Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  በሕግ አምላክየዘላቂ ሰላምና የሕግ የበላይነት ምንና ምንነት

  የዘላቂ ሰላምና የሕግ የበላይነት ምንና ምንነት

  ቀን:

  በውብሸት ሙላት

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ ከፍተኛ ትኩረት ከሰጧቸው ጉዳዮች አንዱ ሰላም ነው፡፡ የሰላም ሚኒስቴር ተቋቁሟል፡፡ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ተቋቁሟል፡፡ የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ሌሎችም  ስለሰላም ጉዳይ አጀንዳ ካደረጉት ሰነባብቷል፡፡ የአገራችን የሰላም ሁኔታ አሥጊ የሚባል ዓይነት ላይ ስለሆነ ይህ ቢሆን የሚደንቅ አይደለም፡፡ በዚህ ጽሑፍም ሰላምንና የሕግ የበላይነት፣ እንዲሁም በተወሰነ መልኩ ዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጋር ያላቸውን ተዛምዶ ብሎም ሰላምን ለማስፈንና ዘለቄታ እንዲኖረው የሕግ ሚና ምን እንደሆነ መቃኘት ይሆናል፡፡

  ሰላም በታጣበት ሰብዓዊ መብት አይከበርም፡፡ ለሰብዓዊ መብት መከበር ሰላም ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ሰላም ሳይኖር ልማት የመኖሩ ነገር የሚታሰብ አይደለም፡፡ ሰላም ሲታጣ የሚከተለው ጥፋት እንጂ ልማት አይሆንም፡፡ ሰላም በሌለበት ልማት በነጠፈበት ሁኔታ ዴሞክራሲም የመኖር ዕድሏ መንማና ነው፡፡ ሰላም በራቀበት ሁኔታ የሚኖር ልማት የጥቂቶችን ኪስ ብቻ ከማድለብ የሚዘል አይሆንም፡፡

  ብዙኃኑ በሰላም ዕጦት እየተሰቃየ ጥቂቶች ግጭት የሀብት ምንጫቸው በሚሆንበት ጊዜ ይዋል ይደር እንጂ አህያ የጅብ ናት እንዲሉ በግጭት ሀብታም የሆኑ ሰዎች ንብረታቸውም መልሶ በአመፅ ብዙኃኑ ይቀራመተዋል፣ ወይም በሌሎች ሕጋዊ ዘዴዎች መንግሥት መውረሱ አይቀርም፡፡ ያው ዞሮ ዞሮ ከጥቂቶች ኪስ ይወጣና ለሕዝቡ ይሆናል፡፡ በብዙ አገሮች የሆነው አስረጂነቱ ይህንን ነው፡፡ ስለሆነም በጊዜያዊነት ሰጥ ለጥ በማድረግ የሚፈጠርን ዝምታ እንደ ሰላም መውሰድ አይቻልም፣ ዘለቄታ አይኖረውምና፡፡

  የሳንቲያጎው የሰላም ሰብዓዊ መብት መግለጫ (Santiago Declaration on the Human Right to Peace) ሰላም የሰብዓዊ መብት ቅድመ ሁኔታም ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ሲከበር ደግሞ የሰው ልጅ መብቱን በነፃነት ስለሚያጣጥም ውጤትም ይሆናልና ይህንኑ መግለጫው ዕውቅና ሰጥቶታል፡፡  ቅድመ ሁኔታም ውጤትም ነው ማለት ነው፡፡

  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመቋቋሙም ዓቢይ ምክንያት ሰላምን በምድር ላይ ማንገሥ ነው፡፡ የድርጅቱ መቋቋሚያ ቻርተር መግቢያው ላይም ሆነ በጥቅሉ ከሌሎች አንቀጾች መረዳት የሚቻለው ሰላም ዓለማ አቀፋዊ እሴት መሆኑን ነው፡፡ ለዓለም አቀፋዊነቱም ቻርተሩ ዕውቅና ችሮታል፡፡

  ሕገ መንግሥቱ በመግቢያው ላይ ማሳካት የሚፈለገውን ግብ ሲገለጽ ዘላቂ ሰላም ማስፈንን እንደ አንዱ አድርጎታል፡፡ በተወሰነ ጊዜ ብቻ ሊሰፍን የሚችልን ፀጥታ፣ ጦርነትና ግጭት አለመኖርን ሳይሆን ዘለቄታዊ እንዲሆንም ጭምር ነው ምኞቱ፡፡

  ሰላም በግልጽ ስሙ ተጠቅሶ እንደ መብት ዕውቅናም ጥበቃም በሕገ መንግሥቱ አልተሰጠውም፡፡ ይሁን እንጂ በራሱ በሕገ መንግሥቱም ይሁን በሌሎች ዝርዝር ሕጎች ውስጥ ሰላም የሚፈጠርበትንም የሚጠበቅበትንም ሥርዓት አበጅቷል ማለት ይቻላል፡፡

  ሕገ መንግሥቱ በጥቅል አገላለጽ በአገሪቱ ውስጥ ዘላቂ ዋስትና ያለው ሰላም ማረጋገጥ እንደ አንድ ማሳካት ስለሚፈልገው ራዕይ በመግቢያው ላይ አስቀምጧል፡፡ የሰላም መስፈን በተራው ደግሞ (እንደ ነገሩ ሁኔታ በተገላቢጦሹም) ዋስትና ያለው የፀና ዴሞክራሲ ለመገንባት መሠረት እንደሆነ ስለሚታወቅ ይህንን ራሱን አስችሎ ሕገ መንግሥታዊ ራዕይ አድርጎታል፡፡

  ሰላምም ለማስፈን ዋስትና ያለው የፀና ዴሞክራሲም ለመገንባት ዜጎችም ሆኑ የተለያዩ ቡድኖች እርስ በራሳቸው ሊኖራቸው የሚችለው ግንኙነትና መስተጋብር እንዴት መሆን እንዳለበት መስማማት ስለሚጠበቅባቸው በራሳቸው ወይም በወኪሎቻቸው አማካይነት በሚወጣ ሕግ ሥርዓት ይዘረጋሉ፡፡

  የዚህ ሥርዓት ተከብሮ መኖር ሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ይህ ሁኔታ የሕግ የበላይነት (Rule of Law) መከበርና በሕግ መሠረት (Due Process of Law) ሁሉን ነገር ከመፈጸም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት መከበር ጋር በተያያዘ የወንጀል ሕግ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በጥቅሉ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ውጤታማ፣ ቀልጣፋ፣ እንዲሁም ፍትሐዊ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡

  ፍትሐዊነቱ ሲዛነፍ፣ ውጤት ከራቀው፣ ቅልጥፍና ሲጎድለው ተመልሶ ፍትሕ ይጠፋል፣ ርትዓዊነት ይጎድላል፡፡ እንዲህ ሲሆን ሰላም ይታወካል፡፡ በዜጎች መካከል መጠራጠርና ፍርኃት (Fear) ይነግሣል፣ መጠቃቃት ወይም ነውጥ (Violence) መርህ እየሆነ መሄዱ አይቀሬ ነው፡፡ ፍርኃትና ነውጥ ሲጨምር ሰላም ይቀንሳል፡፡ ይህ ደግሞ ዜጎች (ማንኛውም ሰውም) የተረጋጋ፣ የታወቀና የሚገመት፣ ፀጥታ የሰፈነበት ሕይወት መምራት ያዳግታቸዋል፡፡

  በፍርኃት፣ በመጠቃቃትና በነውጥ የተናጠ ማኅበረሰብን በእነዚህ አሉታዊ ባህርያት እንዲላቀቅ ቢያንስ ሁለት ዓይነት ዘዴዎችን ሥራ ላይ ማዋል ተገቢ ነው፡፡

   አንዱ ግለሰቦችም ይሁኑ ማኅበረሰቡ ከፍርኃቱ፣ ከመጠቃቃትና ከነውጥ ስሜት እንዲላቀቅ፣ በጎ አመከላከት እንዲኖረው ማድረግ፣ ዕርቅና ትብብር መተማማን፣ ወዘተ እንዲፈጥር የሚደረጉ የዕርቅና ስምምነት ተግባራት ማከናወንን ይመለከታል፡፡

  ሁለተኛው ደግሞ ፍትሐዊ ሕግጋትን በማውጣት በጥብቅ እንዲተገበሩ በማድረግ የሕግ የበላይነትን በማስፈን፣ ሰላምን የሚነሱ አሠራሮች እንዲወገዱ፣ ሰላምን ለማስፈን ምቹ መደላድሎችን በመዘርጋት መጠበቅን ይመለከታል፡፡

   የመጀመርያውን በዋናነት የሲቪክ ማኅበራት (Civil Societies) ሁለተኛው ደግሞ የመንግሥት ተግባር ነው፡፡ እንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ሌላውን ትተን እንኳን ባለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት የተፈጸሙት የሰብዓዊና የቁሳዊ ጉዳቶች፣ የተስተዋለው ኢፍትሐዊነትና ሰቆቃ ግለሰቦችንም፣ ማኅበረሰብንም ሰላም ያሰጡ ብሎም ቀውስ ስለፈጠሩ ይህንን ለማስተካከልና ለማንፃት ሲባል መንግሥት የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን አቋቁሟል፡፡

  ይህ ኮሚሽንም የተጣሉበት ኃላፊነቶችን ብንመለከት ከላይ ካልነው ጋር የተስማማ ነው፡፡ አዋጁም መግቢያ ይህንኑ የሚያፀና ነው፡፡ ከዚሁ ላይ በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል ‹‹በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ማኅበረሰባዊና ፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት በሕዝቦች መካከል የተደራረቡ የቁርሾ ስሜቶችን ለማከም እውነትና ፍትሕ ላይ መሠረት ያደረገ ወርቅ ማውረድ አስፈላጊ በመሆኑ፤›› የሚለው ቅድሚያ ይዟል፡፡

  ይኼው አዋጅ በዚሁ በመግቢያው ላይ ‹‹በተደጋጋሚ የተከሰቱ ጉልህ የመብት ጥሰቶችን ምንነት በግልጽ መለየት አስፈላጊ ስለሆነና ለዕርቀ ሰላሙም አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት፤›› የሚል ግብ አንግቦ እናገኘዋለን፡፡

  ዕርቀ ሰላም የማውረጃ ዘዴውንም ምን መምሰል እንዳለበት እዚሁ መግቢያው ላይ እንዲህ ይላል ‹‹በተለያዩ ጊዜዎችና የታሪክ አጋጣሚዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሌላ በደል ተጠቂዎች የሆኑ ወይም ተጠቂዎች ነን ብለው የሚያምኑ ዜጎች በደላቸውን የሚናገሩበትና በደል ያደረሱ ዜጎች ላደረሱት በደል በግልጽ በማውጣት የሚፀፀቱበትና ይቅርታ የሚጠይቁበት  መንገድ በማበጀትና ዕርቀ ሰላም በማውረድ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት፤›› በሚል ተበዳይና ተጠቂዎች ከተፈጠረባቸው የበደልና የስቃይ ብሎም የውስጣዊ ሰላም ዕጦት ለመሻር በደል ፈጻሚዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው በጥቅሉ አቅጣጫ መሆኑ ነው፡፡

  በጥቅሉ ዓላማውን በሚመለከት ራሱን ችሎ እንዲህ ተገልጿል፡፡ እንዲህ ይነበባል፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ሰላም፣ ፍትሕ፣ ብሔራዊ አንድነትና መግባባት፣ እንዲሁም ዕርቅ እንዲሰፍን መሥራት ነው፡፡” በዚህ መንገድ ሰላም ለማውረድ የሚደረጉ ጥረቶች የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት (Transitional Justice System) በመባል በሰፊው ይታወቃሉ፡፡

  ኮሚሽኑ እንዲፈጽማቸው ተዘርዝረው በአሥር ንዑስ አንቀጾች መካከል በሦስቱ ላይ የሚከተሉት ተግባራት እናገኛለን፡፡

  ‹‹የተለያየ አቋም የያዙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማወያየትና ለአገራዊ ዕርቅ መሠረት የሚሆኑ የጋራ መርህዎችንና እሴቶችን መለየት፣ የግጭቶችንና የመብት ጥሰቶቹን መነሻ ምክንያት ለመለየት፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዓውዶችን፣ የተጎጂዎችንና ጥፋተኞችን አስተያየት በመውሰድ ምርመራ ማካሄድ፣  በሕዝቦች መካከል የተፈጠረ ልዩነት እንዲረግብና መግባባት እንዲፈጠር  ዕርቀ ሰላም እንዲወርድ ማድረግ፤›› የሚሉት ይገኙበታል፡፡

  እንግዲህ ከላይ የቃኘነው ከሕግ አንፃር የሽግግር የፍትሕ ሥርዓት ነው፡፡ በዚህ መንገድ የሚመጣን ሰላም ድጋሜ እንዳይበላሽ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ተገቢ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ሳይሆን እንዳሻኝነት፣ ዘፈቀዳዊነት ከተንሰራፋ በዕርቀ ሰላሙ የሚገኘውን ውጤት ቀጣይነት ያጣል፡፡ በተጨማሪም መንግሥት አሁንም ቢሆን የሕግ የበላይነትን ማክበርም ማስከበርም ይጠበቅበታል፡፡ ካልሆነ ተመልሶ ሌላ የዕርቀ ሰላም ዙር ሊያስፈልግ ይችላልና!

  የወንጀል የሕግ ማዕቀፎች መሠረታዊ ዓላማ ቅርፅና ይዘት፣ እንደዚሁም የወንጀል የፍትሕ ሥርዓቱ ሁለገብ እንቅስቃሴ ከላይ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሚል የተገለጸውን ሕገ መንግሥታዊ ራዕይና ግብ ለማሳካት የሚችል መሆን ይገባዋል፡፡

  የወንጀል ሕግና የወንጀል የፍትሕ ሥርዓቱ ሰላምን ከማስፈን፣ ዴሞክራሲን ከመገንባት፣  እንዲሁም የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና አለው፡፡ ከዚህ አንፃር ወንጀል ሕጉ በራሱ ከዚሁ ጋር የሚስማሙ ግቦች ወይም ዓላማዎች ነው ያሉት፡፡

  ከእነዚህም ውስጥ አንዱ በአገራችን ዘላቂና ዋስትና ያለው ሰላም ለማረጋገጥ የሚቻለው በአገራዊ ደኅንነት በመንግሥትና በሕዝብ ጥቅም በግለሰቦች ደኅንነትና መብት ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊት ዝግጅቶችና ሴራዎችን አስቀድሞ ለመከላከል ሲቻልና ወንጀሎቹ ከተፈጸሙ አጥፊዎችን በሕግ ሥርዓት ተከታትሎ ለፍርድ ማቅረብና ማስቀጣት ነው፡፡ በተናጠል የግለሰብም በጥቅሉ ደግሞ የማኅበረሰቡና የአገሪቱ ሰላምና ደኅንነት እንዲጠበቅ ለእነዚህ ግቦች ተፃራሪ የሚሆኑ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ከተፈጸሙም ለማረም የወንጀል ሕግ በሌላ የማይተካ ሚና ይጫወታል፡፡

  ከእዚህ በተጨማሪም የሕግ የበላይነትና ልዕልና ለማስፈን የመንግሥት አካላትና ባለሥልጣናት፣ እንደዚሁም ማናቸውም ሰው የዕለት ከዕለት ኑሮውንና ተግባሩን ሕግና ሕግን መሠረት በማድረግ ለማከናወን የሚችል ሲሆንና ሕግን በመጣስ የሌላውን ሰው የሲቪልና ሌሎች መሠረታዊ መብትና ነፃነት የጣሱ ሰዎች በአገሪቱ እየተሠራባቸው ባሉ የሕግ ማዕቀፎች መሠረት በዘር፣ ቋንቋ፣ የፖለቲካ አቋምና በሌሎች ማኅበራዊ አቋማቸው ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ተጠያቂ ማድረግና ተጎጂዎች መብታቸውን በማስከበር ሲችሉና በደረሰባቸው ጉዳት ተገቢውን ካሳ ለማግኘት የሚችሉበት ሥርዓት ሲኖርና ሕጉን የሚተገብር የፍትሕ ሥርዓትና መገንባት ነው፡፡

   

  ከላይ ከተገለጹት በተጨማሪም ሰላም ዘለቄታ ይኖረው ዘንድ የፀና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባራት ከሆኑት መካከል በወንጀል ሕግ አማካይነት የሚሳካው የተለያዩ አካላት ለአብነትም የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የንግድ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማኅበራትና ማንኛውም ሰው የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴውን በሕገ መንግሥቱና ሌሎች የሕግ ማዕቀፎችና ድንጋጌዎች መሠረት በማድረግ የማከናወን የዳበረ ባህል ሲያዳብሩና የምርጫ ውድድሮች ጨምሮ ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ሕግና ሥርዓትን መሠረት በማድረግ የሚከናወኑ ሲሆን ነው፡፡

  በዚህ መሠረት አንዳይከናወኑ እንቅፋቶችን ማስተካከል፣ ሥርዓቱን የሚያናጉትን አስቀድሞ በመከላከልና ከተፈጸም ዕርምት ሲወሰድ ማኅበረሰቡ በሥርዓት ይተዳደራል፡፡ በሥርዓት መተዳደር ሥር ሲሰድ፣ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ሥር ሲሰድ፣ ሰላምም ዘላቂነት የመኖር ዕድሉ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ስለሆነም ዴሞክራሲና ሰላም እርስ በራሳቸው አዛይም ታዛይም በመሆን ተደጋግፈው የሚበለፅጉ ናቸው፡፡

  ስለሆነም በአገሪቱ የሕግ የበላይነትና ልዕልና እየተሻሻለ ይሄድ ዘንድ ብሎም የአገሪቱን ሰላምና ደኅንነት የሚያናጉ በማንም ይሁን በማን የሚፈጽሙ ጥቃቶች መከላከል ያስፈልጋል፡፡

  ከላይ ከቀረበው መገንዘብ የሚቻለው ሰላምና የሕግ የበላይነት መከበር ሊነጣጠሉ እንደማይችሉ ወይም በሌላ አገላለጽ ያለ ሕግ የበላይነት ሰላም የመስፈን ዕድሉ አነስተኛ ስለመሆኑ፣ እንዲሁም ዴሞክራሲና ሰላምም ሳይነጣጠሉ አብረው የሚጎለበቱ መሆናቸውንም ጭምር ነው፡፡

  እስኪ ሰላምና የሕግ የበላይነት ይዞታን በሚመለከት በሳለፍነው የፈረንጆች ዓመት የኢትዮጵያን ሁኔታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ያወጡትን ሪፖርት በአጭሩ እንቃኝ፡፡

  ግሎባል ፒስ ኢንዴክስ (Global Peace Index) የሚባለው ዓለም አቀፍ የሲቪክ ተቋም እ.ኤ.አ. የ2018ን የአገሮች የሰላም ሁኔታ በርካታ መለኪያዎችን በመጠቀም ለክቷል፡፡ ደረጃም አውጥቷል፡፡ በጥቅሉ የሰላምን ሁኔታ ለመለካት ልኬት አሰጣጡም እንደሚከተለው ነው፡፡ ከ1.0 ጀምሮ ከ2.0 በታች ያሉት ጥሩ በሚባል ደረጃ ውስጥ የሚገኙ ሲሆኑ፣ ከ2.0 እስከ 3.0 ደግሞ ዝቅተኛ በማለት ሲያስቀምጠው ከ3.0 እስከ ከ4.0 ደግሞ በጣም ዝቅተኛ የሚል ደረጃ ይዘዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ፣ አገሮች የውስጣዊም ይሁን የዓለም አቀፋዊ ግጭት ወይም ጦርነት ውስጥን በሚመለከት 2.695 አግኝታለች፡፡ ይሄ ዝቅተኛ ውስጥ ለዚያውም ጥግ ላይ የደረሰ ነጥብ ነው፡፡

  ማኅበረሰባዊ ደኅንነትና ፀጥታ ሁኔታን 2.909 ያገኘች ሲሆን፣ ይህም ያው በዝቅተኝነት የመጨረሻው ጠገግ ላይ መሆኗን ነው የሚሳየው፡፡ የጦርነት ዝግጅትን 1.704 ስለገኘች ጥሩ በሚባል ክልል ውስጥ ናት፡፡

   የመጨረሻው ምድብ በግጭት ምክንያት የደረሰባት የኢኮኖሚ ተፅዕኖ 19,094.1 ሚሊዮን ዶላር፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ ደግሞ 15,225.7 ሚሊዮን ዶላር ሆኖ፣ ይህም ዓመታዊ የግለሰብ ገቢ ላይ 141.6 ዶላር ጉዳት ሲያደርስ ከጥቅል አገራዊ ገቢው ላይ ዘጠኝ በመቶ እንዲታጣ ምክንያት ሆኗል፡፡

  የሕግ የበላይነትን በሚመለከት ደግሞ ወርልድ ጀስቲስ ፕሮጀክት (World Justice Project) ከዜሮ እስከ አንድ ድረስ ነጥብ ሰጥቷል፡፡ አንድ የሕግ የበላይነት ሁኔታው በጣም የተሻለ መሆኑን ሲያሳይ፣ ወደ ዜሮ እየተጠጋ ሲሄድ ግን እያነሰ ይሄዳል፡፡ ኢትዮጵያ በ2018 ዓ.ም. 0.38 (ወይም 38 ከመቶ) በማግኘት ከ113 አገሮች መካከል 107ኛ ሆናለች፡፡

  የመንግሥትን ሥልጣን የተገራ፣ የተገደበ መሆንን በሚመለከት 0.33 (33 ከመቶ)፣ የሙስና አለመኖር 0.46 (46 በመቶ)፣ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው መንግሥታዊ አሠራርን በሚመለከት 0.28 (28 በመቶ)፣ የሰብዓዊ መብቶች መከበር 0.31 (31 ከመቶ)፣ ፀጥታና ደኅንነት ስለመከበር 0.6 (60 ከመቶ)፣ ሕግና ሥርዓት ማስከበር 0.31 (31 ከመቶ)፣ የፍትሐ ብሔር ፍትሕ ሥርዓት አፈጻጸም 0.39 (39 ከመቶ) የወንጀል ፍትሕ አፈጻጸም 0.34 (34 ከመቶ) አግኝታለች፡፡ ይህ በጥቅሉ ተሠልቶ አማካዩ ነው 0.38 የሆነው፡፡ ከግማሽም በታች ያነሰ ዝቅተኛ የሚባል ነው የሕግ የበላይነት በኢትዮጵያ እየተከበረ ያለው፡፡

  የሕግ የበላይነት የማስከበር ይዞታችን በዚህ መጠን ዝቅ ብሎ የሰላም ሁኔታው የተሻለ ሊሆን አይችልም፡፡ የባለፈው ዓመትም ቢሆን ያው ነው፡፡ አልተሻሻለም፡፡  የሰላም ዕጦትም ይሁን የሕግ የበላይነት አካባበሩ ዝቅተኛ ሲሆን፣ በጥቅል የሰብዓዊ ልማት ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መገመት ከባድ አይደለም፡፡

  ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብት ብሎም ሰብዓዊ ልማት እርስ በራሳቸው የተቆራኙ ስለሆነ እያንዳንዳቸውን ጉዳዮች ትኩረት መስጠት ተገቢነት አጠያያቂ አይደለም፡፡ ሰላም ራሱን ችሎም ቅድመ ሁኔታ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች ከፍተኛ ስለሆነም፣ አሁን አሁን ላይ ሰላም ራሱን ችሎ መብት እየሆነ መጥቷል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ይህንኑ የሚመለከት የሳንቲያጎ መግለጫን አውጥቷል፡፡  

  አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው wuobishett@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...