በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲና በፋሲል ከተማ መካከል የሚደረገው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በመጪው እሑድ በመቐለ ስታዲየም እንደሚካሄድ ከስምምነት ተደርሷል፡፡ በቀጣይ ባሕር ዳርና ጎንደር ላይ የሚደረጉ ጨዋታዎች እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
‹‹ብሔር ተኮር›› በሆነ አለመግባባት በሁለቱ ክለቦች መካከል መካሄድ የነበረበት መደበኛ ጨዋታ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ‹‹በገለልተኛ ሜዳ መካሄድ አለበት፣ የለበትም›› የሚል እሰጣ ገባ ውስጥ ገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ ዘግይቶም ቢሆን በተደረሰው ስምምነትና መግባባት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እሑድ ታኅሣሥ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. በወልዋሎ አዲግራት ሁለተኛ ሜዳ በመቐለ ስታዲየም ይደረጋል፡፡ ጨዋታው በመቐለ ስታዲየም እንዲሆን የተደረገው በአዲግራት ከተማ የሚገኘው የወልዋሎ አዲግራት ሜዳ በዕድሳት ላይ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ የፌዴሬሽኑ ውድድር ክፍል አስታውቋል፡፡
የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የብሔራዊ ሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ውድድሩን ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት በሁለቱ የክልል ኃላፊዎችም ሆነ የክለቦቹ አመራሮች ይሁንታ በማግኘቱ በፕሮግራሙ መሠረት ፋሲል ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ለመጫወት ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ ወልዋሎ አዲግራትም እንግዳውን ቡድን ለማስተናገድ መዘጋጀቱን ለፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡