Tuesday, August 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ልናገርሕገ መንግሥቱን የጣሰው ማነው? ያከበረውስ?

  ሕገ መንግሥቱን የጣሰው ማነው? ያከበረውስ?

  ቀን:

  በመርሐ ፅድቅ መኰንን ዓባይነህ

  ቅዳሜ ኅዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም. አዲስ አበባ ከተማ ላይ ዝነኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ለ13ኛ ጊዜ ቡና በማፍላት ሥነ ሥርዓት ታጅቦ ሲከበር እንደዋለ ሁላችንም አስተውለናል፡፡ እለቱ በመቀሌ ስታዲየም ደግሞ ከዚሁ በዓል አከባበር ጎን ለጎን መሬት አንቀጥቅጥ ሰላማዊ ሠልፍ ተካሂዶ ነበር፡፡

  በሠልፈኛው ተይዘው ከወጡት ግንባር ቀደም መፈክሮች አንዱ ‹‹ሕገ መንግሥቱ ይከበር›› ይላል፡፡ ‹‹በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች በብሔር ላይ እየተነጣጠረ የሚፈጸመው ጥቃት ይቁም›› የሚለው ደግሞ፣ በዕለቱ ከፍ ብሎ የተስተጋባ ሌላኛው ተጓዳኝ መፈክር ነበር፡፡

  የሕግ የበላይነት መከበር ከቶም የማይገደው ዜጋ ሊኖር አይችልም፡፡ ሁለቱም በቁማቸው ሲወሰዱ መቼምና በየትኛውም ሥፍራ ድምፃችንን ከፍ አድርገን ብናስተጋባቸው፣ ያን ያህል የሚነቀፉ ጉዳዮች ባለመሆናቸው ይመስለኛል እምብዛም አልተገረምኩባቸውም፡፡

  ይሁን እንጂ በዚያ ግዙፍ ሠልፍ ላይ የተሰሙት እነዚሁ ጣምራ መፈክሮችና ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ በከተማይቱ አደባባይ ከትግራይ ክልል ባንዲራ ጋር ከፍ ብሎ ሲውለበለብ ያየነው የጎረቤታችን የአገረ ሱዳን ባንዲራ ጭምር፣ ሥልጣን ላይ ባሉት የክልሉ መሪዎችና ዓይነ ህሊናቸውን ያለ ይሉኝታ ጋርደው እየጮሁ በሚከተሏቸው ወገኖች ላይ አንዳንድ ጥያቄዎችን እንዳነሳ አስገድደውኛል፡፡

  የሆነስ ሆነና በዚህ አገር ቀድሞ ነገር ሕገ መንግሥቱን የጣሰው ማነው? ያከበረውስ? የብሔር ጥቃት እየተፈጸመ ያለው የትና በማን ነው? ይኼንኑ ስፖንሰር አድራጊውስ? እነዚህን ነጥቦች ለጊዜው ብናቆያቸው እንኳን ኧረ ለመሆኑ ሱዳን ለትግራይ ምኗ ትሆን? መቀሌስ ብትሆን አሁን አሁን አዲስ አበባን በሾርኒ እየተመለከተች ወደ ካርቱም ማንጋጠጧ ወይም ጠጋ ጠጋ ማለቷ ለምን ይሆን?

  ይህ በዚህ እንዳለ ከእነ ጭራሹ ጉራማይሌ የሆነብን ደግሞ የአገራቸው ሰንደቅ ዓላማ የመቀሌን ስታዲየም በሚያደምቅበት በዚያው ቀን ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋባዥነት ወደ ኢትዮጵያ ጎራ ብለው፣ ከእሳቸውና ከጂቡቲው አቻቸው ከእስማኤል ኦማር ጊሌ ጋር በጂማ ከተማ ተገንብቶ የተጠናቀቀውን የኢንዱስትሪ ፓርክ ሲመርቁና በሌሎች ተጓዳኝ ኩነቶች የማራቶን ጉብኝት ተጠምደው መዋላቸው ነው፡፡

  ሊቃውንት (ንግባእ ኬ ሀበ-ጥንተ-ነገር) ይላሉና ወደ መጀመርያው ጥያቄ መመለስ ሳይበጀን አይቀርም፡፡

  በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት፣ ብሔራዊ ማንነትን ምሰሶ አድርገው ለተዋቀሩት ክልሎች ውስጣዊ ጉዳዮችን በራስ ከመወሰንና በፌደራሉ መንግሥት ውስጥ በመካፈል ውጤታማ ተሳትፎ ከማድረግ በዘለለ የመገንጠል መብትን ያቀዳጃቸዋል፡፡

  ሕገ መንግሥቱ ከወጣ እነሆ ያለፈው ኅዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም. 24ኛ ዓመቱን ደፈነ፡፡ የአገሪቱ የበላይ ሕግ በመሆኑ ያለ ጥርጥር አገራዊ ተፈጻሚነት እንዳለው በአንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ (1) ሥር በማያሻማ ቋንቋ ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡ በዚሁ ድንጋጌ ሁለተኛው ዓረፍተ ነገር ሥር እንደተመለከተው ደግሞ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረኑ ወይም የማይጣጣሙ ዝርዝር ሕጎች፣ ደንቦች፣ መመርያዎች፣ ልማዳዊ አሠራሮችም ሆኑ የባለሥልጣናት ውሳኔዎች ውድቅና ከእነ ጭራሹ የማይተገበሩ ናቸው፡፡

  ይህም አነሰውና ቸሩ ሕገ መንግሥታችን ከራሱ አልፎ አገሪቱ የተቀበለቻቸውንም ሆነ ወደፊት የምትቀበላቸውን አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውሎች ሳይቀር በአንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ (4) መሠረት፣ የብሔራዊው ሕግ ሥርዓት ክፍልና አካል ያደርጋል፡፡ እንዲያውም በምዕራፍ ሦስትማ ይህ ቀረሽ በማያሰኝ ሁኔታ ለመላው የሰው ዘር ጥበቃና ከበሬታ ሲባል በኩሏለማዊው የሰብዓዊ መብቶች መግለጫም ሆነ፣ በዓለም አቀፎቹ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳንና የኢኮኖሚያዊ፣ የማኅበራዊና የባህላዊ መብቶች ሰነዶች ውስጥ በሚገባ ተቆጥረው ዕውቅና ያገኙትን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች በሙሉ ለወጉ ያህል አስፍሯል፡፡

  ምን ይኼ ብቻ? በተለይ በዚህኛው ምዕራፍ ውስጥ የተካተቱትን የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች የፌደራልና የክልል መንግሥታት ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ አካላት ሳይሸራርፉ የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለባቸው በአንቀጽ 13 ንኡስ አንቀጽ (1) መሠረት በፅኑ ያስጠነቅቃል፡፡

  እንግዲህ ከፍ ብሎ እንደተብራራው ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የበላይ ሕግ እንደመሆኑ መጠን፣ በሁሉም ወገኖች ዘንድ ያለ ልዩነት መከበርን ቢመኝና እኩል ተፈጻሚነትን ቢሻ አይፈረድበትም፡፡ ይሁን እንጂ እንዳለመታደል ሆኖ አገራችን ኢትዮጵያ ደጋግሜ እንደምለው ቀድሞውኑ ‹‹መንግሥታዊ ሕገ መንግሥት›› እንጂ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ መንግሥት›› ኖሯት አያውቅም፡፡ ተከታታይ መንግሥታት ራሳቸው የማያከብሯቸውን ወርቃማ ሰነዶች ነበር በሕግጋተ መንግሥታት ስም ያለ ኃፍረትና ያለ አንዳች ይሉኝታ እያወጡ ለዜጎቻቸው (ለተገዥዎቻቸው ማለት ይሻላል መሰለኝ) ሰጠናችሁ በማለት ሲመፃደቁና ሲመለኩ የኖሩት፡፡

  ኢሕአዴግም በቆይታው ከዚህ የተለየ ሥራ እንዳልሠራ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ የመቀሌ ሠልፈኞችም ቢሆኑ (ምናልባትም በባሰ ምክንያት) ይህ ይጠፋቸዋል ብዬ ፈጽሞ አላምንም፡፡ ስለሆነም ‹‹ሕገ መንግሥቱ ይከበር›› እያሉ ጉሮሯቸው እስኪነቃ ድረስ በአደባባይ ሲጮሁ መዋላቸው ባያስከፋም፣ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን የጣሱትንና ያከበሩትን ወገኖች በውል ለይተው ቢያመላክቱን ሸጋ በሆነ ነበር እላለሁ፡፡

  እነሆ ‹‹ጉድና ጅራት የሚከተለው ከወደ ኋላ ነው›› እንዲሉ ኢሕአዴግ በአፈሙዝ ኃይል የተቆጣጠረውን መንግሥታዊ ሥልጣን ሕገ መንግሥታዊ በማድረግ ካወጀበትና ራሱን ካደላደለበት ጊዜ አንስቶ አገሪቱን ሲገዛ የቆየው ለከት ባጣ ፈላጭ ቆራጭነት እንጂ፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንዳልሆነ ዘግይቶም ቢሆን እኮ ራሱ ሳይቀር ተናዞልናል፡፡ ታዲያ ሕገ መንግሥቱን በማናለብኝነት እየጣሰ በሽብር ወንጀል ምርመራ ስም ንፁኃንን ዘብጥያ አውርዶ ጭካኔ በተመላበትና ነውረኛ በሆነ የድብደባ ድርጊት የእጅና የእግር ጥፍሮችን ሲነቃቅል፣ በወንድ ልጅ ኃፍረተ ሥጋ ላይ በውኃ የተሞላ የፕላስቲክ ጠርሙስ ሲያንጠለጥልና ርህራሔ በሌለው ሁኔታ አካላዊ ግርፋት ሲፈጽምና ሲያስፈጽም የኖረው ማን ሆነና ነው ሠልፈኞቹ የሕግ የበላይነት ይረጋገጥ እያሉ በዚህ ደረጃ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የሚያላግጡት? ‹‹ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል›› አሉ እትዬ ማሚቴ፡፡

  ሰውየው ወደ አንድ ወደማያውቀው ሠፈር ዘለቀና የቢጤዎቹን አድራሻ በማፈላለግ ላይ ሳለ በዕድሜ ጠና ያለ አንድ ሠፈርተኛ ያጋጥመዋል አሉ፡፡ ወዳጄ ዕርዳታህን ፈልጌ ነበር ለመሆኑ የቡዶች መንደር የትኛው ነው?›› ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ ሰፈርተኛውም በእጁ ወደሆነ አቅጣጫ እያመላከተ ‹‹ያውልህ እዚያ ማዶ ይታይሀል? (እነሱም እኛን ይላሉ፣ እኛም እነሱን እንላለን፤›› ብሎት አረፈው ይባላል፡፡

  ለነገሩ የመቀሌ ከተማን ጨምሮ በየትኛውም ሥፍራ ሕገ መንግሥቱ እንዲከበርና የሕግ የበላይነት ያለ ልዩነት እንዲሠራበት በአደባባይ መጠየቅ ያን ያህል ክፋት የለውም፡፡ ሆኖም በዚህ ረገድ እኛ ኢትዮጵያውያን ዕድለኞች አይደለንም፡፡ አገራችን እስከ ዛሬ ድረስ የተጻፈ እንጂ የሚከበር ሕገ መንግሥት ነበራት ወይም አላት ለማለት አያስደፍርም፡፡

  ሠልፈኞቹ በተጨማሪ ከያዟቸው መፈክሮች ለመረዳት እንደተቻለው ሕገ መንግሥቱን ጥሷል በማለት ባልተለያየ ድምፅ ሲከሱ የታዩትና የተደመጡት፣ ከራሱ ከኢሕአዴግ የወጣውን የእነ ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) የለውጥ አመራር እንደሆነ እምብዛም አላከራከረም፡፡ ከዚያ ይልቅ አነጋጋሪው ጉዳይ ያንኑ ሠልፍ በበላይነት ያደራጁት አመራሮች ራሳቸው አዲስ አበባን እየለቀቁ ወደ መቀሌ እስከ ኮበለሉበት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፣ ለሕገ መንግሥቱ አለመከበር በትጋት ሲሠሩ የቆዩ ነባር የኢሕአዴግ ቁንጮዎችና የእነሱ ተላላኪዎች የነበሩ መሆናቸው ነው፡፡ እንግዲህ በሠልፉ ላይ ያሉትን ይበሉ እንጂ ሕገ መንግሥቱን በተደጋጋሚ የጣሱት፣ ዛሬም ቢሆን ቅንጣት ያህል ፀፀት ተሰምቷቸው ያላከበሩትና ለሕግ የበላይነት ጨርሶ ደንታ የማይታይባቸው የአዕምሮ ምንዱባን እነሱ ብቻ ናቸው፡፡

  በእውነት ከልባቸው የመነጨ ያድርገውና የትኛውንም የኅብረተሰብ ክፍል መነሻ አድርገው ቢያስተጋቡት ‹‹ብሔሮችን ለይቶ ማጥቃት ይቁም›› ሲሉ ያሰሙትን ጩኸት ግን ሁላችንም እንደግፈዋለን፡፡ ይኼንን በጎ ጥሪ ዲያብሎስ እንኳ ውቃቢ ቀርቦት ቢያሰማው በጋራ ልንቆምለት የሚገባ ጥሪ ነው፡፡ የስፖንሰር አድራጊው ማንነት ተጣርቶ ካለመረጋገጡ የተነሳ ብዙዎቻችንን ገና ግራ እያጋባን ስለሆነ ነው እንጂ፣ የጥቃቱ ሰለባ ማንም ይሁን ማን የእኛው ዜጎች የሆኑትን ይቅርና መላውን የሰው ልጆች በዘራቸው፣ በብሔራቸው፣ በሃይማኖታቸውም ሆነ በቀለማቸው፣ ወዘተ. ምክንያት ለይቶ ማጥቃት ወይም ማሰቃየት በኃይለኛው የሚያስቀጣ ከባድ የወንጀል ድርጊት መሆኑ ከወዲሁ መታወቅ አለበት፡፡

  ከዚህ በተረፈ በሠልፉ ላይ ቀደምት የኮሙዩኒስት ሥርዓቶችን የሚያስታውሰንና ወታደራዊ ትርዒት ሊመስል ትንሽ የቀረው ዓይነት አደገኛ ትዕይንት ተስተውሏል፡፡ ያ ወታደራዊ ትርዒት ከሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አልፎ በሱዳኑ አምባገነን መሪ ምሥልና በዚያች አገር ባንዲራ ታጅቦ መታየቱ ደግሞ በእጅጉ ያስደምማል፡፡ በዚህ ላይ ወጣቶች ለማናቸውም ሁኔታ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ በማለት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ያቀረቡት ጥሪ ሲታከልበትማ፣ የትግራይ ወንድምና እህቶቻችን ለቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊያስተላልፉለት የወደዱት መልዕክት ምን አንድምታ ሊኖረው እንደሚችል ፍንጭ ሳይሰጠን አልቀረም፡፡

  ለመሆኑ ሱዳን ሰፊዋን ኢትዮጵያን ገለል አድርጋ አንደኛዋ ክልላችን ከሆነችው ከትግራይ ጋር ብቻ የተናጠል ወዳጅነት መመሥረቷ በፖለቲካው ረገድ ምን ያህል ያተርፋታል?

  ትግራይስ ብትሆን ቤተሰቧን በህቡዕ ከድታ የሱዳን አንደኛዋ ክፍለ አገር ለመሆን ካልፈለገች በስተቀር፣ ያለ ግብሯ ኦማር አል በሽርን ያን ያህል መለማመጡ ለምን ይገዳታል?

  ይህ ጸሐፊ እስካሁን ባለው እውቀት ሱዳን ለትግራይ ምኗም አይደለችም፡፡ ጉርብትናዋ ከሆነ የጋርዮሽና ሁላችንም የምንንከባከበው ነው፡፡ እንዲያውም ታሪክን የኋሊት እየጠቀሱ ለዛሬው ዘመን ትውልድ ቂም በቀል ቋጥሮ ማቆየቱ አትራፊነት የለውም እንጂ፣ የአፄ ዮሐንስ አራተኛን አንገት መተማ ላይ በሰይፍ የቀሉባት እኮ ሌላ ሳይሆን የጥንታዊቷ ሱዳን መሐዲስቶች ናቸው፡፡

  ስለሆነም ሠልፈኞቹ ለጊዜው በጠባብ ብሔረተኝነት ስካር ናውዘው ለራሳቸው ቃል ሊገቡ እንደ ሞከሩት (የገነቧት አገር ካላስከበረቻቸው የምታስከብራቸውን አገር በመገንባቱ) ረገድ፣ ከሱዳን ጋር መሞዳሞዱ እምብዛም አያግዛቸውም፡፡ ይልቁንም የአገራችን ሰው እንደሚለው ነገሩ ‹‹እናቷን ረስታ አክስቷን ትናፍቃለች›› ይሆንባቸዋል፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1981 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ የቀድሞው የሕግ ፋከልቲ ያገኙ ሲሆን፣  በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ ከነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው clickmerha1@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የአገሪቱ ባንኮች ካፒታል 199.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ

  ከታክስ በኋላ 50 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ የአገሪቱ...

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...