Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ በታክስ አሰባሰብ ተግዳሮት ገጥሞኛል አለ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በተያዘው በጀት ዓመት 34.5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ያቀደው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በሁለት ዋና ጉዳዮች ተግዳሮት ገጠመው፡፡

  የገቢዎች ቢሮ ተግዳሮት እየገጠመው የሚገኘው ከትክክለኛ ዋጋው ዝቅ አድርገው ደረሰኝ በሚቆርጡ (አንደር ኢንቮይስ)፣ እንዲሁም ደረሰኝ ቆርጠው ዕቃ ለመሸጥ ምንም ፍላጎት የሌላቸው ግብር ከፋዮች ነው፡፡

  የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ የሥነ ምግባር መከታተያ ዳይሬክተር አቶ አጃናው ወንድም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቢሮው በሁለቱም ግብር ከፋዮች ተግዳሮት ገጥሞታል፡፡

  በአሁኑ  ወቅት አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ አገሪቱ የሚገኙ ነጋዴዎች በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ከባንኮች ስለማያገኙ፣ እንዲሁም ባንኮች የተወሰነ ቢሰጧቸውም በራሳቸው መንገድ ቀሪውን አፈላልገው ዕቃ ያስመጣሉ ብለዋል፡፡ ነጋዴዎች ከውጭ ያመጡትን ዕቃ ከባንኮች ካገኙት የውጭ ምንዛሪ ጋር አመሳክረው ዕቃው ከወጣበት ዋጋ ዝቅ አድርገው ደረሰኝ በመቁረጥ ሽያጭ ያከናውናሉ ሲሉ አክለዋል፡፡

  አቶ አጃናው እንደገለጹት፣ በአገሪቱ ያለው የውጭ ምንዛሪ ችግር እየታወቀ ነጋዴዎች ከትክክለኛ ዋጋው ዝቅ አድርገው ደረሰኝ የሚቆርጡበት ምክንያት እየታወቀ ዕርምጃ ይወሰድባቸዋል፡፡

  ‹‹ነጋዴዎች በምን ምክንያት ከትክክለኛ ዋጋ ዝቅ አድርገው ሽያጭ እንደሚፈጽሙ እያወቅን ይሠራሉ፤›› በማለት አቶ አጃናው ያስረዳሉ፡፡ 

  ይህን ችግር ባለበት እንዲቀጥል ማድረግ ዘለቄታዊ መፍትሔ ስለማያመጣ በመታመኑ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮና ከገቢዎች ሚኒስቴር የተውጣጣ ኮሚቴ መቋቋሙን አስረድተዋል፡፡ ኮሚቴው ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ በእነዚህ ነገዴዎች ላይ የሚወስደውን ዕርምጃ ያለዘበ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ የመጀመርያ ወራት በመርካቶ ከሚገኝ አንድ ቅርንጫፍ በ28 ነጋዴዎች ላይ ብቻ ዕርምጃ መውሰዱ ተገልጿል፡፡

  አቶ አጃናው ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በበርካታ ነጋዴዎች ላይ ዕርምጃ ተወስዶ እንደነበር አስታውሰው፣ በዚህ ዓመት ግን ዘላቂ መፍትሔ እስኪመጣ ድረስ ዕርምጃው እንዲለዝብ ተደርጓል ብለዋል፡፡

  በሁለተኛ ደረጃ አስተዳደሩን የገጠመው ተግዳሮት ግብር በአግባቡ ከማይከፍሉ የተወሰኑ ነጋዴዎች ነው፡፡ የተወሰኑ ነጋዴዎች ለትክክለኛው ዋጋ ደረሰኝ መቁረጥ እየቻሉ፣ ደረሰኝ ለመቁረጥ ፈቃደኛ ያልሆኑ መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

  ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲገልጹ፣ በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ አዛብቶ በመረዳት፣ ‹‹ደረሰኝ አንቆርጥም፣ አትቆጣጠሩን›› የሚሉ ሥርዓት አልበኛ ነጋዴዎች ተፈጥረዋል ብለዋል፡፡

  ‹‹ኃይል ለመጠቀም የሞከሩም ነጋዴዎች ነበሩ፤›› በማለት ገቢዎች ቢሮ የገጠመውን ተግዳሮት አስረድተዋል፡፡  

  የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ ከለያቸው ከፍተኛ የሥጋት መስኮች መካከል የታክስ ማጭበርበር፣ የታክስ ሥወራ፣ የንግድ ማጭበርበርና ኮንትሮባንድ ይገኙበታል፡፡

  በ2010 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በከተማው በሚገኙ 14 ቅርንጫፎች ተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢ ሆነው ደረሰኝ የማይቆርጡ ተብለው በተጠቆሙ 359 ድርጅቶች ላይ በተካሄደ ዘመቻ 318 ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል ብለዋል፡፡

  በመርካቶ ደግሞ 32 ድንገተኛ ዘመቻዎች ተካሂደው ሁሉም የተሳኩ እንደነበሩ ከቢሮው የተገኘው ማስረጃ ያመለክታል፡፡

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተያዘው በጀት ዓመት 34.5 ቢሊዮን ብር የመሰብሰብ ዕቅድ ይዟል፡፡ ባለፉት አምስት ወራት ገቢ አሰባሰብ ጥሩና በታክስ አሰባሰብ የጊዜ ሰሌዳ ቀሪዎቹ ወራት አስቸጋሪ ጊዜያት እንደሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም፣ የተፈጠሩት ችግሮች አስቸኳይ መፍትሔ ካልተሰጣቸው በሥራ አፈጻጸሙ ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡    

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች