Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፓርትየባለድርሻ ተግዳሮት ያነቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ

  የባለድርሻ ተግዳሮት ያነቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ

  ቀን:

  የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለአምስት ቀናት በአዲስ አበባ ስታዲዮም በክለቦች መካካል ሲያከናውን የሰነበተው የአጭር፣ መካከለኛ፣ ዕርምጃና የሜዳ ተግባራት ውድድር ታኅሣሥ 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ያጠናቅቃል፡፡ ውድድሩ በዋነኛነት ክለቦች የሚገኙበትን ወቅታዊ አቋም እንዲለኩ፣ እንዲሁም በቡድኖች መካከል ጤናማና ስፖርታዊ ጨዋነት የተሞላበት ውድድሮች እንዲያደርጉና ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በቀጣይ ለሚያዘጋጀው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ሠርተውና ተዘጋጅተው እንዲመጡ ቅድመ መመዘኛ መሆኑ በፌዴሬሽኑ የውድድርና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ አስረድተዋል፡፡

  ከረቡዕ ታኅሣሥ 17 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ውድድሩ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ የምትታወቅባቸው ረዥም ርቀት (የትራክ ውድድሮች) በታላላቆቹ የውድድር አዘጋጅ ማናጀሮችና አገሮች ምክንያት በጊዜ ሒደት ትኩረት እያጡ መምጣቸውን ተከትሎ፣ በአጭርና መካከለኛ ርቀቶች ተፎካካሪ አትሌቶችን ማፍራት ይቻል ዘንድ ያለመ እንደሆነም የሚናገሩ አሉ፡፡ ዳይሬክተሩ ይህንኑ እንደሚስማሙበት ገልጸው፣ የአጭር ርቀት መካከለኛ ርቀትን፣ መካከለኛ ደግሞ ወደ ሚቀጥለው የውድድር ተሳትፎ ቅብብሎሽን ጠብቆ እንዲሄድ ያግዛል ብለው እንደሚያምኑ ያስረዳሉ፡፡

  በቀጣይ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ጨምሮ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች፣ ክለቦችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉም ድርሻ ድርሻውን ወስዶ እንዲሠራ ለማድረግ ጭምር መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊው፣ ‹‹የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቀጣይነቱ መረጋገጥ ካለበት ብቸኛው አማራጭ ይህና ይህ ብቻ ነው፤›› ይላሉ፡፡

  እንደ ኃላፊው በዚህ ውድድር ከተሳታፊ አንፃር እንኳን ቢወሰድ ከ25 ክለቦች የተውጣጡ 406 ወንዶችና 299 ሴቶች ተሳትፎ ማድረጋቸው፣ ለቀጣዩ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ተሳታፊዎችን ለመለየት የመግቢያ ሰዓት (ሚኒማ) እንዲኖር አማራጮችን የሚያሰፋ መሆኑ ብቻ ሳይሆን አትሌቶችም የተሻለ ብቃትና አቋም ይዘው እንዲመጡ የሚያግዝ መድረክ ነው፡፡ በቀጣይ አገር የሚወክሉ አትሌቶች ምርጫ የሚደረግበት መድረክም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

  ኢትዮጵያውያን ከረዥም ርቀትና ማራቶን ውጪ በአጭርና መካከለኛ ርቀት ውጤታማ አለመሆናቸውን በመጥቀስ የሚከራከሩ አሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ስታዲዮም ሲካሄድ የሰነበተው የአጭርና መካከለኛ ርቀት ሻምፒዮና ፋይዳው ምንድነው? ለሚለው አቶ አስፋው፣ ‹‹በቅርቡ በአኅጉር ደረጃ አልጀሪያና ናይጀሪያ ላይ ተከናውኖ በነበረው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በአጭር ርቀትም ሆነ በሜዳ ተግባራት ተስፋ ሰጪ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ ይህ የሚያሳየው ብሔራዊ ፌዴሬሽን እንደ ፌዴሬሽን፣ ክልሎች እንደ ክልል፣ የከተማ አስተዳደሮችና ክለቦች ሁሉም ድርሻውን አውቆ ከታች ጀምሮ በጋራ ብንሠራ በዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚወክሉ አትሌቶችን ማፍራት እንደሚቻል እምነቱ አለኝ፡፡ ምክንያቱም ሀብቱ አለ፣ ችግሩ በሁሉም ረገድ ክለቦችን አዋቅሮ በሁሉም ዲሲፕሊን አትሌቶችን እየያዝን አይደለም፡፡ የሜዳ ተግባራትን ብዙዎቹ ክለቦች ቡድን የላቸውም፡፡ ይህ ባልተሟላበት ውጤታችን እንዲህ ስለሆነ ብለን ድምዳሜ ላይ መድረስ ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም ያለንን አቅምና ሀብት አሟጠን እየተጠቀምን ስላልሆነ፤›› ብለው በምሳሌነትም አሁን ላይ ኢትዮጵያውያኑ በዕርምጃ ውድድር ከተፎካካሪነትም አልፈው ውጤት ማስመዝገብ መጀመራቸውን ያብራራሉ፡፡

  ‹‹ፌዴሬሽኑ በአራቱ ክልሎች ለሚገኙ ፕሮጀክቶች መደገፍ በሚገባው ልክ እየደገፈ ነው፡፡ ሙሉ ትጥቅ ይሰጣል፣ የአሠልጣኞች ወርኃዊ ደመወዝ እስከ 6,000 ብር ክፍያ ይፈጽማል፡፡ ለአትሌቶች የላብ መተኪያ ይከፍላል፡፡ አሠልጣኞች የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና እንዲያገኙ ውጭ ድረስ በመላክ እንዲሠለጥኑ ያደርጋል፡፡ ይህ ግን በቂ ነው ማለት አይደለም፤›› የሚሉት ዳይሬክተሩ በዚህ ዓይነት ሁሉም የበኩሉን ቢያደርግ ውጤት የማይመዘገብበት አንዳች እንደማይኖር ጭምር ያምናሉ፡፡

  የተግዳሮቶቹ መንስዔ

  በኢትዮጵያ ከአጭር ርቀት እስከ ማራቶን የአትሌት ችግር እንደሌለ ከሚያምኑት መካከል በፌዴሬሽኑ የሥልጠና ጥናትና ምርምር የሥራ ሒደት ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ብርሃኑ ይጠቀሳሉ፡፡ ዳይሬክተሩ የሚመሩት ይህ ክፍል ደግሞ ለተግዳሮቶች በመፍትሔነት እንደሚያገለግል ከስያሜው መረዳት ይቻላል፡፡

  እንደ አቶ ሳሙኤል፣ ዕድገት በመጣ ቁጥር የተለያዩ አመለካከቶችና ሐሳቦች ይኖራሉ፡፡ ይሁንና እንደ ፌዴሬሽኑ ከሆነ ግን፣ ‹‹ሥልጠናዎች በተቻለ መጠን ዘመኑን የሚመጥኑ እንዲሆኑ ብቻ ሳይሆን ተተኪዎች በተገቢው ልክ እንዲኖሩ እስከ ታች ወርደን እየሠራ ነው፡፡ በቂ ነውን? አይደለም? በተለይ ባለሙያዎችን ከማብቃት አኳያና በክለብ ደረጃ ቅርርብ ተፈጥሮ የተሻለ ሥራ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ክልሎችን በተመለከተም ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ከፍተኛ ሙያተኞች የመስክ ጉብኝት እንዲያደርጉ በማድረግ ግምገማዎች ይደረጋሉ፡፡ በተለይ ዘመናዊ ሥልጠናዎች ከማስረጽ አኳያ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተን ክትትሎችን እናደርጋለን፤›› ይላሉ፡፡

  አገሪቱ ካላት ስፋትና ፌዴሬሽኑ ካለው ውስን የባለሙያ አቅም አኳያ ነገሮችን ከላይ እስከ ታች ክልሎችንና የከተማ አስተዳደሮችን፣ እንዲሁም ክለቦችንና የሥልጠና ማዕከላትን በተገቢው መጠን የተሟላ ግምገማ ለማድረግ ያልተቻለበት አግባብ እንዳለ ግን አልሸሸጉም፡፡ ይህን ለማሟላት ደግሞ ከቁሳቁስ ጀምሮ ብዙ መሠረታዊ ነገሮች እንደሚያስፈልጉም ይናገራሉ፡፡ ከዚህ አንፃር በዓለም ደረጃ ቀርቶ እዚህ አጠገባችን ከሚገኙት ኬንያ እንኳን መወዳደር እንደማንችል በእርግጥ በውጤት ደረጃ የምንመዘው ከዓለም ጋር ነው፡፡ ይህ ማለት ግን አሁንም ግምት ውስጥ እንዲገባ ሲሉ ያከሉት አቶ ሳሙኤል፣ አሠራሮችን ከጊዜው ጋር የተጣጣመ ይሆን ዘንድ ቤቱ የተቻለውን ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ይሁንና ነገሮች በሚገባው መጠን እየሄዱ ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም ይላሉ፡፡

  በአትሌቲክሱ በአንድም ሆነ በሌላ ድርሻ ያላቸው ወገኖች ግን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አሁንም በችግር ውስጥ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡ አትሌቲክሱ በተለይም በአሁኑ ወቅት ከሚገኝበት ደረጃና ኢንቨስትመንት አኳያ ብዙ ዕውቀትና መዋለ ንዋይ የሚፈስበት ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያ እነዚህ አሠራሮች በተግባር እየተሠራባቸው ነው ወይ? ብለን ስንጠይቅ ከፍተኛ በሆነ ልዩነት ውስጥ መሆናችንን ልብ ስለማንል ሰዎች ይህን ቢሉ ብዙም ላይደንቅ እንደሚችል ጭምር ኃላፊው ያስረዳሉ፡፡

  ‹‹ባለፉት ዓመታት የእኛ ብለን በምንወስዳቸው በተለይ የትራክ ውድድሮች ላይ ትኩረት አድርገን መቆየታችን በብዙ መልኩ የጎዳን ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ቀደም ሲል የፌዴሬሽኑ ከፍተኛ ሙያተኞች በሁሉም አቅጣጫ የመስክ ጉብኝት እንዲያደርጉ በተደረገበት ጊዜ እያንዳንዱ ክልል የራሱ የሆነ ተሰጥዖ ማለትም በደቡብ በተወሰኑ አካባቢዎች የሜዳ ተግባራትን ጨምሮ ከአጭር እስከ መካከለኛ ርቀት ጥሩ አቅምና ብቃት እንዳላቸው ታይቷል፡፡ ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት በሁሉም ክልሎች እንደየተሰጥኦቻቸው ተገቢው ሥልጠናና ክትትል ለማድረግ የአቅም ውስንነት በመኖሩ የሀብት አጠቃቀሙ ላይ ክፍተት መፍጠሩ አሌ ሊባል እንደማይችል ጭምር ተናግረዋል፡፡

  እንደ ኃላፊው፣ ‹‹ከብዙዎቹ አገሮች ስንነፃፀር እኛ ሀብቱ አለን እነሱ ደግሞ መሠረተ ልማቱ አላቸው፡፡ እኛ ጋ ሳይንሱ በሚገባ ሠርፆ እየተሠራበት ባለመሆኑ፣ ከሳይንሱ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ባላቸው አገሮች መበለጥ ጀምረናል፡፡ እዚህ ላይ ለምን ብሎ መጠየቅ አያስፈልግም፡፡ ምክንያቱም አሁን ላይ አትሌቲክሱ ራሱ ሳይንሱን መፈለጉ ኬንያውያንን ጨምሮ የብዙ አገሮችን ተሞክሮ በመመልከት መልስ ማግኘት ስለሚቻል፤›› ብለው ያምናሉ፡፡ ሌላው እኛ ቀደም ባሉ ዓመታት በተለይ በረዥም ርቀት ልንቆይ የቻልነው ሌሎች አገሮች አሁን በተገኙበት ደረጃ ላይ ስላልነበሩ ስለመሆኑ ጭምር ያስረዳሉ፡፡

  ‹‹ለዚህ ኬንያውያኑን በምሳሌነት ብንመለከት በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ማለት በሚያስችል መልኩ ሥልጠናዎቻቸው ሳይንሳዊ ሆኗል፡፡ የሚሠሩት ዓለም ላይ ትልቅ ስም ካላቸው ሙያተኞች ጋር ነው፡፡ ካምፖቻቸው ሙሉ በሙሉ ከዋና ዋና ከተሞቻቸው ብዙ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ስፖርቱ ገቢ የማመንጨት ችግር የለበትም፡፡ አንድም ኬንያዊ አትሌት ከካምፕ ውጪ ከተማ ውስጥ ተቀምጦ አይሠለጥንም፡፡ ከዚህ አንፃር የእኛን ስንመለከት ብዙዎቹ ከተማ ውስጥ መቀመጣቸው ከተጨማሪው ተግዳሮት ጋር ተደማምሮ ችግሩ እንዲባባስ አድርጓል፤›› ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ፡፡

  ለዚህ ሌላው ማሳያ ቀደም ሲል እነኃይሌ ገብረ ሥላሴን ጨምሮ ሌሎችም ታላላቅ አትሌቶች አሁን እንደምንመለከተው ‹‹መብቴ ነው›› በሚል መታበይ ያልነበረበት የሥልጠና ሥርዓት መኖሩ በተቃራኒው አሁን ላይ የማናጀሮች ተፅዕኖ ብቻ ሳይሆን አትሌቱ ራሱ አሠልጣኙ የሚያስቀምጥለትን ዓመታዊ የሥልጠና ዕቅድ ፍላጎቱ ካልሆነ በስተቀር የሆነ ቦታ ላይ ለመድረስ አምኖበት የሚሠራ አትሌት እንደሌለ ነው የሚናገሩት፡፡

  እንደ ኃላፊው ከሆነ ኢትዮጵያውያን ውጤት አያመጡበትም ተብለው በተፈረጁት አጭርና መካከለኛ ርቀቶች ላይ ሥልጠና እንዲሰጡ በአንድ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት ጋናዊው ዶ/ር ቻርለስ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአጭር ርቀት በብዙ መልኩ ተስፋ ሰጪ ውጤት ማስመዝገብ የጀመሩበት ሁኔታ እንደነበር ለማስታወስ ሞክረዋል፡፡ ከዚህ በመነሳት አቶ ሳሙኤል፣ ሙሉ በሙሉ የለንም ብለን ድምዳሜ ላይ መድረስ በፍፁም ስህተት እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡ በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ የሚገኙ ኬያውያን በጦር ውርወራ ሳይቀር ዓለም ላይ ተፎካካሪ እየሆኑ መምጣቸውን የሚያክሉት ኃላፊው ‹‹ቁርጠኝነቱ ኖሮን ዕቅዶቻችን መተግበር ከቻልን ከምንታወቅባቸው ውድድሮች ውጪ ባሉ ዓይነቶች ጭምር ውጤት ማስመዝገብ የማንችልበት ምክንያት አይኖርም፤›› ይላሉ፡፡

  መፍትሔውን በተመለከተ አቶ ሳሙኤል፣ ከጅምናዚየም ጀምሮ ዘመናዊ ስፖርት የሚጠይቀውን መሠረተ ልማት ማሟላት ለአፍታም ለድርድር እንደማይቀርብ ያምናሉ፡፡ አሁን ባለው ክልሎችን ቀርቶ አዲስ አበባን ብንመለከት አንድ ለእናቱ ከሆነችው በአዲስ አበባ ስታዲዮም ካለው ትራክ ውጪ ምንም ነገር አለመኖሩ ያለውን ተግዳሮት በማሳያነት በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡ ውጤቱን ካልሆነ ውጤት እንዴት ይመጣል? የሚለው መሠረታዊ ጉዳይ በብዙዎች ዘንድ እስካልተፈተሸ ድረስ ወደፊትም የውጤቱ ነገር ጥያቄ ውስጥ ሆኖ እንደሚቀጥል ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡

  እንደ ባለሙያ ኢትዮጵያ ውስጥ አትሌቱና በአግባቡ ጥቅም ላይ የሚውል ከሆነ ሀብቱ እንዳለ የሚናገሩት ኃላፊው፣ ባለድርሻ አካሉ ከሚመለከተው ጋር ተግባብቶ በቅንነት መሥራት ከተቻለ ኅብረተሰቡ የሚፈልገውን ውጤት ለማስመዝገብ ብዙም እንደማያስቸግር ያምናሉ፡፡ በተለይ የአዲስ አበባ የአየር ብክለት ጉዳይ አሁን ባለበትና አትሌቶቹም እዚህ ተቀምጠው ሥልጠና እንዲያገኙ እየተደረገ ነው የሚለው ፍፁም እንደማያስኬድ መሆኑ ሊወሰድ እንደሚገባውም ሥጋታቸውን ተናግረዋል፡፡

  በእርግጥ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በኩል ከብሔራዊ ሥልጠና ጋር ተያይዞ ከዓምና ጀምሮ አትሌሎቹ በሚገኙበት ክልል እንዲሆን ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ይህ ግን ከአትሌቶቹ ጭምር ክልሎችና ክለቦች ‹‹ከእኔ አውቅልሃለሁ›› ተላቀው ተባባሪ መሆን ሲችሉ ካልሆነ በተቋሙ ጥረት ብቻ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችልም የተግዳሮቱን መጠንም ከማስረዳት አልተቆጠቡም፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...