Thursday, August 11, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ልናገርያልታዩ ጠንካራ ጎኖቻችን

  ያልታዩ ጠንካራ ጎኖቻችን

  ቀን:

  በበላይ ደመቀ

  ኢትዮጵያ የብዙ ዓመታት ታሪክ አላት ቢባልም የሚያመዝነው የጦርነት ታሪኳ ነው፡፡ በተለይ ቀደም ብሎ የቀይ ባህር ዳርቻ ላይ መገኘቷና የጥቁር ዓባይ መነሻ መሆኗ የውጭ ጠላት እንድታፈራ ካገዙ ውጫዊ ምንክያቶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡  ነገሥታቷና መሪዎቿ አገር ከመገንባት ይልቅ ድንበር ሲጠብቁ፣ መከታና ጋሻ የሚሆናቸውን አማራጭ በመፈለግ ሲባዝኑ የኖሩ ናቸው፡፡ የአገር ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ ውጊያ ከማካሄድ ጎን ለጎን ይበጃል ያሉትን የፖለቲካ አስተሳሰብ በሕዝቡ ውስጥ ማስረፅ ችለዋል፡፡ በተለይ ሕዝቡ በአንድነት ጥላ ሥር ካልተሰባሰበ የውጭ ወራሪዎች ልዩነታችንን በመጠቀም የበለጠ ይጎዱናል በሚል አስተሳሰብ የአንድነት ፖለቲካን እጅግ አጉልተው የአገራችንን አንድነት ጠብቀው አቆይተውታል፡፡

  መንገድና ዘመናዊ ትራንስፖርት ወይም መገናኛ በሌለበት ኢትዮጵያን የሚያህል ሰፊ አገር በነፃነት ጠብቆ ማቆየት ትልቅ ፖለቲካዊ ክህሎትና ብልሀትን የሚጠይቅ ነበር፡፡ አፄዎቿ ጠላት በመጣ ጊዜ ሕዝቤ ሆይ ና ተከተለኝ ብሎ ነጋሪት ከመጎሰም ውጪ ሌላ ሕዝብን የሚያስገድዱበት የፖለቲካ መዋቅር ወይም መሣሪያ አልነበራቸውም፡፡ ሆኖም ሕዝቡም ያለ ምንም አስገዳጅነት ስንቁን ሰንቆ ቀዬውን ጥሎ የአገሩን ልዕልና ለማስጠበቅ ከንጉሡ ጋር አብሮ በመዝመት ዳር ድንበሩን ሲያስከብር ኖሯል፡፡

  ቀደም ብለው የነበሩ የኢትዮጵያ ነገሥታትና መሪዎች በክርስትና እምነት ተፅዕኖ ሥር የነበሩና አንዳንዶቹም እንደ አፄ ዮሐንስ ያሉ አጥባቂ ክርስቲያኖች የነበሩ ስለሆኑ፣ አንድ ሕዝብ አንድ ዓይነት ቋንቋ መናገር ወይም አንድ ዓይነት ሰብዕና መቀዳጀት ካልቻለ ዕድገትና ልማትን ለማምጣት አይቻለውም የሚል የፖለቲካ ፍልስፍና ነበራቸው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የባቢሎን ግንብ ታሪክን ያስታውሷል፡፡ በተለይ ደግሞ እነ ፈረንሣይ፣ እንግሊዝ፣ ቤልጅየምፖርቹጋልና ጣሊያን ቅኝ ገዥ አውሮፓውያን የሥልጣኔያቸው መንስዔ የሕዝባቸው በአንድ ቋንቋና ሥነ ልቦና መግባባት መቻሉ ነው የሚል አስተሳሰብም ነበራቸው፡፡

  በታሪክ አጋጣሚ ከ1230 ዓ.ም. አካባቢ ጀምሮ ከአማራ ጋይንት አካባቢ የተነሳው ከአማራ ሕዝብ መስፋፋት ጋር ተያይዞ አማርኛ የቤተ መንግሥትና የፖለቲካ ቋንቋ በመሆን አገልግሏል፡፡ ይኩኖ ዓምላክ የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት ያፈረሰበትን አካሄድ ታሪክ ያስታውሳል፡፡ ከዚህ የፖለቲካ ለውጥና ነውጥ ጋር ተያይዞም ይህን ቋንቋ ማወቅ፣ መናገርና መጻፍ መቻል የተማረና ያወቀ የሚያሰኝበት ጊዜ ነበር፡፡ በተለይ ከሌላ ብሔር ወይም ጎሳ የሆነ ግለሰብ አማርኛ መናገር መጻፍና ማንበብ ከቻለ የተማረ ነው ስለሚባል የሹመት ዕርካብ በቀላሉ ይቆናጠጣል፡፡ ስለዚህ የተለያዩ ታሪካዊ ክስተቶች አማርኛ ብሔራዊ ቋንቋ እንዲሆን አስተዋጽዎ አድርገዋል፡፡ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ብሔርና ጎሳ ሳይለያቸው በዚህ ቋንቋ ተግባብተው ብዙ የሚባሉ አገራዊ ፋይዳዎችን አብረው ከውነዋል፡፡

  እንግዲህ የአማርኛ እንደ ብሔራዊ ቋንቋ መታየት ታሪካዊ አመጣጥ ታሪክ አጥኚዎች ብዙ ሊሉበት የሚችሉት ነገር ያለ ይመስላል፡፡ ነገር ግን የአማራ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ የጫነው የጭቆና መሣሪያ ሆኖ መታየት አይገባውም፡፡ አማራም እንደ ብሔር ጨቋኝ አልነበረም፡፡ ቋንቋውን በተመለከተ ከትግራይ የተነሱ ነገሥታትም ተጠቅመውበታል፡፡ አፄ ዮሐንስ የመንግሥታቸውን ሥራ ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ የነበረው አማርኛ ቋንቋን በመጠቀም እንጂ በትግርኛ አልነበረም፡፡ በወቅቱ ንጉሡ ይህን  ቋንቋ ትተው ትግርኛን ብሔራዊ ቋንቋ ማድረግ የሚገዳቸው ነገር አልነበረም፡፡ ሆኖም አማርኛን በብሔራዊ ቋንቋነት አፅንተው ሠርተውበታል፡፡ በኋላ ላይ የተነሱት እንደ ደጅአዝማች ሱባ ጋዲሳ (ፈረንጆቹ ሰባ ጋዲስ ብለዋቸዋል) ከባህር ማዶ ሰዎች ጋር በአማርኛ ቋንቋ ሲጻጻፉ ነበር፡፡ የየጁ ሥርወ መንግሥትም ቢሆን መሠረቱ ከኦሮሞ ብሔር ቢሆንም አማርኛን እንደ ሥራ ቋንቋ ሲጠቀምበት ነበር፡፡

  በአንፃሩም በአሁኑ ዘመናዊ የፖለቲካ አስተሳሰባችን የብሔር ጭቆና አለ የሚለው አስተሳሰብ አንድነትን ለመሸርሸር ከሚገባው በላይ እየከረረ ነው፡፡ አማርኛ በታሪክ አጋጣሚ የቤተ መንግሥትና የፖለቲካ ቋንቋ በመሆኑ፣ አማርኛን የመናገር ችሎታና ተመሳሳይ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ኢትየጵያን ሲመሩ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም በብሔር ውክልና ባይሆንም በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ርዕዮት የጋራ አመለካከት ያላቸው አማርኛ ተናጋሪዎች ብሔርን በመወከል ሳይሆን፣ ራሳቸውን በመወከል በመንግሥት ሥልጣን ውስጥ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡

  አንድ ነገር ግን መታወቅ አለበት፡፡ አማርኛ የመንግሥት ቋንቋ ሆኖ መመረጡ ለአማራው የሥነ ልቦና ግንባታ አስተዋፅኦ አልነበረውም ማለት አይቻልም፡፡ ይህ ሁኔታ ዕውቀት ባልጠለቃቸው ከአማራው በተገኙ አንዳንድ ግለሰቦች ዘንድ እኛ ከሌላው እንበልጣለን የሚል የንቀት ስሜት ፈጥሮባቸዋል፡፡ ይህ በሽታ ከእረኛ እስከ ምሁር ተዛምቶ አማራው በሌላው ብሔር በተለየ አሉታዊ ሆኖ እንዲታይ አድርጓል፡፡

  እንደተባለው የብሔር ጭቆና ቢኖር ኖሮ የኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊነት ለዚህ ሁሉ ዓመታት ተጠብቆ አይኖርም ነበር፡፡ ምክንያቱም ጨቋኝ የተባለው ብሔር የራሱን ቋንቋና ባህል በኃይል ማስፋፋት ካለበት፣ የሌሎችን ባህልና ቋንቋ ማጥፋት ግድ ይለዋል፡፡ እውነቱን ለመናገር በዚህ ሁኔታ የጠፋ ቋንቋና ባህል ባይኖርም፣ በታሪክ ሒደት በተለያየ ምክንያት የጠፉ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ሁላችንም እንደምናውቀው በጣም አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሕዝቦች እንኳ የማንነት እሴታቸውን፣ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን ጠብቀው ላለፉት በርካታ ዓመታት በዚህች አገር ኖረዋል፡፡

  በኢኮኖሚ ረገድም ያለፉት ነገሥታት አንዱ ብሔር ከሌላው እንዲበልጥ አቅደው የሠሩበት ሁኔታ የለም፡፡ በግልጽ እንደሚታየው የአማራው ብሔር እንኳ ባለፉት ነገሥታት በልማት ደረጃ እጅግ ወደ ኋላ ከቀሩ አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ በእንጭጭ ፖለቲከኞችና የሥልጣን ቁማርተኞች ተታልለን አገራችንንና አንድነታችንን ችግር ውስጥ መክተት የለብንም፡፡

  በቀድሞ ጊዜ ከሰሜን የተነሳው ወደ ደቡብ፣ ከምሥራቅ የተነሳው ወደ ምዕራብ ባደረገው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተዋህዷል፡፡ በዚህ የተነሳ አንድ መልክና አንድ ሥነ ልቦና ፈጥሯል፡፡ ለምሳሌ ወደ ሰሜን ያቀናው ኦሮሞ አማራ ሆኗል፡፡ እንዲሁም ወደ መሀል ምዕራብና ደቡብ ምዕራብ የተጓዘው አማራ ኦሮሞ ሆኗል፡፡ የሞጋሳ ባህል ለኢትዮጵያ አንድነት ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ አፄ ሱስንዮስ በጉዲፈቻ ከኦሮሞዎች ዘንድ ካደጉ በኋላ የንጉሥ ልጅ በመሆናቸው የኦሮሞ ታዋጊዎች ተዋግተው ካሸነፉ በኋላ አንግሠዋቸዋል፡፡

  ይሁንና አሁን ጊዜው እንደ ጥንቱ አይደለም፡፡ አማርኛ እስካሁን ለሰጠው አገልግሎት ምሥጋና ይገባዋል፡፡ አሁን ደግሞ አጋዥ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ከአንድ በላይ የሥራ ቋንቋዎች እንዲኖሩን ቢደረግ አግባብነት አለው፡፡ ይህም በጥናት ተደግፎ እንጂ በስሜትና በፖለቲካ ውሳኔ ባይሆን ደግሞ ተመራጭ ነው፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው belaygez@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...