Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  አገር ሊወድቅና ሊነሳ የሚችለው መንግሥት በሚተገብረው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው!

  በፈቃዱ በቀለ (/)

  የመጨረሻ ክፍል

  ወደ ነፃ ንግድ ስምምነት (Free Trade Agreement) ስንመጣ እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ አገሮች ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ ይመስላሉ፡፡ በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ያለው እምነት የነፃ ንግድ ስምምነት የአንድን አገር የኢኮኖሚ ዕድገት ማፋጠን እንደሚችል ነው።
  በእኔ እምነትና ብዙ የኢምፔሪካል ጥናቶችና የቴዎሪ ትንተናዎች እንደሚያረጋግጡት፣ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮችም ሆነ ከቻይና፣ ከአሜሪካና ከአውሮፓው አንድነት ጋር የነፃ ንግድ ስምምነት ማድረጉ እንደዚሁ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል።

   በመጀመርያ ደረጃ፣ የካፒታሊስት አገሮች ስለነፃ ንግድ አስፈላጊነትና በዚህም አማካይነት ለውጥ ይመጣል ብለው ሲሰብኩ ከጥንካሬ በመነሳት ነው። በታሪክ ውስጥ እንደተረጋገጠው 18ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻና 19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ ላይ እንግሊዝ በኢንዱስትሪ አብዮት ከፍተኛ እመርታን ስታገኝ በብዛት የምታመርተውን ምርት ውጭ አገር ገበያ ላይ ለማራገፍ ስትል የግዴታ የነፃ ንግድ ስምምነት ያስፈልጋል እያለች ትወተውት ነበር። እንደ ጀርመንና አሜሪካ የመሳሰሉት በዚህ ዓይነቱ ሰበካ ባለመታለልና በውስጥ ገበያ ዕድገት (Home Market) ላይ በመሰማራት በአንድ ትውልድ ጊዜ ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ መጥቀው ሊሄዱ ችለዋል። በጊዜው እንደ ፍሪድሪሽ ሊስት (Friedrich List) የመሳሰሉት ታላላቅ የጀርመን የኢኮኖሚና የሶሻል ሳይንስ ሊቆች ከውስጥ በማኑፋክቸር ላይ የተመሠረተ የውስጥ ገበያ የሌላቸው አገሮች ራሳቸውን ከመቻላቸውና ተወዳዳሪ ከመሆናቸው በፊት የነፃ ንግድ ስምምነት ማድረግ እንደሌለባቸው ተሟግተዋል። በእነሱም እምነት ወደ ኋላ የቀሩ አገሮች ከአንድ በኢንዱስትሪ ከበለፀገ አገር ጋር የነፃ ንግድ ስምምነት ካደረጉ በዚያው ቀጭጨው እንደሚቀሩ ነው።

  ስለሆነም በኋላ ላይ አዲስ የዕድገት ፈለግን የተከተሉ እንደ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ (Developmental States) የመሳሰሉ አገሮች ገበያቸውን ዝግ በማድረግ ወይም የዕገዳ ፖሊሲ (Protectionism) በመከተል ነው በአንድ ትውልድ ውስጥ በቴክኖሎጂ ማደግ የቻሉት። እንደዚሁም ቻይና የጥገና ለውጥ ማድረግ ከጀመረች 1978 .. ጀምሮ ሠላሳ ዓመት ያህል በሯን ከዘጋችና የተወሰነ የዕድገት ደረጃ ላይ ከደረሰች በኋላ ነው 2005 .. የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባል ለመሆን የበቃችው፡፡ ዛሬ ደግሞ ራሷ በመወትወትና የአፍሪካ አገሮችን በማታለል የነፃ ንግድ ስምምነት እንዲደረግ ግፊት ታደርጋለች። አሁን በቅርቡ ጂቡቲ የተቋቋመው የነፃ ንግድ ሠፈር ቻይና በብዛት የምታመርተውን ምርት እዚያው በማራገፍ በአካባቢው ያሉ ገበያዎችን ለመቆጣጠር እንጂ ጂቡቲ ውስጥ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት አይደለም። በተለይም በዚህ ዓይነቱ የነፃ ንግድ ስምምነት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች በከፍተኛ ደረጃ ሊጎዱ ይችላሉ። እዚያ የሚራገፈው ምርት ካለምንም ቀረጥ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በማደግ ላይ ያሉ የጫማና የጨርቃ ጨርቅና ሌሎች ኢንዱስትሪዎችን ሊያዳክማቻው ይችላል። ስለሆነም የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አገዛዝ በተለይም ከጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ዕቃዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የታሪፍ ጭመራና ከታሪፍ ውጭ የሆኑ ማዕቀቦችን ተግባራዊ ማድረግ የሚኖርበት ይመስለኛል።

  በአጠቃላይ ሲታይ የነፃ ንግድ ስምምነት አሁን ባለው የዓለም የኢኮኖሚ ሁኔታ አማራጭ መንገድ አይደለም። ደካማ አገሮች ከአቅማቸውና ከሚፈልጉት በላይ ሌሎች አገሮች የሚመረቱ ዕቃዎችንና የእርሻ ውጤቶችን በማስገባት ከውስጥ የማምረት አቅማቸው እንዲዳከም ይደረጋል። ቴክኖሎጂዎችን ለመግዛት የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሪ ወደ ሌሎች ለዕድገት ይህንንም ያህል በማይጠቅሙ ምርቶች ላይ በመዋል እንዲባክን ይደረጋል። ከዚህም ባሻገር የነፃ ንግድ ስምምነት ወደ ውስጥ ሰፋ ያለ በሥራ ክፍፍል ላይ የተመሠረተ የውስጥ ገበያ እንዲያድግ የሚያግዝ ሳይሆን፣ አንድን አገር በተወሰኑ የእርሻ ምርቶች ላይ ብቻ እንድትረባረብ ያስገድዳታል። ይህ ብቻ ሳይሆን የማያስፈለግ የፍጆታ አጠቃቀም በመግባትና በመለመድ የተወሰነውን የኅብረተሰብ ክፍል አመፀኛ ሊያደርገው ይችላል። በተለይም ጥራት የሌላቸው የምግብ ዓይነቶች በመግባት አዳዲስ በሽታዎችን ሊያስከትሉ ይችላሉ።

  በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪ አገሮች የሚመረቱ ምርቶች ዝቅተኛ ገቢ በሚያገኘው የኅብረተሰብ ክፍል ላይ የሚያስከትሉት የጤንነት ጉዳት ከቁጥጥር ውጭ እየወጣ ነው። ይህ ጉዳይ በተለይም አሜሪካ በግልጽ ሲታይ፣ ገቢው ዝቅተኛ የሆነው የጥቁሩ የኅብረተሰብ ክፍል በደም ግፊት፣ በልብ በሽታ፣ በስኳርና በነቀርሳ እንዲሁም በውፍረት ይሰቃያል። ከዚህም ባሻገር ይህ ዓይነቱ የተትረፈረፈ ምርት የብዙ ኢንዱስትሪ አገሮችን ሰዎች ጭንቅላት ወደ ተጠቃሚነት ብቻ እንዲያመሩ በማድረግ የኅብረተሰብን አኗኗር (ኖርም) የሚያናጉ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው።

  ከዚህ ስንነሳ በደንብ ያልተጠናና ገደብ የሌለው የፍጆታ አጠቃቀምና የነፃ ንግድ ስምምነት የመጨረሻ መጨረሻ ኅብረተሰብዓዊ መናጋትን ሊያስከትል እንደሚችል ብዙ ጥናቶች ያመለክታሉ። ይህንን ዓይነቱን ሁኔታም የግሪክ ፈላስፋዎች በጥንቱ ዘመን ቀደም ብለው ያዩትና የተነበዩት ጉዳይ ነው። በእነሱ እምነትም ማንኛውም ነገር በማሰብ መካሄድ ያለበትና ሚዛናዊነትን የጠበቀ መሆን አለበት። መንፈሳዊና ማቴሪያላዊ ሁኔታዎች ሚዛናቸውን ጠብቀው መጓዝ አለባቸው። ከዚህ ስንነሳ ግሎባል ካፒታሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የጤንነትና የአካባቢ ቀውሶችን በማስከተል የተፈጥሮንና የብዙ ኅብረተሰቦችን ሚዛን በማቃወስ ላይ ይገኛል።

  ከዚህ ባሻገር አገራችን አሁን ባለችበት ሁኔታ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ጋር የነፃ ንግድ ስምምነት ማድረጓ ጥቅሙ አይታየኝም። አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ተመሳሳይ ምርቶችን ስለሚያመርቱ ከቴክኖሎጂ ጋር የሚያያዝ የመዋለ ንዋይ ፍሰት ሊኖር አይችልም። በሁለተኛ ደረጃ፣ ኢትዮጵያ ከጉምሩክ ቀረጥ የምታገኘው ገቢ ይቀራል። አገዛዙ ባጀቱን ለማሟላት ሲል ሌላ የገንዘብ ምንጭ መፈለግ ይኖርበታል። በሦስተኛ ደረጃ፣ በአጠቃላይ ሲታይ በማደግ ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎች (Infant Industires) ከውጭ በሚመጣ ተመሳሳይ ምርት ይጎዳሉ። ስለሆነም በእነዚህ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ተቀጥሮ የሚሠራው ሠራተኛ የተወሰነው ከሥራው ሊባረር ይችላል። በአራተኛ ደረጃ፣ የነፃ ንግድ ስምምነት የባህል ጥራትን አያመጣም።

   እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ዋናውና ተቀዳሚ ተግባር በጠንካራ መሠረት ላይ የሚመረኮዝ የውስጥ ገበያ ማዳበርና ማስፋፋት ነው። ከተማዎችንና መንደሮችን መገንባት ነው ቅድሚያ መሰጠት ያለበት፡፡ በተጨማሪም ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ማቋቋም ሰፋ ላለ የሥራ ክፍፍል መዳበር ያመቻል። ስለሆነም የእርሻ መሣሪያዎችን ለማምረትና ለገበሬው ለማቅረብ ይቀላል። ከዚህም ባሻገር በየቦታው ተቋማት (Institutions) እንዲቋቋሙ ማድረግና በብዛት የሰው ኃይል ማሠልጠን ሰፋ ላለ የኢኮኖሚ ዕድገት ያመቻል። እነዚህን የመሳሰሉ ኢንዱስትሪዎችና ተቋማት ከባህላዊ ክንዋኔዎች ጋር ሲያያዙ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ኅብረተሰብዓዊ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። በአንፃሩ የነፃ ንግድ ስምምነት አንድን ደካማ አገር በሁሉም አቅጣጫ እንዳያድግ ቆልፎ ይይዘዋል። ለአንድ ኅብረተሰብ ተስማምቶ መኖር የሚያስፈልጉ የተለያዩ ነገሮች ይታፈናሉ።ይህ ማለት ግን ከተለያዩ አገሮች ጋር የንግድ ልውውጥ አይኑረን ማለቴ አይደለም። ለማለት የፈለግኩት በመጀመርያ ደረጃ አስፈላጊና መሠረታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ እንረባረብ ነው።

  የውጭ ዕርዳታ ጉዳይና የሚያስከትለው ውጤት!
  የውጭ ዕርዳታ (Economic Aid) ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የኮሙዩኒዝምን ርዕዮተ ዓለም መስፋፋት ለመዋጋትና አብዛኛዎችን የሦስተኛው ዓለም አገሮችን በአሜሪካ ቁጥጥር ወይም ተፅዕኖ ሥር ለማምጣት በጊዜው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በነበሩት በትሩማን የቀረበና ወደ ተግባራዊነት የተለወጠ ሐሳብ ነው። ይህም ማለት ሐሳቡ ሲነደፍ ዋናው ዓላማው በተለይም የአፍሪካን አገሮች ወደ ካፒታሊስት ሥርዓት በመለወጥ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ሳይሆን፣ በዕርዳታ ስም በእነዚህ አገሮች ልዩ ልዩ ተቋማት ውስጥ ሰርጎ በመግባትና ለአሜሪካ የሚያድርና የአሜሪካን ትዕዛዝ የሚቀበል ልሂቅ በማፍራት ወደ ውስጥ የተስተካከለና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳይመጣ ማሳሳት ወይም ማገድ ነው።

  የኢኮኖሚ ዕርዳታ ተግባራዊ ከሆነ ወደ ሰባ ዓመት ሲጠጋው በነዚህ ዓመታት ውስጥ ወደ አፍሪካ ብቻ ከአንድ ትሬሊዮን በላይ የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር ፈሷል። አሜሪካኖችም ሆኑ የተቀሩት የምዕራብ አውሮፓ መንግሥታት የሚሰጡት ዕርዳታ እነሱ በሚፈልጉት መልክና ከነሱ ጥቅም ጋር ከሚያያዝ ፕሮጀክት ጋር ስለሆነ ሁለንተናዊነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያግዝ ወይም የሚያፋጥን አይደለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ በተናጠል ፕሮጀክቶች ላይ ያነጣጠሩ ዕርዳታዎች ከውስጥ ኢኮኖሚው ጋር የሚያያዙና የውስጥ ገበያን የሚያዳብሩ ሳይሆኑ ከውጭው የዕርዳታ ሰጪ አገር ኢኮኖሚ ጋር የሚተሳሰሩ ናቸው።

   ይህ ዓይነቱ እያደገ የመጣ የዕርዳታ ኢንዱስትሪ ለካፒታሊስት አገሮች የሥራ መስክ መክፈቻና በተጨማሪም ዕቃን በማራገፍና በዕዳ በመተብተብ ለሀብት ክምችት መሠረት የሆነ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በዕርዳታ ስም በየአገሩ የሚሰማሩ ኢክስፐርቶች ዋና ተግባር ዕውቀትን ይዞ መምጣት ሳይሆን መሠረታዊ የዕድገት ፈለግን በማሳሳት የድህነት ዘመንን ማራዘም ነው። አንዳንድ ጥናቶችም እንደሚያረጋግጡት በዕርዳታ ስም በየቦታው የሚሰማሩ ሰዎች ዋና ተግባር ኢንፎርሜሽኖችን በመሰብሰብ ለየአገሩ መንግሥታት በማቀበል፣ በዚያው መጠንም በየአገር ውስጥ በሃይማኖትና በጎሳ ስም የሚነሱ ግጭቶችን ማስፋፋት ወይም እንዲፋፋሙ ማድረግ ነው። የእርስ በርስ ጦርነት የሚካሄድ ከሆነና አለመተማመን ከተፈጠረ የመንግሥታት ተግባር ጦርነትን ማካሄድ ይሆናል። ሕዝቡም በጦርነት ስለሚጠመድ ለማሰብና ለመፍጠር በፍፁም ዕድል አያገኝም። ስለሆነም የአንድ ደካማ አገር ሕዝብ አስተሳሰብ ችግርን በመቅረፍ ላይና ጤናማ ኅብረተሰብን በመገንባት ላይ ማተኮር የለበትም የሚል ውስጣዊ ስምምነት (Tacit Agreement) አለ። ከዚህም ባሻገር ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ከዕርዳታ ጋር ተጓተው የመጡ በሽታዎች የየአገሮችን እሴቶች በማውደም አንድ አገር በቀላሉ ሊጠቃ የሚችልበትን ሁኔታ እንዳመቻቹ እንመለከታለን።

  እስካሁን ድረስ በኢምፔሪካል ደረጃ እንደተረጋገጠውና እንደምናየውም ባለፉት ሠላሳና አርባ ዓመታት በተከታታይ ዕርዳታን የሚያገኙ አገሮች ከድህነትና ከረሃብ እንዳልተላቀቁ ነው የምናየው። የሚሰጠው ዕርዳታ የባሰውኑ ጥገኛና ራሳቸውን እንዳይችሉ በማድረግ የድህነትን ዘመን እንደሚያራዝም ነው። በታሪክም እንደተረጋገጠው አንድ አገር ሊያድግ የሚችለው በራሱ ኃይልና በጥበብ ከውጭ በሚኮርጀው ወይም በሚሰርቀው ቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ ነው። ስለሆነም አገራችንም ሆነ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ከዕርዳታ ለመላቀቅ አስፈላጊውን ዕርምጃ መውሰድ አለባቸው። ለዚህ ደግሞ በመጀመርያ ደረጃ በአገር ውስጥ ባለው የተትረፈረፈ የጥሬ ሀብትና የሰው ኃይል መመካት ሲሆን፣ ከኒዎሊበራሊዝም ነፃ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ቢደረግ የአፍሪካ አገሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ድህነትን በመቅረፍና በማስወገድ ቀስ በቀስ ወደ ተስተካከለ ዕድገት ሊያመሩ ይችላሉ።

  ይህንንም ለማድረግ በዕርዳታ ስም የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ የሆኑና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ቁጥር መቀነስና የመጨረሻ መጨረሻም ለቀው የሚወጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት አስፈላጊ ነው። በሌላ ወገን ግን ወጣቱን የተለያየ ሙያ የሚያስተምሩና የሚያሠለጥኑ ሰዎችን በማፈላለግ ወደ አገራችን እንዲገቡ መጋበዝ በጣም ጠቃሚ ነው። ያም ሆነ ይህ አንድ አገር እንደ ማኅበረሰብና ኅብረተሰብ በሁሉም አቅጣጫ እንዲያድግ የምንፈልግ ከሆነ የግዴታ መወሰድ ካለባቸው ነገሮች መቆጠብ ያለብን አይመስለኝም።
  ማጠቃለያ

  በአንድ አገር በተለይም ወደ ኋላ በቀረ አገርና ኅብረተሰብ ውስጥ ተግባራዊ የሚሆን የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲያው በደፈናው ተግባራዊ መሆን የለበትም። አንድ ፖሊሲ ከመታቀዱና ከመተግበሩ በፊት የአንድን አገር የማቴሪያልና የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ በቲዎሪ ደረጃ በደንብ መተንተን ያስፈልጋል። የአንድን አገር ተጨባጭ ሁኔታ በቲዎሪና በሳይንስ ብቻ መተንተን የሚቻል እንደመሆኑ መጠን አንድን ተጨባጭ ሁኔታ ለማንበብ የሚጠቅመንን የቲዎሪና የሳይንስ መሣሪያ በሚገባ ማወቅ አለብን። የአንድን አገር የተወሳሰበ ችግር በተሳሳተ መልክ የምናነብና ትንተና የምንሰጥ ከሆነ ለችግሩ ትክክለኛ መፍትሔ ልናገኝ በፍጹም አንችልም።

  እንደምናውቀው ዛሬ አብዛኛዎቹ በዓለም ላይ ያሉ አገዛዞች የሚጠቀሙባቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ የፈለቁት ባደጉ የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ነው። በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ በተለያየ ወቅት የፈለቁት ቲዎሪዎችም ሆነ ፖሊሲዎች በአንድ ጊዜ ከመቅጽበት የፈለቁ ሳይሆኑ ከረዥም ጊዜ ምርምር ባኋላ ነው። ይሁንና ግን የተለያዩ ቲዎሪዎችም ሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች የፍልስፍና መሠረት አላቸው። ስለሆነም በየአንዳንዱ ኤፖክ [ዐረፍተ ዘመን] ብቅ ያለ ምሁር እሱ በሚመስለው መንገድ በጊዜው የነበረውን ተጨባጭ ሁኔታ በማንበብ ለሱ ይስማማል ብሎ ያሰበውንና ያመነበትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ አፍልቋል።

  በሌላ ወገን ግን አንድን ተጨባጭ ሁኔታ ለማንበብ በተለያዩ ምሁራን ዘንድ አንድ ዓይነት ግንዛቤና ስምምነት አልነበረም። አንደኛው የምሁር ክፍል ለተወሰነው የኅብረተሰብ ክፍል ሲያደላና፣ ከዚያ በመነሳት ቲዎሪና ፖሊሲ ሲያፈልቅ፣ ሌላው ደግሞ በዚህ ዓይነቱ ወደ አንድ ወገን በሚያደላው ፖሊሲና ቲዎሪ የማይስማማው የሚያምንበትንና እኩልነትን ሊያመጣ ይችላል የሚለውን ፖሊሲ በማፍለቅ ሐሳቡ ተቀባይነት እንዲያገኝ ይታገላል። ይህ ዓይነቱ በሐሳብ ዙሪያ መታገልና በአመኑበት ፀንቶ መቆየት በአውሮፓ የምሁር እንቅስቃሴ ታሪክ ውስጥ የተለመደ ነው። ስለዚህም ነው በአውሮፓ ምድር ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ ዕድገት ሊመጣ የቻለው።

  ወደ ሦስተኛው ዓለም አገሮች ስንመጣ ግን በተለያዩ ጊዜያት ተግባራዊ ያደረጓቸውና የሚያደርጓቸው ፖሊሲዎች በሙሉ የፈለቁትና የዳበሩት በካፒታሊስት አገሮች ነው። የእነዚህን ዕውቀቶች፣ በተለይም የኢኮኖሚ ፖሊሲን የቲዎሪና የፍልስፍና መሠረት ሳይመረምሩ በደፈናው ተግባራዊ ያደረጓቸውና የሚያደርጓቸው ፖሊስዎች በሙሉ ዛሬ በአብዛኛዎቹ የሦስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ ለሚታየው ድህነት፣ ኢሰብዓዊነት፣ ኅብረተሰብዓዊ መዘበራረቅ፣ የአካባቢ መቆሸሽና በቆሻሻ ቦታዎች መኖርና ሀብት መባከን ተጠያቂዎች ናቸው። በተለይም በአፍሪካ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ልሒቅ (ኤሊት) እምነት ማንኛውም በምዕራቡ ዓለም የፈለቀውና የዳበረው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዓለም አቀፋዊ ባህሪ አለው። ስለሆነም ከፖለቲካ ኃይል አሠላለፍ፣ ከባህል፣ ከአስተሳሰብና ከአደረጃጀት እንዲሁም ከሥራ ባህል ባሻገር በምዕራቡ ዓለም የፈለቀው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማንኛውም አገር ተግባራዊ ሊሆን ይችላል። ይህ ዓይነቱ ጭፍን አስተሳሰብና እምነት፣ እንዲሁም የእያንዳንዱን አገር ኅብረተሰብዓዊ አወቃቀር በደንብ ሳይመረምሩ ተግባራዊ የሚሆን ፖሊሲ እንደምናየው አብዛኛዎቹን አገሮች ለድህነት የዳረገ፣ ለሀብት መባከን ምክንያት የሆነና፣ ከፍተኛ የሆነ የአካባቢ ውድመትን ያስከተለ ነው። በተለይም ካፒታሊዝም ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ በአሸናፊነት ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በአፍሪካ መንግሥታት ላይ በረቀቀ መልክ በሚደረገው ጫና ሳይወዱ በግድ እየደጋገሙ አገር አውዳሚ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ተገደዋል።

  የኒዎሊበራል ማክሮ ኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ በአሸናፊነት ከወጣ ጀምሮ በተለይም ባለፉት አርባ ዓመታት ከልምድ፣ ከባህል፣ ከኢኮኖሚ አወቃቀር፣ ከፖለቲካ ኃይል አሠላለፍና ከታሪክ ባሻገር ሁሉም አገሮች መከተል ያለባቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው እየተባለ ነው የሚናፈሰው። ስለሆነም የሰው ልጅ የገበያን ኢኮኖሚ ሊቀዳጅ የቻለውና የሚችለው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረጉ ብቻ ነው። የገበያን ኢኮኖሚ እንደ ርዕዮተ ዓለም አድርገው በሚያምኑና፣ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ መሆን አለበት ብለው በሚሰብኩ በኒዎሊበራል ኢኮኖሚስቶች እምነት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቦታ የላቸውም። የገበያ ኢኮኖሚም ካለጊዜና ካለቦታ ነው የሚካሄደው። የሰው ልጅም የሚኖርበት ቤትና የሚንቀሳቀስበት ልዩ ልዩ የመመላለሻና የመገናኛ መሣሪያዎች አያስፈልጉትም። ከዚህም ባሻገር እንደፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ፣ ማቲማቲክስ፣ መካኒካል ኢንጂነሪንግ፣ ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ፣ አርኪቴክቸር፣ የከተማ ዕቅድና እንዲሁም ለሰው ልጅ የሚጠቅሙ ልዩ ልዩ የዕደ ጥበብ ሙያዎች በሙሉ ቦታ የላቸውም። ወይም ደግሞ እንዳሉ ወይም እንደተሰጡ (As Given) ተደርገው ነው የሚወሰዱት።

  ይህ ዓይነቱ አሳሳች አመለካከትና ኢኮኖሚ የሚባለው ነገር ካለነዚህ መሠረታዊ የዕድገት አውታሮች ይንቀሳቀስ ይመስል የሰው ልጅ ሁሉ ትርፍን በማካበትና ጥቅምን በማሳደግ ላይ ብቻ መረባረብ አለበት። ስለሆነም የሰውን ልጅ ፍላጎት ገበያ ይፈታዋል፤ የሰው ልጅ በሙሉ በገበያ ኢኮኖሚ ፍልስፋና መሽከርከር አለበት። እንደምናየውና እንደምንኖርበት በተለይም ይህ ዓይነቱ የተዛባ አመለካከት አገሮችን መቀመቅ ውስጥ ከቷቸዋል። ኅብረተሰብዓዊ ውዝግብን የፈጠረና ብዙ አገዛዞችም ሁኔታዎችን ለመቆጣጠር የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።

  የብዙዎቹ የሦስተኛው ዓለም አገሮችም ችግር በዚህ ዓይነቱ አሳሳች እምነትና በሳይንስ ባልተረጋገጠ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ማስነበብ በማይችል ቲዎሪ መሰል ነገር በመመራታቸው ነው። እጅግ በረቀቀ መልክ በማቲማቲካል ሞዴል የሚቀርቡ ፖሊሲዎች አብዛኛዎችን የአፍሪካ አገሮችን መንግሥታት በማሳሳት ያላቸውን የጥሬ ሀብቶች በሥነ ሥርዓት እንዳይጠቀሙና ፍትሐዊነት የሰፈነበትና የተከበረ ኑሮ እንዳይኖሩ ተገደዋል። ኑሯቸውም ወደ አልባሌነት በመለወጥ የሰው ልጅ መጫወቻና የተፈጥሮ ሰለባ ሊሆኑ በቅተዋል። ከዚህ ስንነሳ ፕላቶ እንደሚለው ‹‹ስለተራ ነገር ሳይሆን የምናወራው ስለሰው ልጅ ሕይወት ነው። የሰው ልጅም ሕይወት የተከበረ ነው።›› ስለሆነም መነሳት ያለበት ጥያቄና ክርክር በምን ዘዴና ቲዎሪ በመመራት ነው የተስተካከለ ዕድገት ማምጣትና ፍትሐዊ የሆነ ኅብረተሰብ መመሥረት የሚቻለው? ብለን ነው መጠየቅና መከራከር ያለብን።

  በውጭ ኤክስፐርቶች ወይም በዓለም አቀፍ ኮሙዩኒቲው እየተመራን ተግባራዊ የምናደርገው ፖሊሲ የባሰ ትርምስ ውስጥ የሚከተንና ወደ ጦርነትም የሚያመራን ነው። ስለሆነም ምርጫችን ቀናውን መንገድ በመከተልና አሳሳቹን ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይሆናል። ከዚህ ባሻገር ለአንድ አገር የተፋጠነና የተስተካከለ ዕድገት የአገር ወዳድ ስሜት መኖር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። በምሁሩ ዘንድም የጋራ መንፈስ (Collective Spirit) መኖር ለተስተካከለና ሰብዓዊነት ለሚኖረው ዕድገት ያመቻል። ስለሆነም ለራስ ሕዝብና አገር ቅድሚያ መስጠት የአንድ አገር ምሁር ግዴታ መሆን አለበት። ማንኛውም ምሁር የአገሩንና የሕዝቡን ጥቅም ማስቀደም አለበት። ለዚህ ደግሞ የዓለም አቀፍን የኢኮኖሚ ሥርዓትና መካኒዝሞችን በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል።

  አንድ አገዛዝና ምሁር ካፒታሊዝም በአገር ደረጃም ሆነ በዓለም ደረጃ እንዴት እንደሚሠራና የሦስተኛውን ዓለም አገሮች በሱ የብዝበዛ ወጥመድ ውስጥ ከቶ እንዴት አድርጎ ወደ ድህነትና ወደ ጥገኝነት እንደሚከታቸው በዚህ ላይ ጠለቅ ያለ ዕውቀትና ግንዛቤ እንዲኖረው ያስፈልጋል። ይህ ዓይነቱ ግንዛቤ ሲኖር ብቻ ነው ስለሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በማኑፋክቸር ላይ ተመርኩዞ ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ ስለመገንባት ማሰብና ማውራት የሚቻለው። በመሆኑም ጠንካራ መንፈስ ሊኖረው የሚችል የፖለቲካና የኢኮኖሚ ልሂቅ ማሠልጠኑ የጊዜው አንገብጋቢ መሠረተ ሐሳብና ሊታለፍ የሚገባው ነገር አይደለም። ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይም የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ምሁር ሁሉ የኅብረተሰብንና የኢኮኖሚ ዕድገትን፣ የሳይንስንና የቴክኖሎጂን ጉዳይ. . . ወዘተ. ሊወያይና ሊከራከር የሚችልበት መድረክ መዘጋጀት አለበት። ከአጭር ጊዜም ሆነ ከረዥም ጊዜ አንፃር የአገራችን የተወሳሰቡ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት በዚህ መልክ ነው እያለ እያንዳንዱ ድርጅትና እንዲሁም ግለሰብ የጥናት ጽሑፎችን በማቅረብ በድፍረት መከራከርና ሕዝቡን ማስተማር አለበት። በዚህ መልክ ብቻ ማን ለምን ዓይነት የኅብረተሰብ ራዕይ እንደቆመና፣ በምን ዓይነት የቲዎሪና የፖሊሲ መሣሪያ የአገራችንን የተወሳሰቡ ችግሮች ለመፍታት በቂ ግንዛቤ እንዳለው መረዳት ይቻላል።

   በኛ ዘንድ ያለው ትልቁ ችግር የኢኮኖሚና የኅብረተሰብ ዕድገት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ጥበብና የባህል ዕድገት በሚሉት ለአንድ አገር መተሳሰርና ጥንካሬ በሚያስፈልጉ መሠረተ ሐሳቦች ላይ ለማጥናት፣ ለመወያየትና ለመከራከር ዝግጁ አለመሆን ነው። አብዛኛዎች ለሥልጣን እንታገላለን የሚሉ ድርጅቶች ፖለቲካ የሚባለውን ግዙፍ ጽንሰ ሐሳብ ከነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች ነጥለው በማየት ምሁራዊ ውይይት እንዳይደረግ ከፍተኛ መሰናክል ፈጥረዋል። ስለሆነም በየቦታው ሳይንስንና ቴክኖሎጂን የመጥላት ስሜት አለ። ጊዜው የሳይንስና የቴክኖሎጂም ቢሆንምና ሁላችንም የምንቀሳቀሰውና የምንጠቀመው በቴክኖሎጂ አማካይነት ቢሆንም፣ በነዚህ መሠረታዊ፣ ለአንድ አገር አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አትኩሮ ያለመስጠት አዝማሚያ አለ። ለዚሁ ሁሉ ችግር ሁላችንም ጭንቅላታችንን ብሩህ በሚያደርግ በእውነተኛ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ባለማለፋችን የአገራችንን ዕድል ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ጋር አያይዘን ለማየት እንዳንችል ተደርገናል።

  በተለይም ፖለቲካ የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ችግርን መፍቻ፣ ታሪክን መሣሪያና ለሳይንስና ለቲክኖሎጂ መሠረት ጣይ መሆኑ ቀርቶ ሥልጣንን መያዣ መሣሪያ ተደርጎ በመወሰዱ በፖለቲካው መስክ ሽወዳና ተንኮል እንዲሁም ምቀኝነትና መናናቅ ሰፍነውና ሥር ሰደው ለእውነተኛ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ እንቅፋት ፈጥረዋል። ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ቡድናዊ ስሜትን በማጎልመስ በሐሳብ ዙሪያ ከመሰባሰብና ለዕድገት የሚያመች ሁኔታ ከመፍጠር ይልቅ አብዛኛዎቻችን 21ኛው ክፍለ ዘመን ያለን አስተሳሰብ እጅግ የሚያሳዝንና ወደ ኋላ የሚጎትት ነው። በአውሮፓ ምድር ውስጥ የሳይንስን፣ የቴክኖሎጂን፣ የፍልስፍናንና የቲዎሪን ዕድገት ስንመለከት እነዚህ ዕውቀቶች ሊዳብሩና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊስፋፉ የቻሉት አፍላቂዎች ጭንቅላታቸው ከተንኮል የፀዳ በመሆኑና ኋላቀር አስተሳሰብን አሽቀንጥረው በመጣላቸው ነው። ማንኛውንም ነገር፣ ኅብረተሰብንም ሆነ ተፈጥሮን በፍልስፍና፣ በሳይንስና በቲዎሪ መነፅር በመመልከታቸውና በመመርመራቸው ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ግኝቶች የሚያመቹ ሁኔታዎችን ፈጥረው አልፈዋል። ስለሆነም በአገራችን ምድር መሠረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ከፈለግን የግዴታ የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ አለብን። ተንኮልና ሽወዳ እንዲሁም ምቀኝነት ለአንድ አገር ዕድገት ፀር መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርብናል።

  ከዚህ በተረፈ በአሁኑ ጊዜ አፍጦ አግጦ የሚታየውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመፍታት የግዴታ ምግብ ለሥራ (Food for Work Program) የሚል ለብዙ ዓመታት የሚዘልቅ ዕቅድ መዘጋጀት አለበት። መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት የግዴታ መንግሥትና የየክልሉ አስተዳዳሪዎች ተግባራዊ ሊያደርጓቸው የሚችሉ ደረጃ በደረጃ ሊከናወኑ የሚችሉ ነገሮች አሉ። ከዚህ ቀደም እንዳሳሰብኩት ምግብ ለሥራ (Food for Work) የሚለውን መርሐ ግብር ተግባራዊ ለማድረግ በተለይም ውጭ አገር የሚኖረው ኢትዮጵያዊ እንደየችሎታው በወር የተወሰነ ገንዘብ ቢያወጣ ገንዘቡ ሰፋ ላለ የአገር ግንባታ ላይ ሊውል ይችላል። ቤቶችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ከተማዎችንና መንደሮችን እንዲያም ሲል የባህል ማዕከሎችንና የተግባረዕድ መማርያዎችን ለመደጎምና ለመሥራት ይጠቅማል።

  ሁላችንም እንድምናውቀው አገራችን እንደ ኅብረ ብሔርና እንደ ማኅበረሰብ በደንብ ያልተገነባች አገር እንደ መሆኗ መጠን ማንኛውም ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ከረዥም ጊዜ አንፃር መተለም ያለበት ጉዳይ ነው። ሕይወት ያላቸውና በውኃና በዛፎች የተከበቡና ያሸበረቁ እንዲሁም ልዩ ልዩ ድልድዮች ያሏቸው ከተማዎችና መንደሮች የአንድ ሕዝብ መግለጫዎችና ሊኖርበትም የሚያስችሉ ናቸው። የአገራችንን የተትረፈርፉ የጥሬ ሀብቶች በማንቀሳቀስ ላይ የተዘረዘሩትን ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕውን ማድረግ ይቻላል። በአገር ግንባታ ውስጥ ሰፊ ሕዝብ ሳይንቀስቃሰና ሳይሳተፍ ኅብረተሰብዓዊ ለውጥ የመጣበት አገር የለም። ይህንን አስመልክቶ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አገዛዝ የገንዘብ መሰብሰቢያ የባንክ ቁጥር ከፍቷል። ይሁንና ግን ውጭ አገር ከሚኖረው ኢትዮጵያዊ የሚሰበሰበው ገንዝብ በምን ዓይነት ፕሮጀክቶች ላይ እንደሚውል የሰጠው ማብራሪያ የለም። ስለሆነም የሚሰበሰበው ገንዘብ በምን ዓይነት ፕሮጀክቶች ላይ እንደሚውል አገዛዙ ጥናትና ማብራሪያ ማሠራጨት አለበት። የሚሰበሰበው ገንዘብ ከፕሮጀክት ጋር የሚያያዝ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት። ገንዘቡ የውጭን ዕዳ ለመክፈል ወይም የውጭ ምንዛሪን ለመቅረፍ ሲባል ባልሆኑ ነገሮች ላይ መዋል የለበትም።

   ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓ ምድር የተካሄደውን የገንዘብ ስብሰባ ስንመለከት መሠራት ካለባቸው ነገሮች ጋር የተያያዘ ነው። ይህ ሲሆን ብቻ ለመሰብሰብም ሆነ ውጤቱንም ለመቆጣጠር ያመቻል። ከገንዘብ ስብሰባ ጋር በማያያዝ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ አገዛዝ ወደ ሃያ የሚጠጉ ታዋቂ ሰዎችን ሰይሟል። የአብዛኛዎችን ስም ዝርዝር በምንመለከትበት ጊዜ ስለኅብረተሰብና ስለኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸው ግንዛቤ የቱን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ያስቸግራል። ብዙ ስዎችን ማካተቱ የመደመር ስትራቴጂ አንድ አካል ቢሆንም የሚመረጡት ግለሰቦች ዝና ስላላቸው ብቻ መመረጥ ያለባቸው ሳይሆኑ ስለኅብረተሰብ ሳይንስና ስለአገር ግንባታ በቂና ሰፋ ያለ ግንዛቤ ያላቸው መሆን አለባቸው። በተጨማሪም በራሳቸው የሚተማመኑና የውጭ ኃይሎች ተቀጥያ መሆን የለባቸውም።

  ለማንኛውም ከዚህ አልፈን አሁን ያለውን የዋጋ ግሽበት ለመቋቋም በመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ቁጥጥርና ትመና ማድረግ አስፈላጊ ይመስለኛል። በአሁኑ ጊዜ ሕዝቡ በኑሮ ውድነት በጣም እየተማረረ ነው። በተለይም የጥቁር ገበያን ለመቆጣጠርና የዋጋ ግሽበትን ለመግታት በኢትዮጵያ ብር ላይ ጥገናዊ ለውጥ (Currency Reform) ማድረግ ያስፈልጋል። አዲስና በቀላሉ ሊኮረጅ የማይችል ገንዘብ ሲታተም የድሮውን ገንዘብ አንድ በሁለት በመለወጥ ከዝውውር ውስጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማውጣት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ከዚህ ጋር ተደምሮ የኢትዮጵያ ብር ከዶላር ጋር ያለው ግንኙነት መስተካከል አለበት። እስካሁን ድረስ በተከታታይ ገንዘብን ዝቅ (Devaluation) ማድረጉ የአገራችንን የንግድ ሚዛን አላሳደገውም ወይም ቡናና ሌሎች የጥሬ ሀብቶችን በመሸጥ ብቻ በቂ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አልቻልንም። እንዲያውም የአገሪቱ የንግድ ሚዛን ወደ ታች ማሽቆልቆሉ ብቻ ሳይሆን በዕዳም ለመተብተብ በቅታለች። ከዚህም በላይ የኢትዮጵያ ብር ዝቅ ማለት ግሽበትን አስከትሏል። በተለይም ከውጭ የጥሬ ሀብቶችንና የመለዋወጫ ዕቃዎችን የሚያስመጡ አምራቾች አንድ ዶላር ለመግዛት ብዙ የኢትዮጵያ ብር ማቅረብ ስላለባቸው ይህ በራሱ የማምረቻን ዋጋ ያሳድገዋል። ይህም ማለት የመጨረሻ ምርቶች ገበያ ላይ ወጥተው በሚሸጡበት ጊዜ ዋጋቸው ይወደዳል። ስለሆነም በብርና በዶላር መካከል ያለው ግንኙነት ቋሚ መሆን ሲኖርበት፣ እንደየሁኔታው የኢትዮጵያን ብር ከፍ (Revaluate) ማድረግ ያስፈልጋል። አሁን ካለው የዶላር/ብር ልውውጥ የኢትዮጵያ ብር ከፍ ማለት አለበት። የጥቁር ገበያን ለማስወገድ ከሕግ አንፃርና ተግባራዊ መሆን ያለባቸው የመቆጣጠሪያ መሣሪያዎች አሉ። ችግሩ ግን የተዘበራረቁና ግልጽነት የሌላቸው ከተማዎችና መመሸጊያዎች ለጥቁር ገበያ የሚያመቹ ናቸው።

  ከዚህ ስንነሳ የአንድ አገር የመኖርና ያለመኖር ዕድል፣ የአንድ ሕዝብም የመኖርና ምኞቱን የማሟላቱ ጉዳይ ከተስተካከለ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የተያያዘ ነው። የኢኮኖሚ ዕድገት ደግሞ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ መመሥረት አለበት። ወደዚያ ለማምራት ግን በቅድሚያ የሕዝባችን መሠረታዊ ፍላጎቶቹ መሟላት አለባቸው። አንድ ሕዝብ ሆዱን ሳይሞላ፣ ንፁህ ውኃ ሳያገኝ፣ መጠለያ ሳይኖረው ወይም ጎጆ ቤት ውስጥና ቆሻሻ አካባቢ እየኖረ፣ የመማር ዕድል ሳያገኝ፣ እንዲሁም የመታከም ዕድል ሳይኖረው በደፈናው ስለሳይንስና ስለቴክኖሎጂ አስፈላጊነት ማውራት አንችልም። ከዚህም ባሻገር በደንብ የታቀዱ ከተማዎችና መንደሮች በሌሉበት አገር እንደዚሁ ስለሳይንስና ስለቴክኖሎጂ ማውራቱ ወደፊት የሚያራምደን አይደለም። እንዲያውም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሊያድጉና የተፈለገውን ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉት ተጠንተውና ታቅደው በተሠሩ ከተማዎች ውስጥ ብቻ ነው። እንደምናውቀው አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ከተማዎች በዕቅድ የተሠሩ አይደሉም። የሰውን መንፈስ የመቅረፅ ኃይላቸው በጣም ደካማ ነው። በከተማዎች ውስጥ ፓርኮችና ዛፎች የሉም። ወንዞች ደርቀዋል። በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚሠሩት ቤቶች ዕቅድ የሌላቸው ናቸው። ባለፉት አሥርና ከዚያም በላይ ዓመታት የተሠሩት ሕንፃዎችና በኮዶምኒዩም ስም የሚሠሩት ቤቶች ለአንድ ከተማ ውበት የሚሰጡት አይደሉም። አብዛኛዎች ጓሮና መዝናኛዎች የላቸውም። በተለይም ሕፃናትን፣ ሽማግሌዎችንና ድኩማኖችን በማካተት ታሰበው የተሠሩ ቤቶች አይደሉም። ሽማግሌዎች እስከ አራተኛና ከዚያም በላይ ፎቆች በእግራቸው ሊወጡ የማይችሉባቸው የቤት አሠራሮች ናቸው የተስፋፉት። ይህ ዓይነቱ የቤት አሠራር ቆሞ ከረዥም ጊዜ አንፃር የታሰቡና ብዙ ነገሮችን ያካተቱ የቤት አሠራሮች መለመድና መስፋፋት አለባቸው። በአጭሩ ሰው የሚኖርባቸው ከተሞች መገንባት አለባቸው። በዚህ መልክ ከተሞች ባህላዊ ባህሪ ሲኖራቸው ለፈጠራ ሥራም የሚያመቹ ይሆናሉ፡፡

  ከዚህ ስንነሳ የአንድ መንግሥትና የአገሬ ጉዳይ ያገበኛል የሚለው ምሁር ግዴታና ኃላፊነት የሕዝባችንን መሠረታዊ ጉዳዮችን በማሟላት ላይ ከማተኮር አልፎ አገራችን በአዲስና ዘላቂነት ባለበት መልክ የምትገነባበትን ሁኔታ ማዘጋጀት ነው። ስለሆነም ስለኢኮኖሚ ዕድገት በምናወራበት ጊዜ እነዚህን መሠረተ ሐሳቦች በምንም ዓይነት ከጭንቅላታችን ውስጥ ማስወገድ የለብንም። እንዲያውም የሕይወታችን ፍልስፍናዎች መሆን አለባቸው። ከዚህ በተረፈ በትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ላይ ከማትኮር ይልቅ በትናንሽና በመካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ላይ ማትኮሩ እርስ በርሱ ለተሳሰረ የኢኮኖሚ ዕድገት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። አብዛኛውን ጊዜ እውነተኛ ፈጠራ በትናንሽና በማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚፈልቅ ነው። በመሆኑም እነዚህን መስኮች ከምርምርና ከሳይንስ ጣቢያዎች ጋር ማያያዝ ያስፈልጋል። በተለይም በአገልግሎት መስኩ ላይ መረባረብ መቀነስ አለበት። ካለአግባብና ካለዕቅድ በየቦታው የሚሠሩ ሆቴል ቤቶች ጥሬ ሀብትን፣ ውኃንና ኃይልን በከፍተኛ ደረጃ የሚጋሩ ናቸው። የሆቴል ቤቶች መስፋፋት ከምርት ክንዋኔና ከቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር ያልተያያዘ በመሆኑ የሥራ መስክ ለሚፈልገው ሰፊ ሕዝብ በቂ የሥራ ዕድል ሊያዘጋጅ ወይም ሊሰጥ የሚችል አይደለም። በአጭሩ አገራችን ውስጥ ሥርዓትና የተቀነባበረ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ከተፈለገ አገዛዙ ከኒዎሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ መላቀቅ አለበት። የውጭ ኤክስፐርቶችን ምክር በምንም ዓይነት መስማት የለበትም። አገዛዙ ሁለትና ሦስት ሚሊዮን ዶላር እየከፈለ የአገር ሀብት ማባከን የለበትም። በዚህ መልክ በየጊዜው ለውጭ ኤክስፐርቶች ለምክራቸው የሚከፈለው ገንዘብ አንድ አሥር ሺሕ ሕዝብ የሚኖርበትን የተዝረከረከ ከተማ እንደገና ሥርዓት ባለው መልክ ሊያስገነባና የሥራ መስክ ሊያስከፍት ይችላል። ከዚህ ቀደም በምዕራቡ ዓለም ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ፕሬዚዳንት የነበሩ አሁን ዋና ተግባራቸው የሦስተኛውን ዓለም አገሮች፣ በተለይም የአፍሪካን መንግሥታት በማማከር ገንዘብ መሰብሰብ ነው። አንዳንድ የአፍሪካ መንግሥታት በእነዚህ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በመታለል መቀመቅ ውስጥ ገብተዋል። የእነዚህ ትላልቅ ሰዎች ዋና ዓላማም ሳይንሳዊ ምክር መስጠት ሳይሆን፣ እንዴት አድርጎ ሀብት ከአፍሪካ ወደ ውጭ የሚተላለፍበትን መንገድ ማዘጋጀት ነው። ድሮ የዓለም ባንክ ሠራተኛ የነበረና ከፍተኛ ቦታ የነበረው ጆን ፐርኪንስ እንደነዚህ ዓይነት ኤክስፐርቶችን አሳሳች ኢኮኖሚስቶች (Economic Hit Men) ብሎ ይጠራቸዋል። ፍልስፍናቸውም ነፃ ንግድና የኒዎሊበራል ርዕዮተ ዓለም ነው።

   ስለሆነም በእነዚህ ‹‹ኤክስፐርቶችና አማካሪዎች›› መታለል አያስፈልግም። በታሪክ ውስጥ ውጤታማ የሆኑ አገሮች በሙሉ ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ የቻሉት በውጭ ኤክስፐርቶች በመመከር ሳይሆን በራሳቸው የማሰብ ኃይል ብቻ በመመራትና በራሳቸው በመተማመን ነው። በሌላ ወገን ግን የውጭ ኤክስፐርቶች ሳይንሳዊ አመለካከት እስካላቸው ጊዜ ድረስና የኒዎሊበራሊዝምን አስተሳሰብ የማያስተጋቡ ከሆኑ ከእነሱ ምክር ልንቀበል እንችላለን። እንደነዚህ ዓይነት ኤክስፐርቶች ደግሞ ብዙ ገንዘብ የሚጠይቁ አይደሉም። ለማንኛውም ኢትዮጵያን እንደ አንድ ጠንካራ አገር ለመገንባት የምንመኝ ከሆነ የግዴታ የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ አለብን። የአስተሳሰብ ለውጥ ለማድረግ ደግሞ የግዴታ በሳይንስና በፍልስፍና ዓለም ውስጥ የተደረገውን የጦፈ ክርክር ጠጋ ብሎ መመልከት ያስፈልጋል። በዚህ መልክ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ፈላስፋዎች ተፈጥሮንና ኅብረተሰብን ለምን በተለያየ መልክ እንደሚተረጉሙና ትክክል ነው ብለው በሚያምኑበት የሳይንስ መሣሪያ ኅብረተሰባቸውን ለመቅረፅ እንደሚፈልጉ ለማወቅ ይረዳናል። ስለሆነም ትክክለኛውን ዕውቀትና የአገር ግንባታ ዘዴ ሳይንሳዊነት ከሌለው ነጥሎ በማውጣት አዲስና ጤናማ ኅብረተሰብ ለመገንባት እንችላለን። ተግባራዊ ለማድረግ የምንፈልገው ፖሊሲ በአቦሰጡኝ መሆኑ ቀርቶ ሳይንስንና ፍልስፍናን የሚመረኮዝ ይሆናል ማለት ነው። መልካም ግንዛቤ!

   ከአዘጋጁ፡ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው fekadubekele@gmx.de ማግኘት ይቻላል፡፡

  spot_imgspot_img
  - Advertisment -

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  Related Articles