Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፓርትብሔራዊ የስፖርት አካዴሚ በውጤት ሲለካ

  ብሔራዊ የስፖርት አካዴሚ በውጤት ሲለካ

  ቀን:

  በምሥራቁም ሆነ በምዕራቡ ዓለም በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች በኦሊምፒክም ሆነ በዓለም ሻምፒዮናዎች ስኬታማ የሆኑት አገሮች ለውጤታቸው ልዕልና በምንጭነት የሚጠቀሱት ያቋቋሟቸው አካዴሚዎች ናቸው፡፡ እነዚሁ አካዴሚዎቹ የታዳጊዎችን ዝንባሌ በማየት ከሕፃንነት ዕድሜያቸው ጀምሮ ሥልጠና እየሰጡ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ውጤታማ እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡ ለዚህም በእግር ኳሱና በአትሌቲክሱ እንዲሁም በሌሎችም ስፖርቶች በርካቶችን በመመልከት መጥቀስ ይቻላል፡፡

  ሊዮኒ ሜሲና ሮናልዲንሆ ጉቾ፣ ሌሎችም የዓለም እግር ኳስ ቁንጮዎች መነሻቸው አካዴሚዎች ናቸው፡፡ በአትሌቲክሱም ትጥቅ በማምረት የሚታወቀው ናይኪ ካምፓኒ በአሜሪካ በተለያዩ ግዛቶች በገነባቸው የተለያዩ አካዴሚዎች ባለ ተሰጥኦ አትሌቶችን በማስገባት ሥልጠና በመስጠት በውጤታማነቱ ይታወቃል፡፡

  ሳይንሳዊ ሥልጠና፣ በሕክምና የታገዘ አመጋገብና የጤና አጠባበቅን ከስፖርት እንቅስቃሴዎችና መሰል ክንውኖች የሚኖሩበት የስፖርት አካዴሚን በኢትዮጵያ ዕውን ለማድረግ ካለፉት አሠርታት ወዲህ የተደረገው ጥረት ፍሬ ማፍራት የጀመረው  የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዴሚ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 249/2003 ሲቋቋም ነው፡፡

  በ2005 ዓ.ም. በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተመርቆ ሥራውን የጀመረው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስኬት አካዴሚ፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሲቋቋም በዋናነት በኢትዮጵያ የሚስተዋለውን የተተኪ ስፖርተኞች እጥረትን ለመቅረፍ፣ በዘርፉ የሠለጠነ የሙያተኞች ክፍተት ለመሙላት እንዲሁም በስፖርቱ ዘርፍ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ለመሥራት የተቋቋመ መሆኑ የድርጊት መርሀ ግብሩ ያሳያል፡፡

  ብሔራዊ አካዴሚው በሕግ ከተሰጠው ሥልጣንና ተግባር አኳያ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊ ወጣቶችን በመመልመልና በማሠልጠን ለአገርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ምርጥ ስፖርተኞችን የማፍራት፣ የስፖርት ባለሙያተኞችን አቅም የመገንባት እንዲሁም በስፖርቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚፈታ ጥናትና ምርምር ማካሄጃ ከተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት ዋና ዋናዎቹ መሆናቸው ይታመናል፡፡

  የአካዴሚው ዋና ዳይሬክተር አቶ አምበሳው እንየው እንደሚናገሩት ከሆነ፣ ወደ ማዕከሉ እንዲገቡ የሚደረጉ ባለተሰጥኦ አትሌቶች ዕድሜ፣ ቁመት፣ ክብደትና የቴክኒክ ብቃት፣ የጤና ሁኔታና የሥነ ልቦና ደረጃ፣ የሥነ አካላዊና ሌሎችም መመዘኛዎች ይደረጉላቸዋል፡፡ መመዘኛዎቹ በዋናነት ትኩረት የሚያደርጉት ደግሞ ስፖርቱ የሚዘወተርባቸው ሥፍራዎችን በመለየት ለምሳሌ ጋምቤላ፣ አሰላ በቆጂ፣ ቤንሻንጉል ካማሽ፣ ትግራይ ሽሬ፣ ደቡብ ጅንካ፣ አማራ ደጋ ዳሞትና በሌሎችም ቦታዎች በመዘዋወር እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

  በእያንዳንዱ የስፖርት ዓይነት በተለይም አካዴሚው ሥልጠና በሚሰጥባቸው ስፖርቶች ምልመላው የብሔራዊ ፌዴሬሽን ባለሙያተኞችና የሚመለከታቸው ተቋማትና ማኅበራት ተወካዮች በተካተቱበት እንደሆነ የሚናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ታዳጊዎቹ ቆይታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ፈላጊ እንደማያገኙ፣ ይህ ደግሞ የአካዴሚውን ልፋትና ድካም እንዳያሳንሰው ሥጋት ስለመሆኑ ያስረዳሉ፡፡

  ታዳጊዎቹ የሚወስዱት ሥልጠና ሳይንሳዊ መሠረት ያለው፣ በሙያ ብቃት ሥልጠና ብቃታቸው ከየተረጋገጠ አሠልጣኞች የሚያገኙ መሆኑ፣ ሌላው ደግሞ የሥልጠናውን ደረጃ ለመጠበቅ የሥልጠናው ዓይነትና የሙያ ደረጃ ሥርዓት፣ የትምህርት ዝግጅቱን አካቶ በአጠቃላይ በሳምንት ስድስት የሥልጠና ቀናት ከ12 እስከ 16 ሰዓታት የንድፈ ሐሳብና በተግባር የተደገፈ ሥልጠና መሰጠቱ የአካዴሚውን ተግባርና ኃላፊነት ለየት እንደሚያደርገው ይናገራሉ፡፡

  እንደ ኃላፊው ከሆነ፣ የሥልጠናውን ውጤታማነት ለመከታተል ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል፣ የብቃት ምዘናና ትንተና ማካሄድ፣ ሠልጣኞቹን በማስመዘን በየስፖርት ዓይነቱ ለክለብና ለብሔራዊ ቡድን እንዲበቁ ይደረጋል፡፡ በዚሁ መሠረት በተለያዩ ስፖርቶች ሥልጠና ወስደው ለክለብና ለብሔራዊ ቡድን የበቁ አትሌቶች መካከል ለብሔራዊ በአትሌቲክስ 73 ወንዶችና 69 ሴቶች፣ በእግር ኳስ ስድስት ወንዶችና ሰባት ሴቶች፣ ቅርጫት ኳስ ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች፣ በጠረጴዛ ቴንስ ሦስት ወንዶችና አምስት ሴቶች፣ በውኃ ዋና አራት ወንዶች፣ በወርልድ ቴኳንዶ 15 ወንዶችና 18 ሴቶች፣ በቦክስ ሦስት ወንዶችና አራት ሴቶች፣ በብስክሌት ሁለት ወንድና ሁለት ሴቶች በድምሩ 113 ወንዶችና 106 ሴቶች ተገኝተዋል፡፡

  ወደ ክለብ የተዘዋወሩ ደግሞ በአትሌቲክስ 214 ወንዶችና 208 ሴቶች፣ በእግር ኳስ 35 ወንዶችና 32 ሴቶች፣ ቅርጫት ኳስ ስድስት ወንዶች፣ መረብ ኳስ ስምንት ወንዶችና ስምንት ሴቶች፣ በጠረጴዛ ቴኒስ ሦስት ወንዶችና ስድስት ሴቶች፣ በቦክስ ሁለት ወንዶችና ሁለት ሴቶች፣ በብስክሌት ስምንት ወንዶችና ስድስት ሴቶች በድምሩ 276 ወንዶችና 257 ሴቶች ናቸው፡፡

  ከነዚህ ውስጥ በ2003 ዓ.ም. በስፔን አገር አቋራጭና በፈረንሣይ ሊግ የዓለም ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ በ2004 በስፔን ባርሴሎና የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ በ2005 በዩክሬን የዓለም ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ በ2006 በቻይና ናጅንግ የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮናና በአሜሪካ ዩጅን የዓለም ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ በ2008 በፖላንድ በዓለም ወጣቶች ሻምፒዮናና በሌሎችም ዓለም አቀፍ ውድድሮች ለብሔራዊ ቡድን የበቁ አትሌቶች ከዲፕሎማ እስከ የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገቡ የአካዴሚው ፍሬዎች ስለመኖራቸው ኃላፊው ያስረዳሉ፡፡

  በኢትዮጵያ በተለያዩ ስፖርቶች ሕጋዊ ህልውና አግኝተው የሚንቀሳቀሱ ከ26 በላይ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች እንዳሉ ይታመናል፡፡ ከአንዳንዶቹ በስተቀር ብዙዎቹ ዕድሜ ከማስቆጠር ያለፈ ይህ ነው የሚባል ሊጠቀስ የሚችል ውጤት የሌላቸው መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ይባስ ብሎ አንዳንዶቹ በሕይወት መኖራቸው የሚታወቀው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ሲያደርጉ በሚሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ፋይናንስና የሚዲያ ሽፋን ስለማናገኝ የሚል መሆኑ ሪፖርተር ከአንዳንዶቹ አረጋግጧል፡፡

  ከአሥር ያላነሱ ስፖርቶች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ዘመኑ የሚጠይቀውን ሥልጠናና ክትትል በማድረግ የአካዴሚ ተልዕኮውን በመወጣት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት  አካዴሚ፣ ከብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ጋር ያለው የሥራ ግንኙነት ያን ያህል እንዳልሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአካዴሚው ዳይሬክተር በበኩላቸው፣ ‹‹ተቋሙ በሕግ በተሰጠው ሥልጣንና ተግባር መሠረት ሥራውን እያከናወነ የሚገኘው በተለይ ከምልመላና ምዘና ጋር ተያይዞ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችን ጨምሮ ይመለከተናል ከሚሉ አካላት ጋር ነው፡፡ ምክንያቱም አካዴሚው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሲቋቋም የተተኪ ስፖርተኞችን እጥረት ለመቅረፍ፣ በዘርፉ የሠለጠኑ ሙያተኞች ክፍተትን ለመሙላትና ችግር ፈቺ የሚሆኑ ጥናትና ምርምሮችን ለማድረግ ነው፤›› ብለው በአገሪቱ አትሌቲክሱን ጨምሮ በሌሎችም ስፖርቶች የአቅም ችግር እንደሌለ ጭምር ይናገራሉ፡፡

  በማሳያነት በቅርቡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ከስምንት ያላነሱ የሴት እግር ኳስ ተጨዋቾችን ከአካዴሚው የተረከበ መሆኑን ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ሌሎችም ክለቦችም ሆነ ፌዴሬሽኖች በአካዳሚው የሚፈሩ ታዳጊ ወጣቶችን ያምንም ክፍያና ጥቅማ ጥቅም መውሰድ እንደሚችሉ፣ ነገር ግን ታዳጊዎቹ የአካዴሚ ቆይታቸውን ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው ግን አልሸሸጉም፡፡

  በኢትዮጵያ በስፖርታዊ ክንውኑ ያለውን ክፍተትና ተያያዥ ችግሮችን አስመልክቶ ሪፖርተር እንዳነጋገራቸው አንዳንድ የስፖርቱ አመራሮችና ሙያተኞች ከሆነ፣ ‹‹ሌሎች አገሮች በተለይም በአሁኑ ወቅት ስፖርት ለአንድ አገር ሁለንተናዊ ዕድገት ያለው ድርሻ ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱን በመገንዘብ ልዩ ትኩረት መስጠት በመቻላቸው በዘርፉ ውጤታማ በመሆን ላይ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የትኩረት አቅጣጫው በውጤት ሲመዘን ዝቅተኛ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መንግሥት ዘርፉን እንደ አንድ የልማት መስክ በመውሰድ በዕቅድ ውስጥ ከተካተተ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይሁንና ስፖርቱን እንዲያስተዳድሩ የሚዋቀሩ መሥሪያ ቤቶችም ሆኑ አስፈጻሚ አካላት ከረዥም ዓመታት ጀምሮ አሁን እስካለንበት ድረስ ወጥ ሆኖ ተጠያቂነትና ግልጽነት ባለው መልኩ መደራጀት እየቻለ አይደለም፤›› ብለው በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቀደም ሲል በውጤታማነታቸው የሚታወቁ የስፖርት ዓይነቶች ጭምር በውጤት ቀውስ ውስጥ መገኘታቸው ማሳያ ተደርጎ እንደሚወሰድ ያስረዳሉ፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...