[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሀብት ደወለላቸው]
- ምን እየተሠራ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ሪፎርም ነው፡፡
- የምን ሪፎርም ነው?
- እንደምታውቀው በአገራችን ውስጥ ከፍተኛ ሪፎርም እየተካሄደ ነው፡፡
- አገሪቱ እኮ ከድጡ ወደ ማጡ እየሄደች ነው፡፡
- ምን ማለት ነው?
- በፊት በሥርዓቱ መሥራት እንችል ነበር፡፡
- መስረቅ ነው ያልከው መሥራት?
- ምን ማለት ነው?
- እናንተ በሥርዓቱ ስትሰርቁ እንጂ ስትሠሩ አልነበረም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኔ ልማታዊ ባለሀብት ተብዬ ስንት ጊዜ እንደተሸለምኩ ያውቁ አይደል እንዴ?
- ምን?
- እንዲያውም ሽልማቶቹን የማስቀምጥበት አጥቼ ቢሮዬን ሦስት ጊዜ ነው አፍርሼ የሠራሁት፡፡
- የስርቆት ሽልማት ነዋ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ ልማታዊ ባለሀብት ነኝ?
- በቀድሞው ሥርዓት ልማታዊ ባለሀብት ማለት ምን ማለት እንደሆነ አታውቅም እንዴ?
- ምን ማለት ነው?
- ልማታዊ ሌባ ማለት ነው፡፡
- ይኼን አልቀበልም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እናንተ ሀብት የምታሸሹ ሌቦች ናችሁ እኮ?
- ውጭ ገንዘብ የምናስቀምጠው እኮ የአገሪቱን ሀብት ለማሸሽ ፈልገን አይደለም፡፡
- ታዲያ ለምንድነው?
- ያው ጤናችን ችግር ስለሆነ ከእንቅልፍ ስንነሳ ወገብ አልሠራ ሊል ስለሚችል ለሕክምና ብለን ነው፡፡
- በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ከአገር የምታሸሹት ለሕክምና ነው?
- ክቡር ሚኒስትር ከሕክምናው ባሻገር መዝናናት አለ፣ ሾፒንግ አለ፣ ከዚያም በላይ የልጆች ትምህርት ቤት ክፍያ አለ፡፡
- ልጆችህን እዚህ ለምን አታስተምርም?
- እንዳይማሩማ የትምህርት ፖሊሲውን ገደላችሁት፡፡
- እንዴት?
- ክቡር ሚኒስትር እኔ እስከ አራተኛ ክፍል ነው የተማርኩት፣ ቢያንስ ልጆቼ ደህና ትምህርት ያግኙ ብዬ ነው ውጭ ልኬ የማስተምራቸው፡፡
- ለዚህ ነው እዚህ የማታስተምራቸው?
- እዚህ ያሉት ዩኒቨርሲቲዎች እኮ ልጄን መደባደብ ነው የሚያስተምሩት፡፡
- አንተ ውጭ ልከህ ሌብነት አስተምረህ ታመጣዋለህ?
- ስነግርዎት መቼም ቢሆን ልጄን እዚህ አላስተምርም፡፡
- ለማንኛውም አሁን አንድ ነገር አስታወስከኝ፡፡
- ምን ክቡር ሚኒስትር?
- ስለሕክምና ስታወራ አንድ መድኃኒት እፈልግ ነበር፡፡
- በእርግጠኝነት እዚህ አጡት ልበል?
- መድኃኒቱ በጣም ውድ ሆነብኝ፣ በዚያ ላይ ትክክለኛነቱ ስላጠራጠረኝ እንድትረዳኝ አስቤ ነበር፡፡
- ምን ልርዳዎት?
- ያው አንተ በየጊዜው ከአገር ስለምትወጣ ለምን አታመጣልኝም?
- የሞቀው ሙቅ ያኝካል አሉ፡፡
- ምነው?
- ብረዳዎት ደስ ይለኝ ነበር ግን አዝናለሁ፡፡
- ምነው?
- ዛሬ አደዋወሌ እኮ እሱን ላረዳዎት ነበር፡፡
- ምኑን?
- መውጣት ተከልክያለሁ፡፡
- ከየት?
- ከአገር!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ የፓርላማ አባል ይደውልላቸዋል]
- ኧረ ከጉድ ያውጡኝ ክቡር ሚኒስትር?
- የምን ጉድ?
- የማይሆን ስህተት ነው የሠራሁት፡፡
- የምን ስህተት ነው?
- በአቻዎቼ ግፊት ነው የተሳሳትኩት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አንተን የሚያህል ሰውዬ ደግሞ በግፊት ይሳሳታል እንዴ?
- ግራ ነው እኮ የሚገባው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- መጠጥ አጠጥተውህ ነው ወይስ ድራግ አስወስደውህ?
- እሱ ይሻል ነበር፡፡
- ምን ሆነህ ነው ታዲያ?
- ተዋረድኩልዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ሆነህ?
- ይኸው ሕዝቡ በቲቪ ተመለከተኝ፡፡
- ምን ስታደርግ?
- ለተቃውሞ እጆቼን ሳወጣ ነዋ፡፡
- የት?
- እዚያው ፓርላማ ነዋ፡፡
- ምን እያልከኝ ነው?
- በቃ እንቅልፍ መተኛት አቃተኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይኼን ያህል?
- ክቡር ሚኒስትር የደወልኩት እኮ የእንቅልፍ ኪኒን እርስዎ ጋ አይጠፋም ብዬ ነው፡፡
- ስማ አሁን እንቅልፍ የለም ጊዜው የሥራ ነው፣ ከፈለግክ ግን አንድ ሁለት ካርቶን ኪኒን አለኝ፡፡
- እርስዎ ኪኒኑን መውሰድ ተው እንዴ?
- ያኔ በምንሰርቅበት ወቅት ነበር የምንወስደው አሁን ተደምረናል፣ ሌብነት ትተናል፣ ሌት ተቀን ነው የምንሠራው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኔ እንደ አባት እንዲመክሩኝ ነው የምፈልገው፡፡
- ምን ልምከርህ?
- እንቅልፍ ነሳኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምኑ?
- ሳልፈልግ ነው ክቡር ሚኒስትር፣ እዚያ ያሉ የእኛ ፓርቲ ሰዎች እንድቃወም የገፋፉኝ፡፡
- ታዲያ ምኑ ነው ያስጨነቀህ?
- በቃ በቲቪ ስለታየሁ ሕዝቡን ፈራሁት፡፡
- ዛሬ ተቃውመክ ነገ ደግሞ ልትደግፍ ትችላለህ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ወላዋይ ነው እባላለሁ፡፡
- ይኼ እኮ መወላወል አይደለም መቃወም መብትህ ነው፡፡
- እኔ ግን በጣም ነው የጨነቀኝ፡፡
- ምን ነካህ ለወከልከው ሕዝብ ይጠቅማል የምትለውን ውሳኔ መወሰንህ የአንተ ዴሞክራሲያዊ መብት ነው፡፡
- እሱስ እውነትዎትን ነው ግን የድሮው ሥርዓት አባዜ አሁንም አለቀቀኝም፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- በድሮው ሥርዓት እኮ የተቃወመ ሰው ምን እንደሚደረግ ያውቃሉ?
- አሁን መቃወም ፍፁም ዴሞክራሲያዊ መብትህ ነው፡፡
- እሱን ግን መቀበል አቅቶኛል፡፡
- ለምን?
- ከዛሬ ነገ ይነሳል ብዬ በሥጋት ውስጥ ነኝ፡፡
- ምኑ ነው የሚነሳው?
- ያለመከሰስ መብቴ!
[ከሰሞኑ ኩባንያቸው ከታገዱባቸው ባለሀብቶች መካከል አንዱ ደወለላቸው]
- ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
- ምኑ?
- ምን እየሠራችሁ ነው?
- ለውጡን እያሳለጥነው ነው፡፡
- እኮ ለውጡ ወዴት እያመራ ነው?
- ወደ ሰላም፣ ዕድገትና ብልፅግና ነዋ፡፡
- አልመሰለኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ማለት ነው?
- አሁንም ዕገዳ፣ እስር ምናምን አልተዋችሁም እንዴ?
- አልገባኝም?
- ጊዜው የፍቅርና የመደመር ነው እያላችሁ አይደል እንዴ የምትደሰኩሩት?
- የምንደመረው እኮ ከትክክለኛ ኢትዮጵያዊና ቅን አመለካከት ካለው ጋር ነው፡፡
- ግማሹን ደምሮ ግማሹን መቀነስ ምንድነው?
- ከሌባውና ከአጭበርባሪው ጋር እንድንደመር ጠብቀህ ነበር?
- ሁሉም እኮ ለአገሩ የተቻለውን አድርጓል፡፡
- እዚህ ላይ እንዳትሳሳት፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- እንደፈለገ ሲዘርፍና ሲያዘርፍ ቆይቶ ተጠያቂነት ሲመጣ ለሕዝብ ስል ነው ያደረግኩት ቢል ተቀባይነት የለውም፡፡
- እሱማ ልክ ነው፡፡
- ስለዚህ ሌባውና አጭበርባሪው እስር ቤት መደመር ይችላል፡፡
- ይህ ግን የሚያዋጣ መንገድ አይመስለኝም ክቡር ሚኒስትር?
- አዋጪው ብቻ ሳይሆን አማራጭ የሌለው መንገድ ይኼ ብቻ ነው፡፡
- ምነው እንደዚህ አመረራችሁ?
- ከዚህ በላይ ሕዝቡ ላይ ሲቀለድ መመልከት አንችልም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኛም እኮ ሕዝብ ላይ መቀለድ አንፈልግም፡፡
- ለመሆኑ ምን ፈልገህ ነው?
- ይኸው ድርጅቴ ታግዷል፡፡
- ለምን?
- ከሕገወጥነት ጋር በተገናኘ ምርመራ እየተደረገብኝ ነው፡፡
- የምን ሕገወጥነት?
- እንደሚያውቁት ክቡር ሚኒስትር የሕዝቡን የቤት ጥያቄ ለመመለስ ብዬ ከምሠራቸው ሥራዎች አንዱ የሪል ስቴት ዘርፍ ነው፡፡
- እሺ?
- እናም ስንትና ስንት ሺሕ ሠራተኞችን ቀጥሬ የማሠራበት ድርጅት ታግዶ እየተጣራ ነው፡፡
- ታዲያ በማጣራቱ ንፁህ ከሆንክ ሥራህን ትቀጥላለህ፡፡
- ካልሆንኩስ ክቡር ሚኒስትር?
- ካልሆንክማ ተገቢውን ቅጣት ታገኛለህ፡፡
- ምን ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር? እኔ እኮ ውጤታማ ድርጅት ነው ያለኝ?
- እኮ ውጤታማ መሆን ያለብህ በሥራህ ነው እንጂ በሌብነት መሆን የለበትም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ያችን ዝነኛ አባባል ረሷት ማለት ነው?
- ምን ነበረች?
- ከእያንዳንዱ ውጤታማ ድርጅት ጀርባ…
- እ…
- አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን አለ!
[አንድ ጡረታ የወጡ አንጋፋ ፖለቲከኛ ለክቡር ሚኒስትሩ ደወሉ]
- ሥልጣን የተመችዎ ይመስላል ክቡር ሚኒስትር?
- ምን አሁን ሥራ በዝቶ መላወሻ የለንም፡፡
- እንዴት?
- አለቃችን የዋዛ አይደሉም ቅዳሜ አይሉ እሑድ 24 ሰዓት እንደ ማሽን ነው የምንሠራው፡፡
- ሙሉ ለሙሉ ተደምረዋላ?
- በቃ ማኅበራዊ ሕይወት የለ ዝም ብሎ እንደ ጀርመን ማሽን ሥራ ብቻ ነው፡፡
- እርስዎም የቀድሞውን ሥርዓት እያጣጣሉ አሁን ነው ሥራ የተጀመረው እያሉኝ ነው?
- ምን ጥያቄ አለው?
- ይኼ ሁላ ሾው ግን ምንድነው? ማስፈራሪያ ነው ወይስ ድንፋታ?
- አልገባኝም?
- መንግሥት ሥራው ሰርከስ መመልከት ነው?
- ምን ነካህ ወዳጄ ወታደራዊ ኃይልን ማሳየት እኮ በየትኛውም አገር የተለመደ ነው፡፡
- እኛ እንደ ማስፈራሪያ ነው የተመለከትነው፡፡
- እናንተ ደግሞ ያልጣማችሁን ነገር ማብጠልጠል ታውቁበታላችሁ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እርስዎ እኮ የእኛን ጥቅም ያስጠብቃሉ ብለን እናስብ ነበር፡፡ እንደዚህ መባባል ጀመርን?
- እኔ የሕዝብን ጥቅም ላስጠብቅ ነው የቆምኩት፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ከዳተኛ መሆንዎ አይገርምም፡፡ በፊት ከእኛ ጋር እያሉ ከእኛ ጋር ያጨበጭቡ ነበር፡፡
- እናንተ ግን በማጨብጨቡ ቀጠላችኋ? እኔ ግን ጭብጨባውን ትቼ ወደ ሥራ ገባሁ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ይኼ ሁሉ ድንፋታ ግን አስፈላጊ አልነበረም፡፡
- የተለያዩ ባለሥልጣናት ላይ እኮ የደኅንነት ሥጋት ስላለ እሱን ለመመከት ነው፡፡
- የሚያሳዝነው ያ ሁሉ ጀበና ሲያልቅ ዝም ተብሎ መታየቱ ነው፡፡
- ቆይ ቆይ እርጅና ነው ወይስ የለቀቀ ብሎን አለ?
- ይኼ ከእርጅና ጋር የሚገናኝ አይደለም፣ እናንተ ለአገር ሀብት እንጨነቃለን ትላላችሁ አይደል?
- በሚገባ እንጂ?
- ታዲያ ያ ሁሉ ጀበና ሲያልቅ ዝም ማለታችሁ ያሳዝናል፡፡
- እንግዲህ እንደለመዳችሁት ፍትሕ ለጀበናም ብላችሁ ሠልፍ እንዳትወጡ?
- እኛማ የምናደርገውን እናውቃለን፡፡
- ምን ልታደርጉ?
- በሚቀጥለው ምርጫ በሙሉ ኃይል ተደራጅተን እንመጣለን፡፡
- ምን ለመሆን?
- ተቃዋሚ ፓርቲ ሆኖ ለመወዳደር፡፡
- ይቅናችሁ፡፡
- እንዲያውም የምርጫ ምልክታችን ምን እንደሚሆን ያውቃሉ?
- ምን?
- ጀበና!