አለች እየሳቀች። የሚያስቃት ነገር ገብቶኛል። እነዚያን ዓመታት አፍላ ፍቅረኞች ነበርን። የትናንት አማፅያን የዛሬን አያድርገውና ከተማውን ከበው ጥይት በየአቅጣጫው ሲንጣጣ፣ የእኔና የማንጠግቦሽ ልብ ከፊል በሽብር ከፊል በፍቅር አብሮ ይንጣጣ ነበር። ከቤት ሳንወጣ እንደተቃቀፍን ወሬ በሬዲዮ ስናጣራ ሰንብተናል። ‹‹ግን እንዴት እንዋደድ ነበር አንተዬ?›› ስትለኝ ግን ነገር ደህና አደርክ አልኩ በውስጤ። ከአልጋ ሳትወርዱ ስትነጀሱ ይደብራላ። ‹‹አሁን አንዋደድም እንዴ?›› አልኳት። “ያሁኑማ በሀብት ላይ የተመሠረተ ነው። ያኔ እኮ ምንም አልነበረንም። አገሩ ቀውጢ ሆኖ እኛ መርፌና ክር ሆነን እንውላለን። ዋ! ‘ነበር እንዲህ ቅርብ ነው’ አሉ ጣይቱ?›› ስትል ጭራሽ ጥቅስ ጀመረች። ከንፈር መጠጠች። ይህችን ይወዳል አንበርብር አልኩኝ! ‘ወደው አይጎመዝዙ’ አለች አለ ድፍድፍ!

  ‹‹ምነው ማንጠግቦሽ ገና አፌን ሳላሟሽ ልቤን በነገር የምታደክሚው?›› ብላት ቆጣ ብዬ፣ ‹‹ኧረ ተወው ይቅር! እንዲያው የአንዳንዱ ሰው ታሪክ እየደነቀኝ፣ በወጣትነቱ ተኝቶ በእርጅና ዘመኑ አብዮታዊና ብሔርተኛ ሲሆን ድንቅ እያለኝ እንጂ…›› ብላኝ ተነስታ ወደ ጓዳዋ ገባች። አጠገቤ ብትቆይ፣ ‹‹ከመቼ ወዲህ ነው ደግሞ ለውጥ አመሻሽ፣ ቀትርና ማለዳ ማለት የጀመረው?›› የሚል ጥያቄ ብጠይቃትና የምትለኝን ብሰማ ይወጣልኝ ነበር። ዳሩ አክራሪነትና ጽንፈኝነት ይብቃ እያልን ስለሆነ መካረሩ አልተዋጠልኝም። ውዷ ማንጠግቦሽ አንዳንዴ እንዲህ ዓይነት የሐሳብ አዙሪት ውስጥ ትገባለች። አስጀምራ ሲከርባት ወደ ጓዳዋ ትሾልካለች። እሷ ለኩሳ በሰጠችኝ እሳት ቀኔ እንዴት ሲበጠበጥ እንደሚውል ለመረዳት ብዙ የራቀች ናት። አሉ አይደል ችቦ ሰጥተውን እሳቱ ሲነድ ድራሻቸው የሚጠፋ? የኋላው የማይታያቸው? ‘የፊት የፊቱን አለ ጓያ ነቃይ’ በሚል ብሂል ስንት የጥላሸት ታሪክ የቀቡን? ነፍሳቸው በተቃውሞና በትችት ነሃስ ብቻ የተለበጠች? ከእኔ ወዲያ ላሳር መለያቸው የሆነ? ኧረ እኛ ግን ያላየነው አለ? መቼም እኔና እናንተ ስንገናኝ ኑሮና ትዝብቱ ተወስቶ አያልቅም። ቢያልቅም እንደኛ ለወሬ ሰፊ ጊዜ ያለው ዜጋ ዙሩን ደጋግሞ ማክረር ነው የሚያውቀው። ‹‹እህ ሌላ ምን መሄጄ አለ?›› ይለኛል የባሻዬ ልጅ። እሱ ደግሞ በየነገር መታጠፊያው ስለተከለከልነው የ‘ማሪያም መንገድ’ መተረብ ይቀናዋል። 

  - Advertisement -

  ሕይወትን እዚሁ ከፊል ገነት ከፊል ገሃነም ሆና ስንታዘባት በመሆንና ባለመሆን ሒደት ውስጥ ሰው የመሆን ትርጉም እየጠፋብን፣ በአኗኗራችን የመሀል ሰፋሪነት ፀባይ ሲያጠቃን ስታዘብ እንዴት እንደምገረም አትጠይቁኝ። ደግሞ ከእሱም ብሶ ለስላቅና ለምፀቱ የሚደርስብን የለም። ሲያዩን ቀላል እንመስላለና! ታዲያ አሁን ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ? የአንድ መምህርና ደቀ መዝሙር ቀልድ። መምህሩ ደቀ መዝሙሩን መንገድ ላይ ያገኙታል። ‹‹ከወዴት ነው?›› ይሉታል። ‹‹ገሃነም ደርሼ እየመጣሁ፤››  ይመልሳል። ‹‹ምን ልትሠራ ሄደህ?›› ይሉታል ግራ ገብቷቸዋል። ‹‹እሳት ለመጫር ነበር፤›› ይላል። ‹‹እናስ?›› አሉት። ‹‹እሳት የሚባል ነገር ገሃነም ውስጥ የለም ተባልኩ፤›› አላቸው። ‹‹እህ ታዲያ የት ነው ያለው?›› መምህሩ ሌላ ጥያቄ አቀረቡ። ደቀ መዝሙሩ ተሰናብቷቸው ከመሄዱ በፊት፣ ‹‹ሁሉም ሰው የገዛ ራሱን እሳት ይዞ እንደሚዞር ተነግሮኝ መጣሁ፤›› አላቸውና መንገዱን ቀጠለ። ‘ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ’ አላሉም እንዴ አበው? እውነታውም ከአባባሉ ጋር በአበው ዘመን የቀረ ይመስላል። የዘመኑ ተማሪ ለመምህሩ የሚተርፍ ብቸኛ ዕውቀቱ ‘ቺት እና ቻት’ ማድረግ ብቻ ሆኗል ብሎ በአደባባይ መርዶ እያረዳን ያለው የገዛ መንግሥታችን ነው። ‹‹እግዚኦ! አንበርብር የዘመን ቅራሪ ይሉሃል ይኼ ነው። ሚዲያን በሚያህል ነገር የአሳዳጊና የታዳጊ ውድቀት በይፋ ይለፈፍ? ከዚህ በላይ በዝረራ እንሸነፍበታለን የምለው ነገር በበኩሌ የለኝም፤›› ሲሉኝ ሰነበቱ ባሻዬ። ኩረጃና ተማሪ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ስማቸው ገኖ ሲጠራ፣ ሲሰሙና ሲያዩ። በዜጋ ነግዶ በዜጋ እንደ መክሰር ለየትኛውም አገር የሞት ሞት ነው!

  አሁን ካወራነው ጋር የሚያያዝ ገጠመኝን ባጫውታችሁስ? ጨዋታ ነው ትርፋችን በሚለው ከተስማማን ቆይተናል! ብራቮ! ይኼውላችሁ ዕድሜ ለአባዛኙ ሥራዬ ወዲያ ወዲህ ተፍ ተፍ ስል የማላገኘው፣ የማላየውና የማልታዘበው ነገር የለም። እንዲህ እንደ ዛሬው የጋዜጠኝነት ትርጉም ሰፍቶ ሳያከራክር በፊት ከደላላነቴ ጎን ጋዜጠኛ የምትል ማዕረግ ልትሰጡኝ ይገባ ነበር። እናማ ባለሦስት መኝታ ኮንዶሚኒየም ቤት እያሻሻጥኩ ነው። ከሚሸጠው ቤት አጠገብ በባሻዬ ዕድሜ ክልል የሚገኙ አዛውንት ወይዘሮ ከጎረምሳ ልጃቸው ጋር ይጨቃጨቃሉ። ‹‹ዋ ዘንድሮ! በኩረጃ ተማምነህ ከሆነ ጥናቱን እርግፍ አድርገህ የተውከው የለሁበትም፤›› ይሉታል። የቤቱ ሻጭና ገዥ ጥግ ይዘው ያወራሉ። ገለል ብዬ በረንዳው ላይ ቆሜያለሁ። ‹‹የሌለ እኮ ነው!›› እየተነጫነጨ ወጣቱ ከቤቱ ወጣ። ተጠጋሁና ‹‹ምነው?›› አልኩት። ወጣቱ ጠጋ ብሎ ለራሱ ዓላማ የሚጠመዝዘው እንጂ የሚያዳምጠው ሰው ያጣ ይመስላል። ምናልባት ፈተናው የበዛበትም ለዚያ ሳይሆን ይቀራል? ምናልባት ተግዳሮታችን የበዛው ልቡንና ጆሮውን የሚሰጠን ስላጣን ነው? ተውኩት ለእናንተው! ‹‹ነገራችን ሁሉ የፈሰሰ ውኃ የማፈስ ያህል ነው፤›› ሲለኝ ታዳጊው በቁጭት ደነገጥኩ። የዚህች ምድር ሀቅ በትውፊትና በሥነ ቃል ገና ሳናድግ እንደሚያስረጅ እያወቅኩኝ፣ የልጁ እንዲያ ቃላት ማዋደድ ለምን እንዳስደነገጠኝ አልገባኝም። የልቡን አጫወተኝ። በጅምላ ፍረጃ እየተሸፈነ ማንነቱ በውል ያልታወቀለት ታዳጊ ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ ከጨዋታው አረጋግጬ ስንሰነባበት፣ ‹‹እኛ ማለት በብዙ ነገራችን ዱላውን አስቀምጠን ለቅብብሎሽ ‘ከትራክ’ ውጪ የምንሮጥ ምስኪኖች ነን፤›› ብሎኝ አረፈው። ስንቱን ነገር ይሆን እናንተ ከመሠረቱ የሳትነው?

  መሰነባበቻችን ደርሷል። ሸቃቅዬ በዕለት ድካሜ ላይ ከወዳጆቼ ጋር እየተጫወትኩ አንድ አንድ መባባል ልማዴ ነው። የተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ጢም ብላ ሞልታለች። ዛሬ ውይይቱም ሆነ ጨዋታው የግል አልነበረም። ስገባ ሰው በሁለት ጎራ ግራና ቀኝ ተከፍሏል። መሀል ላይ አንድ በዓይን ሰላምታ የማውቀው ሰው አስማሚ መስሎ ቆሟል። ተውኔት ይታያል። መሀል ላይ የቆመው ሰው አንድ ነገር ብቻ ይላል፣ ‹‹ከ27 ዓመት በኋላ?›› ሲል አንደኛው ደግሞ፣ ‹‹ዓባይን ተዳፍረናል!›› ብሎ ይጮሃል። ‹‹ከ27 ዓመት በኋላ?›› ይላል በድጋሚ። ሌላኛው፣ ‹‹የፍትሕና የዴሞክራሲ ጉዳይ ክፉኛ አስተዛዝቦናል፤›› ብሎ ብርጭቆ ያጋጫል። መሀል የቆመው ሰው ጥያቄ አይለወጥም። መልካሙና መራራው በየተራ ከሁለቱም ወገን ይዘረዘራል። ‹‹በመንገድ አውታሮች ዝርጋታ አልተቻልንም!›› ሲል የወዲህኛው የወዲያኛው ደግሞ፣ ‹‹መንገድ የጠፋበት ትውልድ በማፍራት ተወዳዳሪ አጥተናል!›› ይላል። ‹‹ስንዴ የመለመን ታሪካችን ተረት ሊሆን ምን ቀረን?›› ሲል፣ ‹‹ሐሳብ የመለመን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍተናል!›› ይባላል። ‹‹በታሪካችን አሪፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ እንደደረስን ተመስክሮልናል!›› ሲባል፣ ‹‹የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ በርትቷል!›› የሚለው በሌላ ድምፅ ግሮሰሪዋን ያናውጣታል። ድራማ የማይ መስሎኝ ሳልቀመጥ ትዕይንቱን ስከታተል ቆየሁ።

  ሙግቱና ክርክሩ አብቅቶ ሁሉም ከወዳጁ ጋር ሲጫወት ወደ ባሻዬ ልጅ ጠጋ ብዬ፣ ‹‹ቀኝ ወይስ ግራ?›› አልኩት። ይደግፍ የነበረውን ለማወቅ። ሐሳቤን ተረድቶ፣ ‹‹ጎራ መለየቱ ሲጎዳት ኖረ እንጂ መቼ ይህችን አገር ጠቀማት? ለዚህች አገር የሚበጃት እኮ ግራና ቀኙን መርጦ መጓዝ ሳይሆን በሁለቱ መሀል አማራጭ መንገድ መፈለግ ነው፤›› አለኝ። መማር ደጉ! አልኩኝ በልቤ። ያኔ በቀን ሦስቴ የምንበላበት ደግ ጊዜ እየተቃረበ መሆኑ ሲነገረን የነበረውን ያስታወሰን አንዱ፣ ‹‹ጎበዝ በምግብ ራሳችንን ሙሉ በሙሉ ችለናል መባሉን እንዴት ታዩታላችሁ?›› የሚል ጥያቄ አቀረበ፡፡ ‹‹የዕርዳታ ምግብ ቀንሶ በላባችን መብላት ሳንጀምር፣ ስንዴና ዘይት በግዥ እያስገባንና በወረፋ ተሻምተን እየተከፋፈልን፣ ኧረ ለመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ራሳችንን ለመቻል ግን በቀን ስንት ጊዜ በላን? ለሚለው ጥያቄ መልስ ያስፈልጋል . . .›› እያለ ሌላው ሲመልስ የባሻዬ ልጅ አንገቱን በድጋፍ ነቀነቀ፡፡ አንዱ ደግሞ፣ ‹‹የረባ ልብስና ጫማ ሳይኖረን፣ ከዓመት ዓመት ዝናብ ፍለጋ ወደ ሰማይ እያንጋጠጥን፣ አሁንም በቀላሉ በሕክምና በሚድኑ በሽታዎች እየሞትን፣ ከሥልጣኔ በሚሊዮን ማይሎች ርቀት ላይ ሆነን እርስ በርስ እየተናከስን እዚህ ዓለም ላይ አለን ማለት ይቻላል ወይ…›› እያለ ሲንገበገብ አብሬው ተንገበገብኩ፡፡ በተለይ ለዘመናችን ሰውና ለራሴ ጭምር አሰብኩ፡፡ እስቲ እንተሳሰብ! መተሳሰብ አቅቶን መሰለኝ ወደ አውሬነት እየተለወጥን ያለነው፡፡  መልካም ሰንበት!   

  Latest Posts

  - Advertisement -

  ወቅታዊ ፅሑፎች

  ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት