Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ልናገርኢትዮጵያ አገራችን ሕገ መንግሥቷን ልትፈትሽ ይገባል?

  ኢትዮጵያ አገራችን ሕገ መንግሥቷን ልትፈትሽ ይገባል?

  ቀን:

  በሰይፈ ሥላሴ አያሌው (ዶ/ር)

  የኢትዮጵያ አገራችን ያለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት ታሪክ እንደሚያሳየን አገራችን የአፍርሶ መገንባት አገር ሆና ቆይታለች፡፡ በ1967 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት አካሂዶ መንበረ ሥልጣኑን የያዘው የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ከንጉሣዊ ሥርዓት ጋር የተያያዘን ነገር በሙሉ፣ ንጉሠ ነገሥቱን ማሰር፣ በኋላም መግደልን፣ እንዲሁም ሹማምንቱን መግደልን ጨምሮ ከሥር መሠረቱ ነቃቅሎ ጣለው፡፡ ሥርዓቱ በጥራዝ ነጠቅ ባወቀው የኮሙዩኒስት ርዕዮተ ዓለምና በራሱ በሣላት መሠረትም እንደ አዲስ አገሪቱን ይገነባት ጀመር፡፡ ይሁን እንጂ የደርግ መንግሥት ከሥር መሠረቱ ነቃቅሎ እንደ አዲስ ይገነባት ዘንድ የጀመራት ኢትዮጵያ ረጅም መንገድ አልተጓዘችም፡፡

  ከ17 ዓመታት የሥልጣን ቆይታ በኋላ ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) መራሹ ኢሕአዴግ በ1983 ዓ.ም. በጠመንጃ አፈሙዝ የደርግን ሥርዓት አስወግዶ ሥልጣን ሲይዝ፣ ከቀደመው ሥርዓት የወሰዳትን ኢትዮጵያ ከሥር መሠረቷ ነቃቅሎና እኔ ባሰብኩላት መንገድ ካልሆነ ኢትዮጵያ እንደ አገር አትፀናም፣ አትዘልቅምም በሚል እሳቤ በተመሳሳይ በራሱ ምናብ በሣላት ቁመናና መልክ ኢትዮጵያን እንደ አዲስ ይሠራት ዘንድ ሥልጣን ከተቆናጠጠበት ዕለት ጀምሮ በራሱ መንገድ ተግቷል፡፡

  የአገር ግንባታ እንደ ሕንፃ ግንባታ አንድን ጡብ በሌላው ላይ በማስቀመጥ ሊሆን የተገባ ቢሆንም፣ አገራችን ለዚህ ሳትታደል ቀርታ ይህ ትውልድ የሚያውቀው ታሪካችን የአፍርሶ መገንባት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሥርዓቶች የቀደመውን ሲያፈራርሱ በራሳቸው የመሰላቸውን ሲገነቡ ኖረውባታል፡፡ አገርም በዚህ መሰሉ የአፍርሶ መገንባት ሒደት የብዙዎች ውድ ልጆችዋን ደም ገብራለች፡፡ መተኪያ የሌላቸውን ሕይወቶች አጥታለች፡፡ ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት ሳይኖራት አባክናለች፡፡ በዚህ መሰሉ የመጠፋፋት ሥርዓት የኖረች አገር ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ አዲስ ምዕራፍ የጀመረች መሆኗ በገሃድ የታየ ነው፡፡ የሥርዓቱን ስህተት ለመመስከርና የተሠራውን ጥፋት ለማረም ሌላ አብዮት ሌላ የጠመንጃ አፈሙዝ ትግል ሳይሻ፣ የሕዝቡ እምቢ ባይነትና የአሻፈረኝ ስሜት የወለዳቸው የሥርዓቱ የራሱ በሆኑ አካላት ሥርዓቱ ራሱ ኮትኩቶ ያሳደጋቸው የሥርዓቱን ጥፋት ጭምር ሳይቀር በይፋ መናገር መጀመራቸው፣ ከዚያም አልፎ በተግባር እየታዩ ያሉ ሥራዎች፣ ከዚህ ቀደም በአገራችንም ሆነ በአኅጉራችን ባልተለመደ ሁኔታ ሥልጣን ለሌላ ማስረከብ መቻሉ ለኢትዮጵያ አገራችን የብሩህ ተስፋ ጎህ እንደፈነጠቀ በድፍረት መናገር ያስችላል፡፡

  በ2007 ዓ.ም. ምርጫ መቶ በመቶ የምክር ቤት መቀመጫዎችን የያዘው  ኢሕአዴግ የ2012 ዓ.ም. ምርጫን ፍትሐዊና በሁሉ ዘንድ ተዓማኒነት ያለው ለማድረግ ቆራጥ አቋም መያዙን፣ ይኼንንም በተደጋጋሚ ለሁሉም የተፎካካሪ ፓርቲዎች በበላይ አመራሩ አማካይነት ግልጽ ማድረጉ፣ ከሁሉ ይልቅ ደግሞ የጉዳዩ ባለቤት ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በግልጽ እየተናገረ መሆኑ ጀበእጅጉ የሚያስመሠግን ጅምር ነው፡፡ ይኼንንም ከመተግበር አኳያ የዴሞክራሲ ተቋማትን እንደ አዲስ ተዓማኒነት ባለው መንገድ ለማደራጀት እየተሠራ መሆኑ እሰየው የሚያስብል ዕርምጃ ሲሆን፣ በተደጋጋሚ ጊዜያት ከፍተኛ ትችትና ተቃውሞ ሲሰነዘርባቸው የነበሩ ሕጎችንም በመፈተሽ ማሻሻያ ለማድረግና እንዳስፈላጊነቱም ለመሻር የተጀመረው ጅምር ከሌሎች ጅምር፣ ጥረቶች ጋር ተዳምሮ ለአገራችን ኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡

  ከላይ የተጠቀሱት መልካም ጅምሮች እያሉ አገር የኋላዋን ትታ ወደፊት ለመጓዝ ጥረት በምታደርግበት በአሁኑ ወቅት፣ ኢትዮጵያ አገራችን ዛሬም በየቦታው የልጆቿ ደም ያላግባብ እየፈሰሰና መተኪያ የሌለው ሕይወታቸው እያለፈ ከሥቃይና መከራዋ ጋር አብራ እየኖረች ትገኛለች፡፡ አገሬ ዛሬም የሐዘን ማቋን አልገፈፈችም፡፡ የልጆቿ ሥቃይ ያዝ ለቀቅ እያደረገ አንድ ቀን የተሻለ ሲመስል በሌላኛው ቀን እያገረሸ የአገሬ ኢትዮጵያ ሥቃይ ዛሬም አብሯት አለ፡፡

  ዓለም በሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ፍልስፍና ወደ አንድ መንደርነት እየመጣች ባለችበት ጊዜ፣ የአገሬ ኢትዮጵያ ልጆች ዛሬም በቋንቋ ፖለቲካና ፖለቲካው በፈጠረው የማንነት ጥያቄ እርስ በርስ ይገፋፋሉ፡፡ ቋንቋ መግባቢያችን መሆኑ ቀርቶ የመለያያችን ብሎም የመጠፋፊያ ምክንያት ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ዛሬ እዚህም እዚያም የሚከሰቱ ግጭቶችንና ግድያዎችን ስንመለከት ምንም እንኳ ችግሩን የፈጠሩት ጥቅማቸው የተነካባቸውና በሠሩት ወንጀል አደጋ ያንዣበባቸው አካላት፣ የለውጡ ሒደት ያልተመቻቸው የቀድሞ ሹመኞች፣ በሕገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ የተሳሰሩ አካላት ብለን ለመናገር ብንሞክርም፣ ለግጭቶቹ ሽፋንና መንስዔ ሆኖ እያገለገለ ያለው በቋንቋ ላይ የተመሠረተውና ባለፈው ሩብ ምዕተ ዓመት ተግተን የገነባነው ሥርዓታችን መሆኑን ለመሸፋፈን ጥረት ብናደርግ፣ ፈጥጦ የተቀመጠውን እውነታ ሊለውጠው አይችልም፡፡

  ሰሞኑን የፀደቀበትን ቀን እያከበርን የነበረው ሕገ መንግሥትና በሕገ መንግሥቱ መሠረት ላይ የፀናውን የፌዴራል ሥርዓት ተከትሎ፣ በማንነት ጥያቄ ሽፋን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ሕይወቱን ያጣበት፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አምራች ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው ለተመፅዋችነትና በዕርዳታ ጠባቂነት የተዳረጉበት ሁኔታ መፈጠሩ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ቋንቋ ላይ የተመሠረተው የማንነት ጥያቄ ከዜጎች ሕይወት መጥፋትና መፈናቀል ባሻገር፣ የፌዴራል መንግሥቱን በሚመሠርቱ ክልሎች መካከል በበጎ አለመተያየትን እንዳስከተለ አለመናገር መሬት ላይ ያለውን እውነታ ሊደብቅ አይችልም፣ ወይም ደግሞ የሌለ አያደርገውም፡፡

  አገራችን ለመጪው 2012 ዓ.ም. ምርጫ መዘጋጀት በምትጀምርበት በአሁኑ ወቅት አስቀድሞ ሕገ መንግሥቱ ሊፈተሽ ይገባል የሚሉ ሐሳቦች እዚህም እዚያም ይንፀባረቃሉ፡፡ በሌላ ወገን ለውጡን በግንባር ቀደምነት የመዘወር ኃላፊነት የወደቀባቸው ጠቅላይ ሚኒስትራችን በአሁኑ ወቅት ሕገ መንግሥቱን መፈተሽና ማሻሻያ ለማድረግ መጣር፣ ኢሕአዴግ ሙሉ በሙሉ ወንበሩን በተቆጣጠረበት ምክር ቤት በተፎካካሪዎችም ዘንድ ተዓማኒነት እንደሚያሳጣ በመግለጽ፣ ሕገ መንግሥቱን የመፈተሽና አስፈላጊም ከሆነ ማሻሻያ ማድረግ ከምርጫ በኋላ በአሸናፊው ፓርቲ ሊደረግ እንደሚገባ ጠቆም አድርገው፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጥያቄውን ገፋ አድርገውታል፡፡

  በአብዛኛው ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትና ከበሬታ ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ይህን በቅንነት ማለታቸው እጅግ መልካም ነው፡፡ አልፎም ደግሞ የአገሮች መሪዎች የሥልጣን ቆይታቸውን በሰበብ አስባቡ ለማራዘም ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ በተደጋጋሚ ሲያደርጉ በሚስተዋልባት አኅጉራችን፣ የምርጫው ጊዜ ሊጠበቅ ይገባል ብለው መሞገታቸው ለእርሳቸውና ለመንግሥታቸው ያለንን ከበሬታ ይጨምራል፡፡ ለሌሎች አገሮችም መልካም አርዓያ በመሆን በአኅጉራችን አፍሪካ የፖለቲካ ሥርዓት ላይም የራሱ የሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ ጥርጥር የለውም፡፡

  ይህ በዚህ እንዳለ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የአገራችን ችግሮች ሙሉ በሙሉም ባይሆን፣ በመሠረታዊነት በሕገ መንግሥታችን ውስጥ እንደሆነና ለእነዚህ ችግሮች ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ መፍትሔ ባልተሰጠበት ሁኔታ ምን ተግተን ብንሠራ የምናደርገው የወደፊት ጉዞ ወደምንፈልግበት ማማ ሊያወጣን መቻሉን እጠራጠራለሁ፡፡ ሕገ መንግሥታችን በሚረቀቅበት ጊዜ ከሁለት ዓይነት መንገድ አንዱን እንደተከተለ አምናለሁ፡፡ አንደኛው በመሠሪነት ላይ ተመሥርቶ አገርን ለመከፋፈልና ለመበታተን ሊሆን እንደሚችል ሲሆን፣ ሁለተኛው አገርን ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በቅን ልቦና እንደተሠራ ነው፡፡ ሰው ሆኜ ስፈጠር ለበጎ ነገር የተፈጠርኩ እንደመሆኔ በመሰሪ አስተሳሰብ እንደተጻፈ ላስብ አልፈቅድም፡፡ ይልቁንም በቅን ልቦና ላይ ተመሥርቶና ታስቦ እንደተረቀቀና እንደፀደቀ ላስብ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀ ሩብ ምዕተ ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን፣ በዚህ ሩብ ምዕተ ዓመት አገራችን ከፍተኛ የችግርና የሰቆቃ ዓመታትን አሳልፋለች፡፡ ካለፈችባቸው ችግሮች በመነሳት ሕገ መንግሥቱን እንደገና እንድትፈትሽና የችግሮቹ ምንጭ በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሆኑን ካረጋገጠች፣ ማስተካከያ ለማድረግ በቂ ጊዜ አስቆጥራለች፡፡ የምንናገረው ሕገ መንግሥት ሕገ ምድራዊ መንግሥት እንጂ፣ ሕገ ሰማያዊ መንግሥት ወይም ሕገ እግዚአብሔር አይደለም፡፡ ይህም ደግሞ በተስማማንበት እንዳስፈላጊነቱ ማሻሻያ ለማድረግ ዕድል ይፈጥራል፡፡ የሌሎች አገሮች ልምድም ይኼንኑ ያሳየናል፡፡

  ቋንቋ ላይ የተመሠረተው የፌዴራል ሥርዓታችንን ተከትሎ ያሳለፍናቸው ችግሮችና ከላይ የጠቀስኳቸው ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው፣ ዛሬ የምናስተውለውና እዚህም እዚያም ተነስተው መቋጫ ያልተበጀላቸው የማንነት ጥያቄዎች፣ የክልል መሆን ይገባኛል ሕጋዊ የሆነ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ዛሬ በተነሱት ጥያቄዎች ብቻ የማይቋጭና በምንናገራቸው ቋንቋዎች ልክ ከ80 በላይ ክልሎች ላለመመሥረት ምንም ዓይነት ከልካይ ነገር እንደማይኖር ከወዲሁ መናገር አያዳግትም፡፡ ምክንያቱም በየትኛውም መሥፈርት አንደኛው ቋንቋ ከሌላኛው አይበልጥም፣ የቋንቋው ተናጋሪም እንደዚሁ፡፡ ችግሩ ሰማንያ ክልሎች መፍጠሩ ላይ ሳይሆን፣ ለክልሎቹ በአግባቡ የተሰመረ ድንበር ይኖራል ማለት አልችልም፡፡ በአንድ ወቅት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንዳሉት የአሰተዳደር ወሰን መፍጠር አለመቻሉ ይሆናል፡፡ ይህን ተከትሎ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ወደፊትም ኢትዮጵያዊ በዜግነቱ በአገሩ ኢትዮጵያ ወሰን ከምሥራቅ ጫፍ፣ እስከ ምዕራብ ጫፍ ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ጫፍ እንደ ልቡ የሚንቀሳቀስበት፣ የሚኖርበትና ሀብት የሚያፈራበት መሆኑ ቀርቶ “የእኔ አገርና የእኔ ግዛት” የሚል እሳቤ ሥር እየሰደደ የዜጎችን እንቅስቃሴና መብት ከመገደብና በምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ ዘገምተኝነትን ከማስከተል አልፎ፣ በዚህ ሽፋን ሊፈስ የሚችለውን ደምና ሊያልፍ የሚችለውን ሕይወት ለመገመት ነቢይ መሆን አያሻም፡፡

  በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥታችን በብዙ ምክንያት ሊፈተሽ እንደ ዜጋ፣ ሲሆን ሁላችንም ካልተቻለም አብዛኛው ሕዝብ በጋራ የተስማማባቸውን ጉዳዮችን ሊይዝ እንደሚገባው አምናለሁ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ዋና ዋናዎቹን ለመመልከት ከመቅድሙ (Preamble) ጀምሮ ሕገ መንግሥቱ የእኛ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች? ወይስ የእኛ የኢትዮጵያውያን? የመንግሥት አወቃቀር ፌዴራላዊ? ወይስ አሃዳዊ መሆን አለበት? የፌዴራል የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓት ከተከተልን የፌዴራል ሥርዓቱ በቋንቋ ላይ የተመሠረተ? ወይስ እያንዳንዱ ዜጋ በቋንቋው የመማር፣ የመዳኘት፣ ባህሉንና ወጉን የማጎልበት መብቱ የተጠበቀ ሆኖ የተሻለ አገልግሎት አሰጣጥን ዕውን ለማድረግ በሚያስችል በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ላይ መመሥረት አለበት? ሰንደቅ ዓላማችን ዓርማ ይኑረው? ወይስ አይኑረው? በሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ እንደሰፈረው ሕገ መንግሥታችን የብሔር ብሔረሰቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል (ከሩሲያ የጥቅምት ሶሻሊስት አብዮት የተኮረጀ) ያለገደብ የጠበቀ? ወይስ በቅርቡ እንደታዘብነውና የፌዴሬሽኑን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲያጋጥም  ፌዴሬሽኑን ከአደጋ ለመታደግ እንደ ስፓኝ (Spain) ሕገ መንግሥት አንቀጽ 155 ዓይነት አንቀጽ ያካተተ መሆን ይገባዋል? የመሬት ባለቤትነት የማን ሊሆን ይገባል? የመንግሥት ሥርዓቱ የወራት ትውስታችን እንደሚያመላክተው ካቢኔያቸውን ለመመሥረት በውስጥ ለውስጥ መጓተት ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሲቸገሩበት እንደነበረው ፓርላሜንታዊ ሥርዓት ሆኖ ሊቀጥል ይገባል? ወይስ የአገሪቱ ዜጎች በአብላጫ ድምፅ በሚመርጡት ፕሬዚዳንት የሚመራ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ሊሆን ይገባል? የሚሉና ሌሎችም በሕገ መንግሥታችን የተደነገጉና ሕዝባችን በአግባቡ ተወያይቶባቸው እልባት ሊያገኙ የሚገባቸው አንኳር ጥያቄዎችን መመለስ ለቀጣይ የአገራችን ኢትዮጵያ የሰመረ ጉዞ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡

  የትኛውም መንግሥት ከሁሉም ወገን መቶ በመቶ ድጋፍ አግኝቶ ይመራል ማለት ሕልመኛ መሆንን የሚያመላክት ሲሆን፣ ዛሬ በአገራችን ኢትዮጵያ ያለው አመራር ከሞላ ጎደል በብዙኃኑ የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ዘንድ ተቀባይነቱ አገራችን ዓይታው የማታውቀው ከፍተኛ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ቅቡል የሆነ አመራር ደግሞ እንደ ሕገ መንግሥት ዓይነት መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን ለመፈተሽ ኃይል ስለሚሰጠው ሕገ መንግሥታችን ጊዜ ሳይሰጠው ሊታይ፣ ሊፈተሽ፣ እንደ ዜጎች ፍላጎትም ማሻሻያ ሊደረግበት ይገባል፡፡

  አገራችን ኢትዮጵያ ሁሌም በማፍረስ መንግሥት ነገ መጥቶ ሕገ መንግሥቱን ገንቢ መሆን የለባትም፡፡ በምርጫ የሚያሸንፍ ወደ ጎን አስቀምጦ ሌላ ሕገ መንግሥት እንዲጽፍልን የተገባ አይሆንም፡፡ ሕገ መንግሥት እንዳለን አምነን ተቀብለን ሕገ መንግሥታችንን ግን ካጋጠሙን ተግዳሮቶችና ችግሮች አኳያና ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ተገቢውን ማሻሻያ ልናደርግና የአፍርሶ ግንባታ ሥራችን ላይ መቋጫ በማድረግ ወደፊት ልንጓዝ ይገባል፡፡ ይህን ለማድረግ ቀደም ሲል የጠቀስኩት የወቅቱ  የአገራችን አመራር ቅቡልነት እንዳለ ሆኖ፣ ሕገ መንግሥቱን ያረቀቀውና ያፀደቀው ይኸው በሥልጣን ላይ ያለው ገዥ ፓርቲ መሆኑ ደግሞ የሕገ መንግሥት ማሻሻያውን ለማድረግ የበለጠ የተመቻቸ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡    

  በሕገ መንግሥታችን ስለሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሐሳብ በሚጠቅሰው አንቀጽ 104 ከሰፈረው በስተቀር፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሐሳብ በማን ሊቀርብ እንደሚችል የሕግ ዕውቀቴ ውስን ሆኖ ካልገደበኝ በስተቀር የታየኝ ነገር የለም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ግን የእኔ የኢትዮጵያዊው ዜጋ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የእኔ ሕገ መንግሥት ከሆነ ደግሞ እንዲፈተሽና በዘመናት ውስጥ ሊዘልቅ እንዲችል ተሻሽሎ እንዲበጅ እንደ ዜጋ የመጠየቅ መብት አለኝ፡፡ ይህ ጽሑፍ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ እንዲደረግ በፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይሆን በአንድ ኢትዮጵያዊ የቀረበ ጽሑፍ ሲሆን፣ ፊርማ በማሰባሰብ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ መጠየቅ የሚቻል ከሆነ የመጀመርያው እንደዚህ ያለ ፊርማ ሆኖ ሊወሰድ ይችላል፡፡

  ሕገ መንግሥታችንን ጊዜ ሳንሰጠው ልንፈትሸው ይገባል፡፡ ችግር መኖሩን እያወቅን ችግሩን ለቀጣይ ጊዜ ማቆየት የመግፋት ያህል ሲሆን፣ ምናልባትም አንድ ቀን በወቅቱ እልባት አለመስጠታችን ልንፀፀትበት የምንችልበትን ነገር እንደሚፈጥርም በማሰብ ሕገ መንግሥታችንን ነገ ሳይሆን ዛሬ፣ መፈተሽና እንዳስፈላጊነቱ ማሻሻያ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

  እግዚአብሔር ኢትዮጵያ አገራችንንና ሕዝቧን ይባርክ!

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል seifesa@yahoo.com አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

   

   

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...