Tuesday, August 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  በሕግ አምላክለምርጫ ቦርዱ ቀሪ ሕግ ነክ ተግዳሮቶች

  ለምርጫ ቦርዱ ቀሪ ሕግ ነክ ተግዳሮቶች

  ቀን:

  በውብሸት ሙላት

  /ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አዲስ ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል፡፡ ዓይነተኛውን የቦርዱን ተልዕኮ ተግባራዊ ለማድረግ የሚስችሉ የአሠራር ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የምርጫ ቦርድን ዓይነተኛ ተግባራት ለማከናወን የሚበጁ ደንቦችን፣ የሰው ኃይል ምደባዎችንና የአሠራር ሥርዓታትን በሥራ ላይ ማዋል ተቀዳሚ ተግባርም ይሆናል፡፡ በተለይ ደግሞ በቀጥታ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ምርጫን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ቦርዱ ከእንደገና የመከለስ የቤት ሥራ ይጠብቀዋል፡፡ ምርጫን በሚመለከት ደግሞ እያንዳንዱን የምርጫ ዓይነት መነሻ በማድረግ ለሁሉም እንደ ባህሪያቸው የሚስማማ ብሎም ነፃ፣ ፍትሐዊና ጊዜውን ጠብቆ የሚካሄድ ምርጫ ለማከናወን የሚያስችሉ የሕግ ሥርዓትን ማስፈን ይጠበቃል፡፡

  ከ80 በላይ ቁጥር ያላቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎችን በትክክልም ስለመኖራቸው ማረጋገጥ አንዱ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ እንደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ሕጋዊ ሰውነት አግኝተው ይንቀሳቀሱ የነበሩት ሁሉ በትክክል ሕጉ በሚጠይቀው መሥፈርት መሠረት አባላት ያላቸው ስለመሆኑ፣ ጠቅላላ ጉባዔ ስለማከናወናቸው፣ አባላታቸው በተደራቢ የሌላ ፓርቲ አባል አለመሆናቸው፣ የፋይናንስ ምንጫው ምን እንደሆነ በነፃና ገለልተኛ ኦዲተሮች የተረጋገጠ ሪፖርት መቀበልንና የማስተካከያ ዕርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡

  በዚህ ጽሑፍ የምንቃኘው ከምርጫ ጋር የተያያዙ የተወሰኑ ነጥቦችን ነው፡፡ በቀጣይ ምርጫ ከማከናወኑ አስቀድሞ ሊጨነቅባቸው የሚገቡ የተወሰኑ ነጥቦችን እንመለከታለን፡፡

  የምርጫ ሥርዓቱን ሳይቀየር ፍትሐዊ ምርጫ የማከናወን ፈተና

  1983 ዓ.ም. ጀምሮ ለተለያዩ ዓላማዎችና በበርካታ ምክር ቤቶች አባል የመራጩም እንደራሴ ይሆኑ ዘንድ ለመምረጫነት ተግባር ላይ የዋለው በጥቅል አጠራሩ ‹‹አብላጫ የምርጫ ሥርዓት›› የሚባለውን ነው፡፡

  አሁን ኢትዮጵያ የፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንዲመረጡበት እየተጠቀመችበት ያለው ከአብላጫ የምርጫ ሥርዓት ዘውጎች ውስጥ አንዱ የሆነው በአንድ የምርጫ ወረዳ ውስጥ ከተወዳደሩት መካከል አንደኛ የወጣው ተወዳዳሪ አላፊ የሚሆንበት (ከአሁን በኋላ የአንደኛ አላፊ ሥርዓት በማለት የሚጠራውና በእንግሊዝኛ First-Past-The-Post የሚባለው) የምርጫ ሥርዓት ነው፡፡ ይህ የምርጫ ሥርዓት በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ተሰጥቶታል፡፡ ጥበቃም ተደርጎለታል፡፡

  ይህ የምርጫ ሥርዓት በድምፅ አባካኝነቱ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገር አቀፍ ደረጃም ይሁን በክልሎች ወይም ከዚያ በታች በሚገኙ ምክር ቤቶች ዘንድ ባገኙት ድምፅ መጠን እንዳይወከሉ እንቅፋት እንደሆነ ስለተቆጠረና በሌሎች በርካታ ምክንያቶችም እንደሚቀየር ከታወቀ ዓመት ሞላው፡፡ ይሁን እንጂ ወደ ምን ዓይነት የምርጫ ሥርዓት እንደሚቀየር በቁርጥ አልታወቀም፡፡

  ገዥው ፓርቲ ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ሲያደርገው በነበረው ድርድር ላይ በተቃዋሚዎች (ቢያንስ በተወሰኑት) በጥቅሉ ተመጣጣኝ ውክልና በመባል የሚታወቀውን በአማራጭነት ማቅረባቸው ተሰምቷል፡፡ ገዥው ፓርቲ በበኩሉ ቅይጥ ትይዩ እንዲሆን ሐሳብ አቅርቧል፡፡ ብሎም 80 በመቶው አሁን ሥራ ላይ ባለው የአብላጫ ድምፅ ሥርዓት እንዲቀጥል፣ ቀሪው ሃያ በመቶ ደግሞ ተመጣጣኝ ውክልና እንዲሆን ኢሕአዴግና በድርድሩ ተሳታፊ የነበሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ መስማማቱ ደርሰው እንደነበር ይታወቃል፡፡ በሕገ መንግሥታችን በአንቀጽ 54(2) መሠረት በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ ከቀረቡት ተወዳዳሪዎች መካከል አብላጫ ድምፅ ያገኘው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነት እንደሚመረጥ ስለሚደነግግ የአንደኛ አላፊ ሥርዓት መሆኑን እንረዳለን፡፡

  የክልል፣ የልዩ ዞን፣ ወረዳና ቀበሌ ምክር ቤት አባላት የሚመረጡበት ሥርዓት አሁንም የአብላጫ ድምፅ ይሁን እንጂ ከላይ ለፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ከሚመርጥበት ይለያል፡፡ ለእነዚህ ምክር ቤቶች በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ አንድ ፓርቲ ከአንድ በላይ ተወዳዳሪዎችን ስለሚያቀርብ መራጮችም እንዲሁ ከአንድ በላይ ዕጩዎችን መምረጥ ይችላሉ፡፡ ይኼ የምርጫ ዓይነት በእንግሊዝኛው Block Vote ይባላል፡፡ የበርካታ ፖለቲከኞች ትኩረት በአገር አቀፍ ደረጃ ላለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ሥርዓት እንጂ የክልልና ከእዚያ በታች ባሉት ምክር ቤቶች የሚመረጡበትን ሥርዓት እምብዛም አጀንዳ ሲያደርጉት አይታይም፡፡

  የምርጫ ሥርዓቱን ለማሻሻል ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ማድረግ ግድ ነው፡፡ ምክንያቱም የምርጫ ሥርዓቱ ሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረ ስለሆነ፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በነበራቸው ውይይት ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ከመሞከራችን በፊት አስቀድመን ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ብናደርግ ይሻሻል የሚል ይዘት ያለው ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደምክንያት ያነሱት ሁሉም ፓርቲ የተወከለበት፣ ሕዝቡ በነፃነት የመረጠው የክልልና የፌዴራል ምክር ቤቶች ከተዋቀሩ በኋላ ማድረጉ የማሻሻያውን ተቀባይነት ይጨምረዋል የሚል ነው፡፡ አሁን ላይ ያሉት ምክር ቤቶችን አይወክሉንም የሚል ማኅበረሰብ በበዛበት ሁኔታ የማሻሻያ ሐሳቡን የክልል ወይም የፌዴራል ወይም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውድቅ ካደረገው ወይም ኢሕአዴግ በሚፈልገው መንገድ እንዳያፀድቀው ዋስትና ስለሌለ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል ረገድ የክልልም ሆነ የፌዴራል ምክር ቤቶች ወሳኝ ስለሆነ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት የተሻለ አማራጭ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው የምርጫ ሥርዓት እንከኖች ከቀጣዩ ምርጫ በኋላም ተመሳሳይ የምክር ቤቶች ስብጥር ቢኖርስ የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሐሳብ ተቀብሎ ለመቆየት የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ድክመቶች አስቀድሞ መገምገምና የቀጣዩን ምርጫ ውጤትም አስቀድሞ በመተነብይ መሆን አስፈላጊ ነው፡፡

  ይህን የምርጫ ሥርዓት መቀየር ለምን አስፈለገ? የሚሉትን ለሚለው ቢያንስ ጠቅለል ያሉና በአብዛኛው ወደ ንድፈ ሐሳብ ያጋደሉ ምክንያቶችን እንይ፡፡ የነበሩት ሕገ መንግሥታት ሊቀርፋቸው ካልቻሉት ችግሮቻችን አንዱ እጅግ የጠነከረ/ግትር መንግሥትን ወደ ውይይት ማምጣት አለመቻል፣ የሌሎችን ሐሳብ ወደ ማዳመጥና ልዩነቶችን ወደ ማስተናገድ ማረቅ የሚችል ተቋም መገንባት አለመቻል ነው፡፡ ሌላው አሸናፊው ሁልጊዜም አንድ ፓርቲ በመሆኑ የአሸናፊው ፓርቲና የደጋፊዎቹ ሐሳብና ፍላጎት በቋሚነት እያሸነፈ እንዲኖር የቀሪዎቹ ደግሞ ሁልጊዜም ተሸናፊነታቸውን እየተቀበሉ እንዲኖሩ፣ ሐሳብና ፍላጎታቸው ደግሞ በተካታታይ በፓርላማው እንዳይሰማ፣ ልዩነታቸው እንኳን አለመንፀባረቁም ሌላው እንከናችን ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሥርዓት ቅያሜው እየበረታና እየገነነ እንደሚሄድ ግልጽ ነው፡፡

  የምርጫ ሥርዓታችንና ውጤቱ እያሳየን ያለው በቋሚነት ውክልና ያለው አንደኛውን ቡድን ብቻ ነው፡፡ በተቃራኒው ሌሎች ቡድኖች ቋሚ ተሸናፊ እንዲሆኑ ቀጥለዋል፡፡ ከእኒህ ፓርቲዎች ጀርባ ወይም ገዥው ፓርቲን ከማይመርጠው ውጭ ያለው ሕዝብም በተሸናፊነቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ የምርጫ ሥርዓታችንም ይሁን ፖለቲካው እነዚህን ኃይሎች ለማካተት ሲሞክር አልታየም፡፡ ቢያንስ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በየቦታው የሚያገኙት ድምፅ ወደ ፓርላማ ወንበር ሊቀየርላቸውና በአስፈጻሚው ውስጥ ሊካተቱ ይገባል፡፡ ሊያሳስበንም የሚገባው ይኼው የተሸናፊዎች (Losers) ሁኔታ ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊው የዴሞክራሲ ሥርዓት ተረጋግቶ እንዲቀጥል፣ ሥር የሰደደ መሠረት እንዲኖረው የምርጫ ተሸናፊዎቹ ስምምነት ጉልህ ድርሻ አለው፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ጥናት ያደረጉት ዊሊያም ራይከር የተባሉ ምሁር እንዲህ ብለዋል ‹‹የፖለቲካው መዘውር (Dynamics) ያለው በተሸናፊዎች እጅ ላይ ነው እነሱ ናቸው መቼና እንዴት እንዲሁም እንደሚፋለሙት ወይም እንደማይፋለሙት ሊወስኑ የሚችሉት፡፡››  

  ቀጣዩ ምርጫ ነፃና ፍትሐዊ ሆኖም በተለይ ደግሞ አሁን ባለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር እንዳለ ከቀጠለ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እርስ በራሳቸው ድምፅ በመቀራመት ገዥው ፓርቲ እንዲያሸንፍ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው አይቀሬ ነው፡፡ በመሆኑም ሌሎች የሕገ መንግሥት ማሻሻያ የሚፈልጉ ጉዳዮችን በይደር በመያዝ የምርጫ ሥርዓቱን አስቀድሞ መቀየር ቢቻል የሚባክን ድምፅን በመቀነስ ወካይ ምክር ቤቶችን መመሥረት ይቻል ይሆናል፡፡ ምክር ቤቶቹም የሚያሳልፏቸው ውሳኔዎች እንዲሁ የተሻለ ተቀባይነት ይኖራቸዋል፡፡ ስለሆነም የምርጫ ሥርዓቱን የሚመለከተውን የሕገ መንግሥት አንቀጽ በማሻሻልና የምርጫ ሥርዓትን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በክልል ምክር ቤቶች በሚወጡ አዋጆች እንዲወሰን ቢደረግ፣ ቢያንስ በቀላሉ ለማሻሻል ይረዳል፡፡ የቀጣዩ ምርጫ ውጤትም በራሱ አካታች መሆን አለበት፡፡

  ይህንን ጉዳይ ለማጠቃለል ያህል በርካታ አገሮች የምርጫውን ዓይነት በሕገ መንግሥታቸው አላካተቱም፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ እንደ ሁኔታው መቀየር እንዲቻል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን በሕገ መንግሥቱ ስለተካተተ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ይጠይቃል፡፡ ምናልባት ማሻሻያው ከሕገ መንግሥቱ እንዲወጣ የሚያደርግና በአዋጅ የሚወሰን ቢሆን ጥሩ ነው፡፡ እንደ ሁኔታው ለማሻሻል ያመች ዘንድ፡፡

  የአካባቢ ምርጫዎች

  የፖለቲካ ፓርቲዎች በዋናነት ትኩረት ያደረጉት የፌዴራልና የክልል ምክር ቤቶች ምርጫዎችን ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ምርጫዎች እንደሚከናወኑ የሚጠበቁት በ2012 ዓ.ም. ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከእዚያ በፊት ይደረጋሉ ተብለው የሚጠበቁ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ እንዲሁም የቀበሌ፣ የወረዳና የልዩ ዞን ምክር ቤቶች ምርጫ አለ፡፡ በአንድ በኩል ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ በሌላ በኩል ፓርቲዎች አገርን ከማስተዳደራቸው በፊት ቢያንስ የተወሰኑ ቀበሌና ወረዳ ወዘተ. ላይ በማሸነፍ ከገዥው ፓርቲ ጋር በምን ሁኔታ መሥራት እንደሚችሉ በመለማመድም አሠራር ማዳበርና መለማመድ ይጠቅማል፡፡

  ይህ በእንዲህ እንዳለ የተወሰኑ ክልሎች የከተማ ምክር ቤቶች ምርጫን የሚመለከቱ ሕግጋት ክልሎች በራሳቸው በማውጣት አግላይ የሆነ የምርጫ ሥርዓትን አስፍነዋል፡፡ ለአብነት የኦሮሚያ፣ የደቡብና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የከተሞች ማቋቋሚያ አዋጆች መጥቀስ ይቻላል፡፡ በእነዚህ ክልሎች ለከተማ ምክር ቤት የሚወዳደሩት ከሃምሳ እስከ ስልሳ በመቶ ገደማ ከተማው የሚገኝበት ነባር ብሔር (ለምሳ ሐዋሳ ከሆነ ሲዳማ፣ አዳማ ከሆነ ኦሮሞና አሶሳ ከሆነ በርታ) ሆኖ ሌላ ሃያ ወይም ሃያ አምስት በመቶ ደግሞ በከተማው ዙሪያ የሚገኙ እነዚሁ ነባር ብሔሮች ብቻ ናቸው መወዳደር የሚችሉት፡፡ ለቀሪው ወንበር ደግሞ የምክር ቤቱን የሥራ ቋንቋ የሚያውቅ የከተማው ነዋሪ (ለሐዋሳ ሲዳምኛ፣ ለአዳማ አፋን ኦሮሞና ለአሶሳ ሩጣንኛ/የበርታ ቋንቋ) መወዳደር እንደሚችል የሚያሰገድዱ ሕግጋት አሏቸው፡፡ የምክር ቤቶቹን ቋንቋ ከመቻል አልፎም በደም/በትውልድ ያንን ብሔር መሆንን ይጠይቃል፡፡ የምርጫና የፖለቲካ መብቶችን በሚመለከት ሕግ የማውጣት ሥልጣኑ የፌዴራል መንግሥት ስለሆነ የምርጫ ቦርድ እንዲህ ዓይነት ሕገ መንግሥታዊነት የራቃቸውን ሕግጋት እንዲስተካከሉ በማድረግ ወይም በእነዚህ ድንጋጌዎች መሠረት ምርጫ እንዲደረግ ባለመፍቀድ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡

  የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄዎችን በሚመለከት

  በአገሪቱ ውስጥ በርካታ ምላሽ ያላገኙ ከማንነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ከማንነት አልፎም የክልልና የልዩ ዞን ወይም ወረዳ ጥያቄዎችም አሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን ጥያቄዎች ለመፍታትም ምርጫ የማይተካ ሚና አለው፡፡ የምርጫው ዓይነት ሕዝበ ውሳኔ ነው፡፡ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ የሚጠይቁት አካላት ማንነት፣ ከሕዝበ ውሳኔው በፊት ሊኖር ስለሚችለው ሕዝባዊ ክርክርና ውይይት፣ ሕዝበ ውሳኔው ከተከናወነ በኋላም ስለሚኖረው ሁኔታ ምርጫ ቦርድ የማይተካ ሚና አለው፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሲዳማ፣ የካፋ፣ የወላይታና የጉራጌ ዞኖች ምክር ቤቶች የክልልነት ጥያቄ በማንሳት ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ በእነዚህ ዞኖች ሕዝበ ውሳኔ ከመከናወኑ በፊት የክልልነት ጥያቄውን የሚቃወሙ ካሉ ከሚደግፉት ጋር ሕዝባዊ ውይይትና ክርክር በማድረግ ጥቅምና ጉዳቱን በሕዝበ ውሳኔው ላይ ለሚሳተፈው ሕዝብ ሊቀርብ ይገባል፡፡ ይህ ሁኔታ እንዲመቻችም ምርጫ ቦርድ የድርሻውን መወጣት አለበት፡፡

  ሕገ መንግሥቱ ሥራ ላይ ከዋለ ጀምሮ ጥቂት የማይባሉ ከማንነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተነስተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በርካታዎቹ ግን በቅንነትና እንደማንኛውም የመብት ጥያቄ (ለምሳሌ የፍትሐ ብሔር ጉዳይ) በታወቀ፣ ግልጽ በሆነና ያለ ፍርኃት ሲቀርቡም ሲስተናገዱም አይስተዋልም፡፡ በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ሁሉ የሚቀርቡና ሲቀርቡም የኖሩ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ጉዳዮች እንዴት ለፍትሕ አካላት እንደሚቀርቡ፣ በማን እንደሚቀርቡ፣ እንዴት ውሳኔ እንደሚሰጥና እንዴት የተሰጠው ውሳኔ እንደሚፈጸም ይታወቃል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ከላይ ላነሳናቸው ጥያቄዎች ግን፣ መጥራት ያለባቸውና ግልጽ ያልሆኑ በርካታ አሠራሮች አሉ፡፡ የበለጠ ውስብስቡና አስቸጋሪው እንዲሁም ዋጋ የሚያስከፍለው ደግሞ ከማንነት ጋር የተያያዙት ጥያቄዎች ናቸው፡፡ የተወሰኑት ብቻ እንኳን ለመጥቀስ ያህል የኮንሶ፣ የወልቃይት፣ የአብኣላ፣ የራያ፣ የደንጣ፣ የቁጫና የወለኔ ሕዝቦችን ማንሳት ይቻላል፡፡ በፍትሐ ብሔር ጉዳይ ላይ ማንም ሰው በሕግ ጥበቃ ያለው መብቱ ከተጣሰበት ይህንን ድርጊት በመግለጽና በማስረጃ በማስደገፍ ለፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል፡፡ አቤቱታ አቅራቢዎቹ በርካታ ሲሆኑና የሚከሰሱበት ጉዳይ አንድ ከሆነ በምን ሁኔታ በውክልና ማቅረብ እንዳለባቸው በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 33 እና 38 ላይ በግልጽ ሰፍሯል፡፡ ጉዳያቸውን በጠበቃ አማካይነት መቀጠል ከፈለጉም እንዴት መከናወን እንዳለበት ግልጽ ሕግ አለ፡፡ አቤቱታ ፍርድ ቤት ከገባበት ቀን ጀምሮ ለእያንዳንዱ ነገር ቀጠሮ ይሰጣል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ክርክሩ ይቀጥላል፡፡ ፍርድ ቤቱም ክስና መልስ መርምሮ፣ ማስረጃ መዝኖ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ ውሳኔውም እንዴት መፈጸም እንዳለበት የታወቀ አሠራር አለ፡፡

  ከላይ የተገለጸው የፍትሐ ብሔር ክርክር አመራር ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ከማንነት ጋር ለሚያያዙ አቤቱታዎች ይሠራል ባይባል እንኳን አሁን እየሆነ ባለው መጠን ልክ ግን ሥርዓት የለሽ መሆን የለበትም፡፡ ሥርዓት መዘርጋትና ማስፈንን እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም ‹ማንነቴ ይታወቅልኝ› በማለት መጠየቅ የሚችለው ራሱ ማኅበረሰቡ እንደሆነ የታወቀ ቢሆንም፣ አስቸጋሪው ማኅበረሰቡ ወይም ሕዝቡ ማለት ምን ማለት ነው? መቼም ሁሉም ሕዝብ በአንድነት ተሰባስቦ ይጠይቃል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ስለሆነም የዚያ ማኅበረሰብ ልሂቃን ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ ለአብነት በአብኣላ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ራስ በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በዋናነት 16 ገደማ አባላት ያሉት ኮሚቴ ናቸው ወደ ተለያዩ ተቋማት ያደረሱት፡፡ ዋናው ነገር ማኅበረሰቡን ይወክላሉን? የሚለው ነው፡፡ ይህ በትክክል ይወክላሉ ወይም አይወክሉም የሚል መሥፈርት በማስቀመጥ ለማረጋገጥ የሚከብድና እንደተፈለገ ለመተርጎም የሚመች መለኪያ መስተካከል አለበት፡፡ የሕዝብን ወይም የአንድ ቡድንን ጥያቄ ለማቅረብ ግልጽ የሆኑ መለኪያዎችን ማስቀመጥ በየትም አገር የተለመደ ነው፡፡ ማንም ሰው እንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎችን የሚያቀርብባቸውንና በሽብር ክስ እከሰስ ይሆን ወይስ አልከሰስም ከሚል ሥጋት የሚያላቅቅ መሆን አለባቸው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤትንና የምርጫ ቦርድ ትኩረት ሊሰጠው ከሚገባቸው ጉዳዮች አንዱ ይህ ነው፡፡

  እርግጥ ነው ይሄንን ችግር ለመቅረፍ ከብሔረሰቡ አባላት ውስጥ አምስት ከመቶው ጥያቄውን በመደገፍ መፈረም እንዳለባቸው ይታወቃል፡፡ በአብኣላው ጉዳይ ግን ይህ ስለመጠየቁም ይሁን ስለመፈጸሙ ባይታወቅም ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ወደ አካባቢው በመሄድ ያነጋገሯቸውም ሕዝቦች፣ አምስት ከመቶ እንደማይሞሉ በቦታው ተገኝተው የነበሩ ሰዎች ተናግረዋል፡፡ ችግሩ ግን፣ ይኼንን ያህል ሰው አሁን ባለው በኢትዮጵያ ሁኔታ እንዴትስ ማስፈረም ይቻላል? የሚለው ነው፡፡ ለምሳሌ የተወሰኑ አንቀሳቃሾች ፈቃድ የሚገኙበትና ወጪዎችን የሚሸፈኑበት ሕጋዊ አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ እንደውም ቅስቀሳም ጭምር ሊያደርጉ፣ ስብሰባ ሊያከናውኑ፣ ሰላዊ ሠልፍ ሊጠሩ ሁሉ ይችላሉ፡፡ በርካታ አገሮች ማንም ሰው እንዲህ ዓይነት አቤቱታ ለማቅረብ በማሰብ መቀስቀስ ሲፈልግ ይህንን ድርጊት ከሚከታተለውና ከሚስፈጽመው መሥሪያ ቤት አስቀድሞ ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡ በእኛ ሁኔታ ከክልሉ ሕገ መንግሥት ተርጓሚ ኮሚሽን ወይም ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ወይም እንደ ነገሩ ምርጫ ቦርድ ሊሆኑ ስለሚችሉ በመሆናቸው የምስክር ወረቀት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ፊርማ ለማሰባሰብም፣ ግለሰቦችን ወይም ድርጅቶችን ለማነጋገር በፍቃደኝነት ማረጋገጫ ይሆናል፡፡ ስለሆነም የሕዝብን ጉዳይ በማንሳት ኮሚቴ መሥርቶ መንቀሳቀስ ለከፍተኛ አደጋ የሚያጋልጥ፣ ውሎ አድሮም የግጭት መንስዔ ሲሆንም እያየን ነው፡፡ በአብኣላ የትግራይ ተወላጆች፣ ከኮንሶ፣ ከወልቃይት፣ የራያና ደቡብ ክልል ላይ የተነሱ ሌሎችም ጉዳዮች እንደታዘብነው የኮሚቴ አባላት ዕጣ ፈንታቸው ሕዝብን በማነሳሳት፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ በመሞከር አንዳንዴም በሽብርና በመሳሰሉት ወንጀሎች መከሰስ ነበር፡፡ ስለሆነም እንዲህ ዓይነቱ ችግርን ለመቅረፍ የምርጫ ቦርድ የማንነትና ሌሎች የቡድን መብቶችን በሚመለከት በሕዝበ ውሳኔ የሚፈቱ ጥያቄዎች እንዴት እንደሚቀርቡ፣ እንዴት ቅስቀሳና ውይይት ማድረግ እንደሚቻል ወዘተ. አሠራር ማስፈን አለበት፡፡ ቦርዱ በራሱ ደንብ የማውጣት ሥልጣን ከሌለው እንኳን ይህንን ዓይነቱን አሠራር የሚያሰፍን ሕግ እንዲወጣ ማድረግ አለበት፡፡

  በየትኛውም የፍትሕ ተቋማት ዘንድ የሚቀርቡ አቤቱታዎች ማሟላት ስላለባቸው ዝቅተኛ መሥፈርት በተለያዩ ሕጎች ይገለጻል፡፡ የአቤቱታው ይዘት ብቻ ሳይሆን እንዴት መዘጋጀት እንዳለባቸውም ይታወቃል፡፡ አቤቱታን ለማስረዳት የሚቀርቡ የማስረጃ ዓይነቶች፣ መቼና እንዴት መቅረብ እንዳለባቸውም እንዲሁ ግልጽ ነው፡፡ ከማንነት ጋር የተያያዙ፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ለመጠቀምና ራስን በራስ ለማስተዳደር ያመች ዘንድ ወረዳ፣ ቀበሌ ወይም ልዩ ዞን ለመመሥረት መብት ያለቻው ሕዝቦች ያቀረቡት ጥያቄ በእርግጥም መብታቸው ስለመሆኑ ለማስረዳት ማቅረብ ያለባቸው የማስረጃ ዓይነት በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡ እነዚህ ከምርጫ ቦርድ የሚጠበቁ በጣም ጥቂትና በጣት የሚቆጠሩ ተግባራት ብቻ ናቸው፡፡ በወ/ሪት ብርቱካን መመራት የጀመረው የምርጫ ቦርድ ዴሞክራሲን ለማስፈን ጥሩ መሠረት በመጣል መደላድል ያስቀምጣል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ የሚጠበቅበትን ለመወጣትም በርካታ የቤት ሥራዎች ከፊቱ ይጠብቁታል፡፡ ከላይ የተገለጹት በጣት የሚቆጠሩ ተግዳሮቶቹ ናቸው፡፡ በቀጣይ ማሻሻያ በሚያስፈልጋቸው በሌሎች ተግዳሮቶች ላይ እንቀጥላለን፡፡

  አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው wuobishett@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የአገሪቱ ባንኮች ካፒታል 199.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ

  ከታክስ በኋላ 50 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ የአገሪቱ...

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...