በፀጋዬ ደግነህ (ዶ/ር)
ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያ ዜግነት
ባለንበት ዘመን አንድ ስም ትልቅ ትርጉም አለው። ሰው ምርትን ብቻ ሳይሆን የምርቱን ስምና (ብራንድ) የአገበያየት ደስታንም አብሮ ይሸምታል። እንደ ጥንታውያን ግሪክ፣ ግብፅ፣ ጣሊያንና ቻይናም ሁሉ የእኛ አገር ሉሲ ኢትዮጵያ ስምም ሌሎች ያላገኙት ትልቅ ብራንድ ነው። ኢትዮጵያዊነት ማለትም የአኗኗር መገለጫ ፍልስፍናም ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሚለው ስምም ለአገር ከሚሰጠው ትርጉም በላይም ነው። ኢትዮጵያዊነትን ለማግኘት ሲባል ባህር አቋርጠው የሚፈልሱባት ምድር ነች። ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔረሰቦችን የያዘች፣ የተለያዩ አኩሪ ባህሎችና ድንቅ ቋንቋዎች ያላችው፣ ተቀራራቢ የአኗናር፣ የአመጋገብ፣ የኑሮ ደረጃና ፈሊጥ ያላቸው ዜጎች በጋራ የሚኖሩባትና በጋራ የሚገነቧት አገር ነች። ኢትዮጵያ የሚለው ቃል የብዙ ሺሕ ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠረ፣ ከእንግሊዝ፣ ከጀርመን፣ ከአሜሪካ፣ ከሩሲያ፣ ከስፔን፣ ከቱርክ፣ ከናይጄሪያ፣ ከብራዚል፣ ወዘተ በፊት እስከነ ሥልጣኔው ይኖር የነበረ ሕዝብ መጠሪያ ነው፡፡ በዚህ ስም የሚጠሩ ሰዎች ተመሳሳይ መልክና ገጽ ያላቸው ከመሆናቸውም በላይ፣ ከየትኛውም ብሔረሰብ ወይም የአገሪቱ አካባቢ ቢመጡ እንኳን በመተያየት ብቻ የሚተዋወቁ የደም ዘመዳሞች ናቸው። ለምሳሌ ጥቁር አሜሪካውያን የፈለጉትን ያህል አሜሪካውያን ቢሆኑም፣ አፍሪካ አሜሪካውያን በመባል ከአፍሪካ መምጣታቸው የማይካደውም ከዚህ ጋር በተመሳሰለ ምክንያት ነው። ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ተለይተው መኖር የሚከብዳችው፣ ቢቻላቸው ኢትዮጵያን በሚኖሩበት አገር አስመጥተው መኖር የሚፈልጉ ናቸው። የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በንግግራቸው እንዳሉትም ኢትዮጵያዊነት ሱስ ሆኖ የማይለቃቸው፣ ሲኖሩ በሁለንተናዊው ኢትዮጵያ ሆነው፣ ሲሞቱም ኢትዮጵያ የሚሆኑት እጅግ ብዙ ናቸው። የውጭ ዜግነትን የያዘ ሲሞት እንኳን ‹‹የኢትዮጵያ ዜግነቱን እንደተወ ይቆጠራል›› ወደተባለበት ኢትዮጵያ ሄዶ የኢትዮጵያ አፈር ይሆናል። ታዲያ እንዴት ነው አንድን ሰው የሌላ አገር ዜግነት በተጨማሪ በማግኘቱ ኢትዮጵያዊ አይደለህም የሚባለው?
በኢትዮጵያዊነትና በኢትዮጵያ ዜግነት መካከል ልዩነት መኖሩን መገንዘብ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያዊነት ከዜግነት፣ በኢትዮጵያ ከመኖር ወይም ፓስፖርት ከመያዝ ጋር አንድ አይደለም። ከዚያ በላይ ነውና። መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ‹‹ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ መልኩን ሊቀይር አይችልም›› እንደሚለው፣ ይህም ለረዥም ዓመታት በትውልድ (በደም ሕግ) ሲዋረስ የመጣና ለግለሰቡም ማንነት (Identity) መገለጫ ስለሆነም ነው። ኢትዮጵያ የሚለው ስም በቅዱስ ቁርዓን የተጠቀሰና በሆሜር የተነገረ ነው። የታሪክ ተመራማሪዎች እዚህ ላይ ብዙ የተሻለ ነገር ሊሉ የሚችሉ ይመስለኛል። ኢትዮጵያዊነት የአንድ ግለሰብ ማንነት መገለጫ ማለትም ባህሉን፣ ታሪኩን፣ ቋንቋውን፣ አስተሳሰቡን፣ ወዘተ ተደርጎም ሊወሰድ ሲችል፣ የኢትዮጵያ ዜግነት ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ዜግነትን ለወሰዱ ሰዎች፣ የኢትዮጵያዊ ዜግነትን ይዘው በውጭ ለሚኖሩ መብታቸውን የሚጠብቅ፣ ግዴታቸውን የሚያስቀምጥ፣ ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ ውጭ ያሉትንም ዜጎቼ የሚላቸውን ሁሉ በሕገ መንግሥቱ ጥላ ሥር የሚጠብቃቸው መሆኑን የሚገልጽ ነው። ዜግነት በአጠቃላይ ከአንድ መንግሥትና ሕዝብ ጋር የመብትና ግዴታ ውል አድርጎም ማየት ይቻላል። ቅድመ አያቶቻችን እኮ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ ያስፈልጋችኋል ወይም ዜጋ ናችሁ ተብለው አይደለም ኢትዮጵያዊ የሆኑት (በጊዜው ይህ አሠራር ባይኖርም እንኳን)፣ ኢትዮጵያንም በደማቸው ጠብቀው ያስተላለፉት። የእነሱ ልጅ ልጆች የሌላ አገር ተጨማሪ ዜግነት በመውሰዳቸው ‹‹የኢትዮጵያ ዜግነታቸውን እንደተው ይቆጠራል›› መባሉ ሳይበቃ፣ ኢትዮጵያዊ አይደሉም የሚለው በብዛት የሚሰማ አስተሳሰብ ግን ትክክል አይደለም።
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ስድስት ‹‹ወላጆቹ/ወላጆቿ ወይም ከወላጆቹ/ከወላጆቿ አንደኛው ኢትዮጵያዊ የሆነ/የሆነች የኢትዮጵያ ዜጋ ነው/ናት›› ይላል። ይኸው ነው። ስለኢትዮጵያ ዜግነት በ2003 ዓ.ም. የወጣው አዋጅም ስለ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› ሳይሆን ስለኢትዮጵያ ዜግነት ነው የሚደነግገው። የሌላ አገር ዜግነትን በማግኘት የኢትዮጵያ ዜግነት የሚቀርበትንም በአንቀጽ 19 ሲደነግግ፣ ዜግነቱን ለመተው መፈለጉን በማሳወቅ የዜግነት መልቀቂያ ምስክር ወረቀት ይሰጠዋል ሲል፣ በአንቀጽ 20 ደግሞ በራሱ ፍላጎት የሌላ አገር ዜግነት ካገኘ ዜግነቱን በራሱ ፈቃድ እንደተወ ይቆጠራል ይላል። እነዚህ አንቀጾች ብዙ ሊያከራክሩ የሚችሉ ናችው።
ትውልደ ኢትዮጵያዊ
ትውልደ ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን ሙሉ የሚሆን መጠሪያ ነው። የሌላ አገር ዜግነት ለወሰዱ ብቻ መሆን የለበትም። የትውልደ ኢትዮጵያ መታወቂያ አዋጅ (270/2002) በጣም ጥሩ ጅምር ነው። ጥሩ ተምሳሌት ነው። ቢሆንም በብዙ አገሮች እንደሚታየው የጥምር ዜግነትን መፍቀድ ብዙ ጥቅም አለው። በጀርመን ቋሚ የመቆያ ፈቃድ ያለው የውጭ አገር ዜጋ ልክ ኢትዮጵያ ውስጥ የትውልደ ኢትዮጵያ መታወቂያ የሚሰጠውን ያህል መብት አለው። በዚህ ‹‹የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ ዜጎችን በትውልድ አገራቸው የተለያዩ መብቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ›› በወጣው አዋጅ መሠረት፣ አንድ የተወላጅነት መታወቂያ ያለውን ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሚኒስትር፣ ጳጳስ፣ የባንክ ገዥ፣ ቃል አቀባይ ወይም ሕግ አስከባሪ መሆን አይችልም ብሎ አላስቀመጠም። ገደቡም በብሔራዊ ምርጫ መምረጥንና መመረጥን፣ በደኅንነት፣ በመከላከያ፣ በውጭ ጉዳይና በመሳሰሉት ላይ ነው። በተቃራኒው ካየነውም አንድ ትውልደ ኢትዮጵያዊ በመደበኛነት እስካልሆነ ድረስ በማናቸውም የአገር መከላከያ፣ የአገር ደኅንነት ወይም በውጭ ጉዳይና መሰል የፖለቲካ የመንግሥት መሥሪያ ቤት መሥራት ይችላል ማለት ነው (አንቀጽ 6)። እዚህ ላይ በብዙ መመርያዎችና መተዳደርያ ደንቦች ላይ ኢትዮጵያዊ ብቻ የሚለውን ከወሰድን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም ያጠቃልላል ማለት ነው። ይኼንን የማይቀበሉ ሕጎች፣ ደንቦች፣ መመርያዎች፣ ውሳኔዎች ወይም አሠራሮች ተፈጻሚነት እንደማይኖራቸውና ለአዋጁ ተግባራዊነት የመተባበር ግዴታን ይህ አዋጅ ይደነግጋል (አንቀጽ 15-16)።
ችግሩ ይህን አዋጅ ለማስፈጸም የሚወጣው መመርያ ነው። የትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ የባንክ አክሲዮን ላይ ችግርን ሊፈታ አልቻለም ነበር፡፡ በየአምስት ዓመቱ መታደስ እንዳለበት የሚገልጽ፣ ሲታደስም አዲስ የወጣበትን ዋጋ መልሶ የሚያስከፍል፣ የማሳደሻው ጊዜው ካለፈ በየቀኑ የማሳደሻ ክፍያ በፐርሰንት የሚጨምር፣ በውጭ ለሚኖሩ ለማሳደስ ወራትን መጠበቅ የሚያስፈልግ ነው። በአዋጁ አንቀጽ 14 ይኼንን የመታወቂያ ካርድ ስለሚሰረዝበትም ሁኔታዎች ይደነግጋል።
የጥምር ዜግነት አስፈላጊነት
ጥምር ዜግነት ማለት ጥምር መብትም፣ ጥምር ግዴታ ወይም ኃላፊነትም ነው። አንድ ኢትዮጵያዊ ከኢትዮጵያ ወጥቶ በሌላ አገር ሲኖር በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ በሕይወቱ ላይ የሚፈጠርበትን ጫና ለማቃለል፣ በሚኖርበት አገር መብቱን ለማስከበር፣ ግዴታውን ከአገሩ ነዋሪዎች እኩል ለመወጣት የሚያስችለው፣ በተለይም የሚኖርበት አገር ለዜግነት የሚጠይቃቸውን መስፈርቶችን ሲያሟላ የሚኖርበትን አገር ዜግነትን ይወስዳል። በአብዛኛው አገሮች ይኼንንም ለማሟላት በወንጀል ተከሶ ያልተፈረደበት፣ የሚኖርበትን አገር ቋንቋ የሚናገር፣ ቋሚ ሥራ ወይም ንብረት ያፈራ፣ የሚኖርበትን አገር የሚያውቅ መሆኑንና መልካም ሰው መሆኑንም ታይቶ ነው። አንድ ኢትዮጵያዊ ይኼንን አሟልቶ የሌላውን አገር ዜግነት ሲወስድ የሚኖርበት አገር ጥምር ዜግነትን የማይፈቅድ ከሆነ፣ የኢትዮጵያ ዜግነቱን እንዲተወው ይጠይቃል። ወይም ለመልቀቁ ማስረጃ ያቀርባል። ሌሎች አገሮች ጥምር ዜግነት እንዳለው ወይም መልሶ የመጀመርያ ዜግነቱን ቢይዝ አዲሱ (ሁለተኛው) ዜግነት የማይሰረዝ ለመሆኑ ሰርተፊኬት ይሰጠዋል። ሌሎች አገሮች ደግሞ ምንም አይጠይቁም። በተቃራኒው አንድ ኢትዮጵያዊ የሌላ አገር ዜግነትን ከወሰደ የኢትዮጵያ ዜግነቱን እንደተወ እንደሚቆጠርና ይህንን አስመልክቶ የዜግነት መልቀቂያ ሰርተፊኬት እንደሚሰጠው በኢትዮጵያ ሕግ በአዋጅ ተደንግጓል። በእርግጥ ይህ አዋጅ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ግልጽ የማይሆንበትና የአተረጓጎምና የአሠራር ክፍተት የሚታይበት ነው። ጥምር ዜግነት ክልክል ነው የሚል የለም። ዕድሜያቸው ለአቅመ አዳም ያልደረሰውን በተዘዋዋሪም ጥምር ዜግነትን አይገድብም (አንቀጽ 20 ቁጥር 2)።
የጥምር ወይም ጥምር ዜግነት እሳቤዎች ላይ የተዛቡ አስተያየቶች በአተገባበር ደረጃ ይታያሉ። አንድ ጥምር ዜግነት ያለው ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ሲኖር ሁለት ዜግነት ይኖረዋል፣ ወይም ሁለት ፓስፖርት ይኖረዋል ማለት አይደለም። አንድ የአሜሪካ ወይም የእንግሊዝ ተጨማሪ ዜግነት ያለው ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ሲያሻው የኢትዮጵያ ዜግነቱን፣ ሲከፋው የአሜሪካ ወይም የእንግሊዝ ፓስፖርትን ይጠቀማል፡፡ ኢትዮጵያ ያለው የውጭ አገር ኤምባሲ ይሄዳል ማለት አይደለም። የጥምር ዜግነት ተፈቅዶ ወደ ኢትዮጵያ የተጨማሪ ዜግነት መግለጫ የሆነን የመጓጓዣ ሰነድ (ፓስፖርት) ይዞ የሚመጣ ሰው፣ ልክ የኢትዮጵያን መሬት ሲረግጥ የሌላኛው ዜግነት አይሠራም። እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነው የሚሆነው። ችግር ደርሶብኛል ብሎ ወደ ሌላኛው አገር ኤምባሲ ቢሄድ አቤቱታው ተቀባይነት የለውም። ወይም ከዚህ አገር አውጡኝ ማለት አይችልም። ይህ ማለት በአንድ ጊዜ አንድ ዜግነት ብቻ ነው መጠቀም የሚቻለው፡፡ ይህ አሠራር ጀርመንን ጨምሮ በብዙ አገሮች የተለመደ ሲሆን፣ ማኅበራዊ አድሎዎችን ‹‹ሶሻል ዲስ ባላንስን›› ማስተካከያም ነው። ኢትዮጵያን ለቆ ሲሄድ ግን በፈለገበት አገር ዜግነት ይጠቀማል።
የሁለተኛ ዜግነት የሚጠቀመው ሁለተኛ ዜግነት በወሰደበት አገር ላይ ወይም የኢትዮጵያ ዜግነቱ ከሁለተኛ ዜግነቱ በአብላጫ ሊረዳው የማይችልበት ሦስተኛ አገር ላይ ይሆናል። ለምሳሌ አንድ ፈረንሣይ የሚኖርና ወደ ሌላ አገር ለሥራ የሚመላለስ ሰው የፈረንሣይ ፓስፖርቱ ለብዙ አገሮች ቪዛ ስለማያስፈልገው፣ ብዙ ቦታ በሥራ ምክንያት ያለ ችግር ይሄዳል። በኢትዮጵያ ፓስፖርት ግን ለምሳሌ ከአንዱ አውሮፓ አገር ወደ እንግሊዝ ልሂድ ቢል ቪዛ ለማግኘት ሦስት ሳምንት ሊፈጅበት ይችላል፡፡ ፓስፖርቱ በእንግሊዝ ኢምግሬሽን (ቦርደር ኤጀንሲ) ጋር ስለሚቆይ በመሀልም ወደ ሌላ አገር ሊሄድም አይችልም። ወደ ዜግነት አጠቃቀም ስንሄድ እንደተጠቀሰው ብዙ አገሮች የአገራቸውን ፓስፖርት ይዞ ለመጣ ሰው እግሩ አገራቸው ላይ ሲረግጥና ወዲያውኑ የዚሁ አገር ዜግነቱ ሥራ ላይ ሲጀምር፣ ሁለተኛው ዜግነት ደግሞ ከአገሩ እስከሚወጣበት ጊዜ ድረስ ያቆማል። በአርጀንቲና ለምሳሌ ወዲያውኑ ሳይሆን ከዘጠና ቀናት በላይ ከቆየ የአርጀንቲና ዜግነቱ ብቻ ነው የሚያገለግለው።
እንደ አርሜንያ ያሉ አገሮች ዜግነታቸው የማይለቀቅ መሆኑን በማስቀመጥ አንድ ሰው የሌላ አገር ፓስፖርት ስለያዘ ብቻ ዜግነቱን ያጣል የሚሉትን አይቀበሉም። ይህም በብዛት የሚታወቀው “Jus Sanguins” (Right Of Blood) የሚለው ሲሆን፣ አንድ የዚህ አገር ትውልድ ያለው መቼውንም ዜግነቱን አያጣም። እዚህ ላይ ቤተ እስራኤሎችን፣ ሩሲያዊያን፣ ጀርመኖች፣ ጣሊያኖችን፣ ወዘተ መውሰድ ይቻላል። በሌላ በኩል ሌሎች አገሮች ወደ ውጭ የሚሄዱ ዜጎቻቸውን የሄዱበትን አገር ዜግነት በተጨማሪ እንዲወስዱ ያበረታታሉ። ምክንያቱም የእነሱ ተወላጆች በሄዱበት አገር ተፅዕኖ እንዲፈጥሩና የእነሱን አገር ጥቅም እንዲያስጠብቁላቸውም ነው።
በተጨማሪም እንደ ጀርመን ያሉ አገሮች ዜግነትን እዚያ አገር ውስጥ ለተወለደ ይሰጣሉ። ይህም ዜግነትን በቦታው በመወለድ “Jus Soli” (Right Of Soil) ነው። 60 በመቶ የሚሆነው የስዊዘርላንድ ዜጋ ከስዊዘርላንድ ውጪ ይኖራል። ይህም የጥምር ዜግነትን ለዜግነት መሠረታቸው እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል። አውሮፓ ውስጥ የጥምር ዜግነት በአብዛኛው በተለይም ከአውሮፓ ኅብረት ለመጡት ይሰጣል። ጀርመን ለአውሮፓ ኅብረት ዜጎች ሁለቱንም ዜግነት ለመያዝ ይፈቅዳል። ከአውሮፓ ኅብረት ውጪ ለመጣ ሰው የጀርመንን ዜግነትን ከሚያገኝ ይልቅ የጀርመን ዜጋ ሆኖ የእነዚህን አገሮች ዜግነት ቢጠይቅ ይቀላል። ከአውሮፓ ኅብረት ውጪ ላሉ አገሮች ለወጣቶች ደግሞ የመምረጥ ሞዴል ሲኖር፣ የጀርመን ዜግነትን ብቻ ይዘው የሌላ የጥምር ዜግነት የሚፈቅድን አገር ዜግነት ለመውሰድ ለሚያመለክቱ የጀርመኑ እንዳይሰርዝባችው የዜግነት ማቆያ ሰርተፊኬትን ምክንያታቸውን አቅርበው ያገኛሉ። ዜግነትን የማይለቁ አገሮች ዜጎች ለምሳሌ እንደ አፍጋኒስታን ያሉ የጀርመንን ዜግነት ደርበው መያዝ ይችላሉ።
ጥምር ዜግነት ከ1990ዎቹ ጀምሮ እየተበራከተ በተለይም ባለፉት 15 ዓመታት በተለያዩ የዓለማችን ክፍል በፍጥነት እየተስፋፋ የመጣ፣ ብዝኃነት ባላቸው በተለይም አምባገነን ባልሆኑ አገሮች የሚተገበር፣ የሕገ መንግሥትና ሕግ መሻሻል የተከሰተበት፣ የዜግነት ጉዳይ ቦርዶችንና ካውንስል በመፈጠር እየተስፋፋ ይገኛል። በተለይም ብዙ ዜጎቻቸው ከትውልድ አገራቸው የሚፈልሱባቸው አገሮች መልካም መፍትሔና ዘመናዊ የዜግነት ማሻሻልን እያደረጉ ይገኛሉ። ከላይ እንደተጠቀሰው ለአንድ ሰው ከቁሳዊ ጥቅሞች በላይ መንፈሳዊ እርካታው ከፍተኛ ነው። በትውልድ ወይም በደም ያገኘውን ዜግነቱን ተገፈሃል ሲባል ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ነው። በተለይም በሄደበት አገር ለፍቶ፣ ጥሮ፣ መከራን ችሎ፣ ፈተናን አሸንፎ ያገኘውና በሚኖርበት አገር እኩል የሚያደርገውን የሌላ አገር የዜግነት መብት፣ ለኢትዮጵያ ግን ከኢትዮጵያ ዜግነቱ የሚያስነሳው ወይም እንደ ቅጣት ሆኖ የትውልድ ወይም የደም ዜግነቱን ማሳጣቱ ጥሩ አይደለም። ጥምር ዜግነትን እንደ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት መመልከትም ተገቢ ነው።
ይህ ዕድል ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እኩል ነው። የፈለገ፣ በተለያየ መንገድ መውጣት የቻለና ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቶ የሌላ አገር ዜግነት የወሰደ ኢትዮጵያዊ በሚኖርበት አገር፣ በተለይም በቴክኖሎጂና በኢኮኖሚ ከኢትዮጵያ በአንፃራዊነት የተሻለ ከሆነ በውጭ አገር ዜግነቱና መብቱ በመጠቀም የሚያገኘውን እሴት ወደ ኢትዮጵያ ለማሸጋገር ይቀለዋል። ለምሳሌ አንድ ውጭ የተወለደ፣ ያደገና የዚህ አገር ዜግነት ያለው ስፖርተኛ በተለይም በእግር ኳስ፣ በቦክስ፣ በውኃ ዋና፣ በክረምት ስፖርትና በመሳሰሉት የኢትዮጵያ ዜግነቱ ካለው በፕሮፌሽናል ውድድርም ሆነ ኢትዮጵያን ወክሎ በዓለም አቀፍ መድረኮች ሊሳተፍና ኢትዮጵያን ሊያኮራ ይችላል። ኢትዮጵያም ውስጥ ስፖርቱን ሊያስፋፋ ይቻላል። የሌላ ዜግነትን ወስጄ ይኼንን አገር እወክላለሁ ለሚሉትም የዓለም አቀፍ የውድድር መስፈርቶች እንደተጠበቁ ሆኖ፣ ኢትዮጵያን ሊያስወክልም ይችላል። ውጭ ያፈራውን ሀብትም ያለ ሥጋት ለመጠቀም ያስችላል።
ጥምር ዜግነት የያዙ በፖለቲካ መሳተፋቸው ችግሩ አይታየኝም። ለኢትዮጵያ ዕድገት ብዙ ለሚዳክረው፣ አገሩንና ዘመዱን የሚረዳው፣ ራሱን ዝቅ አድርጎ ያጠራቀመውን ሀብት ኢትዮጵያ ላይ የሚያፈስ፣ ኢትዮጵያ ትጠራሃለች ሲሉት አቤት የሚለው፣ አንድ ዶላር በቀን ለማበርከት ለተዘጋጀው በአብዛኛው የውጭ አገር ዜግነትን የያዘውን ኢትዮጵያዊ ከትውልድ አገሩ ጋር የሚኖረው ቁርኝነት ማጠናከሪያና ትርጉም መስጫ ይሆናል። በብዛት የሚታየው የተደረሰበትን ውጤት እንጂ ምን ያህል ጠጠራማ አቀበትና የብቸኝነት ጉዞ እንደሆነ ብዙው ዳያስፖራ ያውቀዋል። የሚሄድበት አገርና ሰውም የመጣባቸውን ሰው ሊቀበሉት ወይም ላይቀበሉት፣ ሊያከብሩት ወይም ሊንቁት፣ ሊያደንቁት ወይም ሕይወቱን ሊያከብዱበት፣ የትውልድ አገሩን ሊያስረሱት ወይም ማንነቱን ሁልጊዜ የሚያስታውሱት ሊሆኑ ይችላሉ።
ጀርመን አገር የጀርመን ዜጋ ያልሆነ የውጭ አገር ዜጋ እንኳ በማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን ይችላል። በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥም ኃላፊነት መውሰድና መመረጥም ይችላል። የማይችለው በጀርመን ብሔራዊ ምርጫ መሳተፍ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ጥምር ዜግነት ቢኖር በፖለቲካ ላይ ለመሳተፍ ለሚፈልጉ ከላይ እንደተገለጸው ኢትዮጵያ ሲገቡ የኢትዮጵያ ዜግነት ብቻ ተግባራዊ ስለሚሆን፣ የግዴታና የታማኝነት ግጭት ውስጥ አይገቡም። ለምሳሌ ትልቁ ከሆኑት አንዱ የጀርመን ‹ሪጅናል ስቴት› የታችኛው ሳክሶንያ (Lower Saxony) ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ዴቪድ መክኤል ስተር የመጀመርያው የጥምር ዜጋ ርዕሰ መስተዳድር የነበሩ ሲሆኑ፣ የእንግሊዝና የጀርመን ዜጋ ናቸው። አንዳንድ አገሮች የፕሬዚዳንትነት፣ የጠቅላይ ሚኒስትርነት፣ የጦር አዛዥ ቦታዎች ላይ ያለ ሰው በእነዚህ ቦታ ሲመረጥ ሁለተኛው ዜግነቱ እንዲረጋ ያደርጋሉ። ይህ ማለት ዜግነቱን ይለቃል ማለት ሳይሆን፣ በሁለተኛው ዜግነቱ የሚጠቀምባቸው መብቶቹ ይረጋሉ ማለት ነው። በሥራው እስከሚቆይበት ጊዜ ድረስ ፓስፖርቱን ለሁለተኛ አገሩ ይመልሳል። ግልጋሎቱን ሲጨርስ ተመልሶ በፓስፖርቱ መጠቀም ይችላል። ይኼንን መሰል ገድብ ያላቸው የአፍሪካ አገሮች አሉ። ለምሳሌ የግብፅ የጥምር ዜግነት በወታደራዊና በደኅንነት በሚሠሩት ላይ ገደብ ያደርጋል።
በተጨማሪም ጥምር ዜግነት እሳቤነቱ ተበታትነው ከሚኖሩ ዳያስፖራዎች፣ በትውልድ ኢትዮጵያውያንና ከእነሱ ለተወለዱ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው መብትና ጥቅምን፣ ይህም ኢትዮጵያን በቅጡ ለማያውቋት ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ልጆቻቸው ሰብዓዊ መብትና ማበረታቻ ተደርጎ ማየትን ያስፈልጋል። አንድ በዜግነት አሜሪካዊ ነገር ግን ትውልደ ኢትዮጵያዊ፣ ከወላጆቹ አገርና ሕዝብ ጋር መርጦ ሳይሆን ጥሎበት የተሳሰረን ልጅ የኢትዮጵያዊነትን ዜግነት መከልከል ሰብዓዊነትን መጋፋት አይሆንምን?
ዛሬ ሦስት ሚሊዮን የደረሱት ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያኖች ነገ ስድስት ሚሊዮን ማደጋቸው አይቀርም፣ በተለያዩ መስክም ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን የሚያፈሩ መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከእነሱም የተወለዱ፣ የተቀየጡ በመላ ዓለም ላይ በተለያዩ መስኮች ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህም የኢትዮጵያ ድብቅ/ዕምቅ ሀብትና የኢትዮጵያ ዓይን ናቸው።
የጥምር ዜግነት ተፈቅዶ የሚደነግግ ሕግ ሲወጣ ይኼንን አስከትሎ በመመርያዎች አጨቃጫቂና አከራካሪ ሁኔታዎችን በመገደብ የጥምር ዜግነቱ የማይሠራበትን ሁኔታዎችን ማስቀመጥ ይቻላል። ለምሳሌ ሁለተኛ ዜግነት የሰጠው አገር ከኢትዮጵያ ጋር በጦርነት ላይ ያለ ከሆነ፣ በድንበር ግጭት ላይ የሚገኝ፣ በጠረፍ ላይ የሚገኙ ሕዝቦችን በተመለከተ የተለያዩ የይገባኛል፣ የሀብት፣ የንብረት ካሳ የሚያነሱ አገሮችን በተመለከተ ዜግነት ላይ ጊዜያዊ ገደቦችን በተለይም በከፍተኛ የመንግሥት ቦታዎች ላይ (በፕሬዚዳንትነት፣ በጠቅላይ በሚኒስትርነት፣ በጦር አዛዥነት፣ በደኅንነት ኃላፊዎች) ሊያስቀምጥ ይችላል። በአጠቃላይም የሚያስፈልግ ሆኖ ሲገኝም ጥምር ዜግነት የሚፈቀድላችው የአገሮችን ዝርዝርም ሊያወጣ ይችላል።
የጥምር ዜግነት ቢፈቅድም እስከ ዛሬ የነበረው የትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ ወረቀት የግድ መቀጠል አለበት። ይኸውም ጥምር ዜግነት ከማይፈቅድባቸው አገሮች የውጭ ዜግነትን የወሰደሰው በኢትዮጵያ መብቶች እንዲጠቀምና አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ያስችለዋል። ለምሳሌ ጥምር ዜግነት የማይፈቅድበትን ህንድ፣ ባህሬን፣ ወዘተ የመሳሰሉትን ይመለከታል። በተጨማሪም ያለበት አገር የጥምር ዜግነት ቢፈቅድም እንኳን ግለሰቡ በግሉ ኢትዮጵያ ሲገባ፣ የኢትዮጵያ ዜግነት መብትና ግዴታዎች የማይፈልግ ከሆነና በሁለተኛው ዜግነቱ ብቻ መጠቀም ለሚፈልግና ከኢትዮጵያዊያን ጋር በጋብቻ ለሚኖሩ የውጭ አገር ዜጎች የሚጠቅም ነው።
የጥምር ዜግነትን በተመለከት ያሉ የግንዛቤ ግጭቶች
በአንዳንድ ቦታ በጥምር ዜግነት ላይ ተቃውሞ፣ ፍራቻና ፎቢ አልፎም ጥላቻ ይታያል። ይህም በአብዛኛው ለኢትዮጵያ ከመቆርቆር፣ ሉዓላዊነቷ እንዳይደፈር ከመሥጋት፣ ባህልና ክብራችን እንዳይነካ ከመፍራት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ስለጥምር ዜግነት ባለን ሳናውቀው በምንቃወመው ሁኔታ (Unconscious Bias)፣ ከግንዛቤ ማጣት፣ ኢፍትሐዊ ነው ብሎ ስለሚታሰብም ይሆናል፡፡ ሌላው ለምሳሌ በጀርመን የጥምር ዜግነት ተቃዋሚዎች የሆኑ የቀኝ ክንፍና ዘረኞች የሚሉትን ካየን ጀርመናዊነት ይጠፋል፣ መጠቀሚያ እንሆናለን፣ ‹‹እኔ አንድ ዜግነት ብቻ ኖሮኝ እንዴት ሌላው ሁለት ይኖረዋል›› የሚሉና ከቅናትና ከጭፍን ጥላቻም የመነጨ ነው። ጥምር ዜግነት ለኢትዮጵያ ከሚያስገኘው ጥቅምና ጉዳት ማመዛዘን ያሻል፣ ጉዳትም ካለ ይኼንንም በሒደት በውስጥ በመመርያ መገደብ ያስፈልጋል። ስለጥምር ዜግነት ያለ ጭፍን አመለካከትን ጉዳቱ ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ፣ ጥቅሙን አንጥሮ ተመልክቶ ይኼንንም ለመጠቀም መጣር ተገቢ ነው።
የጥምር ዜግነትን አስመልክቶ የሌላ አገር ዜግነትን በተጨማሪ የሚወስድ ሰው ለኢትዮጵያ በከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ኃላፊነትን ለመውሰድ ታማኝና ሞራላዊ ተምሳሌት ሊሆን አይችልም የሚሉ አስተያየቶች አሉ። ይኼንን በሦስት ከፍለን ማየት ተገቢ ነው።
አንደኛ የሚወስነው ከኢትዮጵያ ጋር በጦርነት ያለ አገር ዜጋ እስካልሆነ ድረስ፣ የግለሰቡ ማንነት፣ ለኢትዮጵያ ያለው ፍቅር፣ የሥራ ክህሎቱ፣ የትምህርት ደረጃው፣ ልምዱ፣ ያበረከታቸው ማኅበራዊ ግልጋሎቶች፣ ለኢትዮጵያ ያበረከተው ግልጋሎት ወይም የያዘው ራዕይ ከሁሉም በላይ ይኼንን ሰው እፈልገዋልሁ ብሎ የሚመርጠው እንጂ ‹‹ታማኝ ሊሆን አይችልም›› ብለው በሚጠረጥሩት ሰዎች አይደለም። አንድ ግለሰብ ሁለተኛ ዜግነት ያገኘበት አገር ለምንስ በጥርጣሬ ይታያል? ሁለት ልጆች ያሉት ሰው ሁለቱን መውደድ አይቻለውምን? ይህ ግለሰብስ ኢትዮጵያን እኮ አብልጦ ሁለተኛ ዜግነት ከሰጠው አገር ቢወድስ አይደል ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ ያዞረው ወይም ለፖለቲካ ምርጫ የሚወዳደረው።
ሁለተኛ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ ይሰጣል ተብሎ የሚታሰበው ጥርጣሬያዊ መላምት በተገላቢጦሽ ካየነው፣ የኢትዮጵያ ዜጋ ብቻ ያለው ሰውስ ይኼንን አያደርግም ማለት ነው? ጥምር ዜጋ ያለውስ ይኼንን ሊያደርግ የሚችልበት ማረጋገጫ አለ? ለኢትዮጵያ የሠሩ እንድ ካርል ሃይንስ ቦምና ሪቻርድ ፓንክረስት የኢትዮጵያ ዜግነት አልነበራቸውምን (የክብር ሆነ አልሆነ ለውጥ የለውም)?
ሦስተኛ በዓለም ላይ የጥምር ዜግነት ያላችው አገሮች ብዙ ናቸው። ይህ የጥርጣሬ መላምት ሌላ አገር ተፈጽሞስ ያውቃል ወይ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያን ለረዥም ጊዜ የጥምር ዜግነት የሌላት አገር ነች፡፡ እንደ ጃፓን፣ ቻይና የመሳሰሉት ነችና ይህ መቀጠል አለበት የሚል ሐሳብም ሊኖር ይችላል። በመጀመርያ የማይፈቀድባችው አገሮችን ምሳሌ ከመውሰድ ይልቅ የሚፈቀድባቸውን በቅድሚያ መውሰድ ተገቢ ነው። ሌላው ይህ ለዘመናት የፈጀው የአንድ ዜግነት አሠራርስ ለኢትዮጵያ ምን ጠቀመ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። ወደ ውጭ መፍለስና የሌላ ዜግነትን ከመውሰድ አላስቆመንም። እንኳን ወጣት ቀርቶ አረጋውያንስ እየፈለሱስ አይደል። አንዳንዱ ሰውስ ልጆቹን አሜሪካ፣ እንግሊዝና ጀርመን ውስጥ እንዲወልዱ በመሄድ እነዚህ ልጆች የእነዚህ አገር ዜጎች እንዲሆኑስ ያደርጉ የለምን። የድሮ የኢትዮጵያ ሕጎች ሲውጡ እኮ የሌላ አገር ዜግነት የወሰደ ኢትዮጵያ በጣም ትንሽ ነበር። አሁን ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተሰደው የወጡበት፣ የሰዎች ዝውውር በጣም የፈጠነበት፣ የአገሮች ወሰኖች ትርጉም የተቀየረበትና ዘመነ ዲጂታል ላይ ነው ያለነው።
አንድ ትልቅ ጥንቃቄ መደረግ የሚገባው ነገር ሁለተኛ ዜግነት የሰጠ አገርን ማክበርና ትርጉም መስጠት ያስፈልጋል። ‹‹ፓስፖርታቸውን እመልስላቸዋለሁ››፣ ‹‹ፓስፖርቱን ቀዶ የኢትዮጵያን መውሰድ ይቻላል››፣ ወዘተ ማለቱ እነዚህ አገሮች በችግር ጊዜ ደርሰው ከትውልድ ወይም በደም ዜጎቻቸው ጋር እኩል አድርገው፣ የዴሞክራሲን አየር አስተንፍሰው፣ ሀብት ማፍራትንና መሥራትን ያስቻሉ አገሮችን፣ ሕዝብን በማዋረድ የኢትዮጵያ ዜግነትን ማስመለስ ለኢትዮጵያ ዜግነት ክብርን አለመስጠት ነው። በተለይም ይኼንን ከስሜትና ከፖለቲካ ነፃ ሆነን ማየት እጅግ ተገቢ ነው።
ጥምር ዜግነት በውጭ ያለውን ኢትዮጵያዊ ከአገሩ፣ ከሕዝቡና ከመንግሥቱ ጋር የሚያስተሳስረው፣ በአገሪቱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሳተፍ የሚያስችለው ሲሆን፣ ለመምረጥ ለመመረጥም የሚያስችለው መብትን ልክ ብዙ የኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች ጥምር ዜግነትን ተግባራዊ እንዳደረጉት ሁሉ ያስችለዋል። ግብፅ፣ ሱዳንና ኬንያን መውሰድ ይቻላል። ለምሳሌ ኬንያ በቅርቡ ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል ጥምር ዜግነትን ፈቅዳለች። የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን የጥምር ዜግነትን አስመልክቶ ጥናት ላይ መሆኑ ትልቅ ጅምር ነው። ራሱ የትውልደ ኢትዮጵያዊ አዋጅ አንድ ዕርምጃ ወደፊት መሆኑን እንደተጠበቀ ሆኖ ግን፣ ይኼንን ማስጨረስና ወደ ጥምር ዜግነት መቀየሩ ወሳኝ ዕርምጃ ለኢትዮጵያ ነው። በኢትዮጵያ ጥምር ዜግነትን ለመተግበር የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 6 ማሻሻል አያስፈልግም። ምክንያቱም በአንቀጽ 6 ላይ ከወላጆቹ ቢያንስ አንዱ ኢትዮጵያዊ የሆነ የኢትዮጵያ ዜጋ መሆኑን ስለሚገልጽ። ማሻሻያ የሚያስፈልገው በአዋጅ ቁጥር 378/2003 ስለኢትዮጵያ ዜግነት የወጣው አዋጅ በዋናነት አንቀጽ 19-20 ይሆናል። ይኼንን ሐሳብ ማሻሻል የሚፈልጉ ወይም ተቃራኒውን የሚያሳዩ ሐሳቦች መንሸራሸር እንደሚገባቸው ሳልጠቁም አላልፍም።
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአገር ቤት ካጠናቀቁ በኋላ ጀርመን አገር በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን በማስተርስ ዲግሪ፣ በኢኮኖሚክስ የዶክትሬት ዲግሪ ከሁምቦልት ዮኒቨርሲቲ መመረቃቸውን፣ በፕሮጀክት ማኔጅመንት ስፔሻላይዝድ በማድረግ ለ16 ዓመታት በዳይምለር መርቼዲስ ቤንዝ ኩባንያ በመጀመርያ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዲፖርትመንት በፕሮጀክት ፖርትፎልዮ ማኔጅመንትና ኢንተርፕራይዘር አርክቴክቸር ማኔጅመንት፣ አሁን ደግሞ በሰው ሀብት (ሂዩማን ሪሶርስ) ዲፓርትመንት በብዝኃትነት (ዳይቨርሲቲ) ማኔጀርነት እየሠሩ መሆኑን፣ ለመርቼዲስ ቤንዝ በብራንድ አምባሳደርነት ከሚወከሉ በርካታ ሠራተኞች አንዱ መሆናቸውን፣ በተጨማሪም በተጋባዥ ሌክቸረርነት በፕሮጀክት ማኔጅመንት በተለያዩ የጀርመን ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚያስተምሩ፣ ለተለያዩ መሥሪያ ቤቶች፣ ለዩኒቨርሲቲዎችና ለክልል አመራሮች የፕሮጀክት ማኔጅመንትና የሥራ ባህል ሴሜናሮች በነፃ መስጠታቸውን፣ በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነውን የፕሮጀክት ማኔጅመንት መጽሐፍ በአማርኛ ጽፈው ለጥቅም ማዋላቸውን፣ በበርሊንና በአዲስ አበባ ከተሞች መሀልም ግንኙነት እንዲፈጠር ንግግር እንዲጀመር ጥረት ማድረጋቸውን፣ ዝንባሌያቸው እንደሆነ የሚናገሩትን የጁጂትሱ ስፖርት ወደ ኢትዮጵያ በማስገባትና የጁዶ ስፖርት እንዲስፋፋ በማድረግና በነፃ ዕርዳታ ማድረጋቸውን፣ በዚህ የስፖርት ዘርፍም በጀርመን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ማሠልጠናቸውንና በአፍሪካ ፌዴሬሽን በምክትል ፕሬዚዳንትነትና በዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን የሥነ ምግባር ኮሚሽን በምክትል ፕሬዚዳንትነት እያገለገሉ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው mail@degineh.com ማግኘት ይቻላል፡፡