የዕንቁላል አሠራር በተለያዩ ሒደቶች ይከናወናል፡፡ በመጀመርያ አስኳሉ ዕንቁል ዕጢ ውስጥ ይሠራል፡፡ ከዕንቁል ዕጢ ይወጣና ወደ ማህፀን የሚወስደው ቱቦ (ቦየ ዕንቁል ዕጢ) ውስጥ ይገባል፡፡ እዛም ነጩ የዕንቁላል ክፍል ይጨመርበታል፡፡ ከዛም ወደታችኛው ቱቦ በመውረድ ሜምብሬንና ቅርፊት በነጩና ቢጫው ክፍል ላይ ይደረብበታል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ዕንቁላሉ ለመጣል የሚደርሰው፡፡ የምታሽካካው ዶሮ ልክ በዚህ ጊዜ ነው፡፡
ሕይወት ያለው የዕንቁላል ክፍል ጥቂቱ ብቻ ነው፡፡ ያም ቢጫው ላይ ያለ ነጭ ነጥብ ሲሆን፣ በግንኙነት ጊዜ ከወንዱ ነባዘር ሲመጣ ውሑዱ ሕዋስ የሚሠራው ከዛው ነው፡፡ ዕንቁላሉ ከመፈልፈሉ በፊት ባለው ጊዜም የሚሠራው ከዛው ነው፡፡ ዕንቁላሉ ከመፈልፈሉ በፊት ባለው ጊዜም አስኳሉና ነጩ ክፍል ለሚያድገው ሽል እንደምግብነት ያገለግላል፡፡ ስለዚህም ሽሉ የተለያዩ አካላዊ ዕድገት ኖሮት ጫጩት ሆኖ እንዲፈለፈል ይረዳል፡፡ ይህም ሁኔታ የአዕዋፍን አረባብ ከአጥቢዎች ለየት ከሚያደርጉት አንዱ ነው፡፡ ምክንያቱየም አጥቢዎች በደማቸው አማካይነት ለሽሉ ማደጊያ ምግብ ሲያቀብሉ፤ አዕዋፍ ግን በዕንቁላል ውስጥ የሚያስፈልገውን የምግብ ግብዓት ሰንቀው ነው ዕንቁላል የሚጥሉት፡፡
- ማንይንገረው ሸንቁጥ ‹‹ባለአከርካሪዎች›› (2004 ዓ.ም.)