Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  በቀጣዩ ምርጫ ላይ ለመነጋገር በአስተማማኝ ቁመና ላይ መገኘት ያስፈልጋል!

  ለሚቀጥለው ምርጫ ከወዲሁ ለመነጋገር እንደ መንደርደሪያ የሚሆን ውይይት ሊደረግ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አገር ውስጥ ካሉና በቅርቡ ከውጭ ከገቡ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ጋር ለመወያየት፣ ለማክሰኞ ኅዳር 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ ሰሞኑን አወዛጋቢው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አዲስ ሰብሳቢ ተሹሞለታል፡፡ የምርጫ ሕጉና ሥርዓቱ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ የባለሙያዎች ቡድን እየሠራ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ጥረት መጪውን ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ ለማድረግ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ ምርጫ ቀልድ በሆነበት አገር ውስጥ ነውና ያለነው፣ ከሕግ ማዕቀፉ ጀምሮ እስከ ፖለቲካ ፓርቲዎች ቁመና ድረስ መነጋገር ይገባል፡፡ እርግጥ ነው በዚህ የሽግግር ወቅት ከምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አሿሿም እስከ አወቃቀር ፍተሻ የሚነሱ ጥያቄዎች ቢኖሩም፣ በሒደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን እየፈቱ ማስተካከያዎችን ማድረግ ይቻላል፡፡ ዋናው ቁምነገር ግን ለዴሞክራሲያዊና ለፍትሐዊ ምርጫ መደላድሉን በጋራ ማመቻቸት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡

  ሕገ መንግሥቱ በ1987 ዓ.ም. ከፀደቀ ጀምሮ እስካሁን አምስት ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ እነዚህ ምርጫዎች በውዝግብ የተሞሉ ብቻ ሳይሆኑ፣ የኢትዮጵያዊያንን ሕይወት የቀጠፉም ነበሩ፡፡ በተለይ በምርጫ 97 ማግሥት የደረሰው ቀውስና ቀውሱን ተከትሎ የወጡ አፋኝ ሕጎች አገሪቱን መቀመቅ ከተዋል፡፡ ብዙዎች ሕይወታቸውን ከመገበራቸውም በላይ በርካቶች ለሥቃይ፣ ለእስርና ለስደት ተዳርገዋል፡፡ አራተኛና አምስተኛ ምርጫዎች ደግሞ በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ውለው በመካሄዳቸው በተገኘው አሳዛኝ ውጤት ምክንያት፣ የሕዝብ ብሶት ገንፍሎ ወጥቶ ያጋጠመው ቀውስ አይዘነጋም፡፡ በዚህም ሳቢያ ካለፉት ስምንት ወራት ወዲህ ወደ አዲስ ምዕራፍ ተገብቶ ወሳኝ የሚባሉ መሠረታዊ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፣ እየተወሰዱም ነው፡፡ ከእነዚህ ዕርምጃዎች መካከል መጪውን ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ነፃ የማድረጉ ጅምር ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ቁመና ለመገኘት ዝግጅቱ ምን ይመስላል መባል ይኖርበታል፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጠሩት ውይይት ላይ ስለሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ ሲነሳ፣ የሚገኙበት ቁመና በሚገባ መገምገም ይኖርበታል፡፡ የምንነጋገረው የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ቀርበው ስለሚፎካከሩ ፓርቲዎች ስለሆነ፣  ሕዝብ ፊቱ ቀርቦ ‹‹አለሁ!›› ለማለት አሳማኝ ቁመና ላይ መገኘት የግድ ይላል፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደ አዲስ ይደራጃል የተባለው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መሥፈርቶችን ከዓለም አቀፍ ልምድና ደረጃ አንፃር ሊያዘጋጅ የግድ ነው፡፡ መደራጀት መብት ቢሆንም፣ ሕግና ሥርዓትን የተከተለ መሆን አለበት፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ በምርጫ ጊዜ ብቻ ግር እያሉ የሚያሟሙቁ ሳይሆኑ፣ ለሕዝብ ጠቃሚ አጀንዳ ይዘው የሚቀርቡ ብቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትልቅ ግምት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በድጎማና በተለያዩ ድጋፎች ለማይረባ ዓላማ ተቋቋመው በአገር ላይ የሚቀልዱ ፓርቲ ተብዬዎች ጉዳይ በሕግ ማዕቀፉ በሚገባ መታየት አለበት፡፡ የምርጫ ሕጎችን ከማስተካከልና ቦርዱን ከማደራጀት በተጨማሪ፣ የአገር ከፍተኛ ሀብት የሚወጣበት ምርጫ መቀለጃ እንዳይሆን፣ ብቁ ባልሆኑ ፓርቲዎች ላይ ትኩረት ሊደረግ የግድ ይላል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለዚህ ዘመን የሚመጥን አቋም ላይ መገኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ካሁን በኋላ እየተግበሰበሱ አጃቢ መሆን ያበቃ ይመስላል፡፡

  መንግሥት የፖለቲካ ምኅዳሩን ሁሉን አቀፍና አሳታፊ ከማድረግ በዘለለ፣ ከዚህ በፊት ይታዩ የነበሩ አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎች እንዲገቱ በተግባር ማረጋገጫ መስጠት አለበት፡፡ የመጀመርያው የምርጫ ቦርድ አባላትና አስፈጻሚዎች ገለልተኝነት ትልቅ ሥፍራ ሊሰጠው ይገባል፡፡ በስመ ገለልተኝነት የአንድ ወገን ዓላማ አስፈጻሚዎች ተሹለክልከው ገብተው ትርምስ እንዳይፈጥሩ ነቅቶ መቆጣጠር አለበት፡፡ በሌላ በኩል  የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ተቋሙ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ እንዳያሳድሩ ተገቢውን ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ምርጫው እንደሚፈለገው ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ መሆን የሚችለው ጥብቅ የሆነ መተማመን ሲፈጠር ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን ለትርጉም የሚያጋልጡ ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ፣ አጋጣሚውን ለአንድ የጎራ የበላይነት ለመጠቀም የሚፈልጉ ችግር እንዳያመጡ፣ ከዚህ በፊት ሆን ተብሎም ሆነ በዳተኝነት ይከሰቱ የነበሩ ስህተቶች እንዳይደገሙ፣ ሰላማዊውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በቀላሉ ወደ ጠብና ብጥብጥ የሚወስዱ ድርጊቶች ትኩረት እንዲደረግባቸው፣ ወዘተ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡

  ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በአንድ ወገን ፍላጎት ወይም ጥረት አይደለም፡፡ የጋራ የሆነ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ ለመግባባት ደግሞ በቅጡ መነጋገርና መደራደር ተገቢ ነው፡፡ ምክንያት እየፈጠሩ መጠላለፍ መቆም አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ምሁራን፣ በተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ያገባናል የሚሉ ዜጎች ጭምር በተመሳሳይ ገጽ ላይ መገኘት አለባቸው፡፡ እንደካሁን ቀደሙ በጉልበትና በአጉል ብልጣ ብልጥነት የተጀመረውን በጎ ሒደት መቀልበስ አገርን ችግር ውስጥ መክተት ነው፡፡ ሁሉም ወገኖች ለሕግ የበላይነት ክብደት በመስጠት ለዘመናት ፍትሕ፣ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት የተጠማውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በመጪው ምርጫ ለማርካት ታጥቀው መነሳት አለባቸው፡፡ የአይጥና የድመት ዓይነት ጨዋታ ውስጥ ሆኖ እንኳን ምርጫ ማካሄድ የህልውና ጉዳይም አሳሳቢ ነው፡፡ በተለይ የሞራል ዝቅጠት ማሳያ የሆኑ ቅጥፈቶችና ማጭበርበሮች ከወዲሁ መዘጋት አለባቸው፡፡ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ የሚሰምረው የሚቀጥለው ምርጫ በሁሉም ወገኖች ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ ተዓማኒነት ሲያገኝ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከወዲሁ ንግግር ለመጀመር በአስተማማኝ ቁመና ላይ መገኘት የግድ ይላል!   

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  ለኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸጥበት ታሪፍ ማሻሻያ ተደረገበት

  በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ስምምነቱ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያና የኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል...

  አዲስ አበባ እንዳይገቡ በተከለከሉ ዜጎች ጉዳይ የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ተወያይተው ችግሩ እንዲፈታ አደረጉ

  ለሳምንታት በርካታ ቅሬታ ሲነሳበት የነበረውና ከአማራ ክልል በደብረ ብርሃን...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...

  ለኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸጥበት ታሪፍ ማሻሻያ ተደረገበት

  በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ስምምነቱ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያና የኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ሁለተኛው ተርባይን ሥራ መጀመሩ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈጠረው ደስታ ቃላት ከሚገልጹት...

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን ነፃነትም ተምሳሌት ናት፡፡ የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የሚያኮራ ተግባር ፈጽመው ያለፉት፣ ከአገራቸው በፊት የሚቀድም...