Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  አጉል ጀብደኝነት የአገር ችግር አይፈታም!

  በበርካታ ችግሮች የተተበተበችው ኢትዮጵያ አሁንም ለበለጠ ችግር የሚዳርጋት ፈተና ከፊቷ ተጋርጧል፡፡ በማንነት፣ በአስተዳደራዊ ወሰንና በመሬት ይገባኛል እሰጥ አገባዎች ምክንያት በተለያዩ ክልሎች መካከል በሚከሰቱ አለመግባባቶች ግጭቶች በተደጋጋሚ አጋጥመዋል፡፡ አሁንም ደም ለማፋሰስ የሚያደርሱ እሰጥ አገባዎች እየተሰሙ ነው፡፡ የአማራ ክልል ከትግራይና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች፣ የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች፣ የኦሮሚያና የደቡብ ክልሎች፣ የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ የማንነትና የአስተዳደር እርከን ጥያቄዎች፣ ወዘተ. የወቅቱ የአገሪቱ ፈተናዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ሁሉንም ወገን በሚያስማማ መፍትሔ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት መደረግ አለበት፡፡ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከጎንደርና ከአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች ጋር ባደረጉት ውይይት እንደተናገሩት፣ የወሰንና የመሬት ይገባኛል ጥያቄዎች በብዙ ክልሎች የሚነሱ አገር አቀፍ ችግሮች ናቸው፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስፈልገው ደግሞ አገር አቀፍ መፍትሔ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የሚያጋጥሙ የጋራ ችግሮችን በአገር አቀፍ መፍትሔ ለመፍታት ግን መነጋገርና መደማመጥ ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ ግን በጀብደኝነት የተለመደው ግጭት ውስጥ እየተገባ የንፁኃን ሕይወት ይቀጠፋል፣ የአገር አንጡራ ሀብት ይወድማል፡፡

  መሰንበቻው በምዕራብ ጎንደር ዞንና በአካባቢው በተከሰተ ግጭት የንፁኃን ወገኖች ሕይወት ሲያልፍ በርካቶች ተፈናቅለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ሞትና መፈናቀል እንዳይኖር ጥያቄዎች በሰከነ መንፈስ ቀርበው ምላሽ ማግኘት አለባቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ለመንግሥት ይቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎች በወቅቱ ምላሽ ስለማያገኙና ዳተኝነት ስለሚበዛ አላስፈላጊ መስዋዕትነቶች ተከፍለዋል፡፡ አሁን በተለይ በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል የተፈጠረውን ውጥረት በማርገብ፣ ሁሉንም ወገን የሚያግባባ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡ መፍትሔው ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ብቻ ሳይሆን፣ ታሪካዊ ዳራዎችን የሚፈትሽ ጭምር መሆን አለበት፡፡ በሥራ ላይ ያለውን የክልሎች የአስተዳደር ወሰን አከላለል ጥቅምና ጉዳቱን አጥንቶ መፍትሔ የሚያቀርብ ኮሚሽን እየተቋቋመ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ ይህ ኮሚሽን ምሁራን፣ የታሪክ አዋቂዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንደሚካተቱበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ ለአገራዊ ችግር አገራዊ መፍትሔ ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ኮሚሽን ነፃና ገለልተኛ ሆኖ እንዲቋቋም፣ ኢትዮጵያውያን የጋራ ድምፃቸውን ማሰማት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያን ከግጭትና ከውድመት ለመታደግ የሚቻለው፣ ከወገንተኝነት የፀዳ የጋራ የሆነ መፍትሔ የሚያፈላልግ ኮሚሽን ሥራውን ሲጀምር ነው፡፡

  ዘወትር እንደምንለው ከአገር ህልውና በላይ ምንም ነገር የለም፡፡ ማንነት፣ ወሰን፣ መሬትም ሆነ ማንኛውም ጉዳይ የመነጋገሪያ አጀንዳ መሆን የሚችሉት የአገር ህልውና ሲረጋገጥ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ዓለም ከመቼውም ጊዜ በላይ እጅግ እየተቀራረበ ፍላጎቱንና ጥቅሞቹን እያቆራኘ ነው፡፡ በአገር ደረጃ ከመነጋገር ታልፎ በአኅጉራዊና በዓለም አቀፍ ተቋማትና አደረጃጀቶች አማካይነት የጋራ ጥቅምን ማስጠበቅ የተለመደ ሆኗል፡፡ ችግሮች ሲያጋጥሙም ጦር ከመማዘዝ ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየትና መደራደር የሥልጣኔ ምልክት ተደርጓል፡፡ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ትውልድም የጋራ ተጠቃሚነትን እንጂ የአንድ ወገን የበላይነትን የማይቀበል ከመሆኑም በላይ፣ ከምንም ነገር በፊት ለውይይትና ለድርድር ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የሚነሱ ጥያቄዎች በውይይትና በሰከነ መንፈስ ሲቀርቡ፣ ምላሻቸውም በዚያው መንገድ ስለሚሆን ፍትሐዊ ውሳኔ ይገኛል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በተለይ ማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ በተሰገሰጉ ጽንፈኞች የሚጎሰመው የጦርነት ነጋሪት የኋላቀርነት ማሳያ ነው፡፡ ይዋጣልን እያሉ መፎከርና መደንፋት የዘመነ መሳፍንት ቅሪትነትን ነው የሚያመላክተው፡፡ አገራዊ መፍትሔም አያመጣም፡፡

  ባለፉት ሰባት ወራት ኢትዮጵያ ውስጥ በለውጡ አማካይነት የተለያዩ አዎንታዊ ነገሮች ታይተዋል፡፡ ለብሔራዊ መግባባትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ተስፋ ሰጪ ምልክቶችም እየታዩ ነው፡፡ በዚያው መጠን ደግሞ በተለያዩ ሥፍራዎች በተከሰቱ ግጭቶች የንፁኃን ደም ፈሷል፣ የአካል ጉዳት ደርሷል፣ የአገር ሀብት ወድሟል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል፣ በርካቶች ለሥነ ልቦና ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን በነፃነት ለመኖርና በአገራቸው ዙሪያ መለስ ጉዳዮች አስተዋጽኦ ለማበርከት ለውጡን ደግፈው በምልዓት ሲንቀሳቀሱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በገዛ ወገኖቻቸው ላይ እሳት ያዘነቡ ጽንፈኛ ኃይሎች ተስተውለዋል፡፡ ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ወልደው ከብደው ከኖሩበት ቀዬ እንደ ባዕድ በማፈናቀል፣ ሕፃናትንና አቅመ ደካሞችን ሜዳ ላይ የጣሉ እኩዮች በስፋት ታይተዋል፡፡ ከጭቆና ተላቆ በነፃነት ለመኖር የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፉ ወገኖች ሕዝቡ ውስጥ ተሰግስገው በፈጸሙት እኩይ ድርጊት ምክንያት አገርና ሕዝብ ተሳቀዋል፡፡ ከሞትና ከውድመት የሚገኝ ትርፍ ስለሌለ አገራዊ ችግሮችን በአገራዊ መፍትሔ እንፍታ መባል ይኖርበታል፡፡ ከግጭት ምንም ዓይነት መፍትሔ አይገኝም፡፡

  በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ትልቁ ችግር አለመደማመጥ ነው፡፡ ባለመደማመጥ ምክንያት የደረሱ ችግሮች ምን ያህል ከባድ እንደሆኑ ከበቂ በላይ ማየት ተችሏል፡፡ የፖለቲካ የጥበብ መጀመርያ መደማመጥ መሆን ሲገባው፣ መደማመጥ ባለመኖሩ ምክንያት ሕዝብና አገር መከራ ዓይተዋል፡፡ በአርባ ምንጭ ከተማ በተበሳጩ ወጣቶች ምክንያት ሊደርስ ይችል የነበረውን አሰቃቂ ድርጊት የተከላከሉት የጋሞ የአገር ሽማግሌዎች የፈጸሙት ገድል፣ ለፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በሙሉ ትልቅ ትምህርት መስጠት ነበረበት፡፡ የአገር ሽማግሌዎቹን ተማፅኖ በአንክሮ በማዳመጥ ከጥፋት የታቀቡት ወጣቶች ደግሞ፣ ለቢጤዎቻቸው ያስተላለፉት የጨዋነት ተግባር ትምህርት የሚቀሰምበት ነበር፡፡ የመላ ኢትዮጵያውያን ምሥጋና የጎረፈላቸው የጋሞ ሽማግሌዎችና ወጣቶች ተግባር የአገሪቱ የሞራል የውኃ ልክ መሆን ሲገባው፣ ከዚህ በተቃራኒ እየነጎዱ አገር ለማተራመስ የሚፈልጉ ጽንፈኞች በተለያዩ ክልሎች ውስጥ መሽገዋል፡፡ በተለይ ማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ ያደፈጡ ጽንፈኛ ኃይሎች ወጣቶችን በመመረዝ ደም ለማቃባት የሚያደርጉት መሯሯጥ ሊገታ ይገባል፡፡ ችግሮችን በሰከነ ውይይትና ድርድር ቁጭ ብሎ መፍታት ሲገባ፣ ጠመንጃ መወልወል ውስጥ ለመግባት መንደርደር ዕብደት ነው፡፡ ይህ ዕብደት በሕግ የበላይነት አደብ መግዛት አለበት፡፡ ለአስተዋዩና ለጨዋው የኢትዮጵያ ሕዝብ የማይመጥን ነውና፡፡

  በተለያዩ አካባቢዎች ለሚነሱ ማናቸውም ጥያቄዎች የመንግሥት ምላሽ ፈጣን መሆን አለበት፡፡ ይቋቋማል የተባለው ኮሚሽን በፍጥነት ሥራ እንዲጀምር ብቻ ሳይሆን፣ የኮሚሽኑ አባላት መረጣና ምደባም ግልጽና አሳታፊ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህንን በተግባር ማሳየት ሲቻል አስተዋዩና ጨዋው የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግሮቹ በሰላማዊ መንገድ ተፈተውለት፣ እንደ ቀድሞው በሰላምና በፍቅር አብሮ መኖሩን ይቀጥላል፡፡ ይህንን ተምሳሌታዊ መስተጋብር ወደ ማያስፈልግ አቅጣጫ ለመጎተት የሚጥሩ ኃይሎችም አርፈው ይቀመጣሉ፡፡ አሁንም ቢሆን ሕዝቡ ውስጥ ሰላም፣ ፍቅርና አብሮነት በስፋት ይታያሉ፡፡ ለመነጋገርም ሆነ ለመደማመጥ ምንም ዓይነት መሰናክል የለም፡፡ የመጠማመድና የመጠላላት አዙሪት ውስጥ ያሉ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ወደ ህሊናቸው ተመልሰው፣ ለሚቋቋመው ኮሚሽን አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያበርክቱ፡፡ የንፁኃንን ደም በማፍሰስ ሥልጣን መያዝም ሆነ ተደላድሎ መግዛት አይቻልም፡፡ በማንነት፣ በአስተዳደራዊ ወሰንና በመሬት ይገባኛል ምክንያት ግብግብ ለመፍጠር ከመሯሯጥ ይልቅ፣ ለተጀመረው የሥልጡን መፍትሔ ፍለጋ ጥረት መማሰን ይሻላል፡፡ በአሻጥር፣ በሴራና በቂም በቀል የተለወሰው የአገሪቱ ፖለቲከኞች የተበላሸ ግንኙነት ለዚህ ዘመን አይመጥንም፡፡ ለጋራ ችግሮችም መፍትሔ አያመነጭም፡፡ አጉል ፉከራና ቀረርቶም ፋይዳ የላቸውም፡፡ ለዚህ ነው አጉል ጀብደኝነት የአገር ችግር አይፈታም የሚባለው!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  በቴሌ ብር የማይሠሩ ማደያዎች ቀነ ገደብ ተቀመጠባቸው

  ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ለመሥራት እየመከረ ነው በኢትዮጵያ...

  ሰርጌ ላቭሮቭ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ ምዕራባውያንን አጣጣሉ 

  የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ለአፍሪካ አገሮች ላደረጉት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

  የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ምሥረታና ተጠባቂ ዕድሎቹ

  ነፃ የንግድ ቀጣናዎች የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣናዎች አካል ሲሆኑ፣ በውስጣቸው...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን ነፃነትም ተምሳሌት ናት፡፡ የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የሚያኮራ ተግባር ፈጽመው ያለፉት፣ ከአገራቸው በፊት የሚቀድም...

  የማንም ሥልጣንና ጥቅም ከኢትዮጵያ አይበልጥም!

  የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ፣ የኢትዮጵያን የወደፊት ብሩህ ጊዜ አመላካች ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ይህ የአፍሪካ ታላቅ ግድብ ፕሮጀክት ዕውን...