Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ልናገርለኢትዮጵያ ወቅታዊ የሆኑ አንገብጋቢ ችግሮች መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦች

  ለኢትዮጵያ ወቅታዊ የሆኑ አንገብጋቢ ችግሮች መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦች

  ቀን:

  በእውነቱ ይታያል

  የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ዋነኛ ግብ አድርጎ የያዘው ጉዳይ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ መገንባት ነው። ይኼ ሊሳካ የሚችለው ደግሞ የሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት ሲጠበቅ ብቻ ነው። ከዚህ አልፎ የአንድን ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ወይም ቡድን ያልተገባ ጥቅምና የበላይነት ለማረጋገጥ ጥረት ማድረግ የሕገ መንግሥቱን መሠረታዊ መነሻ ይደረምሳል ብቻ ሳይሆን፣ በማንኛውም መመዘኛ ዴሞክራሲያዊም ፍትሐዊም ሊሆን አይችልም።

  እንዳለመታደል ሆኖ ግን ብዙዎቻችን እንደምንገነዘበው ባለፉት 27 ዓመታት በአንድ ቡድን ብልጣ ብልጥነት፣ አልጠግብ ባይነት፣ ጀብደኝነት፣ እንዲሁም አምባገነንነት በሌላው ወገን ሞኛ ሞኝነት፣ የዋህነት፣ ፍርኃት ወይም ቸልተኝነት ሊባል በሚችል ሁኔታ ሕገ መንግሥት ተጥሶ የዚህን ቡድን የበላይነትና ጥቅም ለማስጠበቅ ጥረት ሲደረግ እንደነበረ ተስተውሏል። ይኼ የአንድን ቡድን የበላይነትና ጥቅም የማስከበር እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠሩ ችግሮች ሁሉ ምንጭ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ኢሕአዴግም ይህን የችግሮች ሁሉ መነሻ የሆነ አደገኛ እንቅስቃሴ አምኖ እንዲታረም ከማድረግ ይልቅ የችግሮች ሁሉ ምንጭ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ነው በሚል ቅርንጫፍ ላይ በመንጠልጠል በክህደት የመከላከል አቅጣጫን በመምረጡ ምክንያት፣ ራሱን መቀመቅ አስገብቶ አገሪቷንና ሕዝቦቿን ሊበታትን ቋፍ ላይ ደርሶ ነበር።

  ለሕዝቡ ምሥጋና ይግባውና ባደረገው ብርቱ ትግልና በከፈለው መስዋዕትነት የኢሕአዴግን እጅ ጠምዝዞ ራሱንና አገሩን ለጊዜውም ቢሆን ገብተውበት ከነበረው አረንቋ ለማውጣት በቅቷል። ይህን ተከትሎም ኢሕአዴግ ውስጥ አጋጣሚውን በመጠቀም የተፈጠረ ኃይል ሕዝቡን በደጀንነት በመያዝ ወደ ሥልጣን ለመምጣት ችሏል። በእርግጥ ይኼ ኃይል ወደ ሥልጣን የመጣበት  ሒደት ዴሞክራሲያዊ ነበር ብሎ መደምደም አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ከተለያዩ የሚዲያ አካላት ዘገባ እንደሰማነው ከሆነ በኢሕአዴግ ሊቀመንበር የምርጫ ሒደት ወቅት በአንድ ወገን ተራው የዚህ ወይም የዚያ ብሔር መሆን አለበት የሚል መከራከሪያ ሲቀርብ፣ በሌላ ወገን ደግሞ የቡድንተኝነት ዝንባሌዎችና እንቅስቃሴዎች ይታዩ እንደነበረ ለመገንዘብ ከባድ አልነበረም። ከዚህ ባለፈ ከምርጫው በፊትም ቢሆን ቡድንተኝነት የተስተዋሉባቸው እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ መካድ አይቻልም። በግልጽ ሲነገር እንደሰማነውም ቢሆን፣ የምርጫውን ሒደት ከእግር ኳስ ጨዋታ አሠላለፍ ጋር በማመሳሰል አሸንፎ የመውጣት ብርቱ ጥረት እንደነበረ ተገንዝበናል።

  ከዚህ ሁሉ ይልቅ የምርጫ ሒደቱም ምሉዕና ዴሞክራሲያዊ ሊሆን ይችል የነበረው ያሉት 180 የሚሆኑ የኢሕአዴግ ምክር ቤት አባላት እያንዳንዳቸው ሉዓላዊ ሆነው፣ በነፃና በፍላጎት ከቀረቡ ተጠቋሚዎች መካከል ብቃት አለው ብለው ያመኑበትን ሰው ቢመርጡ ኖሮ ነበር። ይኼ እዚያው ሳለ በአራቱም የኢሕአዴግ አባል በድርጅቶች መካከል መተማመንና የአብሮነት ስሜት ሊያጎለብት የሚችል አጋጣሚ ነበር። በነገራችን ላይ በዚህ መንገድ ተኪዶም ቢሆን ውጤቱን ላይቀይረው ይችል እንደነበረ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። ከዚህ ስንነሳ በዚህ ምርጫ ወቅት የለውጥ ኃይል ነኝ የሚለው አካል ያመለጠው ታሪካዊ ዕድል እጅግ በጣም ፈታኝ በሆነ ጊዜም ቢሆን በምርጫ ውጤቱ ብቻ ሳይሆን፣ በሒደቱም ዴሞክራሲያዊነት ላይ የማይደራደርና የፀና አቋም ያለው መሆኑን ማሳየት አለመቻሉ ነው። ምክንያቱም ዴሞክራሲ የሚለካው በውጤቱ ብቻ ሳይሆን፣ በሒደቱም ነው። እንዲያውም በዴሞክራሲ ዕይታ ከውጤት ይልቅ ሒደት በጣም ወሳኝ ቦታ አለው። ሒደቱ ምንም ይሁን ምን በሚል እሳቤ ውጤቱ ላይ የሚያተኩር መንግሥት ‘የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው’ በሚል ማኪያቬሊያዊ ፍልስፍና የሚመራ አምባገነናዊ መንግሥት መሆኑ አይቀርም።

  ወጣም ወረደ የዚህ ምርጫ ውጤት የሆኑት የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሚመሩት ድርጅታቸው ውሳኔ መሠረት፣ ምናልባትም ከእዚያ ባለፈ ሁኔታ የተለያዩ አዎንታዊ ተግባራትን አከናውነዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊገለጽ የሚገባው ዓብይ ነገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያከናወኗቸው ተግባራት አዎንታዊ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ የፈጸሙበት ጊዜም ቢሆን ከኢሕአዴግ ዘገምተኛ ባህል በእጅጉ በወጣና ፈጣን በሆነ መንገድ ነው። እኚህ ጠቅላይ ሚኒስትር ከፈጸሟቸው አዎንታዊ ተግባራት ውስጥ የእስረኞች መፈታት ትልቁን ቦታ የሚይዝ ነው። የተፈቱት እስረኞች አገር ቤት ያሉት ብቻ ሳይሆኑ፣ በተለያዩ የውጭ አገሮች የነበሩትንም ያካትታል። ሌላው ወሳኝ የሆነው አዎንታዊ ተግባራቸው ደግሞ የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲሰፋ የወሰዱት ዕርምጃ ነው።

  በዚህ ረገድ ሊነሳ የሚገባው ትልቅ ጉዳይ ከአገር ውጪ የነበሩ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች/ድርጅቶች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡና አገር ውስጥ ያሉትም ጭምር በነፃና በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስ እንዲችሉ ማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት የሚያበረታታ መንገድን መከተላቸው ነው። ከዚህ ሳንርቅ ከአገር ውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉ የሚዲያ ተቋማት (ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ጨምሮ) በነፃ እንዲንቀሳቀሱ ያላሰለሰ ጥረት ማድረጋቸው የሚዘነጋ አይደለም። የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነትም ቢሆን በአልጀርሱ ስምምነት መሠረት እንዲፈታ አቋም መያዛቸውና ይኼንኑ አቋማቸውን ለማስፈጸም እያደረጉ ያለው ጥረትም አንዱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዎንታዊ ተግባር ተደርጎ ሊገለጽ የሚችል ነው። ሌሎች አዎንታዊ የሆኑ ተግባራትንም መዘርዘር ይቻላል። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ እሱ ባለመሆኑ ግን በዚህ ረገድ ያለውን ሐሳቤን እዚህ ላይ መግታት መረጥኩ። የጠቅላይ ሚኒስትሩን አዎንታዊ ተግባራት በዚህ መንገድ እንደማሳያ ካነሳሁ አይቀር፣ አሉታዊ ናቸው የምላቸውን ደግሞ እንዲሁ ለማሳያ ያህል አጠር አድርጌ እንደሚከተለው ለመግለጽ እሞክራለሁ።

  የመጀመርያውና ዋናው አሉታዊ ጉዳይ የተቋማት ግንባታና ገለልተኝነትን የተመለከተ ነው። በዚህ ላይ ዶ/ር ዓብይ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ስህተት ሊማሩ ይገባል። ነፍሳቸውን ይማርና አቶ መለስ እንደ ግለሰብ አንድም ስስታም ሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ከማንም ሰው በላይ ምናልባትም ደግሞ ከፈጣሪ ጋር እንደ እኩያ እየታዩ ሃይ ባይ ሳይኖራቸው፣ ፖለቲካውን አመሰቃቅለውት እንዳለፉ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ በመሆኑ ደግሞ ተቋማት ቀጭጨው፣ ተዳክመውና ተልፈስፍሰው የሕዝቡን ጥያቄ መመለስ ይቅርና የራሳቸውን ሥልጣንና ተግባራት እንኳን በሚገባ የተረዱ የማይመስሉበት ደረጃ ደርሰዋል። ከዚህ አንፃር የሕግ አውጭው አካል ሥራ አስፈጻሚውን የመቆጣጠር ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ያለው ቢሆንም፣ የተገላቢጦሽ በሥራ አስፈጻሚው ቁጥጥር ውስጥ ገብቶ የቆየ መሆኑን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይገነዘባል። የፍትሕ አካላቱም ቢሆኑ ሕገ መንግሥቱ ያጎናፀፋቸውን ገለልተኝነት ዘንግተው በአብዛኛው የሥራ አስፈጻሚው ጉዳይ አስፈጻሚ የሆኑበት ሁኔታ የተፈጠረ መሆኑም ሌላው ግልጽ የሆነ ነገር ነው።

  አሁን ባለንበት ወቅት ላይም ቢሆን ዶ/ር ዓብይ የሚመሯቸው የመንግሥትም ሆኑ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አካላት የእነዚህን ሁለት ተቋማት፣ በተለይም የሕግ አውጭውን ሉዓላዊ ሥልጣን የመጋፋት አዝማሚያዎች እየፈጸሙ እንደሆነ የሚያመላክቱ ማሳያዎች መጥቀስ ይቻላል። ከእነዚህ ማሳያዎች አንዱ ከኢትዮ ኤርትራ የአልጀርስ ስምምነት ጋር የተያያዘው ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው ይኼን ስምምነት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት በ1993 .ም. የወሰደው አቋምና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም እንዲፀድቅ የተደረገው አዋጅ፣ አምስት የሚሆኑ የሰላም ቅድመ ሁኔታዎችን ያካተተ ነበር። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ይኼን አዋጅ የሻረ ሌላ በተወካዮች ምክር ቤት የወጣ አዋጅ፣ መኖሩን አልታዘብኩም። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ዶ/ር ዓብይ በሚመሩት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ ብቻ ኢትዮጵያ የአልጀርሱን የሰላም ስምምነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደተቀበለች ለሕዝብ ተገልጾ ወደ ተግባር ተገባ። ይህ ሒደት በውጤቱ ሲለካ አዎ”11ንታዊ ቢሆንም፣ በሒደቱ ሲመዘን ግን ዶ/ር ዓብይ የሚመሩት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተወካዮች ምክር ቤትን ሉዓላዊ ሥልጣን የተጋፋ መሆኑን መረዳት አይከብድም። ይህ ደግሞ የዶ/ር ዓብይ አስተዳደር ለሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ ግንባታ ያለውን የተዛነፈ አቋም ያሳያል። ከዚህ ይልቅ ሒደቱ ዴሞክራሲያዊና ሕገ መነግሥታዊ ሊሆን ይችል ዘንድ በ1993 ዓ.ም. የወጣው የተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ እንዲሻር ወይም እዲሻሻል በማድረግ፣ በምትኩም አሁን ዶ/ር ዓብይ በሚመሩት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተያዘው አቋም በተወካዮች ምክር ቤት ተቀባይነት አግኝቶ አዋጅ እንዲወጣለት መደረግ ነበረበት።

  ሁለተኛው ማሳያ ደግሞ ዶ/ር ዓብይ ወደ ኃላፊነት ሲመጡ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ የተደረገበት አግባብ ነበር። በእርግጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱ በማንኛውም መመዘኛ ሲታይ የሚደገፍ ነው። በተለይም የሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ ለማድረግና የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት ይቻል ዘንድ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ መደረጉ ከአስፈላጊም በላይ አንገብጋቢ ነበር። ይሁንና የተወካዮች ምክር ቤት ገና ሳያፀድቀው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቢኔያቸውን ውሳኔ መሠረት አድርገው አዋጁ እንደተነሳ ለሕዝብ መግለጫ መስጠታቸው፣ አሁንም በተወካዮች ምክር ቤት የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤትነትና ዴሞክራሲያዊ ሒደት ላይ ያላቸውን የተዛነፈ ዕይታ ያሳያል።

  ከተቋማት ገለልተኛነትና ከሕግ የበላይነት አንፃር የዶ/ር ዓብይ አስተዳደር የፈጸመው ሌላው ዝንፈት ደግሞ ከአዲስ አበባ ወጥቶች ጋር ተያይዞበት ፈጠረው ሁኔታ ላይ ነው። እነዚህ ከአንድ ሺሕ በላይ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ወጣቶች ጦላይ ወታደራዊ ካምፕ የታጎሩት ሕጋዊ በሆነ መንገድ ክስ ቀርቦባቸውና በፍርድ ቤት ውሳኔ መሠረት ሳይሆን፣ ለፌዴራል መንግሥቱ ተጠሪ በሆነው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ውሳኔ ነው። ይህ የሚያሳየው የመንግሥት የሥራ አስፈጻሚ አካል በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የሥልጣን ክፍፍል በመጋፋት፣ የፍትሕ (የፍርድ ቤትን) ሥራ እየሠራ ያለ መሆኑን ነው። በነገራችን ላይ እንዲህ ዓይነት ሰውን ሰብስቦ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝና ውሳኔ እንደ እንስሳት ካምፕ ውስጥ ማጎር እንደ ባህል የተወሰደው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ካልሆነ በስተቀር ሌሎች አገሮች ውስጥ ጭራሽ የሚታወቅ አይመስለኝም። አንድ የመንግሥት የሥራ አስፈጻሚ ዘርፍ ይኼን ዓይነትና መሰል ተግባራትን ለመፈጸም ሥልጣኑ ከየት እንደሚመነጭ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም፣ ጉልበትና ማናለብኝነት ካልሆነ በስተቀር።

  ሌላው ከሕግ የበላይነት ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው በዶ/ር ዓብይ የሚመራው መንግሥት አሉታዊ ድርጊት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ኃላፊ (አሁን ምድባቸው የውጭ ቋንቋዎችና የዲጂታል ዴስክ ኃላፊ ሆነዋል ተብሏል) ሹመት የሚመለከተው ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት የውጭ አገር ዜጋ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ሊሾም የሚችለው፣ ቦታውን ለመያዝ የሚያስችል ብቃት ያለው ኢትዮጵያዊ ማግኘት የማይቻል ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው። ይህ ከሆነ ታዲያ ቦታውን ሊሸፍን የሚችል ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጠፍቶ ነው የውጭ አገር ዜጋ እንዲሾም የተደረገው? ብሎ መጠየቅ አግባብነት ይኖረዋል። መልሱ ደግሞ በፍፁም ሊሆን አይችልም የሚል ነው። ምክንያቱ ደግሞ ቦታውን ሊሸፍን የሚችል ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ሰው ይጠፋል ተብሎ ስለማይገመት ነው። ይልቁንም ዋናው ምክንያት መንግሥት ለጡንቻ እንጂ ለሕግ የበላይነት ያለው ግንዛቤ አሁንም የተዛነፈ መሆኑ ነው። በነገራችን ላይ ኃላፊዋ ለቦታው ያላቸውን የብቃት ማነስ በመጀመርያው ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ከጋዜጠኞች ይቀርቡ ለነበሩ ጥያቄዎች ይሰጧቸው የነበሩትን ቁንፅልና ግልብ ምላሾች በማየት መረዳት የሚቻል ይመስለኛል። እነዚያ ይሰጡ የነበሩ ምላሾች የሚያሳዩት ትልቅ ቁምነገር ቢኖር ኃላፊዋ ምን ያህል ለመንግሥት ፖሊሲዎች፣ ሕጎችና አገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎች እንግዳ እንደነበሩ ነው።

  ከዚሁ ከሕግ የበላይነት ጉዳይ ሳልወጣ ማንሳት የምፈልገ ነጥብ፣ በመንግሥት መሪ ደረጃ ‘ፀጉረ ልውጥ’ በማለት ሕገ መንግሥታዊ የሆነውን የዜጎች በነፃ የመንቀሳቀስ መብት ለመገደብ ጥረት የተደረገበትን ሁኔታ ነው። እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ለዜጎች ከሚሰጣቸው መብቶች ውስጥ አንዱ በነፃ የመንቀሳቀስ መብት ነው። የዜጎች በነፃ የመንቀሳቀስ ብቻም ሳይሆን፣ በመረጡት ቦታ የመኖርና ሠርቶ የማደር መብቶችም ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል። ከዚህ አንፃር ሳየው ፀጉረ ልውጦችን ነቅታችሁ ጠብቁ ብሎ መልዕክት በማስተላለፍ የዜጎችን በነፃ የመንቀሳቀስ፣ በመረጡት ቦታ የመኖርና ሠርቶ የማደር መብቶችን ለመጣስ መሞከር ለሕግ የበላይነት መከበር ካለ የተዛባ ግንዛቤ ካልሆነ በስተቀር ሌላ መነሻ ሊኖረው አይችልም።

  በዚህም አለ በለዚያ ግን እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አዎንታዊ ጎኖች የበለጠ እየተጠናከሩ፣ አሉታዊ ጎኖች ደግሞ በሒደት እየታረሙ ሊሄዱ ይችላሉ በሚል እሳቤ ወደ ተነሳሁበት የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ልግባ። ይኼን ጽሑፍ እንድከትብ ያነሳሳኝ ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆማ ስለታየችኝ ነው። በአንድ በኩል ብሩህ የዴሞክራሲና የብልፅግና ተስፋ ይታየኛል። ይኼን ተስፋ እንድሰንቅ ያደረገኝ ዋናው ምክንያት የሕዝቡ በተለይም የወጣቱ ለዴሞክራሲ፣ ለእኩልነት፣ ለፍትሐዊነትና ለዕድገት ያለው ግንዛቤ ዕያደገ መምጣቱ ነው። በሌላ አነጋገር ሕዝቡ የሥልጣኑ ባለቤት ራሱ መሆኑን የተረዳበት ወቅት ላይ መድረሱ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ይኼን ተስፋ የሚያጨልሙ የአካሄድ ስህተቶች እየተመለከትኩ ነው። በተለይም የቅንነት መጓደልና የጋራ እሴቶቻችንና ጥቅሞቻችን ላይ ያለመግባባት ችግሮች ጎልተው እየታዩ ነው። በዚህ ላይ በምክንያት ሳይሆን በመንጋ የማሰብ፣ አለመደማመጥ፣ አለመተማመን፣ የአብሮነት መጓደልና እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚሉ ነገሮች እየገነኑ መጥተዋል። ይኼ አለመተማመን፣ ሽኩቻና አለመደማመጥ ሌላው ይቅርና በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች በተለይ ደግሞ ኢሕአዴግን በመሠረቱት ሕወሓትና ብአዴን (አዴፓ) ጎልቶ እየታየ ነው። በእኔ እምነት ለዚህ ሁሉ ምክንያት ይሆናሉ ብዬ የማስባቸው በኢሕአዴግ በራሱ በተለይም ደግሞ በሕወሓት ሰዎች የተፈጠሩ ችግሮች ናቸው። እነዚህን መሠረታዊ የሆኑ ችግሮችና መፍትሔ ይሆናሉ ብዬ የማስባቸውን ፍሬ ነገሮች ከዚህ በታች ለማሳየት እሞክራለሁ።

  አንደኛው መሠረታዊ ችግር ከማንነት ጋር ተያይዞ እየተነሳ ያለው ውዝግብ ነው። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት የወሰን ሥሪትተከናወነው ቁንቋን፣ ባህልንልምድን፣ ሥነ ልቦናዊ ትስስርንና የቦታ አቀማመጥን መሠረት አድርጎ ነው። ይኼ የወሰን ሥሪት ሲከናወን በተለያዩ ክልሎች የተለያዩ ጥያቄዎች ይነሱ እንደነበረ ግልጽ ነው። ጥያቄዎቹ ሲነሱ የተፈቱበት መንገዶች ደግሞ ተመሳሳይነት የሚጎድላቸው ነበሩ። ይህም ማለት በአንዳንድ አከባቢዎች ተነስተው የነበሩ ችግሮች እንዲፈቱ የተደረገው በሕዝብ ውሳኔ ነው። ይኼ መንገድ ተመራጩና ለሕዝብ ጥያቄ ተገቢውን ቦታ የሰጠ ምላሽ ነበር። በአንዳንዶቹ አካባቢዎች ደግሞ የተመረጠው የችግር አፈታት ዘዴ አስተዳደራዊ ነበር። የዚህ መንገድ ዋና ገፊ ሐሳብ ደግሞ ስግብግብነት ላይ የተመሠረተ የግዛት መስፋፋት ስለነበር፣ አሁን እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮች መነሻ መሆኑ አልቀረም። በተለይ ደግሞ በአማራና በትግራይ ክልላዊ መንግሥታት መካከል ባሉ አንዳንድ አከባቢዎች ለምሳሌ በወልቃይት፣ በራያና በመሳሰሉ አከባቢዎች በነበረው የወሰን ሥሪት ምክንያት የተፈጠረው ቁርሾ እያስከተለው ያለው ውጣ ውረድ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። እነዚህ አከባቢዎች ወደ ትግራይ ክልል የተካለሉበት መንገድ በሕወሓት ሰዎች እጀ ረጅምነትና በመሣሪያ የተደገፈ ጡንቻ ምክንያት የእነሱን የቆየ ፍላጎት ለማሟላት እንጂ፣ በአከባቢው ይኖር የነበረውን የሕዝብ ፍላጎት ባገናዘበ መንገድ ባለመሆኑ በተለያዩ ጊዜያት በሚከሰት ግጭት የሰው ሕይወት እየጠፋ፣ ንብረት እየወደመ፣ እንዲሁም በሁለቱ ክልሎች መካከል የእሰጥ አገባ መነሻ እየሆነ መጥቷል። ምናልባትም በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ ችግሮች ሚዛናዊና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በአስቸኳይ የማይፈቱ ከሆነ፣ በአማራና በትግራይ ክልላዊ መንግሥታት መካከል የጦርነት መነሻ ምክንያት ሆነው የአገሪቱን አንድነት ሊያናጉ የሚችሉ ችግሮች መሆናቸው የማይቀር ነው። ስለዚህ በእነዚህ አከባቢዎች ያሉ ችግሮች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ በአስቸኳይ የመፈታት ያለመፈታት ጉዳይ የኢትዮጵያን አንድነት የማስቀጠልና ያለ ማስቀጠል ጉዳይ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም።

  ጥያቄው ያለው በምን መንገድ ቢፈታ ዘላቂ ይሆናል የሚለው ላይ ነው። በእኔ እምነት ችግሩን በዘላቂነት ሊፈታው ይችላል ብዬ የማስበው ዕርምጃ የሕዝብ ውሳኔ ብቻ ነው። በሕዝበ ውሳኔው ተሳታፊ ሊሆን የሚገባው ሕዝብ ደግሞ የወሰን ሥሪቱ በተከናወነበት ወቅት በቦታው ይኖር የነበረው ሕዝብ እንጂ፣ ከዚያ በኋላ ታስቦበትም ሆነ በሌላ መንገድ የሠፈረውን ሕዝብ ሊጨምር አይገባም። በወቅቱ በቦታው ይኖር የነበረውን ሕዝብ ለመለየት ደግሞ የተካሄዱ የሕዝብና ቤት ቆጠራዎች፣ ግብር የተከፈለባቸውንና ሌሎች ሰነዶችን መመርመር ይቻላል። ይህ መሆን አለበት ብዬ ሐሳብ እያቀረብኩ ያለሁት ኢሕአዴግ በፈጸመው ድርጊት ምክንያት ጉዳት ደርሶብኛል ያለ አካል በራሱ በኢሕአዴግ መታከሙ/መጠገኑ፣ የተጓደለው ፍትሕ የተመለሰበትን ሒደት ፈረንጆቹ እንደሚሉት (Restorative Justice Process) ከቂምና ከቁርሾ የፀዳ ያደርገዋል የሚል እምነት ስላለኝ ነው። የሕዝብ ውሳኔው ከተካሄደ በኋላ የመሬት ይገባኛል ጥያቄ የሚያነሳ ክልል ካለ ታሪካዊ፣  ሕጋዊና ሌሎች ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ጥያቄውን ለፍትሕ ሥርዓቱና ከዚያም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርቦ እንዲፈታ ማድረግ ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው። በዚህም አለ በለዚያ ኢሕአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ቦታዎቹ ላይ የሠፈሩ ሰዎች ካሉ የሕዝብ ውሳኔው አካል መሆን ባይችሉም፣ በየሚኖሩበት አካባቢ የተለመደ ኑሯቸውን ለመቀጠል እስከፈለጉ ድረስ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

  ሁለተኛው ትልቅ ችግር ከሰንደቅ ዓላማ ጋር ተያይዞ እየተነሳ ያለው ውጥንቅጥ ነው። እስካሁን ባለ ልምድ የሚታወቀው ሰንደቅ ዓላማ አንድ አገር በውስጥም ሆነ በውጭ የሚመሰልበት ግዑዝ ነገር ነው። ለዚህም ነው የማንኛውም አገር ሰንደቅ ዓላማ በየመንግሥት ቢሮዎች፣ ክብረ በዓላት፣ ስፖርታዊ ውድድሮች፣ ሁሉም ዓይነት ሠልፎችና ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ የሚታየው። ይህ በመሆኑም ሰንደቅ ዓላማ ቢቻል በሁሉም ካልሆነም በአብዛኛው በአገሩ ዜጎች ተቀባይነት ሊያገኝ መቻል ይኖርበታል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ስናይ ግን ውጥንቅጡ የወጣ የሕዝብ ዕይታ ነው ያለው። አንዳንዱ ሰንደቅ ዓላማ ቀይ፣ ቢጫና አረንጓዴ ሆኖ መሀሉ ላይ ኮከብ ያለበት ነው ይላል። ሌላው አይ የእኔ ሰንደቅ ዓላማ ኮከብ የሌለው ምናልባትም የአንበሳ ዓርማ ያለበት ቀይ፣ ቢጫና አረንጓዴ ነው ይላል። ከእነዚህ ውጪ ያለ የኅብረተሰብ ክፍል ደግሞ ሰንደቅ ዓላማ የፖለቲካ ድርጅት እንደ ዓርማ እየተጠቀመበት ያለ ምሥል ነው ይላል። በዚህ ምክንያትም የተለያዩ ግጭቶች እየተከሰቱ የሰው ሕይወት ሲቀጠፍና ንብረት ሲወድም ይታያል። አሁንም ቢሆን በሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ላይ አገራዊ መግባባት እስካልተፈጠረ ድረስ፣ የግጭትና የብጥብጥ መነሻ ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም። ስለሆነም ችግሩን ለመፍታት ሕዝቡ የተለያዩ አማራጮች ቀርበውለት በግልጽ፣ በነፃና በቅንነት ውይይትና ክርክር አድርጎ የሚፈልገውን በአብላጫ ድምፅ እንዲወስን ሊደረግ ይገባል።

  ሦስተኛው ጉዳይ የፌዴራል መንግሥትን የሥራ ቋንቋ በሚመለከት እየተነሳ ያለው አተካሮ ነው። እንደሚታወቀው የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ አማርኛ ቋንቋን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ስለሚናገር የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ሆኖ እንዲቀጥል ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅን አግኝቷል። አንዳንዶቹ ይኼ ሁኔታ ባይዋጥላቸውም ከእውነታ ጋር መጋጨት ሆኖ ስለሚታያቸው ተቃውሟቸው ያን ያህል የከረረ አይደለም። ይልቁንም በዚህ ረገድ እየተነሳ ያለው ዋናው ጉዳይ ተጨማሪ የፌዴራል መንግሥት ቋንቋ እንዲኖር የማድረግ ፍላጎት ነው። በእኔ ዕይታ መነሻው ምንም ይሁን ምን አንድን ቋንቋ ተጨማሪ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆን የሚቀርብ ጥያቄ በራሱ ችግር የለውም። ምናልባት የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋዎች መብዛት የሕዝብ ለሕዝብ መቀራረብን የማጎልበት አስተዋጽኦ ሊኖራቸው ይሆን እንደሆነ እንጂ ጉዳት ሊኖረው አይችልም። ከዚህ አንፃር ሲታይ ኢኮኖሚያዊና ነባራዊ ሁኔታው እስከ ፈቀደ ድረስ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ የፌዴራል የሥራ ቋንቋዎች ቢኖሩ ምናልባትም ተመራጭ ሊሆን ይችላል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ እጅግ በጣም አፅንዖት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ግን አለ። ይህም ሊጨመር የታሰበው ቋንቋ በሕግ ሊጫን የማይገባው መሆኑ ነው። ‹‹ዘመኑ የእኛ ነው›› ከሚል የተዛባ ግንዛቤ ተነስቶ ቋንቋን በሕግ ብቻ ሌላው ላይ ለመጫን መሞከር በማንኛውም መመዘኛ ዴሞክራሲያዊ አይሆንም ብቻ ሳይሆን፣ የአገርን ህልውና ጭምር አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል አምባገነናዊ አካሄድ ነው። ይልቁንም መሆን ያለበት ልክ እንደ ሰንደቅ ዓላማው ሁሉ የሚቀርቡ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ልሁን ጥያቄዎች ወደ ሕዝቡ ቀርበው፣ ነፃና ግልጽ ውይይት/ክርክር ተደርጎባቸው በአብላጫ የሕዝበ ውሳኔ ድምፅ እልባት እንዲያገኙ ማስቻል ነው።

  አራተኛው መሠረታዊ ቁምነገር የመገንጠል መብትን ጨምሮ የፌዴራል ሥርዓት አወቃቀሩን በተመለከተ የሚነሳው ክርክር ነው። በዚህ ዙሪያ ሁለት ፅንፍ ላይ ያሉ ጎራዎች አሉ። አንዳንዶቹ ኢትዮጵያ ወደ አሀዳዊ የመንግሥት ሥርዓት መመለስ አለባት የሚል ክርክር ያነሳሉ። ይኼን ሐሳብ የሚያቀነቅኑ ኃይሎች መገንጠል የሚል መብትን በፍፁም አይቀበሉም። በዚህ ጎራ የሚካተቱ ኃይሎች የኢትዮጵያ የወሰን አከላለል መልክዓ ምድርን መሠረት ባደረገ መንገድ መሆን አለበት ይላሉ። በሌላኛው ጎራ ያሉት ደግሞ አሁን ያለው አወቃቀር የመገንጠል መብትን ጨምሮ እንዳለ መቀጠል አለበት የሚሉ ናቸው። ችግሩ ያለው እነዚህ የተለያዩ ሐሳቦችና ፍላጎቶች መንፀባረቃቸው ላይ አይደለም። እንዲያውም ሰው የሚሰማውን መግለጹ የሚበረታታና ዴሞክራሲን የሚያጠናክር ሒደት ነው። ይኼ ሒደት ችግር መሆን የሚጀምረው አንዱ ወይም ሌላው የእኔ ፍላጎትና ሐሳብ ብቻ ነው እንከን የሌለበት ብሎ፣ ይኼንኑ ፍላጎትና ሐሳብ በሌላው ላይ በኃይል ለመጫን እንቅስቃሴ የሚጀምር ከሆነ ነው። በዚህም አለበለዚያ የፌዴራል ሥርዓት አወቃቀሩ የመገንጠል መብትን ጨምሮ በዚህ ደረጃ የሚያከራክር ከሆነ፣ መፍትሔ የሚሆነው አሁንም ከላይ እንደተገለጸው ሁሉ ሕዝቡ ያልተገደበ ነፃና ግልጽ የሆነ ውይይት እንዲያደርግባቸው ሁኔታዎችን ማመቻቸት ለነገ የማይባል ሥራ ተደርጎ መወሰድ አለበት። ውይይቱና ክርክሩ በነፃና በግልጽ ከተካሄደ በኋላ የትኛው አወቃቀርና በምን አኳኋን የሚለውን ጉዳይ ሕዝቡ ዴሞክራሲያዊ በሆነ የድምፅ አሰጣጥ ሒደት በአብላጫ ድምፅ እንዲወስን ማድረግ ይጠይቃል።

  ይሁንና ከላይ የተነሱትን አራት መሠረታዊ ችግሮች በሚገባ ለመፈተሽና በተጓዳኝ የተቀመጡትን መፍትሔዎችም በትክክለኛው መንገድ ገቢራዊ ለማድረግ፣ የሚከተሉት ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተው መገኘት ይኖርባቸዋል። አንደኛው ቅድመ ሁኔታ ኢሕአዴግ በውስጡ ያለውን በግልጽ የሚታይ መሻኮት፣ ትርምስ፣ አለመተማመንና ግልጽነት መጓደል አስወግዶ አንድነቱን አጠናክሮ መገኘት ይኖርበታል። ምክንያቱም የራሱን አባል ድርጅቶች ማቀራረብና መተማመን እንዲችሉ ያላደረገ ኢሕአዴግ፣ ሕዝቡን ከዳር እስከ ዳር አቀራርቦ ከላይ በተነሱ መሠረታዊ ችግሮች ዙሪያ ቅን የሆነ ውይይት እንዲኖር፣ እንዲሁም የተቀመጡት የመፍትሔ ሐሳቦች በሚገባ ተግባራዊ እንዲሆኑ ያደርጋል ተብሎ ስለማይታሰብ ነው።

  ሁለተኛው ቅድመ ሁኔታ በሕዝቡ ውስጥ የሚደረጉ ውይይቶችና ክርክሮች ነፃ መሆን ይኖርባቸዋል። ይህ ማለት ደግሞ ማንኛውም ሰው የፈለገውን ሐሳብ የማራመድና የመሰለውን አቋም የመያዝ መብቱ ሊከበርለትና ሊጠበቅለት ይገባል ማለት ነው። ማንም ሰው ሐሳብ በማራመዱና አቋም በመውሰዱ ምክንያት ሊሸማቀቅ፣ ማስፈራሪያና ዛቻ ሊደርስበትና ሊታሰርም አይገባውም። በተጨማሪም ማንም ሰው የሕዝብ ውሳኔ ድምፅ ከመሰጠቱ በፊትም ሆነ ድምፅ በሚሰጥበት ጊዜ፣ ወይም ከዚያ በኋላ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ እንዳያርፍበት አስፈላጊው ጥንቃቄ ማድረግ የነፃ ሐሳብ ዝውውርን ለማጎልበት እጅግ በጣም ጠቃሚ ዕርምጃ ነው። እነዚህ ሁኔታዎች ገቢራዊ እንዲሆኑ ደግሞ ሥርዓት እንዲበጅላቸው ማድረግ ያስፈልጋል።

  ሦስተኛው ቅድመ ሁኔታ ደግሞ ሪፖርቶችና ግብረ መልሶች እውነተኛ መሆን የሚኖርባቸው መሆኑ ነው። ከአሁን ቀደም ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የኢሕአዴግ ሰዎች የሚታወቁት የውሸት ሪፖርትና ግብረ መልስ በመፈብረክ ነው። ይህ ደግሞ ኢሕአዴግንም ሆነ እመራዋለሁ የሚለውን ቀና ሕዝብ ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። ስለዚህ በማንኛውም ውይይትና ክርክር ላይ የሚነሱ ሐሳቦችና የሚያዙ አቋሞችን የተመለከቱ ሪፖርቶችና ግብረ መልሶች ወደ ሚመለከተው አካል ሲተላለፉ፣ ምንም ዓይነት ውሸት ሳይጨመርና ሳይቀነስ መሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል። በዚህ ረገድ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ለመከላከልና ለማረም ይረዳ ዘንድ፣ የሪፖርቶችንና የግብረ መልሶችን እውነተኛነት ዕውን ለማድረግ የሚያስችል አሠራር መዘርጋት አስፈላጊ ይሆናል።

  በሌላ በኩል ከላይ በተገለጸው መሠረት ሕዝባዊ ውይይቶች፣ ክርክሮችና የድምፅ አሰጣጥ ሁኔታዎች በሚኖሩበት ጊዜ የሚከተሉት ነጥቦች ተግባራዊ ቢሆኑ ሒደቱን የበለጠ ዴሞክራሲያዊና ታማኝ ሊያደርጉ ይችላሉ። እነዚህም ሁሉም ሕዝብ በጉዳዮቹ ላይ ሰፊ ውይይት ማድረጉ መረጋገጥ ይኖርበታል። ውይይቱ ደግሞ እንደተለመደው ለይስሙላ ሳይሆን ጥልቅና ነፃ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡  ሁሉም መገናኛ ብዙኃን ሕዝቡ በውይይቱና ክርክሩ ላይ እንዲሳተፍ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንዲችሉ ሁኔታዎች ሊመቻቹላቸው ይገባል፡፡ ዘገባዎቻቸውና ትንታኔዎቻቸውም ሕዝቡ ሁኔታውን በተገቢው መንገድ እንዲረዳው የሚያደርግ አቅጣጫን ቢከተሉ፣ ሒደቱን ውጤታማ እንደሚያደርገው ተገንዝበው ለዚሁ ቀና የሆነ ዕገዛ ቢያደርጉ ይመረጣል፡፡  የፖለቲካ ፓርቲዎችም አንዱን ወይም ሌላውን ሐሳብ ደግፈው ወይም ተቃውመው የመሰላቸውን ሐሳብ እንዲያራምዱ፣ ለሕዝቡም ይህን ሐሳባቸውን ያለምንም ገደብ በነፃ እንዲገልጹ ሁኔታዎች ሊመቻቹላቸው ይገባል።

  በተጨማሪም ገለልተኛ የሆኑ ታዛቢዎች እንዲኖሩ ማድረግም እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ መፍትሔ ያልተሰጠውና እግረ መንገዴን ላነሳው የፈለኩት መሠረታዊ ችግር ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እየተቆራኙ የሚነሱ የንግድ ድርጅቶችን (Endowments) የሚመለከተው ጉዳይ ነው። እነዚህ ድርጅቶች በተለይም ‘ኤፈርት’ አብዛኛው የመነሻ ካፒታሉ የተገኘው የሕወሓት አመራሮች እንደሚሉት፣ ውጭ አገሮች ከነበሩ የሕወሓት ንብረቶች ሽያጭና ከአባላት መዋጮ አልነበረም፡፡ በወቅቱ የሆነው ነገር አንድ ከተማ ወይም ቦታ ከደርግ ይዞታ ነፃ ሲወጣ በአካባቢው ከሚገኙ ባንኮች፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና ሌሎች ሕዝባዊ ተቋማት የሚዘረፍ ንብረትና ገንዘብ በጆንያ እየተሞላ ለኢሕአዴግ ፋይናንስ ገቢ ይደረጋል፡፡ በየቦታው የነበሩ የኢሕአዴግ ፋይናንስ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ደግሞ በአብዛኛው የሕወሓት አባላት ነበሩ፡፡ እነዚህ የሕወሓት ሰዎች ገንዘቡን ይሰበስቡና የሚልኩት ትግራይ ውስጥ ወደሚገኘው ማዕከላቸው ነበር፡፡ ይህ ገንዘብና ንብረት ነው እንግዲህ ተጠራቅሞ የኤፈርት ማቋቋሚያ መነሻ ካፒታል የሆነው፡፡ ከዚህ ስንነሳ ኤፈርት እንደ መነሻ የተጠቀመበት ጠርቀም ያለ ገንዘብና ንብረት የተገኘው ከመላው ኢትዮጵያ ኪስ ውስጥ እንደሆነ ለመረዳት አይከብድም፡፡

  የዚህ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ኪስ በተዘረፈ ገንዘብ የተቋቋመ ድርጅት ዓላማ፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በሞኖፖል መቆጣጠር ነበር፡፡ ይህን ለማስፈጸም በየቦታው ተሰግስገው የነበሩ የሕወሓት አመራሮችና አባላት ጉልህ ድርሻ ነበራቸው፡፡ በዚህም መሠረት በኤፈርት ሥር ያሉ ድርጅቶች ንግዱን ያለ ምንም ጠንካራ ተወዳዳሪ እንዳሻቸው ሲፈነጩበት እንደነበር ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰወረ ሚስጥር አይደለም፡፡ አንዳንድ ጠንካራ ተወዳዳሪዎች ሊኖሩ ቢችሉም እንኳን የነበረው አሠራር ለኤፈርት ድርጅቶች ቅድሚያ የሚሰጥ ስለነበር፣ እነዚህ ድርጅቶች የሚፈልጉት የንግድ እንቅስቃሴ ከሆነ ለሌላ አሳልፎ መስጠት አይታሰብም፡፡ በሌላ በኩል የኤፈርት ድርጅቶችን የሚጠቀምባቸው ቡድን ሌላ የእነዚህ ድርጅቶች ሸቀጥ ማራገፊያ የሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ደግሞ ሌላ፣ ሆኖ መቆየቱ ገሃድ የወጣ ሚስጥር እንደነበር መካድ አይቻልም፡፡ ይህ በመሆኑ ምክንያት በአገሪቱ የነበረው የተጠቃሚነት ሚዛን ወደ አንድ ቡድን ያጋደለ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በዚህ ረገድ ያለውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል መፍትሔ ሆኖ የሚታየኝ፣ ሁሉንም ድርጅቶች (Endowmments) አፍርሶ አንድ ላይ በማምጣት በፌዴራል ደረጃ አንድ የልማት ድርጅት እንዲፈጥሩ ማድረግ ነው፡፡ የዚህ በፌዴራል ደረጃ የሚቋቋም የልማት ድርጅት ዓላማ ደግሞ ፍትሐዊ የሆነ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ የፌዴራል አወቃቀሩን ሒደት ሊያጠናክር በሚችል መንገድ መሆን ይኖርበታል፡፡ ቸር እንሰንብት!

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...