Tuesday, August 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  በሕግ አምላክሕገ መንግሥቱ ተረቆ የፀደቀበት ሒደት በቅቡልነት መነጽር ሲታይ

  ሕገ መንግሥቱ ተረቆ የፀደቀበት ሒደት በቅቡልነት መነጽር ሲታይ

  ቀን:

  በውብሸት ሙላት

  ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀ 24 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሩብ ክፍለ ዘመን ሊሞላው የአንድ ዓመት ፈሪ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በፀደቀበት ወቅት የተወለደ ሰው፣ አሁን ላይ ከጉርምስና ዕድሜ ክልል ተላልፏል፡፡ ሕጉ ከመፅደቁ በፊት በተለያዩ ሒደቶች ሦስት ዓመታትን አሳልፏል፡፡   

  ሕገ መንግሥቱ ማሳካት የሚፈልጋቸውን ግቦች በመግቢያው ላይ አስፍሯል፡፡ በተለይ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በመፍጠር ረገድ ስኬቱ አዎንታዊ እንዳልሆነ መደምደም ይቻላል፡፡ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው አስተዳድረው በፍትሐዊነት በፌዴሬሽኑ ተወክለው፣ የሰብዓዊ መብቶች ተከብረውና የሕግ የበላይነት ሰፍኖ፣ ዘላቂ ሰላም ተረጋግጦ፣ በኢኮኖሚ አንዱ ከሌላው ተቆራኝቶ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በመፍጠር መጨረሻው ላይ ሁሉም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ (የፖለቲካ) ማኅበረሰብ የሚተያይባትን አገር መፍጠርን ነው በዝርዝር ሲታይ በግብነት ያስቀመጠው፡፡

  ይሁንና አሁን ላይ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ የተገለጸውን ልዩነትን በመብትን አስተናግዶ ነገር ግን አንድ ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ በመገንባት ረገድ ልምሻ ይዞታል ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ ባለፈም የቅቡልነት የማጣት ድረጃውም እየባሰበት እንጂ እየተሻሻለ ነው የሚያስበል አቋም ላይ አይደለም፡፡

  እንግዲህ የሕገ መንግሥቱ ይዘት ላይ የሚነሱት ችግሮችና ሕገ መንግሥቱን አክብሮ ከመሥራት ይልቅ በተቃራኒው የተሄደው መንግሥታዊ ጉዞ እንደተጠበቁ ሆነው ሕገ መንግሥቱን ከማርቀቅ ጀምሮ እስከማፅደቅ ድረስ ያሳለፋቸው ሒደቶች በራሱ በአንድ በኩል በይዘቱ አማካይነት ለተፈጠሩት ችግሮች፣ በሌላ በኩል ቅቡልነት እንዲጎድለውና ብሎም እየባሰበት እንዲሄድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

  በዚህ ጽሑፍ ቅኝት የሚደረገው የሕገ መንግሥቱን አርቃቂዎች አመራረጥ ጀምሮ እስከፀደቀበት ድረስ ያሳለፋቸውን ሒደቶች በማስታወስ ከሕገ መንግሥታዊ ቅቡልነት አንፃር ጥቂት ነጥቦችን ማንሳት ነው፡፡

  የደርግ አስተዳደርን የተካው ኢሕአዴግ መራሹ የሽግግር መንግሥት ሕገ መንግሥት እስኪወጣ ድረስ በደርግ ዘመን የፀደቀውን ሕገ መንግሥት የሚተካ ቻርተር አፅድቋል፡፡ የሽግግር ወቅት ቻርተሩ የደርግ መንግሥት ሲወድቅ አገሪቱን በጊዜያዊነት ለመምራት የተመሠረተው የሽግግር ወቅት መንግሥት የሚመራባቸውን መርሆዎች የመንግሥትን አወቃቀር ተዋጽኦና ሥልጣንና ተግባር፣ እንደዚሁም የሽግግር መንግሥቱ ሊያከብራቸውና ሊያስፈጽማቸው የሚገቡ የዜጐች መብትና የብሔር ብሔሰቦችን መብት የሚደነግግ ለሽግግር ወቅት ብቻ የሚያገለግል ሕግ እንደሆን ታስቦ ነው የተዘጋጀው፡፡

  የተጻፈ ሕገ መንግሥት ባላቸው አገሮች ሕገ መንግሥት የማውጣት ሒደት ጠቅለል ሲደረግ በአራት ደረጃዎች ይከፈላል፡፡ እነርሱም የማርቀቅ (Drafting)፣ የመወያየት (Deliberation)፣ የመቀበል (Adoption) እና  የማፅደቅ (Ratification) ደረጃዎች ናቸው፡፡ የሽግግር ወቅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንን በቻርተሩ የተሰጠውን ተግባር በነሐሴ ወር 1984 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 24/1984 ዓ.ም. የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ በማወጅ የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን አቋቁሟል፡፡

  በሽግግር ቻርተሩ መሠረት የሽግግር መንግሥቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ በወቅቱ የሽግግር መንግሥቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ፡፡ ፕሬዚዳንትም አፈ ጉባዔም ነበሩ ለማለት ነው፡፡ በምክር ቤቱ እንዲካተቱ ያልተፈቀደላቸው ፓርቲዎች እንደነበሩት ሁሉ ኋላ ላይ የለቀቁም ነበሩ፡፡

  በአጭሩ ሕገ መንግሥት ማርቀቅ ማለት የተለያዩ የሙያ ዘርፎች ማለትም የቋንቋ፣ የሕግ፣ የታሪክ፣ የፖለቲካ ሳይንስ፣ ወዘተ ባለሙያዎች በጋራ ኮሚቴው በኩል መጀመርያ ለውይይት መነሻ የሚሆን ሰነድ የሚያዘጋጁትን የሚመለከት ነው፡፡ ሕገ መንግሥትን በማርቀቅ ደረጃ ሰነዱ ግልጽ የሚሆንበት፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በተለይም ከማኅበራዊ፣ ከኢኮኖሚያዊና ከፖለቲካዊ ለውጦች አንፃር ታይቶ የመጀመርያው ወሳኝ መሠረት የሚጣልበት ደረጃ ነው፡፡

  ይህ ደረጃ አብዛኛውን ጊዜ መነሻ የሚያደርገው የለውጥን መፈክር፣ የፖለቲካ ድርጅቶችን ኘሮግራም፣ የሕዝቡን ፍላጐት፣ ታሪክ፣ ወዘተ ነው፡፡ ለዚህም ነው አብዛኛውን ጊዜ እንደ ሌሎች ሕግጋት፣ ሕገ መንግሥትን በውጭ ዜጐች ማርቀቅ የማይደገፈው፡፡ በዚህ ደረጃ አርቃቂው ኮሚቴ በርካታ መነሻዎችን ከግምት ውስጥ ማስቀመጥ ይጠበቅበታል፡፡ የአገሪቱን የውጪና የውስጥ ጉዳይ ፖሊሲ፣ የመከላከያና የአገር ሉዓላዊነት ጉዳይ ፖሊሲን፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ሌሎችንም ወሳኝ ሕጎች የማርቀቅ ሒደቱን በጥንቃቄ መቃኘት ይጠይቃል፡፡

  የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን በተወካዮች ምክር ቤት የተሰየሙ ተልዕኳቸው፣ ሥልጣንና ኃላፊነታቸው በሕግ ተዘርዝሮ የተሰጣቸው 29 የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን አባላት ሲሆን፣ በኮሚሽኑ ውስጥ የአባላቶች ተዋጽኦን በተመለከተ፣ በአዋጁ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 2 እንደተመለከተው፣ ከተወካዮች ምክር ቤት ሰባት፣ ከፖለቲካ ድርጅቶች ሰባት፣ ከሠራተኛ ማኅበራት ሦስት፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ሦስት፣ ከሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ሁለት፣ ከኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ሁለት፣ ከኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ማኅበር ሁለት፣ ከሴቶች ተወካይ ሦስት አባላት እንደተካተቱበት ለመረዳት ይቻላል፡፡

  የአርቃቂ ኮሚሽኑ ዋና ተልዕኮን በሚመለከት ደግሞ በቻርተሩ መንፈስ አዲሲቷ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የምትመሠረትበትንና የምትተዳደርበትን ሕገ መንግሥት ማርቀቅ፣ ረቂቁን በሽግግር ወቅት ለነበረው ለተወካዮች ምክር ቤት ማቅረብና የምክር ቤቱን ስምምነት ሲያገኝ ለሕዝብ ውይይት ማቅረብ፣ ከሕዝብ በውይይት በተገኘው አስተያየት መሠረት ረቂቁን በማሻሻል የመጨረሻ ረቂቁን አዘገጅቶ በተወካዮች ምክር ቤት ማፀደቅ፤ በተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀውን ረቂቅ፣ ለሕገ መንግሥት ጉባዔ ማቅረብ እንደሆነ በአዋጁ አንቀጽ አራት ተደንግጓል፡፡

  ከሽግግር መንግሥቱ ቻርተር ዝግጅት ጀምሮ የኮሚሽንኑ አባላት እስከ መሰየም ብሎም የኮሚሽኑ ተጠሪነት በራሱ ተቀባይነት ያለው ሕገ መንግሥት ይኖር ዘንድ ወሳኝ የሆነ ሚና አለው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ማንፀባረቅ ያለበትንና ምን ዓይነት መንፈስ ያለው ሕገ መንግሥት መኖር እንዳለበት ሳይቀር ቻርተሩ ላይ ሠፍሮ እናገኘዋለን፡፡ ቻርተሩን በማዘጋጀት ረገድ የሕወሓት፣ ሻዕቢያና ኦነግ ሚና ከፍተኛ እንደነበር በብዙ ሰነዶች ውስጥ ተገልጾ እናገኘዋለን፡፡ በሰላም ጉባኤው የጸደቀው በዋናነት ይህ በሦስት ድርጅቶች የተዘጋጀው ሰነድ ነው ካልን፣ የቀጣይ የሕገ መንግሥቱን መንፈስ የቃኙት እነዚሁ የሦስቱ ድርጅቶች አመራሮች ናቸው ማለት ነው፡፡

  በመሆኑም ገና ከጅምሩ ማለትም ሕገ መንግሥቱ ምን ይምሰል የሚለው ነጥብ በቻርተሩ ስለተቀመጠና የቻርተሩ አዘጋጆች ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መሠረት አካታች ስላልነበረ ከጅምሩ ጉድለት ነበረበት ማለት ይቻላል፡፡ በቻርተሩ አማካይነት የተቋቋመው ምክር ቤት ውስጥ ተሳታፊ ያልነበሩና ጥለው የወጡ ፓርቲዎች እንደነበሩም ግልጽ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በተራው የምክር ቤቱ ማኅበራዊ መሠረት ላይ አሉታዊ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

  እንግዲህ ይህ ምክር ቤት ባወጣው አዋጅ መሠረት አርቃቂ ኮሚሽኑ ተቋቋመ፡፡ አባላቱም ተመደቡ፡፡ ኢሕኣዴግ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር) እና በቀድሞው የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ በአቶ ዳዊት ዮሐንስ ተወከለ፡፡ አቶ ዳዊት ጸሐፊ፣ አቶ ክፍሌ ወዳጆ ደግሞ ሊቀመንበር ሆነው ኮሚሽኑን መሩ፡፡ ከአርቃቂ ኮሚሽኑ ቃለ ጉባዔ መረዳት የሚቻለው፣ ሊቀመንበሩና ጸሐፊው በፍፁም መስማማት ያልቻሉ ሰዎች እንደነበሩ ነው፡፡ አቶ ክፍሌ ወዳጆን የሚደግፉ ጥቂት በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከሕገ መንግሥቱ መግቢያ ጀምሮ በብዙ ጉዳዮች ላይ የተለያየ ሐሳብ ነበራቸው፡፡ ሁልጊዜም በቋሚነት አቶ ዳዊት ዮሐንስ የሚመራው ቡድን በድምፅ ብልጫ እያሸነፈ ሕገ መንግሥቱ ተዘጋጀ፡፡

  በአንድ በኩል በኢሕአዴግ ወገን የሚቀርበውን ሐሳብ በቋሚ ደጋፊነት የሚቀበሉ አባላት ነበሩ፡፡ በአንፃሩ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ በቋሚነት የሚቃወሙ ሰዎችም ነበሩ፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነጥብ ማንሳት አስፈላጊ ነው፡፡ የአርቃቂ ኮሚሽኑ አባላት ይሠሩ የነበሩት በትርፍ ጊዜያቸው በሚመስል አኳኋን ነበር፡፡ ከቃለ ጉባዔው መገንዘብ እንደሚቻለው፣ የተወሰኑ አባላት በርካታ ውይይቶች ላይ አልተገኙም፡፡ ቢገኙም አርፍደው ይገኙ እንደነበርና በዚህ ድርጊታቸውም እንደሚናደዱ ዳንኤል ተፈራ ባዘጋጀው መጽሐፍ ውስጥ ነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር) መስክረዋል፡፡  ኮሚሽኑ አርቅቆ እንደጨረሰም ለሰየመው ምክር ቤት አቀረበ፡፡

  ቀጣዩ ሒደት በምክር ቤቱ እንዲፀድቅ ተደርጎ ከሕዝብና ከሌሌች አካላት ጋር ውይይት ማድረግ ነው፡፡ በዚህ መልክ በባለሙያ የተረቀቀው ሰነድ፣ ለሰነዱ ባለቤት ለሆኑት ለኢትዮጵያ ዜጐች ለውይይት ይቀርባል፡፡ ይህ የውይይት ሒደት ራሱን የቻለ ደረጃ ሲሆን፣ የውይይት  (Deliberation) ደረጃ ይባላል፡፡ በዚህ ደረጃ ዜጐች በሰነዱ ላይ ያላቸው አስተያየት በጥንቃቄና በዝርዝር ተሰብስቦ በሰነዱ ውስጥ እንዲካተት ይደረጋል፡፡

  ይህ ደረጃ በጣም ጥንቃቄ ይጠይቃል የሚባለውም በዚህ ደረጃ ሰነዱ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ማለትም የብዙኃኑንና የአናሳውን ዜጐች መብቶችን ማስጠበቅን ስለሚያጠቃልል ነው፡፡

  ኮሚሽኑ የመጀመርያውን ረቂቅ አዘጋጅቶ የሽግግሩን የተወካዮች ምክር ቤት ስምምነት ካገኘ በኋላ፣ ረቂቁን በተመለከተ በሕገ መንግሥታዊ ጽንሰ ሐሳቦችና በረቂቅ ሕገ መንግሥቱ ላይ በተለያዩ የትምህርት ተቋሞችና በመንግሥት መገናኛ ዘዴዎች ውይይቶችን፣ ሴሚናሮችንና ሲምፖዚየሞችን በማዘጋጀት ረቂቁን ሊያዳብሩ የሚችሉ ሐሳቦችንና አስተያየቶችን አሰባሰበ፡፡ ረቂቁ ለክልል አስተዳደር ምክር ቤቶችና ለወረዳ ምክር ቤት አባላት ቀርቦ እንዲወያዩበትና አስተያየታቸውን እንዲሰጡበት በማድረግ፣ ከምክር ቤቶቹ የተሰጠውን አስተያየት በግብዓትነት እንዲጠቀምበት ይጠበቃል፡፡

   እንደዚሁም በረቂቅ ሕገ መንግሥቱ ላይ ሕዝቡ በየቀበሌው ውይይት በማድረግ አስተያየት ሊሰጥ የሚችልበትን መድረክ በማመቻቸት ሕዝቡ በረቂቁ ላይ የሰጠውን ትችትና አስተያየት በማሰባሰብና በግብዓትነት በመጠቀም ማካተትን ታሳቢ ያደርጋል፡፡ በተለያየ ጊዜ ረቂቅ ሕገ መንግሥቱን አስመልክቶ ከሕዝብ ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች ማብራሪያና ገለጻ በመስጠት፣ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የቀረቡትን አስተያየቶችና የማሻሻያ ሐሳቦች ጨምሮ እንዲያቀርብ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡

  የተደረገውን ውይይት በሚመለከት በአንድ በኩል ስለሕገመንግሥታዊ ጉዳዩች ንቃተ ህሊናው የዳበረ ማኅበረሰብ ሳይፈጠር፣ ለመፍጠር ምቹ ሁኔታም ሳይዘረጋ ያለቀውን ሰነድ ለሕዝብ ማቅረቡ ብዙም ፋይዳ የለውም፡፡ በሌላ በኩል በየቀበሌው የተደረጉትን ውይይቶችና የተነሱትን ሐሳቦች አጠቃልሎ ከዚያም ከፍተኛ ድጋፍ ያላቸውን ከሌላቸው መለየቱ በራሱ አድካሚና በወቅቱ ከነበረው የቴክኖሎጂ ደረጃ  አኳያም ጠቀሜታው ዝቅ ያለ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን የማስረፅ እንጂ ሥራው ውይይትና ግብዓት መሰብሰብ አይመስልም ነበር፡፡ እንደውም ለረቂቅ ሕገ መንግሥቱ ማብራሪያ ሁሉ ተዘጋጀቶ ሰው በማብራሪያው መልክ እንዲረዳው የማድረግ ሒደት ነው የተከተለው፡፡ ማለትም ያለቀ ሰነድ ነው የመሰለው፡፡

  ከሕዝብ ውይይት መለስ ያለውም ቀድሞ የነበረው ረቂቅ ምናልባትም የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት የሚለውን የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሚል የስም ቅያሪ በማድረግ የመጨረሻ የተባለው ረቂቅ የቀረበለት የተወካዮች ምክር ቤት በማፅደቅ ለሕገ መንግሥት ጉባዔ አቀረበው፡፡

  እስካሁን ድረስ በመረቀቅ ላይ የነበረው ሕገ መንግሥት ሁለቱን ደረጃዎች ጨርሷል፡፡ ከዚያ ወደ ሦስተኛው ደረጃ ማለትም መቀበል (Adoption) ወደሚባለው ተሸጋገሯል፡፡ ይህ ከውይይት ቀጥሎ የሚመጣ ወሳኝ ደረጃ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ሕዝቡ የተወያየበት ለተወካዮቻቸው እንዲካተቱ የተሰጡት ዋና ዋና ጉዳዮች መካተትና ያለመካተታቸው የሚረጋገጥበት ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ሰነዱ ገዥ፣ የበላይ ሰነድ ሆኖ ከመፅደቁ በፊት የሰነዱ ባለቤት ሰነዱን መቀበልና ያለመቀበሉን የሚያሳይበት ወሳኝ ደረጃ ነው፡፡

   በዚህ ደረጃም ቢሆን ኅብረተሰቡ መካተት ያለበትን መሠረታዊ ጉዳዮች በማጣራት እንዲካተት ማድረግ ወይም የመጨመርም ሆነ የመቀነስ ሙሉ መብት አለው፡፡ ይህ የሚሆነው ግን አፅዳቂ ጉባዔያተኞቹ በትክክል የሕዝቡ ወኪል ሲሆኑ ነው፡፡ በመላው ኢትዮጵያ ለሕገ መንግሥት አፅዳቂነት ሰዎች ተመረጡ፡፡ ቁጥራቸው ከአሁኑ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ቁጥር ጋር ተቀራራቢ ነበር፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሻለቃ አድማሴን ጨምሮ በጣት የሚቆጠሩ ከአዲስ አበባ ከተማ ከተመረጡት ውጪ ሁሉም የኢሕአዴግና አጋር ድርጅቶች አባላት ብቻ ነበሩ፡፡

  በዚያ ላይ ለማፅደቅ የተመረጡት ሕገ መንግሥትን መረዳት፣ መገንዘብና መተንተን የሚችሉ ስለመሆናቸው የሚጠይቅ መሥፈርት አልነበረም፡፡ አማካሪም ይሁን ሌላ ባለሙያ አልተቀጠረላቸውም፡፡ የአርባ ቀናቱ ቃለ ጉባዔዎችን የተመለከተ ሰው በቀላሉ የሚረዳው ይሄንኑ ነው፡፡ ጥቅምት 19 ቀን 1987 ዓ.ም. የማጽደቅ ሒደቱን በመጀመር ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. ማለተም በአርባኛው ቀን አጽድቀው ሒደቱን ጨረሱ፡፡ እንግዲህ የአፅዳቂ ጉባዔው ሰብሳቢ ነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር)፣ ምክትላቸው አቶ አዲሱ ለገሰ፣ ጸሐፊያቸው የቀድሞው የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አባተ ኪሾ ነበሩ፡፡ የተለያዩ ኮሚቴዎችን በመምራት እነ አብዱል መጂድ ሁሴን (ዶ/ር)፣ አቶ ግርማ ብሩ፣ ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ፣ ወ/ሮ እንወይ ገብረ መድኅን ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ከላይ በተገለጹት ሰዎች አጋፋሪነት የ40 ቀናት ቆይታው ተጠናቀቀ፡፡ ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥቱ ፀደቀ፡፡ በዚሁ ዓመት ነሐሴ 25 ቀን ሥራ ላይ ዋለ፡፡ ይህ የመጨረሻው አራተኛው ደረጃ ነው፡፡

  ሕገ መንግሥትን የማፅደቅ ደረጃ ሕግ ሆኖ ከመውጣቱ በፊት ያለው ሌላ ወሳኝ ደረጃ ነው፡፡ ይህ ደረጃ ከመቀበል ቀጥሎ የሚመጣ ሲሆን፣ የሰነዱ ባለቤት የሆነው ሕዝብ በወከላቸው ሰዎች የተዘጋጀውን ሰነድ መቀበል አለመቀበሉን የሚያሳይበት ደረጃ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ እንደ ተራ ወካይና ተወካይ ግንኙነት ሳይሆን፣ ውክልናው ከተራ ውክልና የተሻገረ ኃላፊነት ያለው ተግባር መፈጸሙ የሚረጋገጥበት ደረጃ ነው፡፡

  በዚህ ደረጃ ሒደቱን ጠብቆ ለዘመናት ማገልገል የሚችልና በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሰነድ የሚፀድቅበት ነው፡፡ ስለዚህም የማፅደቅ ደረጃው ከላይ የተጠቀሱትን ተከታታይ ደረጃዎች ማለትም የማርቀቅ፣ የውይይትና የመቀበል ደረጃዎችን አልፎ የሚመጣ የመጨረሻው ደረጃ ነው፡፡ ይህን ደረጃ አልፎ ሰነዱ ከፀደቀ ወደ ገዥነትና የበላይነት ያለው ሰነድ ደረጃ የሚያድግበት ሒደት ነው፡፡ በአጭሩ ሕገ መንግሥቱ ዕድገቱን በመጨረስ እንደሙሉ ሰነድ የሚቆጠርበት ደረጃ ነው፡፡

  በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ተቀባይነት ባለው የዓለም ተሞክሮ መሠረት አንድ ሕገ መንግሥት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ተቀባይነት ያለው ሰነድ ለመሆን፣ እነዚህ ደረጃዎችን በጥንቃቄ ማለፉ በተቀባይነቱ (Legitimacy) ላይ ከፍተኛ ሥፍራ እንዲኖረው አስተዋጽኦ ይደርጋል፡፡

  ይሁን እንጂ በእነዚህ ደረጃዎች ያላለፉ የበርካታ አገሮች ሕገ መንግሥቶች አሉ፡፡ የአሜሪካን ብንወሰድ ሙሉ በሙሉ እነዚህን ደረጃዎች ተከትሎ የደቀ ነው ማለት አይቻልም፡፡ የአውስትራሊያና የካናዳንም ብንወሰድ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሥር በነበሩበት ዘመን ከእንግሊዝ የተላኩ (ቢያንስ በእንግሊዝ የፀደቁ) ሆነው ይገኛሉ፡፡ የጃፓንና የጀርመን ሕገ መንግሥቶችም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ በዋናነት ከአሜሪካኖች የበላይ ቁጥጥር የወጡ ናቸው፡፡

  ከዚህ የምንረዳው ነገር ቢኖር የሕገ መንግሥት አወጣጥ ሒደቱ በራሱ የሕገ መንግሥትን ተቀባይነት የማያሳይ ስለመሆኑ ነው፡፡ ከአወጣጡ ሒደት ይልቅ ሥራ ላይ ሲውል ያመጣው ለውጥ የበለጠ ዋጋ አለው፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአንድ ጎኑ ከጅምሩ የአካታችነት ጉድለት አለበት፡፡ ለአብነት አንዳንድ የተለየ የማኅበረሰብ ክፍልን የሚወክሉ ቡድኖች ከሒደቱ ተገልለዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በብሔር ብሔረሰቦች መካከል የነበረው የብሔርተኝነት ደረጃ የተለያየ ስለነበር፣ አንዳንድ ብሔሮች ቀድመው ስለብሔራቸው የሚያስቡ ተወካዮች ሲኖራቸው፣ ሌሎች ደግሞ በዚህ መልኩ ያልተወከሉም ያልወከሉም ነበሩበት፡፡

   የማኅበራዊ ውሉ ተደራዳሪዎችና ባለቤቶች ብሔሮች ስለሆኑና በወቅቱ ይህ ዓይነቱ ማኅበራዊ ንቃተ ህሊና ሳይኖራቸው የተደረገ ውል ነበር ማለትም ይቻላል፡፡ ተቀባይነት ይኖረው ዘንድ በቅነልቦና በየጊዜው እየፈተሹ ማሻሻል ይቻል ነበር፡፡ ይህ አለመሆኑ ደግሞ የቅቡልነቱን ዕጦት እያባባሰው ነው ማለት ይቻላል፡፡

  አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው wuobishett@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የአገሪቱ ባንኮች ካፒታል 199.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ

  ከታክስ በኋላ 50 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ የአገሪቱ...

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...