Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ልናገርለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ችግር የኅብረተሰብ ተኮር ትምህርት

  ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ችግር የኅብረተሰብ ተኮር ትምህርት

  ቀን:

  በጌታቸው ይልማ (ኢንጂነር)

  ቀደም ባሉት ጊዜያት በአፄ ኃይለ ሥላሴና በደርግ ሥርዓቶች ኢትዮጵያውያን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለሕዝቦች ነፃነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ሲታገሉ ከብሔርና ጎሳ ሙሉ በሙሉ ባይባልም በመራቅ ለሕዝባቸው ታግለዋል፣ ቆስለዋል፣ ሞተዋል፡፡ ይህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አመለካከት መንግሥታቶቹ በዩኒቨርሲቲዎች ይከተሉት ከነበረው ፖሊሲ የሚመነጭ ሲሆን፣ መንግሥታቱ አንድን ብሔር ለይተው በአንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የማግነንና የሌሎች ተማሪዎች አለቃና መሪ ያደረጉበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ይሁንና ለመንግሥታቸው ታማኝና የተማሪዎችን ንቅናቄ ለመግታት የሚችሉባቸውን ሰዎች በዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትነት ቢበዛ ቢሰይሙ ይሆናል፡፡

  አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ወደ 50 የሚጠጉ ዩኒቨርሲቲዎች በየዞኑ በመክፈት አገራዊ ፋይዳቸው ሳይጠና ጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ብቻ ለማግኘት፣ ዩኒቨርሲቲዎችን እንደ ስኳር በማደል በአገር ሀብትና በዜጎች ኑሮ ላይ ተዘዋዋሪ ተፅዕኖ እንዲፈጥሩ ተደርገዋል፡፡ የዋናው ኦዲተር ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ከፍተኛ የአገር ሀብት ዘረፋ ከሚደረግባቸው ተቋማት መካከል ዩኒቨርሲቲዎች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የተሠራው ደባ በትውልድ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በቀላሉ ለመገንዘብ፣ ያህል አንድ ተማሪ ዩኒቨርሲቲው ከሚገኝበት ክልል የመጣ ሆኖ ከፍተኛ ውጤት የሚያመጣና የክልሉን ተማሪዎች የሚበልጥ ከሆነ በተማሪው ላይ የሚደረገው ጫና ከፍተኛ እንደሆነ፣ አሁን በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎችን በማነጋገር መገነዘብ የሚቻል ሀቅ ነው፡፡

  ለቀደሙት ችግሮች ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን ተጠያቂ ማድረጉ እንዳለ ሆኖ፣ በቀጣይ ምን ይደረግ የሚለው በእጅጉ ሊያሳስበን ይገባል፡፡ ኅብረተሰቡ ከዩኒቨርሲቲዎቹ ማግኘት ያለበትን ጥቅም እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል የሚለው ሌላው ወሳኝ ነጥብ ነው፡፡ ከላይ በርዕሱ እንደተገለጸው ኅብረተሰቡ ዩኒቨርሲቲዎቹ ከሚያደርጉት ምርምር ተጠቀመ ወይም ተጐዳ ለማለት ጥናት የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ ይሁንና አንዳንድ ዩኒቨርሰቲዎች የአካባቢውን ኅብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ የተለዩ የትምህርት ዓይነት እንዳላቸው ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ኅብረተሰብ ተኮር ትምህርት (Community Based Training) በተለይም በጂማ ዩኒቨርስቲ የሚሰጠውንና አሁን ላለንበት ችግሮች ሊሰጥ የሚችለውን ጥቅም ሳስብ ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ወሰንኩ፡፡

  ይህ ትምህርት ተማሪዎች ዋናውን የትምህርት ኘሮግራማቸውን እንደጨረሱ ወደ ቤታቸው ከመመለሳቸው በፊት፣ በየዓመቱ ወር ለሚሆን ጊዜ ወደ ኅብረተሰቡ በመግባት ኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ችግር በማጥናት መፍትሔ የሚሰጡ ሲሆን፣ የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውን በሚያጠናቅቁበት የመጨረሻው ዓመት በየዓመቱ ያጠኑትንና መፍትሔ ብለው ያወጡትን በተግባር የሚተገብሩበት ጠንካራ የሆነ የግምገማ ሒደት እንዳለው ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡

  ይህን የትምህርት ፕሮግራም በደርግ ዘመን የኅብረተሰብ ዘመቻ ተብሎ ተማሪዎች ዜጎችን ከመኃይምነት ለማላቀቅ ከሠሩት ድንቅ ሥራ ጋር በማዛመድ፣ ለሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች አዲስ የኅብረተሰብ አቀፍ ትምህርት ማዘጋጀት ያስፈልጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

  የዚህ ትምህርት ጠቀሜታ በዋነኛነት ተማሪዎችን የተግባር ተኮር ትምህርት እንዲኖራቸውና የአገራቸውን ሕዝብ አኗኗር በቅርበት በማጥናት ወደፊት ወደ ሥራ ሲሰማሩ፣ ችግር ፈቺና ጠባብ የሆኑ የቀበሌ አመለካከቶችን ወደ አገራዊ አመለካከት በመቀየር፣ ሕዝባችን ያለበትን የኑሮ ሁኔታ በመረዳት ሕዝባዊነትን በተማሪዎች ውስጥ ማስረፅ ይቻላል፡፡

  ተመሳሳይ የሆነ አሠራር ታላቁ የታንዛኒያ መሪ የነበሩት ጁሊየስ ኔሬሬ የአገራቸውን ሕዝብ ወደ አንድነት ለማምጣት የተጠቀሙበት አካሄድም ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ በታንዛኒያ ዙሪያ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በማስገንባት የአገሪቱ ዜጐችን ከአካባቢያቸው ርቀውና ከሌሎች ወገኖቻቸው ጋር ተደባልቀው እንዲማሩና የጎሰኝነት ስሜት ላይ ውኃ በመቸለስ፣ የአገሪቱ ሕዝቦች በጎሳ በሃይማኖትና በቆዳ ቀለም ሳይለያዩ ታንዛኒያ በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ አገሮች ሰላማዊ ሕዝብ የሚኖርባት ብቸኛዋ አገር አድርገዋታል፡፡

  ይህን ለማድረግ ያነሳሳቸው አንድ የበለፀገ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በታንዛኒያ ብሎም በአፍሪካ ለመመሥረት ከነበራቸው ቅን አመለካከት የተነሳ ነበር፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ታንዛኒያ ወደ 250 የሚጠጉ ጎሳዎች ያሏት ሲሆን፣ የጎሳና የሃይማኖት ልዩነቶች ለሕዝቡ ትርጉም አይሰጡትም፡፡

  በመሆኑም ተማሪዎች ከመንደር አስተሳሰብ ተላቀው ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ወገናቸውን በእኩልነት በማየት ሕዝባቸውን የሚያገለግሉ ዜጎች እንዲሆኑ ለማስቻል፣ የማኅበረሰብ ተኮር ትምህርት በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ወጥ በሆነ መንገድ ይሰጥ ዘንድ ምክረ ሐሳብ ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው getchyilma@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...