Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  እኔ የምለዉየሽግግር ፍትሕ በኢትዮጵያ

  የሽግግር ፍትሕ በኢትዮጵያ

  ቀን:

  በይሄይስ ወልደ መስቀል   

  የሽግግር ፍትሕ ጽንሰ ሐሳብ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ሰፊ ተቀባይነትን ያገኘ፣ በሰፊው እየተጻፈበትና አሁንም እየተጠና ያለ ርዕስ ነው፡፡ የዚህ ጽሁፍ ዓላማ በርዕሱ ላይ ሰፊና ጥልቀት ያለው ትንተና ማቅረብ ሳይሆን የጽንሰ ሐሳቡን ዋና ዋና ፀባያት ማስጨበጥ፣ እንዲሁም እነዚህ ፀባያት አሁን በአገራችን ከሚካሄደው የፖለቲካ ዕድገት ጋር ያላቸውን ተዛምዶ ማሳየት ይሆናል፡፡ ሌላው ዓላማ አንባቢያን በጉዳዩ ላይ እንዲወያዩበትና ሐሳቡን እንዲያዳብሩት መጋበዝ ነው፡፡

  የሽግግር ፍትሕ (ትራንዚሽናል ጀስቲስ) አንድ ወጥ የሆነ ትርጉም የለውም፡፡ ሁለት ትርጉሞች ግን ይጠቀሳሉ፡፡ ሁለቱም ትርጉሞች ያተኮሩት የሽግግር ፍትሕ በአንድ አገር አምባገነን ሥርዓት ወድቆ የሥርዓት ለውጥ ሲመጣ፣ ላለፈው ጭቆናና የመብት ጥሰት የሚሰጥ ሕጋዊ ግብረ መልስ መሆኑ ላይ ነው፡፡ እነዚህ ከዚህ በታች በቀረቡት ትንታኔዎች ይገለጻሉ፡፡

  በአንድ አገር የፖለቲካ ታሪክ ላይ የሽግግር ፍትሕ እንደ አንድ የመወያያ ርዕስ ሆኖ የሚቀርበው ይህ አገር ከፍተኛ ከሆነ ጦርነት ሲወጣ፣ በተለይም አንድ አምባገነን ሥርዓት ወድቆ ወይም ራሱን ለውጦ በተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመተካት ላይ ባለበት ጊዜ ነው፡፡ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ጥንታዊ፣ እንዲሁም በአብዛኛው አሁንም ሰፊ ተቀባይነት ያለው አቋም፣ አንድ ወንጀል የፈጸመ ሰው ወንጀሉ ከባድም ሆነ ቀላል፣ እጁ ተይዞ ለፍርድ መቅረብ ይገባዋል የሚል ነው፡፡ ይህ ብዙም ያልተወሳሰበና ብዙዎችም የሚስማሙበት ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ወንጀል ፈጻሚን ፍርድ ቤት አቅርቦ ማስቀጣትና ቅጣቱንም እስኪፈጽም በእስር ቤት ማስቀመጥ ከፍተኛ ገንዘብና የባለሙያዎች ርብርብን የሚጠይቅ ሒደት መሆኑ የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ተቋማት የመንግሥት ተቋማት በመሆናቸው፣ የሚተዳደሩትም በሕዝብ ገንዘብ ማለትም ከመንግሥት በሚመደብላቸው በጀት ነው፡፡ ስለዚህም እያንዳንዱ የወንጀል ጉዳይ ከፍተኛ የሕዝብ ገንዘብ የሚጠይቅ ሒደት ነው፡፡

  አገር ሰላም በሆነበት ጊዜ ለአንድ መንግሥት ይህንን የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋትና አቅሙ እስከፈቀደለት ድረስ ፍትሕ እንዲሰፍን ማድረግ የተለምዶና መደበኛ የመንግሥት ሥራ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን አንድ አገር በአምባገነን ሥርዓት መገዛት ሲጀምር፣ በተለይም ይህ ሥርዓት ለረዥም ጊዜ በሥልጣን ማማ ላይ ሲቆይ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ወይም የወንጀል ድርጊቶች እየበዙ መምጣታቸው በየጊዜው የታየ ሀቅ ነው፡፡ የአምባገነን ሥርዓቶቸ አንደኛው ፀባይ በመሠረቱ ለመልካም ሕዝባዊ አስተዳደር የተቋቋሙ ወይም መቋቋም የነበረባቸውን መንግሥታዊ ተቋማት ለወንጀል አፈጻጸም መጠቀማቸው ነው፡፡

  እንዲህ ባሉ ወቅቶች የሚፈጸሙ ወንጀሎች ተራ ወንጀሎች ሳይሆኑ ብዙዎችን ለጉዳት የሚዳርጉ ወንጀሎች ናቸው፡፡ ዘር ማጥፋትና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአምባገነን ሥርዓት ሥር የሕዝቦች የእርስ በርስ ግጭት ወይም ጦርነት መከሰቱ ተዘውትሮ የሚታይ እውነታ ነው፡፡

  ከላይ በምሳሌነት የተጠቀሱት ወንጀሎች ሲፈጸሙ የወንጀሉ ተጠቂዎችና የወንጀል ፈጻሚዎች ቁጥር እጅግ ብዙ ነው፡፡ በመሆኑም አንድ የሥርዓት ለውጥ ሲከሰት በመሠረቱ ባለፈው ሥርዓት ወቅት ወንጀል የፈጸሙ ሁሉ ተይዘው ለፍርድ ሊቀርቡ እንደሚገባ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለዚህም አዲሱ ሥርዓት የሕግ የበላይነትን የማስፈን ዓላማ ካለው የፍትሕ ሒደቱ የቱንም ያህል ገንዘብና የሰው ኃይል ቢጠይቅ፣ ወጀለኞችን ሁሉ ለፍርድ ማቅረብና ተጎጂዎችን መካስ ይኖርበታል፡፡ ይህ መደምደሚያ ለአባባል ቀላል ቢሆንም በተግባር ማዋል ግን እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ዋናው ችግር የፍትሕ ሥርዓቱን በተገቢው መንገድ ለማስተዳደር የሚያስፈልገው የገንዘብና የሠለጠነ ባለሙያ እጥረት ነው፡፡ ይህ አገር ካለፈው አምባገነናዊ የፖለቲካ አስተዳደር የተነሳ ምጣኔ ሀብቱ ተንኮታኩቶ ከሆነ፣ ይህን ሒደት በተገቢው መንገድ በሥራ ላይ ማዋል የማይታለም ይሆናል፡፡ በመሆኑም የፍትሕ ሥርዓቱ የሚፈለገውን ፍትሕ ሊያስገኝ አያስችልም፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ከበጎ አድራጊዎች ከሚገኝ ገንዘብ ማቋቋምና ማጠናከር ይቻላል ሊባል ቢቻልም፣ ለአንድ ሉዓላዊ አገር ግን ይህ የስድብ ያህል ነው፡፡

  ከዚህ በተጨማሪ የአምባገነን ሥርዓቶች ሌላ መገለጫ ሊደርሱበት የቻሉትን የኅብረተሰብ ክፍል ሁሉ ታዛዣቸው ማድረግ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ታዋቂ ምሁራን፣ ሀብታሞች፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ ወዘተ. ሁሉ የሥርዓቱ ደጋፊዎች እንዲሆኑ ይበረታታሉ ወይም ሊገደዱም ይችላሉ፡፡ በተለይ የፍትሕ ተቋማት ባለሙያዎች በስፋት መሳተፋቸው የታወቀ በመሆኑ፣ ቢያንስ ዋና ዋና ኃላፊዎችን ከተቻለም ሁሉንም ከየተቋማቱ ሳያስወግዱ አዲሱን የፍትሕ ሥርዓት እውነተኛ የፍርድ ሥርዓት ማድረግ አይቻልም፡፡ ይህ ችግር በአዲሱ ሥርዓት ላይ ራሱን የቻለ የባለሙያ እጥረት መፍጠሩ የማይቀር ነው፡፡

  አዲሱ ሥርዓት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከሆነ በሁሉም መንገድ ከቀድሞው የተለየ መሆን ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም በተለይረለኑምልዊወም የፍትሕ ሥርዓቱ የወንጀል ተጠርጣሪዎችን መብቶች ሙሉ በሙሉ የሚያስከብር፣ የተጎጂዎችንና የሰፊውን ማኅበረሰብ የፍትሕ ጥማት የሚያረካ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ መደምደሚያ ለማለት የሚቀል ቢሆንም በተግባር ግን እጅግ ፈታኝና አስቸጋሪ ግዴታ ነው፡፡ በዚህ ሒደት ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው ዋና ዋና የተጠርጣሪዎች መብቶች፣ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር የሚውሉበት ሒደት በኃይል ወይም በፈቃደኝነት መሆኑ፣ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ በቁጥጥር ሥር ከዋሉበት ጊዜ ጀምሮ በራሳቸው ወይም መንግሥት በነፃ በሚያቆምላቸው ጠበቃ የመወከል መብት፣ በአፋጣኝ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት፣ ለመርማሪው አካል ቃላቸውን ሳይገደዱ በፈቃድ የማሰጠት መብት፣ የተሰበሰባቸው ማስረጃ ክስ ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑ በዓቃቤ ሕግ ሲታመንበት በፍጥነት ክስ እንዲመሠረት የመጠየቅ መብት፣ ጉዳዩ በፍርድ መታየት ከጀመረ አፋጣኝ ፍትሕ የማግኘት መብትና ፍርድ ቤት ማስረጃዎችን መርምሮ የጥፋተኛነት ውሳኔ ከማስተላለፉ በፊት ንፁህ ሆኖ የመገመት መብት፣ ሳይፈረድባቸው በፊትና ከተፈረደባቸውም በኋላ በእስር ቤት ሰብዓዊ በሆነ አያያዝ የመጠበቅ መብት ናቸው፡፡

  ከላይ እንደተመለከተው የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የሽግግር ፍትሕን የሚመለከቱ፣ ሁሉንም ጭብጦች መተንተን ባለመሆኑ ሌሎች አሳሳቢ ጭብጦች መኖራቸውን ማወቅ ይገባል፡፡ በዚሁም መሠረት ከላይ የቀረቡት በርዕሱ ላይ ሊነሱ ከሚገባቸው የሌሎች ጭብጦች የበረዶ ክምር ጫፉን ብቻ እንደሆነ ከታወቀ በቂ ነው፡፡ በሽግግር ወቅት አገርን የሚመራ መንግሥት ወደ ኋላና ወደ ፊት ተመልካች መንግሥት በመሆኑ ባለፈው ለተፈጸሙ ወንጀሎችም ሆነ ሌሎች ጉዳት አድራሽ ድርጊቶች ፍትሕ የመስጠት ኃላፊነት እንዳለበት ሁሉ፣ አዲሱን ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ ማድረግም ሌላው ግዴታው ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ወደፊት የሚገነባው ሥርዓት እንዳይቀለበስ የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ግዴታው ነው፡፡

  በሽግግር ወቅት ዋናው ፈተና በወደቀው ሥርዓት ደጋፊዎችና በአዲሱ መንግሥት መካከል የሚኖረው የኃይል ሚዛን ነው፡፡ ተሸናፊው ኃይል በምጣኔ ሀብትና በተለይም በመንግሥታዊ ተቋማት ላይ ያለው የመቆጣጠር ኃይል ከአዲሱ ሥርዓት ኃይል ጋር ሲነፃፀር የላቀ ከሆነ፣ ሽግግር ወይም የሥርዓት ለውጥ የሚታሰብ አይሆንም፡፡ ሆኖም የሥርዓት ለውጡ ከራሱ ከቀድሞው መንግሥት ወዶም ሆነ ተገዶ  የመጣ ከሆነ ሽግግሩ በሥርዓት ሊካሄድ ይችላል፡፡ አዲሱ ሥርዓት በማናቸውም መንገድ ቢመጣ በሽግግር ወቅት ያለው የኃይል ሚዛን የወደፊቱን አቅጣጫ ለማቀድ ዋናው ምሰሶ ነው፡፡

  በዚህም መሠረት ያለፈው ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ተወግዶ ከሆነና ደጋፊዎቹና ተጠቃሚዎቹ ችግር ለመፍጠር የሚያስችላቸው ጉልበት የሌላቸው መሆኑ ከተረጋገጠ፣ ሽግግሩ ብዙም እንከን አያጋጥመውም ተብሎ ሊገመት ይችላል፡፡ ሁለቱም ኃይሎች ተመጣጣኝ የሆነ ኃይል ካላቸው ግን ሽግግሩ በመስጠትና በመቀበል ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል፡፡ የኋለኛው ሁኔታ ሲያጋጥም የተሸናፊው ሥርዓት ወገኖች ለድርድር ከሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች መካከል ዋነኛው ምሕረት (አምነስቲ) ይሆናል፡፡ ምሕረት በተለምዶ ይቅርታ (ፓርደን) ከሚባለው የተለየ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ተቀባይነትን ካገኘ በወንጀለኛነት ተጠርጥረው ሊቀጡ የሚችሉ ሁሉ ከወንጀል ኃላፊነት ነፃ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህም ምሕረት ማድረግ አዲሱን ሥርዓት በሰላም ለማስቀጠል የሚከፈል መስዋዕትነት ይሆናል፡፡

  ምሕረት አንድ ራሱን የቻለ የሽግግር ፍትሕ አማራጭ ቢሆንም፣ በሽግግር ወቅት አሸናፊው አዲሱ ኃይል የተሻለ የኃይል ሚዛን ኖሮት እንኳን የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር በተለምዶ በሚሠራበት መንገድ፣ ማለትም ወንጀል የፈጸመ ሁሉ በፍርድ ሊዳኝ ይገባዋል የሚለውን መርህ መከተል ላይመርጥ ይችላል፡፡ በወንጀል ሊከሰሱ የሚችሉ ሰዎች ብዛት ከዚህም የተነሳ አፋጣኝ ፍትሕ መስጠት አስቸጋሪ መሆኑ፣ለፍትሕ ተቋማት ሊመደብ የሚገባው በጀት በቀላሉ ሊገኝ ያለመቻሉ ከዋና ባለሥልጣናት በቀር ሌሎች የወንጀል ተሳታፊዎች ብዙም የጠነከረ የወንጀለኛነት ባህሪ የሌላቸው የማያሠጉ ተራ ሰዎች ለምሳሌ በከንቱ ስብከት የተደለሉ ሲሆኑ፣ ወዘተ. ከመደበኛ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር የተለየ ሥርዓት መዘርጋት ግዴታ ሊሆን ይችላል፡፡ በተለይ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት በኋላ በግጭት ታምሰው አዲስ ሥርዓት ከገነቡ የተለያዩ አገሮች ልምድ በመነሳት ዋና ዋና የሽግግር ፍትሕ ማስፈጸሚያ መንገዶች ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብና መመርመር፣ የእውነት ኮሚሽን ማቋቋም፣ የደኅንነት ተቋሙን ጤነኝነት ማረጋገጥና ማፅዳትና የካሳ አከፋፈል ሥርዓትን ማቋቋም በላቲን አሜሪካ የቀድሞዎቹ አምባገነን መሪዎችና ሲቪል ደጋፊዎቻቸው በሽግግሩ ወቅት ታላቅ ኃይል ስለነበራቸው ፍላጎቶቻቸው ካልተጠበቁ በስተቀር ችግር ሊፈጥሩ እንደሚችሉ የታወቀ ስለነበር ሽግግሩ በሰጥቶ መቀበል ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡

  ከዚህ በተጨማሪ የሥርዓት ለውጡ በልሂቃን ድርድር እንጂ፣ በአንድ ወገን ተሸናፊነትና በሕዝባዊ አመፅ ወይም ግጭት የመጣ አልነበረም፡፡ ስለዚህም ምሕረት ዋናው በድርድር የተገኘ መፍትሔ ሆኗል፡፡ ይህም ሆኖ የተወሰኑ ባለሥልጣናት ለፍርድ ቀርበዋል፡፡ በምሥራቅ አውሮፓ አብዛኞቹ የመብት ጥሰቶች ከረዥም ጊዜ በፊት የተፈጸሙ ቢሆኑም በሕዝቡ ላይ የሚያንዣብቡ ክትትሎችና የዘፈቀደ ቅጣቶች የተዘወተሩ ስለነበሩ፣ የደኅንነት ተቋሙን የሰነድ ግምጃ ቤት ለሕዝብ ክፍት ማድረግ፣ የእውነት ኮሚሽን ማቋቋምና ወንጀለኞችን ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ማስወገድ ዋና ዋናዎቹ የሽግግር ፍትሕ ዘዴዎች ተደርገው ተወስደዋል፡፡

  የደቡብ አፍሪካ ሽግግር በእውነትና በዕርቅ ኮሚሽን አማካይነት የተፈጸመ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት በፈቃደኝነት ጥፋተኛነታቸውን አምነው እውነቱን ላሳወቁ ምሕረት የተደረገላቸው ሲሆን፣ የቀሩት ግን ለፍርድ ቀርበዋል፡፡ ኮሚሽኑ ጥፋት አድራጊዎች ጥፋታቸውን በአደባባይ እንዲገልጹ፣ ከተጎጂዎች ጋር ዕርቅ እንዲፈጽሙ ማስቻል፣ የጥፋተኞችን የእምነት ቃል መሠረት በማድረግ የተፈጸሙትን የመብት ጥሰቶችን መዝግቦ ማኖርና በአዲሱ ሥርዓት ሊደረጉ ስለሚገባቸው ለውጦች የውሳኔ ሐሳብ የማቅረብ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በአርጀንቲና፣ በብራዚል፣ በቺሊ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በጓቲማላና በፔሩ ለተጎጂዎች ካሳ መክፈል እንደ አንድ አማራጭ ተወስደዋል፡፡ በተለያዩ አገሮች ወንጀለኞች በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ተዳኝተዋል፡፡ ለምሳሌ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያና ሩዋንዳ፡፡

  እያንዳንዱ አገር የሚመርጠው የሽግግር ፍትሕ በሽግግር ወቅት ባለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ የተመሠረተና በተለይም የኃይል ሚዛንን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ በመሆኑም ከአማራጮቹ መካከል አንዱን ብቻ መውሰድ የተሟላ ውጤትን ስለማያመጣ፣ ከአንድ በላይ የሆኑ አማራጮችን መጠቀም የተሻለ መሆኑ የየአገሮቹ ተሞክሮዎች አመላክተዋል፡፡ ከላይ የተዘረዘሩትና ሌሎችም አማራጮች በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ ሳይሆኑ በሰፊው የሚተቹም ናቸው፡፡ ሆኖም ሁሉም ጸሐፍት የሚመክሩት የሽግግር ፍትሕ ዋና አማራጭ ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ ማቅረብ ብቻ ካልሆነ ተጎጂዎች በሚገባ መካስ እንዳለባቸው፣ ጥፋተኞች እውነትን በአደባባይ ሲገልጹ ጥፋታቸውን አምነውና በእውነት ተፀፅተው እንጂ ለይስሙላና ከቅጣት ለማምለጥ ብቻ መሆን እንደሌለበት፣ የዕርቅ ሥነ ሥርዓትም ተጎጂና ጎጂን አቀራርቦ ወደፊት አብረው በሰላም እንዲኖሩ የሚያስችል መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሰው የናኦሚ ጽሑፍ ገጽ 1 እስከ 14 በተለይም ‹‹Ruti G. Teitel, Transitional Justice, Oxford University Press, Inc. 2000›› ጠቃሚ ምንጮች ናቸው፡፡ ‹‹Boraine, Alexander L. Transitional Justice: A holistic interpretation, Journal of International affairs.60.1 (2006)›› ዋና ዋና የሽግግር ፍትሕ አማራጮች ጥፋተኞችን ለፍርድ ማቅረብ፣ እውነትን ማውጣትና ለታሪክ መሰነድ፣ ዕርቅ፣ ተቋማዊ ጥገና (ሪፎርም)፣ እና ካሳ (ሬፓሬሽን) መሆናቸውን በስፋት ዘርዝረው፣ ጥሩ አማራጭ የሚሆነው ከሁሉም ጥቂት ጥቂት በመውሰድ ተግባራዊ ማድረግ መሆኑን አበክረው ያሳስባሉ፡፡

  በአገራችን በተላያዩ ጊዜያት የሥርዓት ለውጦች የተደረጉ ቢሆኑም ለውጡ ሥርዓትን ማስቀጠል እንጂ፣ ወደ ተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማሸጋገር ባለመሆኑ ይህን አጋጣሚ ሳንጠቀምበት ቀርተናል፡፡ የወታደራዊ መንግሥት አብቅቶ ሌላ ሥርዓት ሲዘረጋ ወንጀል የፈጸሙትን ሁሉ በተለይም አገር ውስጥ ያሉትን ለፍርድ ለማቅረብ የተደረገው ሙከራ የቀይ ሽብር ልዩ ችሎቶችና ልዩ ዓቃቤ ሕግን በማቋቋም በአገራችን ብዛት ያላቸው ተጠርጣሪዎች በአንድ ጊዜ ለፍርድ የቀረቡበትና ፍርድ ቤቶችም ምናልባትም ለመጀመርያ ጊዜ የዓለም አቀፍ ወንጀሎችን በመተርጎም በሥራ ላይ ያዋሉበት ልዩ ዓቃቤ ሕግ የተለየ ሥልጣን የነበረው በመሆኑ፣ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መንገድ በተጠርጣሪዎች ላይ ብዛት ያላቸውን ማስረጃዎችን አሰባስቦና አደራጅቶ ክስ መሥርቶ መከራከሩና ወንጀለኞች እንዲቀጡ ከፍተኛ ሙከራ አድርጓል፡፡

  ሆኖም አንደኛ የፍትሕ አሰጣጥ ሒደቱ ፖለቲካዊ ጥላ ያጠላበት መሆኑ፣ ሁለተኛ የተጠርጣሪዎች ብዛት ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ ተጠርጣሪዎች ላይ የሚቀርቡ ክሶች ብዛት ያላቸው ስለነበሩ፣ አንዳንዶቹ ከአንድ መቶ በላይ የሆኑ ክስ ቀርቦባቸው ነበር፡፡ ሦስተኛ የፍርድ ሒደቱ ወደ 17 ዓመታት መፍጀቱ ተጎጂዎች ማስረጃ ከማሰባሰብና ምስክር ከመሆን ያለፈ ሚና እንዳይኖራቸው በመደረጉና በሌሎች ጉዳዮች የተነሳ፣ የባለሙያዎቹ ጥረቶች ሁሉ የታሰበውን ሕዝባዊ እርካታ አላመጡም፡፡

  ይህ ሒደት ሲጀመር ከላቲን አሜሪካ በስተቀር የሽግግር ፍትሕ ገና ባልዳበረበት ጊዜ ቢሆንም፣ ተጠርጣሪዎችን በሁሉም ድርጊቶች ከመክሰስ ይልቅ በተወሰኑ ከባድ ወንጀሎች ብቻ መክሰሱ (ሴሌክቲቭ ፕሮሴኩዊሽን) ሥርዓቱ ባይፈቅድም፣ የተፋጠነ ፍትሕ ለማስገኘት ሲባል በተለየ ሁኔታ ሊወሰን ይችል የነበረ አማራጭ ይሆን ነበር፡፡ ተጎጂዎች የሚካሱበት መፍትሔ ቢዘጋጅ የተሻለ ውጤት ያስገኝ ነበር ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ እነዚህ አማራጮች በራሳቸው የተሳካ ሽግግር ያመጡ ነበር ማለት ግን አይቻልም፡፡ ልዩ ዓቃቤ ሕግን ያቋቋመው አዋጅ ዓላማው ከፍትሕ ሒደቱ መጪውን ትውልድ ታሪክ እንዳይደገም ማስተማር ነው የሚል መንፈስ ቢኖረውም፣ ይህ ትውልድ ምን ያህል ትምህርት እንዳገኘበት ለአንባቢያን ፍርድ የሚተው ጉዳይ ነው፡፡

  በቅርቡ እያስተዋልነውና እየኖርንበት ያለው የፖለቲካ ዕድገት በየትኞቹ የሽግግር ፍትሕ አማራጮች እንደሚቃኝ ቆይተን የምናየው ቢሆንም፣ አንዳንዶቹ አማራጮች በሥራ ላይ እየዋሉ እንደሆነ ግን በተጨባጭ የሚታይ ነው፡፡ ይቅርታ ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ ማቅረብ፣ የሰላም ሚኒስቴር ማቋቋም፣ የዕርቅ አዋጅ ማርቀቅ፣ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የዕርቅ ሥነ ሥርዓት ማካሄድ፣ ላለፉት የመብት ረገጣ ድርጊቶች በአደባባይ ይቅርታ መጠየቅና የመሳሰሉት የሽግግር ፍትሕ ሒደት መጀመሩን የሚያበስሩ ዕርምጃዎች ናቸው ሊባሉ ይችላሉ፡፡

  ይህም ሁሉ ሆኖ ሒደቱ በተለምዶ እንደሚደረገው የልሂቃን ድርድር አይደለም ሕዝቡ በስፋት የሚሳተፍበትና በመጨረሻም የራሱ የሚያደርገው እንጂ፣ ከላይ ወደ ታች ብቻ የሚፈስ መሆን የለበትም፡፡ ተጎጅዎችም ተገቢ መድረክ የሚያገኙበትና ካሳ የሚያገኙበት ዘዴ መቀየስ ይኖርበታል፡፡ የዕርቅ ሥርዓቶችም ጎጂና ተጎጂ በአካል የሚገናኙበትና እውነተኛ መፀፀትና ይቅርታ አድራጊነት የሚገለጹበት መድረኮች እንጂ፣  የማስመሰያ መድረኮች አለመሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

   በመጨረሻም የሽግግር ፍትሕ ዋና ዓላማው የወደፊቱን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት በመሆኑ፣ ላለፉት ጥፋቶች ፍትሕን መስጠት በጣም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ወደፊት ለሚገነባው የተሻለ ሥርዓት ሲባል ይህ ምርጫ ቢሰዋ ተመራጭ መሆኑን በሰፊው ማስተማርና መተግበር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በላይ የቀረቡት ትንታኔዎች በጣም ግርድፍ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ጽንሰ ሐሳቡን ለሰፊ አንባቢያን ለማስተዋወቅ በቂ ናቸው የሚል ግምት አለኝ፡፡ በጉዳዩ ላይ ጠለቅ ያለ ዕውቀት ለማግኘት የሚፈልጉ አንባቢዎች ከጉጉል ሰርች ብቻ ድንቅ ጽሑፎችን በነፃ አውርደው መጫን ይችላሉ፡፡ በተረፈ አንባቢያን አስተያየታቸውን በሀቅ ቢያቀርቡ የጽሑፉ ዓላማ ግቡን ይመታል፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...