Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ልናገርፌዴራሊዝም ለምን የወቅቱ መነጋገሪያ ሆነ?

  ፌዴራሊዝም ለምን የወቅቱ መነጋገሪያ ሆነ?

  ቀን:

  በመስከረም አሰግድ

  እንደ አገር አሁን ከደረስንበት አስከፊም ሆነ አሳዛኝ ሁኔታ አንፃር በአገራችን ጉዳይ ሆነ በፖለቲካው መስክ አይመለከተንም ብለን ለመቀመጥ ከቶም የሚቻል አይሆንም፡፡ ይልቁንም ገንቢና መፍትሔ አመላካች (ችግርን በችግር በመቆስቆስ አይደለም) የመሰለንን ሐሳብ ሁሉ በዜግነታችን ለመሰንዘርም እንገደዳለን፡፡ በተለይ  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን እያንዣበበ ስላለው ፖለቲካዊ ክስረትና የዴሞክራሲው ተጠናክሮ አለመውጣት፣ ብሎም አብሮነታችንን የሚያቆሽሽ የዘረኝነት አካሄዳችን የፌዴራል ሥርዓቱን ቀና መንገዶች ጭምር ቅርቃር ውስጥ እየከተተ ስለመምጣቱ በጥሞና መነጋገር  ተገቢነት ይኖረዋል፡፡

  ሕገ መንግሥት ፀድቆ ተግባራዊ ከሆነ 24 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ እነዚህ ዓመታት በሰው ዕድሜ አንፃር ሲታዩ አጭር ባይሆኑም በመንግሥታዊ ሥርዓት ግንባታ አኳያ ሲመዘኑ ግን፣ በጣም ውስን ጊዜያት ናቸው ቢባሉ ስህተት የለውም፡፡ በዓለማችን ያሉና ዛሬ በስፋት የሚነገርላቸው የፌዴራል ሥርዓቶች የሃምሳና የመቶ ዓመታት ዕድሜ፣ አንዳንዶቹም የዚህን እጥፍ ዘመን ያስቆጠሩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንፃር የእኛ ፌዴራሊዝም ለጋ ዕድሜ ያለው መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን በዚህ ለሦስት አሥርት ጥቂት ጉዳይ ዘመን ውስጥ የጠነከረ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ከመታየት ይልቅ ጠባብነትና የገነነ ብሔርተኝነት መሥፈኑ፣ ዴሞክራሲውም በሕገ መንግሥቱ በተጻፉ ድንጋጌዎች ልክ እንኳን መተግበር ባለመቻሉና በአፈጻጸም ጉድለት ስም እየተዳከመ በመሄዱ የብሔራዊ መግባባት ልዕልና ካለመረጋገጡም በላይ፣ ሥርዓቱን ቅርቃር ውስጥ እየከተተው እንደመጣ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡

  የበርካታ አገሮች ልምድ እንደሚያሳየን የማንኛውም ሥርዓት ግንባታ ሕገ መንግሥት ከማፅደቅና አደረጃጀት ከመዘርጋት ባሻገር፣ ረዥም ዓመት ወይም ጊዜ የሚጠይቀው በዚህ ተግባራዊነት ላይ የሚካሄደው የአስተሳሰብ ትግል ነው፡፡ ሕገ መንግሥት የማፅደቅና የፌዴራል አደረጃጀት የመፍጠር ሥራ ብቻውን በቂ ውጤት ሊያስገኝ አይችልም፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓቱም ዕውን ሆኗል ማለት አያስችልም፡፡ ከዚህ በላይ ረዥም ዓመት የሚጠይቀው ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለመፍጠር የሚያስችል የአስተሳሰብ ትግል ሕዝብን መሠረት ያደረገ ሥራ ማካሄድ ግድ ይላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን እየታየ ያለው ዝንባሌ ግን ይህ ሥርዓት በሚፈለገው ደረጃ የሕዝቦችን ብዙኃነት እንጂ፣ አንድነት ማረጋገጥ በሚችልበት ቁመና ላይ አለመሆኑን  ነው፡፡

  አሁን ያለው የፌዴራል ሥርዓት ባለፉት ሥርዓቶች በአገራችን ይፈጠሩ የነበሩትን የእርስ በርስ ጦርነቶች ያስከተሏቸውን ውጥረቶችና ጠባሳዎች በማረም፣ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተረጋጋ ሰላምና በልማት ጎዳና እንዲጓዙ ያስቻለ ሕገ መንግሥታዊ መፍትሔ እንደሚሆንም ታምኖበት ነበር፡፡ በእርግጥም እስካሁን ድረስ አልፎ አልፎ ከሚታዩ የውስጥ ችግሮችና የሕዝብ ግጭቶች በስተቀር፣ የጎላ እንከን ሳይገጥመው በአንፃራዊነት ተረጋግቶ ቀጥሏል ሊባል ይችላል፡፡ ምንም እንኳን የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ቢወድቅም፡፡

  የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ በአገራችን የፈጠረውን ብዝኃነትን የማስተናገድ ሚናውን ያህል፣ ሕዝቦችን አንድ ከማድረግ ይልቅ ኅብረቱን አላልቷል የሚሉ ወገኖች የሚያነሱት መከራከሪያ ግን ፈጦ እየታየ ነው፡፡ ቀዳሚው ክልሎች በብሔር መከፋፈላቸው፣ የዜጎች የብሔር ማንነትና ጎሳ በቀበሌ መታወቂያ ላይ መጠቀሱ (በዚህ ረገድ ከሁለትና ሦስት ዝርያ የተገኙና በኢትዮጵያዊነታቸው መጠራት የሚሹ ሚሊዮኖችን መግቢያና መውጫ የሚያሳጣ አሠራር መሆኑ መታመን አለበት) የተሽከርካሪ ሰሌዳና የአንዳንድ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች መለያ በክልል ስያሜ መጠቀሱ፣ ኢሕአዴግ ራሱን ጨምሮ አገሪቱን የሞሉት የብሔር ፖለቲከኞች ጎሳዊና ክልላዊ እንጂ፣ አገራዊ ኅብረት ሲያንፀባርቁ አለመታየታቸው፣ ከመንግሥት መደበኛ በጀት ባሻገር ክልሎች በልማት ማኅበርና በኢንቨስትመንት ስም በሚያከናውኗቸው ተግባራት የልማት ልዩነት እየተንፀባረቀ እንደሚገኝ በመረጃ ላይ ተመሥርተው የሚያነሱ ትንሽ አይደሉም፡፡

   ከዚሁ ሁሉ በላይ ትናንትም ሆነ ዛሬ ድረስ ሥርዓትን መሪዎች ከወጡበት ማኅበረሰብ ጋር በማቆራኘት ገዥና ተገዥ ብሔረሰብ እንዳለ የሚያስመስለው አደገኛ ዘመቻም መቆሚያ አላገኘም፡፡ ባለፉት ዓመታት የነፍጠኛ ሥርዓቶችን ከአማራው  ሕዝብ ጋር እያዛመዱ (እስካሁንም በድህነትና ኋላቀርነት የሚኖረውን ጭቁን ሕዝብ ሁሉ) የማጥላላት ዘመቻ፣ በገዥው ፓርቲ አንዳንድ ጥራዝ ነጠቅ ካድሬዎች ጭምር ሲነዛ ነበር፡፡ በዚህም በሕዝቡ ውስጥ ከፍተኛ መደናገር ከመፈጠሩም በተጨማሪ ቀላል የማይባል ጉዳት ሲደርስ መክረሙም የሚታወቅ ነው፡፡ አሁን ደግሞ በኢትዮጵያዊነት ታሪክ፣ እምነትና ሥልጣኔ ረግድ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ በሆነው የትግራይ ሕዝብ ላይ ተመሳሳይ ፍረጃና ጥላቻ የመንዛት ቀላል የማይባል ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን በግልጽ ማንሳት ይቻላል፡፡  

  ለዚህ መነሻው በአንድ በኩል በታሪክ አጋጣሚ አሁን ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት በአገሪቱ እንዲሰፍንና አምባገነናዊው ወታደራዊ ሥርዓት እንዲገረሰስ፣ በትግራይ ሕዝብና በክልሉ መሪ ድርጅት የተወጠነው ፍሬ የሚያበሳጫቸው አሉ፡፡ በሌላ በኩል የክልሉ ጥገኞች ወይም በብዙ መሥርያ ቤቶች የብሔሩ ተወላጆች በኃላፊነት እንደበዙ፣ በኢንቨስትመንት መስክም በተለይ አንድ ኮንስትራክሽንና የመካናይዝድ እርሻ በጥረትም ሆነ በአቋራጭ በርከት ያሉ ተወላጆች ተሠማርተው መገኘታቸውን እንደ ልዩ ተጠቃሚነት በሚቆጥረው ኃይል፣ ከራሱ ከገዥው ፓርቲ አባል ድርጅቶች አባላትና አመራሮች ጨምሮ በእጅጉ ብዙ ተብሎበታል፡፡ ሁሉም ይህንኑ ዘርና መንደር እየቆጠረ ምን አጣ? ምን አገኘ? ቢል የማይደንቀው የተካረረ የብሔር ተኮር አካሄዳችን ሁሉም ነገር በዚሁ መጠን ልክ እንዲመነዘር ስለሚያስገድድ መሆኑ ሊካድ አይችልም፡፡ እንግዲህ ይኼን የተዛነፈ አሳዛኝ ነገር በዚህ ጊዜ አለመታገል ያለጥርጥር የሚያፋጥነው የሥርዓትን ብቻ ሳይሆን፣ የአገርንም ውድቀት እንደሆነ መጠርጠር አዳጋች ነው፡፡

  በመሠረቱ የፌዴራል ሥርዓቱን የየብሔሩን የታሪክ፣ የማንነትና የቋንቋ ማሳደጊያና ማስተዋወቂያ ለማድረግ የተደከመውን ያህል፣ ለጠንካራ አገራዊ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዳልገነባንበት የሚቆጩ ዜጎች ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም፡፡ ለዓብነት ያህል በብዙ አካባቢዎች ከክልል ሰንደቆች በበለጠ አገራዊ ዓርማችንን ከፍ አድርገን አለመታየታችን፣ በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና የተሰጠውን ኅብረ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ በሰበብ አስባቡ ገለል ለማድረግ መፈለጉ፣ በተከወነም ባልተፈጸመም አፍራሽ የታሪክ ውዝግብ ውስጥ እየገቡ እዚያና እዚህ የሚላጉ እየበዙ መምጣታቸው፣ የአንድ ሉዓላዊ አገር ዜጎች መሆናችን እየታወቀ በአንዳንድ ክልሎች የመኖርና የመሥራት ዕድል በነባርና መጤ መሥፈርት መገደቡ. . . እንዲህ ያለውን ሁኔታም እንደ አገራዊና ሥርዓታዊ ድክመት በመቁጠር ሌት ከቀን የሚያራግበው የውጭ ኃይልም ሳይቦዝን እየሠራ መሆኑ ችግሩ ቀላል እንዳልሆነ የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ ቀስ እያለ የተጠራቀመ መጠራጠር እንዲያቆጠቁጥ ምክንያት ሆኗል የሚሉ ወገኖች መከራከሪያም ይኼው ነው፡፡

  በተጨማሪም ስለአንድ አገር ሕዝብነታችንና ስለኖረው የተሳሰረ ማንነታችንን ከመተረክ ይልቅ፣ በአንዳንድ ፖለቲከኞች (በገዥውና በተቃዋሚውም) ቢጨበጥም ባይጨበጥም የታሪክ ንትርክ መምዘዝ እየቀናን ነው፡፡ ሌላው ይቅር የቀደመው ትውልድ በሠራው ስህተት ይኼኛው ትውልድ ሊወቀስ ሳይገባው፣ የጥላቻና የቂም ግንብ ለመገንባት መሞከር ፋይዳው ጥፋት ብቻ እንደሆነ ነባራዊው ሁኔታ እያሳየ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በችግር ጊዜ ብቅ እያሉ ስለዕርቅና ስለአንድነት የሚነግሩን የሃይማኖት መሪዎችና የእምነት ተቋማትም ቢሆኑ፣ የዕርቅና የአንድነት ወይም የፀረ ጥላቻና የፀረ ቂም በቀል አስተምህሮን አጠናክረው አለመያዛቸው ሲያስተዛዝብ የከረመ እውነታ ነው፡፡ አንዳንዶቹማ በውስጣቸው የሚያሳዝን ዘረኝነትና የመባላት ችግር ያለባቸው መሆኑን ለታዘበ ወደ ተስፋ መቁረጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡ 

  ኢትዮጵያ ከሃያ ዓመታት በፊት ከነበረችበት ፀረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተላቃ የማንነት፣ የባህል፣ የታሪክ፣ የሃይማኖትና የአመለካከት ብዝኃነትን ማስተናገድ የሚችል ሥርዓት መገንባት መጀመሯ አሁንም በበጎ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ የግድ አስፈላጊም  ነበር፡፡ የሕዝቦችን በመቻቻልና በመፈቃቀር ላይ የተመሠረተ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት መመሥረት እንድትችል ግን፣ በሕገ መንግሥቱ ከተጻፉ መተማመኛዎችም በላይ በተግባር የተሠራበት አለመሆኑ በሕዝቦች መካከል ‹የእኛና የእነሱ› የሚል ጎራ እየተፈጠረ እንደመጣ ያለ ይሉኝታ መገንዘብ አለብን፡፡ አንዱ ሌላውን ከአካባቢዬ ውጣ፣ የዚህ ክልል ተሽከርካሪ በዚህ አያልፍምና በእኔ መሬት አንተ በልፅገሃል እያለ በየጊዜው የዜጎችን በየትኛውም አካባቢ የመኖርም ሆነ ተንቀሳቅሶ የመሥራት ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ሲንድ የሚታየው ኃይል ትንሽ አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ ራሳቸው የፖለቲካ ድርጅቶቹ፣ ሕዝብና ፖለቲከኛን (ሥርዓትን) ነጣጥሎ በማሳየት ረገድ ቀሪ ሥራ እንዳለባቸው አሁንም ግልጽ እየሆነ ነው፡፡

  አሳዛኙ ነገር ይህንን ሁሉ ተፅዕኖ የፈጠረው ማኅበራዊ መፈላቀቅ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችን ቀደም ሲል ያልነበረ ጋብቻ፣ ዕድር፣ አክሲዮን፣ ማኅበርና ዕቁብ ሳይቀር የብሔር ታፔላ እየተጫነበትና አገራዊ መልክ እያጣ ሲመጣ ኧረ ይኼ ነገር ምንድነው? ብሎ የመረመረና ይስተካከል ያለ የአገር ሽማግሌም ሆነ የሃይማኖት መሪ አልታየም፡፡ ቀደም ሲል መንግሥትም ቢሆን፣ በተለይ በባንክና በልዩ ልዩ ኢንቨስትመንቶች የሚደራጁ አክሲዮኖች ጭምር የነበራቸውን የብሔር ካባ ለመፈተሽ አለመሞከሩ አገራዊ ኅብረቱ እንዲመናመን ማድረጉን አጥብቀው የሚከራከሩ ወገኖች፣ አንዱ የሌላውን ጥቅም ለመጉዳት እስከ ማሰብ እየጎተተ መምጣቱን ያስረዳሉ፡፡ የኳስ ክለቦችን በብሔር ጌጥ፣ አብያተ ክርስትያናትንም በጎሳ መጠሪያ (በተለይ በውጭ አገሮች) እስከ መሰየም የሚገፋ የዘረኝነት አዙሪት የኢትዮጵያዊያንን ጭንቅላት እየሞላው መምጣቱ፣ ያለ ጥርጥር ትልቅ የአንድነት ዓብዮትና የዕርቅ መንፈስ የሚያስፈልገው ነው፡፡

  አሁንም ቢሆን ሕገ መንግሥቱ ከእነ ችግሩም ቢሆን ለሁላችንም በፈቃደኝነት ወይም ወዶና ፈቅዶ የሚለበስና በየአደባባዩ በኩራት የሚጠቀስ ማንነት እንዲኖረን እንዳስቻለን ጥርጥር የለውም፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ግን ኢትዮጵያዊ የጋራ ማንነትን በኩራት ብቻ ሳይሆን፣ በልበ ሙሉነት እንድንጎናፀፍ የከለከለን ምኑ ላይ ነው? እኛስ ስለምን በብሔር ጎጆ ብቻ ሳንወሸቅ በጋራ አገራዊው አዳራሽ ለአንድ ዓላማ መሰባሰብ ተሳነን? ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ የሆነበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ተገኝተናል፡፡  

  ከዚያም አልፎ በአገራችን ሉዓላዊነት፣ የባህር በር ፍላጎት ወይም አገራዊ ድንበር ጉዳይ አይሉት በክልል፣ በዞንና በወረዳ አነስ ሲልም በመንደር  ወሰንና ጠገግ ሰበብ እየተነታረክን አንዳችን ከሌላችን ለመባላት ጦር መምዘዝ የሚቀናን እንዴት ልንሆን ቻልን? ማለት ተገቢና ወቅታዊ ጥያቄ ነው፡፡ በተለይ  አዲሱ ትውልድ በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ረገድ መያዣ መጨበጫ የሌለውና ሁሉም የራሴን አገር ልውለድ የሚል ቅዠት ውስጥ እየገባ የመጣ መምሰሉ የሚያሳስብ ፈተና  ሆኗል፡፡ ይህ ችግር በተለይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ በስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችና  በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱ ሥጋቱ ጣሪያ ለመንካቱ ማሳያ ነው፡፡  

   በሕገ መንግሥቱ በአንድ በኩል ለዘመናት በጋራ ያካበትናቸውን መልካም እሴቶች በመጠበቅና ያለፉ ስህተቶችን በማረም፣ በሌላ በኩል የምልዓተ ሕዝቡን ሁለገብ ተሳትፎ በማረጋገጥ በአገራችን አዲስ ብሔራዊ የአርበኝነት ስሜት እንደሚቀሰቅስ በብርቱ ታምኖበታል፡፡ በእርግጥም እስካሁን ባለው የሩብ ክፍለ ዘመን ዕድሜ በልማት ረገድ ተስፋ ሰጪ ጉዞ ቢታይም፣ በመቻቻልና አብሮነት ረገድ አዲስ የአርበኝነት ስሜት ስለመፈጠሩ ግን መተማመኛ አልታየም፡፡ እንዲያውም አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ የመፍጠር ፍላጎታችንን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጠናከረ ይመጣል የተባለ ሥርዓት፣ የግለኝነትና የኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ዓረም እንዳይበላው የብዙዎች ሥጋት ሆኗል፡፡ (በክልሎች ተወላጅና ተወላጅ ባለመሆን ያለውን ልዩነትና መናቆር ያጤነዋል)

  የኢትዮጵያ ሕዝቦች የየራሳቸው ቋንቋ፣ ባህልና ወጎች ተጠብቆ ከፀረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመላቀቅ የማንነት፣ የባህል፣ የታሪክ፣ የሃይማኖት ብዝኃነትን በሚያስተናግድ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መመራታቸው ሊጠቅም የሚችለው፣ ተወደደም ተጠላም ኅብረ ብሔራዊ አንድነታቸውን የበለጠ ማጠናከር ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ይኼ እሳቤ በሕገ መንግሥቱም ሠፍሮ ይገኛል፡፡ ይሁንና በኢኮኖሚው መስክ በመንግሥት በኩል የተሠሩ የጋራ መንገዶችና ሌሎች መሠረተ ልማቶች አካባቢን ከአካባቢ ከማስተሳሰራቸው ውጪ ሌሎች ልማቶች አንዳችንን ከሌላችን የሚያስተሳስሩበት መልክ ያላቸው አይመስሉም፡፡ ለምሳሌ ዩኒቨርሲቲዎችን ብንወስድ ብዛታቸው ቢያስደስትም፣ ዜጎች ወደ ተመደቡበት ክልል በነፃነት ለመሄድ የማይደፍሩበት መጠራጠር  እየታየ ለምን መጣ? ብለን ማሰብ ግድ ይለናል፡፡

   ልብ ለልብ ኅብረት ሳይኖረን በአገሪቱ የሚሠራ ግድብን ወይም የባቡር መስመርን ሳይቀር እነ እገሌን ብቻ ለመጥቀም የሚል ተጠራጣሪ ትውልድ በመፈጠሩ፣ ሁላችንም ተጠያቂነት ሊሰማን ይገባል፡፡ በጋራ ልማትና ሰላም ያልተግባባ ያበጠው ይፈንዳ የሚል ትውልድ እንዴት ሆኖ በአንድ አገራዊ ሰንደቅ ዓላማ ሥር ሊሰባሰብ እንደሚችል በግልጽ ተነጋግሮ የጋራ መፍትሔ ማስቀመጥ ግድ የሚል ሆኗል፡፡ ለዚህ ደግሞ ባለፉት 27 ዓመታት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ላይ መለፈፉ፣ ከዕርቅና ይቅር መባባል ይበልጥ የቀደመው ጥፋትና ቁስልን ማመርቀዝ ላይ መሆኑ፣ ከሰፊው አገራዊ ሥዕል በጎላ ደረጃ የመንደርና የጎጥ ወሰን ላይ ማነጣጠር መለመዱ፣ እውነተኛውን ኪሳራ እያስከፈለ እንደ መጣ በገሃድ ለይቶ ማስተካከያ ማበጀት በቀዳሚነት የመንግሥት መሆን ይኖርበታል፡፡

  ይህን ማድረግ ሲጀምር ነው በክልሎች ውዝግብ ውስጥም ሆነ በልዩነቶች ውስጥ ዘርና ብሔርን እየለዩ ለማሳደድ መሞከርን፣ የንፁኃን ሕይወት ሕልፈትንና ንብረትን የማውደም አካሄድን መታገልና ማስቆም የሚቻለው፡፡ ብሎም ኢትዮጵያውያን ክፉንም ሆነ ደጉን በጋራ እያሳለፍን አንድነታችንን እያጠናከርን ለመሄድ የምንችለው፡፡ በመሠረቱ የትኛውም ፓርቲ፣ መንግሥትም ይሁን መሪ አላፊና ጠፊ ነው፡፡ ሕዝብ ግን ዘለዓለማዊና ለመቼውም ቢሆን አብሮ የሚዘልቅ ነው፡፡ ይህን በተለይ ኢትዮጵያውያን ከማንም በላይ ጠንቅቀን የምናውቀው ሀቅ ሆኖ ሲያበቃ፣ መግፋት ለማንም የማይበጅ አፀያፊ ተግባር መሆኑን በመገንዘብ በጋራ መቆም እንደ ዜጋ የሚጠበቅብን ኃላፊነት ነው፡፡

  ይህ አካሄድም ሕገ መንግሥቱ ካበረከታቸው ወርቃማ ድሎች ዋና የሆነውን  የአገሪቱን ሰላም ለመጠበቅ የሚያስችል መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለሆነም በዘርና በብሔር ላይ ካነጣጠረ ዘመቻም ሆነ ከማንኛውም ሕገወጥ እንቅስቃሴ በመውጣት፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ኅብረት የመሰለውን ትልቅ የጋራ አገራዊ እሴት እንደ ሕዝብ በጋራ እንዴት ጠብቀን እናስቀጥል? ብለን መነሳት ይኖርብናል፡፡ አሁን ያለችው  አገራችን ልማቷ ቢኖርም (እሱም እየተቀዛቀዘ መምጣቱ ይታወቃል) በአንድ ጊዜ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በግጭት የሚሞቱባትና እርስ በርስ የሚጠቃቁባት እየሆነች መሆኑ ሁሉንም ወገን ሊያስቆጭ ይገባል፡፡ በተለይ መንግሥትን ሁሉን አቀፍና ፈጣን የለውጥ ዕርምጃና ማሻሻያ እንዲወስድ የሚያስገድድ ነባራዊ ሀቅ ነው፡፡

  በመሠረቱ እንደ አገር የሁላችንም የራዕያችን፣ የዕድገታችን፣ የአንድነታችን፣ የመሠረተ ልማታችን፣ የሰብዓዊ ብልፅግናችን ዋልታና ማገሩ ሰላም መሆኑን  መገንዘብም ያስፈልገናል፡፡ ራሱ ፌዴራላዊ ሥርዓቱን ለማጠናከርና ክፍተቱን ለመሙላትም ሆነ በሌላ በተሻለ ሥርዓት ለመቀየርም ሲታሰብ፣ አገራችንና ሕዝቦቿ በሰላም መርጋት አለባቸው፡፡ ሰላም ደፍርሶ፣ የተደከመበት ሁሉ ጠፍቶና እርስ በርሳችን እየተጠቃቃን ወደ ኋላ ከተመለስን እንደ አገር ቀና ለማለት እንኳን መቸገራችን አይቀሬ ነው፡፡ ይህን እውነታ ደግሞ ከፖለቲከኛው የተሻለ የሚገነዘበው ይኖራል ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ እስካሁን እንደሚታየው የፌዴራል ሥርዓቱ ከመጣ ወዲህ በትንንሽና መለስተኛ  ጉዳዮች (ትልቁን አገራዊ ሥዕል ወደ ጎን በመተው) በአንድ በኩል አንዱ ክልል ከሌላው ክልል ጋር የሚፈጥረው ግጭት አለ፡፡ በሌላ በኩል በዚያው በአንድ ክልል ውስጥ በሚገኙ ጎሳዎች መካከል የሚፈጠር ግጭትም እየታየ ነው፡፡ ይህ በተለያዩ ብዝኃነት እንደ ሞላባቸው አገሮችም እንዳለው በውኃ፣ በእንስሳት ግጦሽ ወይም በኢኮኖሚ ጥያቄ የተፈጠረ ቢሆን ምንም ማለት አልነበረም፡፡

  በአንድ ሰንደቅ ዓላማና በአንድ ሉዓላዊ ግዛት ሥር ዛሬ ሳይሆን፣ ለዘመናት እርስ በርሳችን ተሳስረን የኖርን ሕዝቦች መሆናችን እየተረሳ ግን፣ ፖለቲካን ከብሔር ጋር በማጋመድ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ የማይፈቅደውን አንዱ ገዥ ሌላው ተገዥ እንደሆነ በማስመሰል በንፁኃን ላይ ጉዳት የሚያደርስ ዕርምጃ እንዲንሰራፋ ማድረግ በታሪክም የሚያስጠይቅ፣ ከኢትዮጵያውያን የሞራልና የእምነት ፀጋም የሚያስወጣ ተግባር ነው፡፡ በዚህ ረገድ እንደ ሕዝብ በተለይም እንደ ወጣት በሁሉም አካባቢ ብርቱ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ በእርግጥ ይህን ድርጊት ሊያርም የሚችለው መንግሥት ብቻ ሳይሆን ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ ሚዲያውና ሌሎችም መሆን ሲገባቸው ሁሉም በዝምታና በምንቸገረኝነት ስሜት ዝምታን መምረጣቸው ሊወገድ የሚገባው አስተሳሰብ ነው፡፡

  በመሠረቱ የአገር አንድነቱ እንዲዳከምም ሆነ ፌዴራሊዝሙ እንዲሸረሸር አንዳንድ ክልሎችና አመራሮቻቸው አሉታዊ ሚና እንዳላቸው እየታየ ነው፡፡ አሁን ባለው የእኛ አገር ሁኔታ የግጭቶቹ ሰበቦች ምንም ይሁኑ ምን (ዋነኛው ፖለቲካ ፍላጎት እንደሆነ ባይካድም) ለመከላከልና ለመፍታት በፌዴራሉ መንግሥት እገዛ ክልሎች  ብዙ መሥራትና ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ማዶና ማዶ ቆሞ መወዛገብ ‹‹እነዚህ ሰዎች ዕውን በአንድ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ ሥር ናቸውን?›› እስኪያስብል ድረስ እየተካረሩ መግለጫ ማውጣትና የሕዝብ ግጭትን ማባባስ ከታሪክና ከሕግ ተጠያቂነት ለማምለጥ አያስችልም፡፡ ትዝብት ላይ የሚጥል ኢሞራላዊ ተግባርም ነው፡፡ ትግል መደረግ ካለበት ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ለማስፈን ብሎም አገራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ መሆን አለበት፡፡

    በአጠቃላይ በአገራችን የሕዝብ አንድነት ተዳክሟል ብቻ ሳይሆን ታውኳል፡፡ በጣም ትንሽ የምትመስለን የአካባቢ ግጭት ወይም የሰላም መደፍረስ መዘዟ እጅግ በጣም ከፍተኛ እንደሆነ እየተሰማን ያለው ደግሞ ብሔር ተኮር መልክ እየያዘ በመምጣቱ ነው፡፡ በየአካባቢው ያለው የሰላም መደፍረስ የተከበረውን የሰው ልጅ ሕይወት ይቀጥፋል፣ አካል ያጎድላል፣ የተደከመበትን የሕዝብና የግል ሀብትም እንዳይሆን ያደርጋል፡፡ ብሎም ወደ መበታተንና መዳከም ይከተናል፡፡ ይህ እንዲሆን አለመፍቀዳችንን እንደ አገር ማረጋገጥ ያለብንም በዋናነት መንግሥትና ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ሊሆኑ ይገባል፡፡ በመቀጠል ሕዝቡ ራሱም ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ከዘረኝነትና ከጥላቻ ወጥቶ አገራዊ አንድነት መገንባት አለበት፡፡ አገራዊ ዕርቅና ብሔራዊ መግባባትን ሳንፈራ ለማምጣት መረባረብ አለብን፡፡ ይህ ሲሆን ፌዴራሊዝሙን ለተሻለ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ለማዋል የሚከብድ አይሆንም፡፡

  በሌላ በኩል ለመንግሥትም ሆነ ለሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በግልጽ መነገር ያለበት እልህ፣ መካረርና ጥላቻ ወይም እኔ ብቻ ነኝ የማውቀው የሚለው የማይበጅ የፖለቲካ አካሄድ መስተካከል እንዳለበት ነው፡፡ ይልቁንም ሁሉን አቀፍ በሆነ ተሳትፎ በአገራችን ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ሁሉ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ መሳተፍና የየራስን በጎ አስተዋጽኦ ማበርከት ይበጃቸዋል ይበጀናል፡፡ መቼም ይህን በጎ ተግባር በአንድነትና በመተማመን አለመፈጸም ጎረቤት ሶማሊያና ደቡብ ሱዳንን ወይም አለፍ ብሎ ሊቢያን ብቻ ሳይሆን፣ የመካከለኛው ምሥራቆቹን አፍጋኒስታን፣ ኢራቅ፣ ሶሪያና የመንን ለመሆን እንደመመኘት የሚቆጠር ነው፡፡ ስለሆነም ግጭትን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ባይቻል እንኳን፣ በጣም መቀነስ፣ መደማመጥና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ብሎም ከጠባብነት የተላቀቀ ጠንካራ ኅብረትን ሳንወድ በግድም ቢሆን ከወሬ በላይ መገንባት ያስፈልገናል፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...