Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ልናገርእንፈራለን ለማለት እንፈራለን ወይስ አንፈራም ለማለት አንፈራም?

  እንፈራለን ለማለት እንፈራለን ወይስ አንፈራም ለማለት አንፈራም?

  ቀን:

  በዕዝራ ኃይለ ማርያም

  በደርግ መጨረሻ ይሁን በኢሕአዴግ መጀመርያ ዘመናት፣ አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁር የፍራቻችንን መጠን ለመግለጽ ‹‹እንፈራለን ለማለት እንፈራለን›› ብለው ነበር፡፡ ዛሬስ ወደ ‹‹አንፈራም ለማለት አንፈራም›› ተሸጋግረናል? ወይስ ‹‹እንፈራለን ለማለት እንፈራለን›› ላይ ነን? የመጣጥፌ ዓላማ ፍራቻና ድፍረትን የተመለከተ አይደለም፡፡ በሰሞኑ የሚዲያዎችን ዜናና ፕሮግራም ስለተሻማው ዝርፊያና ጭካኔ ስለተሞላበት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ትንሽ ለማለት ነው፡፡

  በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ‹‹ምናባዊው. . . ›› በሚል ርዕስ የቀረበው የሜቴክ ገመናና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ አንዳንድ ባለ ጊዜ የነበሩ ባለሥልጣናትና ቅጣዮቻቸው በሕዝብ ላይ ያደረሱትን ጭካኔና ወራዳነት አሳይቷል፡፡ ለኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ውርደት ነው፡፡ ማፊያም እንደዚህ አልዘቀጠም፡፡ የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነትና አገልግሎት አመራሮችና አባላት በሽብር ተጠርጥረው የተያዙ ግለሰቦች ላይ ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል፡፡

  እንደ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ፣ በሽብር ተጠርጥረው የሚያዙ ግለሰቦች ወደ መደበኛ እስር ቤት ከመወሰዳቸው በፊት በስውር እስር ቤቶች እንዲቆዩ ይደረጋሉ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ከሰባት በላይ ስውር እስር ቤቶች ነበሩ። ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር የሚውሉት በአብዛኛው በአምቡላንስ ሲሆን፣ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አመራሮችና አባላት አስገዳጅነት የራሳቸው ያልሆኑ የጦር መሣሪያዎችን “የእኔ ነው” ብለው እንዲፈርሙ ይገደዳሉ።

  በአጋንንት የሚመሰሉት መርማሪዎች ዛፍ ላይ ሰቅሎ መግረፍ፣ በኤሌክትሪክ መጥበስ፣ በፒንሳ የብልትን ቆዳ መሳብ፣ በአፍንጫ እስክሪብቶ ማስገባት፣ በአፍና አፍንጫ እርጥብ ፎጣ መወተፍ፣ በሙቀታማ ሥፍራዎች ላይ ለረዥም ጊዜ ፀሐይ ላይ ማስቀመጥ፣ ብልት ላይ የውኃ ኮዳ ማንጠልጠልና ጥፍር መንቀልን የመሳሰሉ ማሰቃያዎችን ይጠቀሙ ነበር፡፡ አስገድዶ መድፈርና ግብረ ሰዶም መፈጸሙን፣ በምርመራው ወቅት የተገደሉ ሰዎች መኖራቸውንና ያሉበት የማይታወቅ ግለሰቦች እንዳሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ተናግረዋል።

  የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ያለ ምንም ጨረታ በስድስት ዓመታት በ37 ቢሊዮን ብር የውጭ አገር ግዢ ፈጽሟል፡፡ ግዥው የተፈጸመው ከኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች ጋር የሥጋ ዝምድና ወይም የጥቅም ትስስር ባላቸው ግለሰቦች ድለላና ሌላ ግንኙነት አማካይነት ሲሆን፣ እስከ 400 ፐርሰንት ድረስ የተጋነነ ነው፡፡ በአንድ ድርጅት ብቻ የ205 ሚሊዮን ብር ግዥ ያለ ጨረታ ተከናውኗል። የባህር ትራንዚትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ‘አንድነት’ እና ‘ዓባይ’ የተሰኙ መርከቦች ከ28 ዓመታት በላይ በማገልገላቸው እንዲሸጡ ሲወሰን፣ ብረቱን አቅልጦ ለመጠቀም ሜቴክ መርከቦቹን ገዝቷል፡፡

  ሜቴክ መርከቦቹ እንዲቀልጡ አላደረገም፡፡ ዱባይ በመላክ 513 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጎ መርከቦቹን በማስጠገን ለጥገና የተሰጣቸውን ፈቃድ በመጠቀም በንግድ ሥራ አሰማርቷል፡፡ መርከቦቹ ከኢራን ሶማሊያ መስመር ጭምር በመንቀሳቀስ 500 ሺሕ ዶላር ገቢ ቢያስገኙም ለድርጅቱ ገቢ አልተደረገም። መርከቦቹም በ2.6 ሚሊዮን ዶላር ተሽጠዋል። በሌላ አገር ሰንደቅ ዓላማ ሕገወጥ ንግድ (የጦር መሣሪያ) ሲነገድ እንደ ነበር አፈትላኪ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

  ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ እንዳሉት ሜቴክ የአገር ውስጥ ፕሮጀክቶችን ለመከታተል ከአንድ የእስራኤል ኩባንያ ከ50 ዓመታት በላይ ያገለገሉ፣ የነዳጅ ፍጆታቸው ከፍተኛ የሆነና የቴክኒክ ችግር ያለባቸው አምስት አውሮፕላኖችን ገዝቷል፡፡ አራቱ አውሮፕላኖች አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ሲሆን፣ አንዱ የት እንዳለ አይታወቅም። ደርግ በብሔራዊ የአገር ክህደትና በሌብነት አይታማም፡፡ በደርግ የመጨረሻ ዘመን አብርሃም ያየህ (የሕወሓት የቅርብ ሰውና ገመና አዋቂ) እና ገብረ መድን አርዓያ (የሕወሓት የፋይናንስ ኃላፊ የነበሩ) የዛሬ ውርደት እንደሚደርስብን የሕወሓትን ሥውር አጀንዳ በመተንተን አስጠንቅቀው ነበር፡፡

  ደርግ በሕዝብ ስለተጠላና የመጡትም ደርግ ሲያጣጥር በመሆኑ ሰሚ አላገኙም፡፡ እነሱም ቀድመው ባለመምጣታቸው ‹‹ብለን ነበር›› ከሚል ‹‹የህሊና ወቀሳ›› ከመዳን በቀር፣ የሕወሓትን ግስጋሴ ማስቆም አልተቻለም፡፡ የ“ሕወሓት” ልሂቃን ሥልጣን በያዙ ማግሥት ራሳቸውን “ሊቃውንት” እና “ምሉዕ በኩለሄ” አደረጉ፡፡ አንዳንድ የሕወሓትና ቅጥልጣዮቻቸው ልሂቃን ለሃያ ሰባት ዓመታት እግዚአብሔር ባልወደደውና ሕዝብ ባልመረቀው መንገድ የሚጠሏትና የማያውቋት ኢትዮጵያ ጌታ ሆነው፣ በጥፍራችን ውስጥ እንድንደበቅና ተሸማቀን ጭብጥ እንድናክል አላደረጉምን? ከማኅበራዊ ሱታፌ ይልቅ ገደብ የለሽ ራስ ወዳድነት እንዲነግሥብን አልተጉምን? ለዘመናት የተገነቡት የትምህርት፣ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊና የወታደራዊ ተቋማት እንዲፈርሱና እንበለ ጥራት እንዲሆኑ አላደረጉምን? የወረደብን ያልታሰበ፣ የማይታሰብና ሊታሰብ የማይችል ዕርቃንነት፣ ባዶነት፣ ብሔራዊ ክስረት፣ የመንፈስ ድህነትና አጥፍቶ የመጥፋት አደጋ ነው፡፡

  ተራዳኢያችን ቸር እግዚአብሔር ፊቱን መለስ አድርጎልን ፀሐያቸው እየጠለቀች ቢሆንም፣ በእጃቸው ብረቱና ገንዘቡ ስላለ ትግሉ ቀላል አይደለም፡፡ ሕወሓታውያን አገራቸውን ከአውሮፓ የመጨረሻ ደሃና መኃይም ያደረጓት የአልባንያው መሪና ፈላስፋ ኤንቨር ሖዣ ደቀ መዝሙርና የፖለቲካ ቀመራቸው አማኝ እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡ በትግል ዘመናቸው የጠንካራ ዲሲፒሊን ጌታ የነበሩት የትናንቱ “ተጋዳላዮች” በወቅቱ ይታሙ የነበረው ይከተሉት በነበረው አጥፊ ‹‹መኃይማዊ ፍልስፍና›› እና ‹‹ቃርሚያ ቲዎሪ (ነባቤ አዕምሮ)›› እንጂ በእምነት ማጉደል አልነበረም፡፡

  ጫካ እያሉ “ተራ ተጋዳላዮች” በአፋቸው ጨው የማይሟሟ ታማኝ ትሁታን ነበሩ፡፡ ፍትሕ ላጣው፣ በረሃብ ለሚቆላው፣ በጫማ ዕጦት እግሩ በንቃቃት ለሚሰቃየው፣ አዳም ገላውን የሚደብቅበት ጨርቅ ላጣው ዜጋ “አርነት” ቆመናል ካሉት ውስጥ አንዳንድ “ተጋዳላዮች” ይህን ይፈጽማሉ ብሎ እንደምን ይታሰባል? ከባንክ የዘረፉትን ኩንታል ብር በታማኝነት የሚጠብቁት፣ ለእግራቸው ጫማ ያልነበራቸው፣ የብር መልክን እንኳ የማያውቁት፣ ከሃምሳ ኪሎ በላይ የማይመዝኑት “ባት የለሽ”ዎቹ የጉስቁልና ሥዕሎች ዛሬ እንዴት ለወሬ የሚያስቸግር ዘራፊና ነውረኞች ሆኑ? ሕዝቡ በአሰቃቂ ድህነት ሲሰቃይና ኪሱና ቡሐቃው ባዶ ሲሆንበት፣ ሞትን በሚያስመኝ ምንዱባንነት ሲንከላወስ እነሱ በገንዘብ ናዳ ተጥለቅልቀው በዱባይና በአውሮፓ ከተሞች እንዴት ይዶርራሉ? በትግሉ የተሰውት “ተጋዳላዮች” አንዴ ቀና ብለው ጓዶቻቸውንና ሰማይ ጠቀስ ፎቆቻቸውን፣ ቪኤይት መኪኖቻቸውን፣ ካምፓኒዎቻቸውን፣ 12ኛ ክፍል ሳይጨርሱ ያገኙትን ውሽልሽል ማስትሬትና ዶክትሬት ዲግሪዎቻቸውን፣ የሚጠጡትን ዊስኪ፣ አሜሪካና አውሮፓ የሚማሩ ልጆቻቸውን፣. . . ቢያዩ ምን ይሰማቸው ይሆን? ከጠመንጃ ላንቃ ከተገኘው ሥልጣናቸው በስተቀር የሕዝብን የልብ ትርታና የአገራችንን ትኩሳት ማዳመጥ የማይፈልጉት እነዚህ ልሂቃን ይሉኝታ ቢስ ሆነው ብዙ ጅላ ጅል ነገር ፈጽመዋል፡፡

  በጂቡቲ የኢትዮዽያ የቀድሞ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ በጂቡቲ ቆይታቸው የታዘቡትን ለኤልቲቪ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት፣ የሌሎች መንግሥታዊ ድርጅቶች ገመና “ሜቴክን ማረኝ” ያስብላል። አገራችን እኩዩና ሰናዩ የሚዋጉባት (አርማጌዶን) ሆናለች፡፡ ቸር እግዚአብሔር “ኤሎሄ”አችንን ሰምቶ የደረሰብንን ግፍ፣ በደል፣ ሰቆቃና ብካይ በቃ ይበለን፡፡ የትግራይን ሕዝብ ያጋጠመው ‹‹ላም እሳት ወለደች፣ እንዳትልሰው እሳት፣ እንዳትተወው ልጇ ሆነባት፤›› እንዲሉ ነው፡፡ በአንዳንድ ወራዳ ሕወሓት እኩይ ተግባርም አይደሰትም፡፡ የወራዳ ልሂቃን መሸሸጊያ ጫካ መሆን የለበትም፡፡ እንኳን ለሌላው ለራሱም የማይጠቅሙትን ወራዳዎች ከመሀሉ አጋልጦ ሊያወጣቸው ይገባል፡፡

  ‹‹የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ›› በሚለው ብሂልና “የየብሔረሰብ ቱጃሮች”ን ለመፍጠር በሚል ቅኝት አንዳንድ የኦሕዴድ፣ የብአዴን፣ የደኢሕዴንና የአጋር ድርጅቶች ልሂቃን ቃርሚያ፣ ቃርሚያውን ለቃቅመዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ብሔረሰብ ሳይመረጥ በሁሉም “ተላላኪ” ዘራፊዎች ላይ ዕርምጃ ሊወሰድ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን በመሆን የፖለቲካችን ሕመም ያመጣውን ብሔራዊ ውርደት ከዘረኝነት፣ ከበቀልና ከስሜት በፀዳ መንገድ ሊታገል ይገባል፡፡

  ‹‹የነብርን ጭራ አይዙም፣ ከያዙም አይለቁም›› እንዲሉ፣ መንግሥት ዘራፊ ሽፍቶችን የማደን ዘመቻ አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ አሁን ያለንበት ጊዜ ከፍራቻ የተላቀቅንበት ነው፡፡ መፍራትም ካለብን ቸር እግዚአብሔርንና ህሊናችንን እንጂ ሌላ መሆን የለበትም፡፡ ታድያ እኛ ከወዴት ነን? እንፈራለን ለማለት እንፈራለን ወይስ አንፈራም ለማለት አንፈራም? የሥነ ልቦና ጠበብት እንደሚሉት ሕፃናት በርካታ መጫወቻዎች ቀርበውላቸው አንዱን መርጠው እንዲወስዱ ቢታዘዙ፣ ከአዕምሮዋቸው ያለመብሰል የተነሳ ያዩትን ሁሉ እያነሱ አንዱንም ሳይመርጡ ይቀራሉ፣ ሁሉንም እንዲሰጧቸው ይጠይቃሉ፡፡ ካልተሰጣቸው ያለቅሳሉ፡፡ ይህ ምሳሌ ለአንዳንድ የሕወሓትና ቅጥልጣዮቻቸው ልሂቃን ስግብግብነትና ወራዳነት የተገባ ነው፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

  ከአዘጋጁ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው   ehailemariam2@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...