Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  ሞኝ አህያ ጅብን ካልሸኘሁ ይላል!

  ሰላም! ሰላም! የዛሬ ጨዋታዬን ስጀምር በውስጠ ዋቂ ማንጠግቦሽን አምቼ ለመጀመር ነበር ሐሳቤ። ዳሩ ‘አይኤስ በመባል ይጠራ የነበረ የአረመኔና የወሮበላ ስብስብ በውስጠ ታዋቂነት የኃያላን አገሮች ድጋፍ ይደረግለት ነበር’ የሚል ወሬ በአንድ ወቅት ሰምቼ ስለነበር ውስጥ ለውስጥ መሄዱን ሰረዝኩት። ምነው ዕቅድ መሰረዝ በእኔ ተጀመረ እንዴ? ይልቅ በአሉባልታ ጋጋታ ያሰብነውን ስንዞር ከምንኖር ምናለበት አላስኖር አላሠራ ያለንን የጥፋት ጎዳና መሰረዙ ላይ ወኔ አጣን? የምር እኮ ነው። ቀልዴን አይደለም። ወኔ ስላችሁ ታዲያ አደራ መወራጨት አላልኩም። አጉል በመወራጨት ሰሞኑን ሲፎክሩ ከሰማናቸው የአገር መሳቂያ ከሆኑት ጉረኛ ፖለቲከኛ ተብዬዎች ካልተማርን ከማን እንማራለን? አይደል እንዴ? አዎ። ‘ውቀት እንዲህ በበዛበት፣ ‘ኢንፎርሜሽን’ በሽ በሆነበት ዘመን ተነጋግሮ፣ ተደማምጦና ድጡን አፈር ማልበስ እንዴት ሊሳነን ቻለ?’ ነው እያልኩ ያለሁት። ይኼን ብዬ ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ስጠያየቅ፣ ‹‹እንጃ ምናልባት ከዕውቀት ይልቅ ‘አዋቂ ነኝ’ ባዩ በዝቶ ይሆናላ!›› አለኝ። ባልዞርኩበት የሚያዞረኝን፣ ባላማተርኩበት የሚያስቃኘኝን ብሩህ ጭንቅላቱን ብወድለትም፣ ድምፁ ውስጥ የሚደረበው የመሰልቸትና ተስፋ የመቁረጥ መንፈስ አሁን አሁን ቅር ያሰኘኛል። እውነት እውነት እላችኋለሁ ሰው በገዛ አገሩ ተስፋ ሲቆርጥ ይከፋኛል፡፡

  ቆይ ተስፋ በመቁረጥና ሐዘን በማብዛት እንኳን አገር የወደቀ ዕቃስ ይነሳል? እሱን ነዋ የምላችሁ። ውበት እንደሚያረጅ፣ ሕልም እልም እንደሚል፣ ዕድሜ እንደሚያከትም በየደቂቃው ማወቅ ቢኖርብን ኖሮ እንደ ግድግዳ ሰዓት ልባችን ላይ ‘ትክ ትክ’ የሚል መዘውር አይኖረንም ነበር? ይኼ በፈጣሪ ሥራ መግባት ነው ካላችሁኝ ወደ ሰው ሥራ ልመለስና ባለችን አጭር ዕድሜ ለአገርና ለትውልድ እንደ መረባረብ፣ በታሪክ የሚያስጠራ መልካም ሥራ ሠርቶ ለማለፍ እንደ መሻማት ምንድነው የታሪክ አተላ ለመሆን እያንገበገበን ያለው? በበኩሌ ትናንት ላይ ቆሞ ዛሬ ላይ መተኛት፣ ከታሪክ አለመማር፣ ታጥቦ ጭቃ መሆን፣ በዛገ አስተሳሰብ አገር ማተራመስና የትውልድ መሳቂያ ሆኖ መወገዝ የሚያዛልቀን መስሎ አይሰማኝም። ያውስ የመናገር ነፃነት በሕግ ዕውቅና በተሰጠበት ጊዜ ድርጊትንና ንግግርን አለማሳመር ከውግዘት የሚያድን ይመስላችኋል? አደራ ደግሞ እንዲህ አልክ ብላችሁ እያንዳንዳችን ንግግር የምናደርግበት ሠልፍ ካልተጠራን እንዳትሉ እንጂ ሌላውስ ሌላ ነው!

  እንዴት መሰላችሁ? እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ዝም ብዬ ሁኔታችንን ሳየው በተጨባጭ ካሉብን ችግሮቻችን በላይ እያሰቃየን የተቸገርነው፣ በፍፁም ራስ ወዳድነት ክፉ የአጥፍቶ መጥፋት ስሜት ራሳችንን አግዝፈን ወገናችንን ማኮሰሳችን ነው። ምንም እንኳን ደላላ ብሆንም ይኼ ዓይነቱ ያፈጠጠና ያገጠጠ ድርጊታችንን እፀየፈዋለሁ። እስኪ መቼ ዕለት የገጠመኝን ልንገራችሁ። አንድ ወዳጄን፣ ‹‹እኔስ ሰውን ወደ ውስጥ ሲተነፍስ ሳየው ግራ እየገባኝ ነው። ለመሆኑ ትናንት ያ ደንበኛችን ያችን ከርካሳ አይሱዙ ሲገዛ ጓደኞቹን አስተውለሃቸዋል?›› አልኩት። ለጥገና ብዙ ወጪ የሚያስፈልጋት አይሱዙ ሳሻሽጥ አብሮኝ ነበር። ‘ከመሰደድ በአገር ርቶ መክበር’ የሚለውን የከረመ መፈክር ለማድመቅ መኪና ገዝቶ ዕቃ የማጓጓዝ ሥራ ለመሥራት ስላሻሻጥኩለት ደንበኛዬ ነበር የማወራው። ይገርማችኋል እንደዚያን ቀን ደላላ መሆኔ ያስጠላኝን ቀን አላስታውስም።

  በልጁ አገር ውስጥ ሠርቶ የመኖር ሞራል የተነሳ ከዚያች ጣጠኛ አይሱዙ ሌላ አማራጭ ልፈልግ ላይ ታች ብያለሁ። አላገኘሁም። እናም የነበረኝ ተስፋ ጓደኞቹ ከአሁን አሁን ‘ይኼማ አይሆንም! አተርፋለሁ ብለህ በየጋራዡ ገንዘብህን ልትጨርስ ነው እንዴ?’ ምናምን ብለው ያስተውታል እያልኩ በጉጉት ተጠባበቅኩ። ምስኪኑ ወጣት ደንበኛዬ ከቤተሰብ የአብሮ አደግ ሐሳብ ይሻላል ብሎ ሰብስቦ ያመጣቸው ጓደኞቹን በተደጋጋሚ ‹‹እንዴት ይሻላል?›› ይላል። ‹‹አሪፍ ነው!›› አንዱ። ሌላው ደግሞ፣ ‹‹ዋናው ልብህን ማዳመጡ ነው። ከወደድከው ይሆነኛል ካልክ ግዛው፤›› ይላል። ‹‹አሁን ይኼ ምን ዓይነት ምክር ነው? ‘ቲሸርት’ መሰላቸው የሚገዛው? ‘ኢንቨስት’ እያደረገ እኮ ነው፤›› ብዬ በንዴት ስጦፍ ወዳጄ፣ ‹‹አንተ ምን አገባህ ከተሸጠልህ?›› እያለ ትከሻውን ሲሰብቅ ነበር የዋለው። በኋላ ጥያቄዬን ሲመልስ፣ ‹‹አይ አንበርብር! ስንት ነገር አለ? ኋላ ‘እሱ ብሎኝ፣ እሷ አደፋፍራኝ ነው እዚህ ጣጣ ውስጥ የገባሁት’ ይመጣል። ‘የለም ሌላ ይፈለግ ተረጋጋ’ ብንለው ተመቅኝተው ቶሎ ሊያልፍለት ነው ብለው ይለናል ፍራቻም ይሆናል። ዘንድሮ ጥግህን ይዘህም አልሆነ እንኳን ተንቀሳቅሰህ፤›› ብሎ መለሰልኝ፡፡ በዚህ አያያዛችን ገና በአራቱም ማዕዘናት ላንሰደድ ነው? እንዲህ እያሰብን ነው እንዴ አንድ ላይ የምንቆመው?

  - Advertisement -

  ከባሻዬ ጋር ጊዜ አግኝተን ቡና ስንጠጣ ይኼን አሉባልታና ሽሙጥ ያጦዘውን ፊት ለፊት ‘አካፋን አካፋ’ ብሎ የመናገር ድፍረት ማጣት አነሳሁ። ‹‹አይ ልጅ አንበርብር. . .›› ብለው ቡናቸውን እያጣጣሙ ትንፋሽ ይስባሉ። ትንፋሽ ሲሰበስቡ ደስ አይለኝም። አንድም ‘ልጅ አንበርብር’ ብለው ሲጀምሩ ካልገባኝ ካልተረዳሁት ስለሚጀምሩ፣ አንድም ብዙ ስለሚናገሩ በአጭሩ ማጠቃለያ ሐሳቡን ማደራጀት ስለሚከብደኝ ነው። ግን አዳምጣለሁ። ‹‹እውነቱን ሲነግሩን መቼ እንዲህ ዋዛ ነን? ተርብ እኮ ነን። ወዶ መስሎህ ነው ሰው የተፈራራው? ደግሞ ነገር ያልተፈራ ምን ይፈራል? ስትናገር በቀና ልቡና ለማለት የፈለግከውን አጣሞ ‘እከሌ ልኮት’ ነው!’፣ ‘እሱ ስለደላው ነው!’ ካለህ ዓይቶ እንዳላየ ከማለፍ ውጪ፣ ዞሮ ከማማት በቀር፣ ከዝምታስ ሌላ ምን መሸሻ አለህ? ንገረኝ እንጂ?›› ብለው ያፈጡብኛል። ‹‹እሱማ የሰው ተፈጥሮ አስቸጋሪ ነው፤›› ብዬ ዝም እላለሁ። ወዲህ ቢሉን ወዲያ እንከን አያጣንምና እንዳሉት ከዝምታ ውጪ መሸሻ አጣለሁ። ‹‹ግን እንዳልከው እንደ አገር በትክክለኛ መንገድ የምናድገው ፊት ለፊት ስንነጋገርና በገንቢ ሂስ ስናምን መሆን አለበት። ያ ደግሞ ከዕውቀት ብዛት ሳይሆን ከማስተዋል ነው የሚገኘው። ‘ጠቢብ ልጅ ተግሳጽ አይንቅም ምክርንም ገንዘቡ ያደርጋል’ የሚለው ቅዱስ መጽሐፉ አስተዋዮችን ነው። ይኼ ካልሆነ ግን አየህ ‘የሰው ዜማ ደግመህ አዚመህ አትመፃደቅ፣ ራስህን ሁን!’ ወይም ‘ከሁሉ በፊት ሰውን ማልማት ይቀድማል። በበጎ ልቦና የተቃኘ ንቃተ ህሊና የሌለው ዛሬ የተገነባውን ነገ ከማፍረስ ወደ ኋላ አይልም’ ስትል፣ ወይ ለስደት ወይ ለመወገር ራስህን ማዘጋጀት አለብህ፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹እንዲያ ሆኖ እንጂ ስንቱ ምሁር በሩን ዘግቶ ይቀመጥ ነበር?›› ሲሉ አጉተመተሙ። አይ ባሻዬ የእኔ ባይሆኑ መቼም ይቆጨኝ ነበር!

  የሆነው ሆነና በስንተኛው ቀን በሥራ ናውዤ ከአንድ ባለ ተሳቢና ባለሦስት መኝታ ኮንዶሚኒየም ቤት ሽያጭ የሚደርሰኝን ‘ኮሚሽን’ ተቀባብዬ ወደ ሠፈሬ አመራሁ። ሕፃናት ጨዋታ በሚያዘወትሩበት ሥፍራ አዝምሞ የነበረ ግንብ አንድ ብላቴና ላይ ተንዶ ጉዳት ደረሰበት። አያሳዝንም? ባሻዬ ስንት ቀን ዕድሩን እየሰበሰቡ፣ ‹‹የዚህ ግንብ አጥር ነገር አንድ ይባል፤›› ሲሉ መክረማቸውን አውቅ ነበር። ይኼው እሳቸው ከአደጋው በፊት መላ እንፍጠር ሲሉ፣ ‹‹ወር እስከ ወር ከማታቆየን ደመወዝ ላይ ደግሞ አዋጡ ሊሉን ነው?›› እየተባሉ ታምተዋል። ዛሬ ግን ከገንዘብ ለባሰ የሐዘን መዋጮ ያልተሰባሰበ የለም። መ ያልቃል የእኛ ጉድ! እኔም ጥጌን ይዤ በተቀመጥኩበት የባሻዬ ልጅ ሰተት ብሎ መጥቶ አጠገቤ ተቀመጠ። ባሻዬ ላይ አንደኛ አሳዳሚ የነበሩ ሰውዬ፣ ‹‹ለመሆኑ ይኼ ግንብ ዝም ብሎ የተናደ ይመስላችኋል? በበኩሌ የሰው እጅ ሳይኖርበት አይቀርም እላለሁ. . .›› ይላሉ። ባሻዬን ሲደግፉ ከነበሩት ጥቂት የመፍትሔ ሰዎች አንደኛው ቀበል አድርገው በምፀት፣ ‹‹ማለት? የአሸባሪዎች ማለትዎ ነው የወሬኞች?›› ይሏቸዋል። ‹‹የለም እንዲሁማ መርጦ ክፉና ደጉን ያለየ ሕፃን ላይ አይወድቅም። በራሱ ቢሆን ኖሮ ሌሊት አይደረመስም ነበር? ምን ነካችሁ?›› ይላሉ ግትሩ ሰው መልሰው። ባሻዬ በታላቅ ሐዘን ጋቢያቸውን ተከናንበው ተቀምጠው በሩቅ እመለከታቸዋለሁ። ‹‹ኧረ በቃ ዝም ይበሉ። ማንስ ቢገፋው ወዳቂ መሆኑን ዓይተን መዋጮ ፈርተን ልጁን ለጉዳት የዳረግነው እኛ፤›› ሲሏቸው ከጎናቸው የተቀመጡ በመንደሩ የታወቁ ሰው አንገታቸውን ደፍተው ዝም አሉ። ኃላፊነት የማይሰማቸው በዘባረቁ ቁጥር ለምን አንገት እስክንደፋ እንደምንጠብቅ እኮ ነው የማይገባኝ!

  በሉ እንሰነባበት። ከመሰነባበታችን በፊት አንዳንዴ እዚች መከዳዬ ላይ ደገፍ ብዬ በጥሞና የምታዘበውን ልንገራችሁ። ‘ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል’ ሲባል አይደል የምናውቀው? እናም ዝም ብዬ አልፎ ሂያጁን እየቃኘሁ ሳበጥረውና ሳዳምጠው ነገረ ሥራችን ሁሉ ይገርመኛል። እንግዲህ ጎዳናው ማለት እኛ፣ እኛ ማለት ጎዳናው ነን። መንገድ እኮ ከእነ ገመናችን ተዘርግፈን የምንታይበት መድረክ ማለት ነው (ይኼን እንድትቀበሉኝ ሼክስፒር ነው ያለው ማለት አለብኝ መሰል?)፡፡ መንገዱን ሳይ ታዲያ የሚታየኝ ቆሞ የሚያወራው ተራማጁን ሲያማና ሲኮንን፣ የሠራውን ሲያንኳስስ ነው። ጉረኛውም በርምጃው እየተመፃደቀ ቀርፋፋውን ሲንቅ፣ ሲያንጓጥጥ ነው የማየው። አፀፋ በመመላለስ የሚነጉደውን ጊዜ አለመቁጠር ይሻላል። መረጃ በመረጃ ላይ፣ ወሬ በወሬ ላይ፣ መርዶ በመርዶ ላይ እየተግተለተለ ሰው ቆም ብሎ ከራሱ የሚጠበቀውንና የድርሻውን መወጣቱን ሲዘነጋ ይታየኛል። በዚህ መሀል ታዲያ የሰው ልጅ ከንቱነት ገዝፎ ስመለከት የሽበት ዋጋ ያንስብኛል፡፡ ሽበት ማስከበሪያ መሆኑ ቀርቶ ግራ ገባን እኮ!

  በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኜ ወደ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ደወልኩ። የተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ተሰይሞ እየጠበቀኝ መሆኑን ነገረኝ። ስደርስ ከተለመደው ለየት ባለ ሁኔታ ጫጫታ አይሏል። ‹‹ምንድነው ዛሬ?›› ስለው፣ ‹‹ስማ!›› ብሎኝ እሱ ይስቃል። አንዱ መንግሥት ሕግ ማስከበር አቅቶታል ብሎ ይወቅጠዋል። ሌላው ደግሞ ትጥቅ አልፈታም ያለው ላይ የስድብ ናዳ ያወርዳል። እዚያ፣ ‹‹እሷ ከሄደች ጀምሮ ይኼው እንዳልሆን ሆኜ ቀረሁ፤›› ሲል ከጎኑ፣ ‹‹አንተ እንዲህ እስክትሆን ግን እሷ አልነበረችም?›› ሲል ያሾፍበታል። አጠገባችን ከተቀመጡት አንዱ ደግሞ፣ ‹‹ተው አንተ ፈጣሪ አግባባን? ምሕረትህን ላክ?›› ብሎ ሳይጨርስ፣ ‹‹ወይድ ማንን ነው የምትለምነው? እሱ ለራሱ ሥልጣን በቃኝ ብሎ ወደሚሄድበት ከሄደ ቆይቷል። እንደኛ እንደ ሥጋ ለባሾች የሥልጣን ጥማት ያለበት መሰለህ እሱ?›› ይለዋል ከጎኑ። ይኼን ከሚሰሙት አብዛኞቹ መዓት ፈርተው ይመስላል ሰውዬን በስድብ እያጥረገረጉ ሒሳብ ከፍለው ይወጣሉ። ‹‹ትዕግሥት፣ መደማመጥና መግባባት የሚባል እንዳልተፈጠረብን ምነው ይኼን ያህል?›› ስለው የባሻዬን ልጅ፣ ‹‹ገና ምኑን አይተህ? ዘመኑ እኮ የ‘ኮሜንት’ እና የ‘ፖስት’ እንጂ የማሰብና ‘እኔ ማን ነኝ? የድርሻዬን እየተወጣሁ ነው?’ ብሎ ከራስ ጋር የመታረቂያና የመናበቢያ አይመስለኝም፤›› አለኝ። ‹‹በተለይ በተለይ ‘መናበብ’ የሚለው አባባል ለጊዜው መሰጠኘ፡፡ መንግሥት እርስ በርሱ ካልተናበበ፣ ፖለቲከኞችም ሆኑ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እስከ ቤተሰብ ድረስ ካልተናበቡ እንዴት መሥራት ይቻላል? እስኪ እንዴት እንደምንናበብ እንምከርበት?›› ሲል አንዱ ከአጠገባችን ሌላው ከት ብሎ እየሳቀ በጭብጨባ በታጀበ ማሳሰቢያ፣ ‹‹አንዴ ስሙኝ!›› አለ፡፡ ምን ሊል ይሆን ብለን ቀና ቀና ስንል፣ ‹‹የመሰንበቻችንን ነገር ምን አስታወሰኝ መሰላችሁ? በሰላማዊ መንገድ አገርን ወደ ዴሞክራሲ ለመውሰድ በነፃነት የምንወዳደርበት ሜዳ እናመቻች ተብሎ በባሌ ሳይሆን በቦሌ የተቀበልናቸው ሲበጠብጡን አርፋችሁ ተቀመጡ መባል አለበት፡፡ አለበለዚያ ትዕግሥታችን ያለቀ ጊዜ ‹ሞኝ አህያ ጅብ ልሸኝ ይላል› ብለን ተርተን ልክ ማስገባት ይኖርብናል. . .›› እያለ ሲስቅ እኛም በሳቅ አጀብነው፡፡  ሞኝ አህያ የጅብ ሸኚ ከሆነ ከሳቅ ውጪ ምንም ማድረግ አይቻልማ፡፡  መልካም ሰንበት!                

  Latest Posts

  - Advertisement -

  ወቅታዊ ፅሑፎች

  ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት