Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

  የሳምንቱ ገጠመኝ

  ቀን:

  በቀደም ዕለት እንዲህ ሆነላችሁ፡፡ የፖለቲካ ወሬ ስልችት ሲለኝ በከተማችን ከሚገኙ ሲኒማ ቤቶች ወደ አንዱ አዲስ የወጣ ፊልም ለማየት እሄዳለሁ፡፡ የዚህን ፊልም ‹‹እንከን የለሽነት›› በተለያዩ ማስታወቂያዎች ስለሰማሁ እስኪ ልየው ደግሞ በማለት ነው እዚህ ሲኒማ ቤት የተገኘሁት፡፡ ሲኒማ ቤቱ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከተሠሩት መካከል ስለሆነ ደረጃውን የጠበቀ ይመስላል፡፡ እንደ ድሮዎቹ ድብርታምና ዝጋታም አይደለም፡፡ ሰዓቱ ደርሶ መብራት ከጠፋፋ በኋላ ብዙ የተወራለት ፊልም መታየት ጀመረ፡፡ እንደ ነገርኳችሁ ይኼ በተለያዩ ዘገባዎች እሪ እምቧ የተባለለትን ፊልም በትኩረት መከታተል ጀመርኩ፡፡ እንደ ሌሎቹ ፊልሞች አልስብ አለኝ ሳይሆን፣ ለአቅመ ፊልም በቅቶ ለሕዝብ መቅረቡ አስገረመኝ፡፡ ብዙ የተወራለት ፊልም አርቲ ቡርቲ ነገሮች ብቻ ናቸው የታጨቁበት፡፡ የዘመናችን ፖለቲካስ አርቲ ቡርቲ በዝቶበት አይደል እንዴ እጅ እጅ የሚለው፡፡

  እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ የህንድና የሆሊውድ ፊልሞችን ስኮመኩም ያደግኩኝ ያራዳ ልጅ ነኝ፡፡ ከማዘር ኢንዲያ እስከ ብላክ ፓንተርና ሌሎች ዘመን አመጣሽ ፊልሞችን ከልጅነት እስከ ጎልማሳነት ስመለከት የኖርኩ ሰው የአገራችንን የፊልም ደረጃ እረዳለሁኝ፡፡ በመስኩ ብቁ ባለሙያዎችና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያልታጠቀው የእኛው የፊልም ቢዝነስ ብዙ ጉድለቶች ቢኖሩበት አይደንቀኝም፡፡ እያስከፋኝ ያለው ነገር ግን ከ100 ዓመታት በላይ ቴአትርና ድራማ ሲሠራባት በኖረች አገር ውስጥ፣ ጠንከር ያሉ ሐሳቦችን የያዙ የፊልም ጽሑፎች አለመዘጋጀታቸው ነው፡፡ ትልልቅ ጉዳዮችን እናነሳለን ብለው ያላቅማቸው እንጣጥ የሚሉትም አላስፈላጊ መዘባረቅ ውስጥ እየገቡ ናቸው፡፡ ሁሉም ነገር ውስጥ ጥልቅ ማለት የሚወዱት እነዚህ ‹‹ደፋሮች››፣ ባለሙያዎችን ተጠቅመው የረባ ነገር ማምጣት ሲጠበቅባቸው ውዥንብር እየፈጠሩ ናቸው፡፡

  ይኼንን ያዙኝ ልቀቁኝ ዓይነት ፉከራ የተፎከረበትን ፊልም እስከ መጨረሻው ድረስ በትዕግሥት ማየት እንዳለብኝ ራሴን አሳምኜ እስኪበቃኝ አየሁት፡፡ ፊልሙ አበቃ ተብሎ ከሲኒማ ቤቱ ስወጣ ግን ባዶነት ተሰማኝ፡፡ በቃ ምንም ተይዞ የሚወጣ ማስታወሻ ውስጤ አልነበረም፡፡ በዘመቻ መልክ የተለፈፈለት ፊልም እዚያው እንደ ጉም በኖ ቀርቷል፡፡ ቢቸግረኝ ገጸ ባህርያቱን እያስታወስኩ አንዳንድ የተባሉ ነገሮችን ለማስታወስ ሞከርኩ፡፡ ባዶ ቃላት ብቻ፡፡ ገባኝ፡፡ ሁሌም በተለያዩ ማስታወቂያዎች ላይ የምንሰማቸው ቃናዎቻቸው ያልተለወጡ ድምፆች ብቻ እንደ ገደል ማሚቶ ያስተጋባሉ፡፡ ከዚያ ውጪ ረብ ያለው መልዕክት ለማስተላለፍ አቅም የላቸውም፡፡ የአገራችን አብዛኞቹ ፖለቲከኞችም እኮ ከእነዚህ የተሻሉ አይደሉም፡፡

  አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምር ጓደኛዬን ስለገጠመኝ ነገር አጫወትኩት፡፡ እሱም እንደኔ በግኖ ኖሮ ለካ፣ ‹‹ምን ይደረግ ብለህ ነው? እዚህ አገር ዕውቀትን ከመቅሰም ይልቅ ገንዘብንና ሥልጣንን ዕውቀት ማድረግ ፋሽን ሆኗል፤›› አለኝ፡፡ ‹‹ሁሉም ይነሳና ከእኔ በላይ ለአሳር ይልሃል፡፡ በዚህ መስክ ምንም እንኳን ያን ያህል የሠለጠኑ ባለሙያዎች ባይኖሩም፣ በቴአትሪካል አርትና በሥነ ጽሑፍ ዘርፎች ውስጥ ካሉ ባለሙያዎች ጋር ምክክር ቢደረግ እኮ ቢያንስ መሠረታዊ የሚባሉት ችግሮች ይቀረፋሉ፡፡ ከዚያ በኋላ በፖለቲካል ሳይንስ፣ በኢኮኖሚክስና በሌሎች የትምህርት መስኮች ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች አስተዋፅኦ ያበረክታሉ፡፡ ከዚያም በተፈጥሮ ሳይንስ ውስጥ ያሉ ሙያተኞች እገዛቸው ይቀጥላል፤›› እያለ ተነተነልኝ፡፡ ‹‹አሁን ግን ሁሉም ሙያ ውስጥ ዘው ተብሎ እየተገባ መዘባረቅ ዋነኛው መለያ ሆኗል፡፡ እንደ ዘበት ያለ ዕውቀት በተገባበት የማስታወቂያ ሥራ ስንቶች ገንዘብ በቀላሉ ሲያፍሱ፣ ሌላውስ ምን ይቸግረናል ወደ ማለት ተሄደ፡፡ በፖለቲካው መስክ ደግሞ ልክ እንደ ማስ ስፖርት ዘው ብለው የገቡ ሥራ ፈቶችና ጡረተኞች በአገር ይቀልዳሉ፡፡ በአጠቃላይ በአገር ላይ የሚቀልዱ በዝተዋል፤›› ብሎኝ አሳረገ፡፡ ‹‹ልብ አንጠልጣይ፣ ኮሜዲ፣ ሮማንቲክ፣ ወዘተ እያሉ ገበያውን ከሚያጥለቀልቁ ፊልም ሠሪዎችና ከእኛ በላይ ላሳር ከሚሉ ስመ ፖለቲካዊ ተውኔተኞች ይልቅ፣ የሠፈራችን ልጆች ቀልዶችና ወጎች ይበልጣሉ፡፡ ያውም በሳቅ እያንፈራፈሩን፤›› ያለኝን ሌላኛውን ጓደኛዬን አስታወስኩ፡፡

  በቅርቡ ፒያሳ ውስጥ አንድ ሬስቶራንት ምሣ ለመብላት እገባለሁ፡፡ የሬስቶራንቱ አጋማሽ የሚሆን ሥፍራ ተለይቶ ቀረፃ እየተካሄደ ነው፡፡ ካሜራ የያዘው ሰውና ‹‹ዳይሬክተር›› የተባለው ሁለት ኮረዶችን በተለያዩ ማዕዘናት ይቀርፃሉ፡፡ ይኼንን ትዕይንት በግምት ለ30 ደቂቃዎች ያህል ከተመለከትኩ በኋላ ‹‹ዳይሬክተር›› የተባለውን ጠጋ ብዬ፣ ‹‹ምንድነው የሚቀረፀው?›› አልኩት፡፡ ኮራ ብሎ፣ ‹‹ፊልም ነው፣ ድንቅ ፊልም›› አለኝ፡፡ ‹‹ስሙ ምን ይባላል?›› ስለው፣ ‹‹ገና አልወጣለትም›› ሲለኝ በጣም አስገረመኝ፡፡ የሁለታችንን ምልልስ የሰማ አንድ ወጣት እየሳቀ፣ ‹‹አይ ጋሼ በአሜሪካ ሆሊውድ፣ በህንድ ደግሞ ቦሊውድ የሚባሉ ዝነኛ የፊልም ተቋማት አሉ፡፡ እኛ ዘንድ ግን በርካሽ ካሜራ እየቀረፁ ፊልም ሠራን የሚሉ በዝተዋል፡፡ ስማቸውም ያስቃል፤›› አለኝ፡፡ የወጣቱ አነጋገር ከንክኖኝ፣ ‹‹ስማቸው ማን ይባላል?›› በማለት ጠየቅኩት፡፡ እየሳቀ፣ ‹‹ዜሮ ውድ ይባላሉ›› ሲለኝ ኃፍረት ተሰማኝ፡፡ ይህ በጣም ቀልደኛ ወጣት ስለፖለቲከኞቹ ምን እንደሚሰማው እንደ ዋዛ ስጠይቀው፣ ‹‹ፖለቲከኞቻችን እኮ ካለፈው ስህተታቸው በተደጋጋሚ ስለማይማሩ በርካታ ክብረ ወሰኖችን በመስበር፣ አንድ ቀን በዓለም ታዋቂነታቸው በጊነስ ድንቃ ድንቅ መዝገብ እንደሚሠፍር አትጠራጠር…›› እያለኝ ሲስቅ፣ እኔም ከመሳቅ ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረኝም፡፡ ‹‹ማሽላ እያረረ ይስቃል›› የተባለው እኮ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡

  (ከድር ሸምሰዲን፣ ከአጠና ተራ) 

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...