Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፓርትመግባባት የተሳነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ

  መግባባት የተሳነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ

  ቀን:

  የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ “ደረሰብኝ” ባለው የውስጥና የውጪ ተፅዕኖ በፌዴሬሽኑ ከነበረበት ኃላፊነት የለቀቀ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ኅዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ቦሌ በሚገኘው የግል ጽሕፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ፣ በፌዴሬሽኑ ሊኖር የሚገባውን ሕግና ሥርዓት ለማስከበር የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በአጠቃላይ በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ማጣታቸው አሁን ለደረሰበት ውሳኔ እንዳበቃው ተናግሯል፡፡

  ከአትሌቲክሱ የውጤት ቀውስ ጋር ተያይዞ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ከሁለት ዓመት በፊት ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት ሲያስተዳድር የቆየው ኃይሌ፣ “በቃኝ” ማለቱን ተከትሎ በፌዴሬሽኑ መግባባትና መደማመጥ መጥፋቱ እየተነገረ ይገኛል፡፡ እንደ ፌዴሬሽን ምንጮች ከሆነ ኃይሌ ውሳኔውን እንዲያጤን ለእሱ ቅርበት እንዳላቸው የሚታመንባቸው ሰዎች እያነጋገሩት መሆኑም ተሰምቷል፡፡

  ውሳኔውን ተከትሎ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ ለዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ በርካታ ችግሮች መኖራቸው የሚካድ እንዳልሆነ፣ በዚህ ቅሬታ ያደረባቸው አንዳንድ አትሌቶችም ሆነ አሠልጣኞች የተቃወሙት፣ ‹‹ፌዴሬሽኑን እንደ ተቋም እንጂ ኃይሌ ላይ በተናጠል አይደለም፤›› በማለት ኃይሌ ውሳኔውን እንዲያጤን ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጭምር ይናገራሉ፡፡

  ፌዴሬሽኑን በቀናነት ለማገልገል ካልሆነ የተለየ ጥቅም ፍለጋ እንዳልመጣ የተናገረው ኃይሌ፣ ‹‹ላለፉት ሁለት ዓመታት ከባልደረቦቼ ጋር በተቋሙ ለዓመታት ሲንከባለሉ ዛሬ ላይ የደረሱ ችግሮችን መስመር ለማሲያዝ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳልል ስሠራ ቆይቻለሁ፡፡ መመሪያና ደንቦች እንዲፈጸሙ ሲደረግ ምላሹ ሌላ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ደግሞ መሥራት ስለማይቻል ጉባዔው ሐሳቤን ተቀብሎ እንደሚያፀድቅልኝ  በመተማመን ነው፤›› ያለው ኃይሌ ውሳኔውን እንደማይቀይርም ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡

  የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 22ኛ መደበኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን ቅዳሜ ጥቅምት 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል ማከናወኑ አይዘነጋም፡፡ በጉባዔው ወቅት ‹‹ክለቦች የጠቅላላ ጉባዔ አባል መሆን አለባቸው የለባቸውም›› በሚል በተነሳው ነጥብ ላይ በተለይ ከኦሮሚያ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የክለቦች ተወካዮች፣ ክለቦች የጉባዔ አባል መሆን እንደሚገባቸው ጠንካራ አስተያየት ሲሰጡ ተደምጠዋል፡፡

  በክርክሩ ክለቦች የጠቅላላ ጉባዔ አባል መሆን የሚችሉባቸው ቅድመ ሁኔታዎች በሙያተኞች ጥናት ተደርጎበት በሚቀጥለው ጉባዔ ውሳኔ እንዲሰጠው በአብላጫ ድምፅ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ የጉባዔውን አካሄድ በፅኑ የተቃወመው የኦሮሚያ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ባለፈው የውድድር ዓመት ያስመዘገበውን ውጤት መነሻ በማድረግ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የ240 ሺሕ ብር ተሸላሚ ቢያደርገውም ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን መቅረቱ አይዘነጋም፡፡

  ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ባለፈው እሑድ ኅዳር 2 ቀን 2011 ዓ.ም. በሱሉልታ ባዘጋጀው አገር አቋራጭ ውድድር ላይ በርካታ አትሌቶች ፌዴሬሽኑን በመቃወም የተለያዩ መፈክሮችን በመያዝ አደባባይ የወጡበት አጋጣሚ መከሰቱ ይታወቃል፡፡ አትሌቶቹ ከያዟቸው መፈክሮች መካከል አትሌቶች በማዘውተሪያ ዕጦች ችግር ላይ እየወደቁ በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ትኩረት መስጠት እንደሚገባው፣ ትጥቅና መሰል ቁሳቁሶች እንዲሟሉላቸው የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተቃውሞ የተሳተፉ አትሌቶች የሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴን እጅ አንጨብጥም እስከማለት መድረሳቸው ለኃይሌ ውሳኔ በዋናነት እንደሚጠቀስም እየተነገረ ይገኛል፡፡

  የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ፣ ኅዳር 3 ቀን የፌዴሬሽኑን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን በመሰብሰብ በተለይ ከትጥቅና መሰል ጉዳዮች ጋር ተያይዞ አትሌቶች ላቀረቧቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ውሳኔ ላይ መድረሳቸው ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ፌዴሬሽኑ አንዳንድ አመራሮች ከሆነ፣ በፌዴሬሽኑ እየተፈጠረ ያለው ጉዳይ እጅጉን ሊታሰብበት ይገባል የሚል ፅኑ እምነት አላቸው፡፡

  በአትሌቲክሱ ትልቅ ስምና ዝና ያተረፈው ኃይሌ ገብረ ሥላሴ “አልቻልኩም” ብሎ ሲወጣ ‹‹የሱን ኃላፊነት የሚረከበው ሰው በምን ሞራል ነው ይህን ተቋም ሊመራ የሚችለው?›› ሲሉ ሥጋታቸውን ጭምር ይገልጻሉ፡፡ በቅርቡ የሚጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔም ጉዳዩን በትክክል አጢኖና መርምሮ ውሳኔ እንዲያሳልፍ ይጠይቃሉ፡፡  

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...