Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ትራንስፖርት ሚኒስቴር በዘርፉ ተዋናዮች ክፉኛ ተተቸ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ትራንስፖርት ሚኒስቴር በቀረፀው የ100 ቀናት ዕቅድና የ2011 ዓ.ም. ሩብ ዓመት ሥራ አፈጻጸም ላይ ዋነኛ የዘርፉን ተዋናዮች ለማወያየት ዓርብ ኅዳር 14 ቀን 2011 ዓ.ም. በጠራው ስብሰባ፣ ክፉኛ ሲተች ዋለ፡፡

  አዲስ የተሾሙት የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ ሚኒስትር ዴኤታዎቹ ወ/ሮ ሕይወት ሞሲሳና ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር በመሩት ስብሰባ ከሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት፣ ከአገር አቋራጭ ደረቅ ጭነት ትራንስፖርትና ከአገር አቋራጭ ነዳጅ ማመላለሻ ትራንስፖርት ባለንብረቶች፣ እንዲሁም ከትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን ከረር ያለ ትችት ቀርቧል፡፡

  የትችቱ መነሻ በትራንስፖርት ዘርፍ የተንሰራፉትን ችግሮች ሚኒስቴሩ መፍታት እንደሚኖርበት በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብለትም፣ ሊፈታ ባለመቻሉ የትራንስፖርት እንቅስቃሴው ሊገታ ጫፍ ላይ በመድረሱ ነው ተብሏል፡፡

  የሊማሊሞ ሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ባለንብረቶች አክሲዮን ማኅበር ሊቀመንበር አቶ በሪሁን አስፋው፣ በአገሪቱ የሚገኙ መንገዶች ክፉኛ የተበላሹ በመሆናቸው የትራንስፖርት እንቅስቃሴው ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባቱን በማስታወስ ትችት አቅርበዋል፡፡

  ‹‹በተለይ ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ክልል በሚያስወጣው እንጦጦ፣ ሱሉልታና ከጎሃ ጽዮን እስከ ደጀን ያለው መንገድ ከጥቅም ውጪ ሆኗል፤›› በማለት የገለጹት አቶ በሪሁን፣ ‹‹ከዛሪማ እስከ ደባርቅ ያለውን መንገድን ጨምሮ ወደ ኤርትራ ጉዞ ይደረግባቸዋል የተባሉ መንገዶች የተበላሹ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

  ከአዲስ አበባ ወደ ሱዳን የሚደረገው ጉዞም የፀጥታ ችግር ያለበት መሆኑን፣ ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ የትራንስፖርት ጉዞ የሚደረግ ከሆነም ጉዳዩ ሊታይ እንደሚገባ፣ ከዚህ ባለፈም ከኤርትራም ሆነ ከሱዳን ጋር ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት መልክ ሊይዝ እንደሚገባ አቶ በሪሁን ጠይቀዋል፡፡

  ‹‹ትግራይ ውስጥ ያለ ነዳጅ በገፍ ወደ ኤርትራ እየተጓዘ ነው፡፡ ይህ ተፅዕኖ አያሳድርም ወይ? በአሁኑ ወቅት በሁለቱ አገሮች መካከል የተጀመረው ኢመደበኛ የንግድ ልውውጥ ሥርዓት ይያዝ በሚባልበት ወቅት በቀላሉ ሊስተካከል ይችላል ወይ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

  የዩኒክ ደረቅ ጭነት ማመላለሻ ባለንብረቶች አክሲዮን ማኅበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጠና ታደለ ቅሬታ ካቀረቡት ውስጥ ናቸው፡፡

  አቶ ጠና እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ ዋነኛው የወጪና የገቢ ዕቃዎች ማጓጓዣ የሆነው የጂቡቲ ኮሪደር፣ በተለይም እስከ ጋላፊ ወደብ ድረስ ያለው 120 ኪሎ ሜትር መንገድ እጅግ በመበላሸቱ የትራንስፖርት ሥራን አክብዶታል፡፡ መንገዱ በመበላሸቱ የመለዋወጫ ዕቃዎች እየተሰባበሩ፣ ምልልሱም ብዙ ጊዜ እየወሰደ ነው ብለዋል፡፡

  ‹‹የትራንስፖርት ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብለትም መፍትሔ ሊያበጅ አልቻለም፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

  አቶ ጠና ጨምረው እንደገለጹት፣ ጂቡቲ ውስጥ አንድ ከባድ ተሽከርካሪ ሲገለበጥ ክሬን አግኝቶ ለማንሳት አስቸጋሪ ነው፡፡ ሥራው የተሰጠው የጂቡቲ ድርጅት ሲጠየቅ፣ አሥር ተሽከርካሪ ሲገለበጥ መጥቼ አነሳለሁ የሚል ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን አቶ ጠና ተናግረዋል፡፡ ‹‹ጂቡቲ ውስጥ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ችግር ከመኖሩም በተጨማሪ፣ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ዕጦት የሰፈነበትና አሽከርካሪዎችም የሚዋከቡበት ነው፡፡ መንግሥት መፍትሔ ሊያበጅ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

  የትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ዘሩ እንደሚሉት፣ ትራንስፖርት ሚኒስትር በተደጋጋሚ ቅሬታ ቢቀርብለትም አስቸኳይ ብቻ ሳይሆን ጭራሹኑ ውሳኔ አይወስንም፡፡

  የሕዝብ ትራንስፖርትና የነዳጅ ማመላለሻ ታሪፍ በተደጋጋሚ ታይቶ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥያቄ ቢቀርብም፣ ሚኒስቴሩ እስካሁን ጥያቄውን አንድ ነገር ላይ ባለማድረሱ ባለንብረቶች ከሥራ እንዲወጡ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

  ‹‹በአገሪቱ በየጊዜው የዋጋ ግሽበት እየታየ ቢሆንም፣ የትራንስፖርት ታሪፍ ማሻሻያ አልተደረገም፡፡ በቁጥር አነስተኛ በሆነ ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ በሚደረግ ጫና አገር ይለማል? እኛ እየሞትን ነው፤›› ሲሉ አቶ ብርሃኑ የችግሩን አሳሳቢነት ተናግረዋል፡፡

  የደጀን ደረቅ ጭነት ማመላለሻ ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክብረት ዓለማየሁ፣ በጂቡቲ ወደብ በተመሳሳይ ሰዓት የሚደርሱ ገቢ ዕቃዎች ችግር እያመጡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

  ‹‹በየዓመቱ 15 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ አገር ውስጥ ይገባል፡፡ ማዳበሪያ ወደብ ላይ አንዴ ሲደርስ በገቢና በወጪ ዕቃዎች ላይ ተፅዕኖ ይፈጠራል፡፡ የትራንስፖርት ድርጅቶች ማዳበሪያ እንዲያነሱ ስለሚደረግ፣ ለፋብሪካ ግብዓት የሚሆኑ ዕቃዎች ዘግይተው የሚገቡ በመሆኑ በፋብሪካ ባለቤቶች ላይም ችግር እየተፈጠረ ነው፤›› ሲሉ አቶ ክብረት የችግሩ ስፋት ሌላም ጉዳት እያመጣ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

  በውይይቱ ላይ በትራንስፖርት ሥምሪት፣ በመናኸሪያና ተርሚናል፣ በመኪና ማቆሚያ፣ መስቀል አደባባይን እንደ መናኸሪያ መጠቀምና ሌሎችም ችግሮች በስፋት ተነስተዋል፡፡

  በስብሰባው ላይ ትራንስፖርት ሚኒስቴርንም ሆነ ተጠሪ ተቋማትን ያወደሰ ሐሳብ አለመነሳቱ ተስተውሏል፡፡

  አዳዲሶቹ ሚኒስትሮችም ሆኑ ተጠሪ ተቋማቶችን የሚመሩ ባለሥልጣናት የተነሱትን ትችት ያረገዙ ሐሳቦች እንደ ግብዓት መውሰዳቸውን አስታውቀው፣ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑንና እየተከናወኑ ስላሉ ሥራዎች ገለጻ አድርገዋል፡፡  

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች