Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ተሟገትለፖለቲካው ስኬት ኢኮኖሚውም ስንቅ መሆኑ አይዘንጋ

  ለፖለቲካው ስኬት ኢኮኖሚውም ስንቅ መሆኑ አይዘንጋ

  ቀን:

  በታደሰ ሻንቆ

  የፖለቲካ ብልሽት ኢኮኖሚንና የኢኮኖሚ ልማትን ያጎሳቁላል፡፡ የኢኮኖሚ ልማት መሳካት ለፖለቲካ ሰላም ስንቅና መሠረት ይሆናል፡፡ የሁለቱን ተወራራሽነት በተረዳ ዕይታ ዛሬ አገራችን ያለችበትን እውነታ መመርመር፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ አወቃቀራችን ውስጥ ያሉ ገመናዎችን፣ በልማት ጥረቶቻችን ውስጥ የደረሱ ወድቀቶችንና ስኬቶችን ለይቶ ማወቅ፣ የድክመቶቻችንና የውድቀቶቻችንን ምክንያቶች መረዳት፣ ተረድተንም እንደምን ልንወጣቸው እንደምንችል አጥንቶ ወደ አራሚ ተግባር መሸጋገር ያስፈልገናል፡፡

  ውድቀቶችንና ጉድለቶችን ተረድቶ ማሸነፊያ በመቀየስ ተግባር ውስጥ ከራስ አልፎ፣ ከሌሎች አገሮች አሉታዊና ስኬታማ ልምድ ትምህርት የመቅሰም ሰበዞች አሉ፡፡ በዚህ ረገድ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ሰዎች ከቻይና፣ ከታይዋንና ከደቡብ ኮሪያ ስኬት ስለመማር ብዙ አውርተውናል፡፡ በተለይ ከ1993 ዓ.ም. የኢሕአዴግ ቀውስ ወዲህ ከእነሱ ትምህርት የወሰዱ የተባሉ የልማት ስትራቴጂዎች ተዘጋጅተው በሥልጠና ስንጠጣቸው ኖረናል፡፡ በእነሱ መሠረት ልማታችን ተቀይሶ እየተተገበረ ነው ሲባልልንም ተቆይቷል፡፡

  ብሔረተኛ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ አወቃቀር የብሔረሰቦችን ሰላም እንዳላመጣ ሁሉ፣ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ አጠባና ድርጅታዊ ሰንሰለት ኅብረተሰብን መጠረዝም ሕዝብን አሹሮ የማሠራትን ውጤት አላስገኘም፡፡ የኢሕአዴግ ምክር ቤት የኦሕዴዱን ዓብይ አህመድ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከሰየመልን ወዲያ፣ ቡትርፍርፉ ከወጣው መንግሥታዊ ፕሮፓጋንዳ በታች የተገለጠው እውነታ ያሳየን ነገርም፣ ከእነ እንከኖቹ ጉልህ ፍሬ ከታየበት የመሠረተ ልማት ግንባታ በስተቀር ሲወራለት የኖረው የኢንዱስትሪ መሠረትን የመጣል ሥራ ብዙ ነገሩ (በዓውደ ርዕይ ተውኔት ሰው አስደምሞ የነበረውን ‹‹ሜቴክ››ን ጨምሮ) ውስጡን ለቄስ መሆኑ ነው፡፡ በልማት ሽፋን ሲካሄድ የኖረው ዘረፋና አባካኝነት የህዳሴ ግድቡን ግንባታ እንኳ ያልማረ ነበር፡፡

  በዚያው ሥርዓት አመራር ውስጥ የኖረው በረከት ስምዖን ስለ‹አይጦች ሩጫ› እያወራና መለስ ዜናዊን እያወደሰ ከ27 ዓመታት በኋላም ከቻይና፣ ከደቡብ ኮያሪና ከታይዋን ውስጣዊ የፍብረካ አቅምን ፈጥሮ ስለመመንደግ ሲያስተምረን እንኳ፣ በራስ ላይ መሳለቅ ከለመደበት የሥርዓቱ ፀባይ አላመለጠም፡፡ በ20 እና 30 ገጾች ሊጠናቀቁ ይችሉ የነበሩ አንኳር ነጥቦቹን ቅልብጭ ባለ ምጣኔና በቀላል ዋጋ ለማቅረብ የሚሆን አስተዋይነትን፣ የአገር ተቆርቋሪነቱ ሳያጎናፀፈው ቀርቶ፣ ያታከተንን ፕሮፓጋንዳዊ አርቲ ቡርቲ በመዘብዘብ 400 ገጾች ገደማ ያባከነ መጽሐፍ ጽፎና ህንድ አሳትሞ በ300 ብር ቸብችቧል፡፡

  የኢንዱስትሪ ኢኮኖሚ ግንባታ ከትናንት ወዲያም፣ ትናንትም፣ ዛሬም የውስጥ ሰላም በቀጠለበት አኳኋን የሀብት ስንቅን ከፈጠራና ከቴክኖሎጂ አቅም ጋር ማዛመድን ይጠይቃል፡፡ በቀደምት የካፒታሊስት ዕድገት ታሪክ ውስጥ ለአውሮፓውያን አዲስ አገር ማሰስና ከዘረፋ ያልተናነሰ ድንበር ዘለል ንግድ የሀብት ስነቃ መገለጫዎቹ እንደነበሩ ብዙ ተጽፏል፡፡ በብሪታኒያ ውስጥ የነበረው የፈጠራ ዕምቅ አቅም ተነቃንቆ የኢንዱስትሪ አብዮትን ሊወልድ የቻለው ይህን የመሰለ የሀብት ፍሰት ጀርባ ስላገኘ ነበር፡፡ አዲስ ምድር አስሶ ከመያዝና ሀብት ከማጋዝ ጀርባ የአውሮፓ መንግሥታት እጅ እንደ ነበር ሁሉ፣ የኢንዱስትሪ አብዮት ያስገኛቸው ጨቅላ ኢንዱስትሪዎች የጎለበቱት ከውጭ የገበያ ተሻሚዎች መንግሥታዊ ጥበቃ እየተደረገላቸው ነበር፡፡ የብሪታኒያ ታዳጊ ኢንዱስትሪዎች የቻይናና የህንድ የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች እንዳይሻሟቸው መንግሥታዊ  ጥበቃ ይደረግላቸው ነበር (Peter Nolan, China and the Global Economy)፡፡ በቅኝና በሠፈራ መልክ የአውሮፓውያን ሌላ አዲስ አገር የሆነችው አሜሪካ በ19ኛው ምዕተ ዓመት ኢንዱስትሪያዊ መሆን የቻለችውም በገበያ ጥበቃ ነው፡፡ ኖላን እንደሚያወሳልን ከ1820 እስከ 1930 (እ.ኤ.አ.) አሜሪካ በገቢ ዕቃ ላይ ትጥለው የነበረው ገደብ ከ25 በመቶ አንሶ አያውቅም፡፡ በአመዛኙ ይልቅ ነበር፡፡ በዓለም የንግድ መድረክ የነፃ ገበያ ጠበቃነትን ብሪታኒያም ሆነ አሜሪካ የተያያዙት፣ ደካማ ኢኮኖሚዎች ገበያ ውስጥ እየገቡ ለማትረፍ የሚችሉ ትልልቅ ኩባንያዎችን ከፈጠሩ በኋላ ነበር፡፡

  አውሮፓውያን የደረጁባቸው የቅድመ 19ኛ ክፍለ ዘመን መንገዶች በዘገዩት አገሮች ሊቀዱና ሊደገሙ የሚችሉ አልነበሩም፡፡ የኢንዱስትሪ አብዮት ምዕራባዊ መስፋፋትና መጎልበት የአውሮፓውያንን ወታደራዊ ጉልበት የማላቅ፣ የጥሬ ዕቃና የሸቀጥ ገበያ ፍላጎታቸውን የማናር ውጤት አስከትሎና ዘመኑን ቀይሮ ባመጣው የቅኝ ግዛት ሽሚያ የብዙ ደካማ አገሮች ዕጣ ተወርሮ መያዝና መታለብ ሆኖ ነበር፡፡ እኛም ሆንን ሌሎች ብዙ ኋላቀር አገሮች በአርዓያነት ሊቀዷቸው የሚሞክሯቸው የ‹እስያ ነብሮች› አዲስ መጥ ኢንዱስትሪያዊ ግስጋሴ የተከሰተበት የ20ኛ ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ሌላ ዓይነተኛ ዘመን ነበር፡፡ ካፒታሊዝምን እሽራለሁ ብሎ የተነሳ ሶሻሊስት ንቅናቄ አንደኛ የዓለም ጦርነትን ተንተርሶ እንደ አገራዊ ሥርዓት ከተቋቋመ ወዲያ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመጥፋት ተርፎ፣ ይዞታውንና ተሰሚነቱን የማስፋፋት ዘመነ ግብግብ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ በአሜሪካ ወታደራዊ ከለላና የገንዘብ ዕገዛ ውስጥ በመሆን ምዕራብ ጀርመን በሶቪየት ኅብረት ከምትደገፈው ምሥራቅ ጀርመን ትይዩ ያደረገችው ኢንዱስትሪያዊ ግስጋሴ፣ እነ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያና ታይዋን ከቻይናና ከሰሜን ኮሪያ ትይዩ ሆነው ያደረጉት የግስጋሴ ትግል የሁለት ሥርዓት እኔ አስንቅ ኢኮኖሚያዊ ፉክክር የተካሄደባቸው መድረኮች ነበሩ፡፡ ወደ ኢምፔሪያሊስት ኃይልነት ወጥተው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተሸናፊነት የተንኮታኮቱት ጀርመኖችና ጃፓን ዋና ትግል፣ በፊት የነበራቸውን ኢንዱስትሪ ነክ የጥበብ ዕውቀትና ልምድን ለመልሶ ግንባታ የመጠቀም ጉዳይ ነበር፡፡ የእነሱ የማንሰራራት ጉዞ ከእነ ታይዋንና ከደቡብ ኮሪያ አዲስ ጉዞ ጋር በአንድ ዓይን የሚታይ አይደለም፡፡ ለእኛ ቢጤ አገር በምሳሌነት ለመጥቀም ቀረብ የሚሉትም ከፊተኞቹ ይልቅ የኋላኞቹ ናቸው፡፡

  ያም ሆኖ ያለንንና የሌለንን በቅጡ አውቆ አንዱን ጉድለት በሌላ ጥንካሬ እያካካሱ የመራመድን ብልህነት ለመቅሰም የጃፓንን አካሄድ በጨረፍታ እንቃኘው፡፡ ሮበርት ጊልፒን እንዳለው፣ ጃፓን በተፈጥሮ ሀብት ያለባትን ድህነት የገንዘብ ካፒታልን በጥንቃቄ ቆንጥጦ የፍብረካ ሥራ ላይ በማሰማራት የፍብረካ ምርታማነትንና የምርት ጥራትን ከቴክኖሎጂ መጎልበት ጋር እያሻሻሉ፣ ተወዳዳሪዎችን በሚረታ ዋጋ ወደ ውጭ በመላክ ስኬት አካክሳዋለች (The Challenge of Global Capitalism)፡፡ ከዚህ ስኬቷ ጀርባ ከምዕራባዊያን ከቀሰመችው ጥበብ ባሻገር አገር በቀል የሆነና ሥር የያዘ ዛሬም ምዕራባውያን ለመኮረጅ የሚሞክሩት ልቅም ያለ ልኬትንና ጥራትን ባህርዩ ያደረገ የዕደ ጥበብ ቅርስ (በእንጨት፣ በቀርከሃና በቤት ሥራዎች፣ ወዘተ ላይ የሚገለጽ) ነበራት፡፡ ጥበብንና የምርት ጥራትን እያተቡ (እያሻሻሉ) በሚማርክ ዋጋ በልጦ መሸጥን የገበያ ኢኮኖሚ በራሱ አላቀዳጃትም፡፡ የጃፓን መንግሥት ለዚህ ውጤት አልሞና አቅዶ ሠርቷል፡፡ የገንዘብ ካፒታልን ሳያበካክኑ ለአዲስ ሀብት ማፍሪያ የማዋል ጥንቁቅነታቸው፣ ኅብረተሰቡ የማኅበራዊ ዋስትና ሥርዓት ላይ ሐሳቡን እንዳይጥልና ሠርቶ ፍራንክ አጠራቃሚ እንዲሆን አድርጎ እስከ መቀየስ ድረስ የሄደ ነበር፡፡ ፒተር ኖላን በጠቀስነው መጽሐፉ እንደሚያወሳልንም ጃፓን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተሸነፈች በኋላ፣ በጦርነቱ ጊዜ የጃፓን ኢኮኖሚ ነፍስ የነበሩት የኢንዱስትሪ ቡድኖች (“Zaibatsu” ይባሉ የነበሩት) በአንበርካኪያቸው በአሜሪካ እንዲፈራርሱ ቢደረጉም፣ ጃፓኖች ለአሜሪካ ዕርምጃና ምክር ፍዝ ተቀባይ አልነበሩም፡፡ በዓለም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ጠንካራ ተወዳዳሪ የሆኑ ኩባንያዎችን በማደራጀት ረገድ አቅደው በመሥራት፣ በጥቂቶች ሞኖፖሊ ይዞታነት ለመዋጥ ያልተመቹ፣ አንዱ ኩባንያ በሌላው ኩባንያ ውስጥ አነስተኛ (ልል) የባለቤትነት ድርሻ በያዘበት አኳኋን የተሳሰሩ ጠንካራና ዥንጉርጉር የኢንዱስትሪ ቤተሰቦችን “Keiretsu” የተባሉ ሊፈጥሩ ችለዋል፡፡ በአንድ የኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ውስጥ ያሉ ባለቤቶች ትንንሽ ድርሻ ተደማምሮ ከ30 በመቶ የማይበልጥ ሆኖ 70 በመቶ ያህል ድርሻዎች ደግሞ በሌሎች ኮርፖሬሽኖች የተያዙ እንዲሆኑ በማድረግ፣ ኮርፖሬሽኖች ከኮርፖሬሽኖች ከአንዳቸው ወደ አንዳቸው የተሸጋገረ የባለይዞታነት ጥልፍልፍ እንዲሠሩ አድርገዋል፡፡ ትስስሩ ሁሉም ዘንድ የእኔ/የእኛ ባይነት ትርታንና ቅንጅትን ከፉክክር ጋር ሊፈጥር በመቻሉም፣ የኩባንያዎች መመንደግ ተከትሎ ዓለምን ካካለሉት 500 ያህል  ግዙፎች  ውስጥ የመቶ ያህሉን ቁጥር ሊይዙ ችለዋል (ፒተር ኖላን፣ 10-11)፡፡

  በታይዋንና በደቡብ ኮሪያ ውስጥ በጊዜው የነበሩት መንግሥታት፣ ከአሜሪካ ዕገዛ ባሻገር የግብርና አቅምን ከአሮጌ የኢኮኖሚ ግንኙነት በማላቀቅ ለኢንዱስትሪያዊ ለውጥ ስንቅ እንዲውል አድርገዋል፡፡ ሁለቱም በኢንዱስትሪ ዕድገት ጨቅላ ጉዟቸው ላይ ከፍተኛ ታሪፍ በመጣል ገበያቸውን ጠብቀዋል፡፡ ሁለቱም መጀመርያ ላይ ገቢ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ አምራችነት በመተካትና የቀላል/ብዙ ሠራተኛ አሳታፊ ኢንዱስትሪዎች ምርቶችን በመላክ ላይ አትኩረው ሠርተዋል፡፡ በስተኋላ ደግሞ ወደ ግዙፍና ከባድ ኢንዱስትሪዎች ተሸጋግረዋል፡፡ የታይዋን መንግሥት በመንግሥት ይዞታነት ከባድ ኢንዱስትሪዎች (የብረታ ብረት፣ የመርከብ ግንባታ፣ የነዳጅና የኬሚካል፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ወዘተ) እንዲመዘዙ ከማድረግ ጋር የግል ዘርፉም በቴክኖሎጂ ለውጥ እየተገነባ ለውጥ አነቃናቂ እንዲሆን ቃኝቷል፡፡ ማትጊያንም ከስኬታማነት ጋር አገናኝቶ የከፍተኛ ቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ እንዲጎለብት ማድረግ ችሏል፡፡ በንግድ ሥራ ኃያል ቤተሰቦችን መሠረት ያደረጉ ትልልቅ ኩባንያዎች እንዲጎለብቱ ያደረገችው ደቡብ ኮሪያ፣ የጃፓንን ዘይቤ ተመርኩዛ እነዚህ ኩባንያዎች ዘርፈ ብዙ ጥልፍልፍ እየሠሩ እርስ በርስ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ቃኝታለች፡፡ ከቀላል ኢንዱስትሪ ወደ ከባድና ወደ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ በተካሄደው ሽግግርም ውስጥ ሆነ በዓለም ተወዳዳሪ የሆነ ድንበር ዘለል ተዋናይነትን በመቀጃጃት ውስጥ የመንግሥት ቃኝነትና ተላሚነት ሚና ነበረበት፡፡ ሁለቱም አገሮች ጃፓን የተያያዘችው በአምርቶ ላኪነት ላይ ያተኮረ ፖሊሲ፣ ለዘመኑ አዋጪና ተሻሚ የለሽ መሆኑን አጢነው በቀጥተኛና ኢቀጥተኛ ማትጊያ የየአገራቸውን ኩባንያዎች እየኮረኮሩ ማሠራት መቻላቸው ዘመንን የማንበብ ብቃት ነበር፡፡ ኢትዮጵያም መቅሰም ያለባት አንዱ ችሎታ ይህንን ዘመንን የማንበብ ንቁነትን ነው፡፡

  የጊዜው ውጤቶች ሁሉ በአገሮቹ ብልህ አመራር፣ ዘመኑን በተረዳ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ በኩባንያዎቹ መለኝነት፣ በጊዜው በነበረው የሁለት ሥርዓቶች ፉክክር አጋዥነት ብቻ የሚብራራ አልነበረም፡፡ ጃፓን፣ ቻይናና ‹‹ትንንሾቹ ነብሮች›› የሚባሉት (ሆንግ ኮንግ፣ ሲንጋፖር፣ ታይዋንና ደቡብ ኮሪያ) በሙሉ የሚገኙት ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ በሚካሄድበት የባህር መስመር ደጃፍ ነው፡፡ ደጃፍ ላይ ከመገኘትም ባሻገር ሆንግ ኮንግና ሲንጋፖር የከተማ አገር መንግሥታት ናቸው፡፡ ታይዋን ገጠር ያላት ብትሆንም ከእነ ቅንጥብጣቢ ምድሮቿ ትንሽዬ ልትባል የምትችል (36 ሺሕ ካሬ ኪሎ ሜትር ብቻ ስፋት ያላት) ደሴት ነች፡፡ ጃፓንም ትልቅ ብትሆንም ወርደ ሰፊ ያልሆነች ረዥም ምላስ መሰል ደሴት መሆኗ በሁሉም አቅጣጫ ለባህር ቅርብ ያደረጋት ምድር ነች፡፡ ደቡብ ኮሪያም በስተሰሜን የየብስ ጉሮሮ ያላት ከመሆኗ በቀር በሦስት አቅጣጫ በውኃ የተከበበች ምላስ ምድር ነች፡፡ በጥቅሉ እነዚህ አገሮች ዘንድ በየትም የምድራቸው ክፍል ውስጥ የተቋቋመ ኢንዱስትሪን ከውጭ ገበያ ጋር በማያያዝ ረገድ ከባህር ወደብ የመራቅ ነገር ችግራቸው አይደለም፡፡ ይህ መዘንጋት የሌለበት ጥቅም ነው፡፡

  ኢትዮጵያ በሰሜን ምሥራቅና በምሥራቅ ለቀይ ባህርና ለህንድ ውቅያኖስ የንግድ እንቅስቃሴ መስመር ቅርብ ብትሆንም የባህር በር የለሽ አገር ሆናለች፡፡ እናም አሁን የወደብ መውጫዋ ከሰሜን እስከ ምሥራቅና ደቡብ ምሥራቅ ድረስ ካሏት ጎረቤቶቿ ጋር ባላት ግንኙነት መለስለስና መሻካር ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ የወደብ ግልጋሎት ውጪም አለባት፡፡ በዚያ ላይ ለውጭ ገበያ የሚሆን ኢንዱስትሪን የትም ቦታ ከፍቶ ወደ ባህር በር በማድረስ በኩል ከትልቅ አገርነቷ የሚመጣ የርቀት ልዩነት፣ በማጓጓዣ ወጪ አዋጭነት ላይ የሚፈጥው ልዩነት ተቃልሎ የሚታይ አይደለም፡፡ በቀላል ማነፃፀሪያ ይህንን ለማሳየት፣ ጃፓንና አራቱ ትንንሽ ነብሮች አንድ ላይ ያላቸው የአገር ስፋት ቢደመር የኢትዮጵያን ከአንድ ሚሊዮን መቶ ሺሕ ካሬ ሜትር የዘለለ ስፋት ግማሽ እንኳ አይሞላም፡፡

  ይሁን እንጂ ትንሽ ወይም ሾጤ ቅርፅ ይዞ ከወዲያም ከወዲህ ለባህር ቅርብ መሆን ብልጫ ጥቅም ቢሆንም፣ ለምናወሳቸው የእስያ አገሮች ኢንዱስትሪያዊ ልማት ማማሃኛ መሆን ግን አይችልም፡፡ ከዚያው አካባቢ ሙሉ ለሙሉም ሆነ ከሦስት በኩል በውኃ የተከበቡ አገሮች አሉ፡፡ ከእነ ቬትናም፣ ፊሊፒንስ፣ ኢንዶኔዥያ አንስቶ እስከ ህንድና ሲሪላንካ ድረስ ቢኬድ በጊዜው እነዚህ አገሮች በተለያዩ ምክንያቶች እንደ እነሱ አልተመነደጉም፡፡ የቬትናም አካባቢ የሁለት ሥርዓት የጦርነት እሳት ይወርድበት ነበር፡፡ ከዋና የጦርነት ቀጣናነት በመለስ ደግሞ የሁለት ሥርዓት ትንንቅ በሸምቅ ውጊያ መልክም ሆነ በሌላ መልክ የሚያብጣቸው ነበሩ (እነ ኢንዶኔዥያና ፊሊፒንስ ለምሳሌ)፡፡ የህንድና የፓኪስታን ክፍፍልና ንቁሪያ ያስከተለው ለአካባቢ የተረፈ የፍልሰት ችግርም የማይዘነጋ ነው፡፡ እነዚህን ከመሳሰሉ ችግሮች ባለፈ፣ ዕድገት ጎታች ከሆኑ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ግንኙነት ጭርንቁሶች ጋር መንገታገትም ነበር፡፡ እንዲያም ሆኖ ከጦርነት ዓውድማነት ውጪ በነበሩት አገሮች ውስጥ በፍለጠው፣ ቁረጠው ዘይቤም ሆነ በሌላ ሕዝብን እረጭ አድርጎ እያፈጉና ከውስጥ ይልቅ ወደ ውጭ በሚያይ አምርቶ ነጋጅነት የማትረፍ ፖሊሲ መጉደሉ በሰበብ የሚጣጣ አይደለም፡፡

  ወደ አሁኑ ዘመንና ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታችን በፊት፣ ዘግየት ብላ በጥገናዊ ማሻሻያ ወደ ምዕራቡ ዓለም በከፊል መለስ ብላ ላኪነት ላይ ባተኮረ ቅያስ ከፍተኛ ግስጋሴ ለማድረግ የቻለችውን (በስፋት ከኢትዮጵያ ስምንት ጊዜ ያህል የምትልቀውን) ቻይናን በአጭሩ ማየት ይጠቅማል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1960ዎች ማለቂያ ከማኦ ዜ ዱንግ ሞት በኋላ ወደ ሥልጣን መሰስ ላለው ዴንግ ዚያዎ ፒንግ፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ለማድረግ የሚገፋፉና የሚያነቁ ነገሮች መሬት ላይ ነበሩለት፡፡ ቻይና በ‹ሶሻሊዝም› ውስጥ የገነባቻቸው የድንጋይ ከሰል፣ የብረታ ብረት፣ የሲሚንቶ፣ የኬሚካል፣ ወዘተ ከባድ ኢንዱስትሪዎች በፈጠራና በአዲስ ሀብት ክምችት የሌሎች ኢንዱስትሪዎች መቀጣጠያ ከመሆን ፈንታ አትራፊነታቸው ደካማ የሆነ፣ ብዙ ወጪና ብክነት ከብቃት ችግር ጋር የነበረባቸው፣ ማለትም እዚያው ፈላ እዚያው ሞላ በሚባል ዓይነት ችግር የተጠመዱ ነበሩ (John Farndon China Rises 33)፡፡ የኅብረት እርሻዎችም በአዲስ ሀብት ስነቃ የግስጋሴ ሞተር መሆን የተሳናቸው መሆናቸው በግልጽ የሚታይ ነበር፡፡ እንዲያውም በዚህ ጥቅል ችግር ውስጥ ማሻሻያን ጠቋሚ ፍንጭ ነበር፡፡ ገበሬዎች የመንግሥት ፖሊሲ የነበረውን የኅብረት እርሻን ቅርፅ ከላይ እንዳለ ጠብቀው ከውስጥ ግን በድብቅ መሬትን ተከፋፍለው ውጤታማ የሆኑበት ልምድ ብቅ ብሎ ነበር፡፡ ለእነ ዴንግ ይህ ዓይን ገላጭ ሆኖ ገበሬዎች መሬታቸውን በግል እየያዙ ያሻቸውን እንዲያመርቱ ሲለቋቸው አስገራሚ የገቢ መመንደግ ሊንተረከክ ቻለ፡፡ ከግብርና የሚገኝ ከፍተኛ ትርፍም ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪ ነክ ሥራዎች በየገጠር ከተማ ተብዬ አጥቢያዎች ሁሉ በሺዎች፣ በሚሊዮን፣ በመቶ ሚሊዮን ቁጥር መፍለቅ መፍለቅለቅ ቻሉ (ከላይ የተጠቀሰው 81)፡፡ የፈዘዙ ሌሎች የመንግሥት ኢንዱስትሪዎችም በስተኋላ በአትራፊነት በሚወሰን ህልውና ራሳቸውን ችለው፣ ሥራው የሚሻውን የሠራተኛ ቁጥርና ጥራት ይዘው፣ የአሠራር ለውጥ አድርገውና በውስጥና በውጭ ሽርክና ተይዘው ወይም ሙሉ ለሙሉ ወደ ግል ተዛውረው እንዲንቀሳቀሱ ሲደረጉ ግስጋሴ ማሳየት ሰምሮላቸው ነበር (33-36)፡፡

  ወደ ውጭ በመላክ ላይ ያነጣጠሩ የቻይና ኢንዱስትሪዎች ልማት የተካሄደው ግን በዋናነት በደቡብና በደቡብ ምሥራቃዊ የባህር ዳር የአገሪቱ አካባቢ ነው፡፡ ይህን አካባቢ ‹‹ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና” አድርገው እነ ዴንግ ዚያዎ ፒንግ ሲያቅዱ የዋጋ ተወዳዳሪ አዋጭነትን አስበው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ዕቅዳቸውም በቻይና ምሥራቃዊ የባህር ዳር አገር አካባቢ ኢንዱስትሪያዊ የሥራ ከፈታና ክተማ እንደ እንጉዳይ እንዲፈላ አድርጓል፡፡ ለዚህም አንዱ ዋና ሳቢ ጥቅም የሠራተኛ ዋጋ መርከስ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ1990 በሆንግ ኮንግ አማካይ የፋብሪካ ሠራተኛ ዋጋ በሰዓት አራት የአሜሪካ ዶላር በነበረ ጊዜ፣ በቻይና ደቡባዊ ክፍል ጉዋንዶንግ ውስጥ 50 የአሜሪካ ሳንቲም ነበር (ገጽ 17)፡፡ ይህ የሰፋ ርካሻነት የሆንግ ኮንግ ባለፀጎችንና ሥራ ከፋቾችን ወደ ቻይና ደቡብ ምድር አጉርፏል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1991 ብቻ 25 ሺሕ የሆንግ ኮንግ ሰዎች ሦስት ሚሊዮን ቻይናውያንን የቀጠሩ ሥራዎችን በዚያ አካባቢ መክፈት ችለው ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ1985 2.9 ቢሊዮን ዶላር ያህል ወጪ ሸቀጥ ከጓንግዶንግ ተልኳል፡፡ በ1994 ዓ.ም. ወጪ ንግዱ ወደ 50 ቢሊዮን ዶላር ተተኩሷል፡፡ አሁንም እ.ኤ.አ. በ1990ዎች ከቻይና ወጪ ንግድ ውስጥ የጓንግዶንግ ድርሻ 40 በመቶ ነበር፡፡ በጓንግዶንግ የጀመረ ለባህር ዳርቻ የቀረበ የኢንዱስትሪ መስፋፋት በሌሎች የባህር ዳርቻ አካባቢዎችም ተዛምቶ፣ የዓሳ አጥማጆች ትንሽ ከተማ የነበረችው ሼንዜን በጥቂት ዓመታት ውስጥ የኢንዱስትሪ ሌላ ማዕከል ለመሆን ቻለች፡፡ (በረከት ስምዖን ‹‹ትንሳዔ ዘኢትዮጵያ›› በተሰኘ መጽሐፉ ገጽ 325 ላይ፣ ከገጠር ኢንዱስትሪና ከዓሳ አጥማጆች ከተማነት ተነስታ በ30 ዓመታት ውስጥ ‹‹12 ሚሊዮን ቻይናውያን የሚኖሩባት ሜትሮፖሊ ከተማ›› ብሎ የሚለን፣ ይህችን ለባህር ዳር ቅርብ የነበረችና በልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና ዕቅድ መስፋት ውስጥ የተመዘዘች ከተማን ነው፡፡)

  በቻይና ደቡብ ምሥራቃዊ የአገሪቱ ክፍል የታየው የኢንዱስትሪ መስፋፋት ብዙ ነገር ለዋውጧል፡፡ የአገሪቱ የሕዝብ ክምችት ምዕራባዊና ሰሜናዊ አካባቢ ላይ እየሳሳ፣ ወደ ምሥራቅ አካባቢ ግን እየተጨናነቀ እንዲሄድ አድርጓል፡፡ ከፍተኛ የሀብት/የገንዘብ እንቅስቃሴና የሥልጣኔ መናኸሪያ ምሥራቃዊው ክፍል የሆነበት፣ ምዕራባዊውና ሰሜናዊው አካባቢ ደግሞ የድህንት አካባቢ የሆነበት መዛባት ተፈጥሯል፡፡ ቤተሰቡን እርሻ ሥራ ላይ ትቶ የሚፈልስና ደቡብ ምሥራቃዊ አካባቢ በጊዜያዊ ነዋሪነት እየቆየ የሚመለስ፣ ድህነትን ለማራገፍ ለረዥም ሰዓት በርካሽ ዋጋ የሚሠራ፣ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ተነቃናቂ ሠራተኛም ፈጥሯል (China Rises, 66)፡፡

  ዛሬ አሜሪካን በልዕለ ኃያልነት ልቆ የማለፍ አፋፍ ላይ ቻይናን ያደረሳት ግስጋሴ 1980ዎችን ይዞ በ40 ዓመታት ውስጥ የተገኘ የምዕራባዊ ዘይቤ በረከት ተደርጎ ይቃለላል፡፡ ይህ ግን የተሳሳተ ነው፡፡ በቅድሚያ ቻይና በኢምፔሪያሊስት ወረራ ሥር ከመውደቋ በፊትና የእነ እንግሊዝ ኢንዱስትሪ አብዮት ለውጥ ከማምጣቱ በፊት፣ በኢንዱስትሪ ቀመስ ዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ በጉልህ የምትታወቅ አገር እንደነበረች መዘንጋት የለበትም፡፡ ያ የኢንዱስትሪ ቀመስነት ቅርስ ከ1949 ዓ.ም. ወዲህ ለነበረችው የማኦ ዘመን ቻይናም ይሁን ለእነ ታይዋን፣ ለሆንግ ኮንግ፣ ለሲንጋፖር፣ በአጠቃላይ ቻይናውያን ለተሠራጩባቸው የፓስፊክ እስያ አካባቢ ሁሉ የጀርባ ማኮብኮቢያ ሆኖ ጠቅሟል፡፡ በሆንግ ኮንግ የመመንደግና የብልፅግና ታሪክ ውስጥ ከሻንጋይ የተሰደዱ ሥራ ፈጣሪዎች ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ዋናዋ የቻይና ምድር የፖሊሲ ለውጥ ካደረገች በኋላ ደግሞ በምዕራባዊ ዘይቤ ውስጥ ያደጉት በሆንግ ኮንግ፣ በታይዋን፣ በሲንጋፖርና በአካባቢው ተሠራጫጭተው የነበሩትና አሜሪካ ድረስ የተሻገሩት ቻይናውያን ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፡፡ የቻይናን ዋና ምድር እያሳደጉ እነሱም አድገዋል፡፡ ከዚህ ጋር፣ በ‹ሶሻሊስትነት› ውስጥ ከሶቪየት ኅብረት ዕገዛ ጋር የተፈጠሩ ኢንዱስትሪዎችም የራሳቸውን የመንደርደሪያ ድርሻ ተጫውተዋል፡፡

  ቻይና በ1980ዎች (እ.ኤ.አ.) ውስጥ በሚኒስቴር አስተዳደር ውስጥ ለየብቻ ቆመው የነበሩ የልማት ኢንተርፕራይዞችን እርስ በርስ የማያያዝ ሥልት ቀይሳ፣ በ1990ዎች ውስጥ 120 ትልልቅ ድርጅቶችን በ‹ብሔራዊ ቡድንነት› ለመምረጥ መሠረት የሆናት የሶሻሊስት ዘመን ኢንዱስትሪያዊ መነሻ ነበር፡፡ ከአሜሪካና ከአውሮፓ ትምህርት ወስዶ፣ ከምዕራብ የተወሰደውንም ትምህርት ከምሥራቅ እስያ (በተለይም ከጃፓን ፈጣን የኮርፖሬት ኩባንያዎች አስተዳደግና በማራኪ ዋጋ ወደ ውጭ ከሚልክ ነጋዴነት) ጋር አጣጥሞ፣ የውስጥ ኢንዱትሪያዊ መነሻን ከአካባቢያዊው አቅም ጋር በማዛመድ ግስጋሴ፣ ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ማትረፍ የቻሉ ኩባያዎችንና የንግድ ምልክቶችን የማጎልበት ዕርምጃን የመምራቱ ስኬት ደግሞ የቻይና መንግሥታዊ ሚና መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡

  እስካሁን ከተባለው ለባህር በር ቅርብ መሆን በላኪ ንግድ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ ሰበዝ እንደሆነ፣ ቻይናን የሚያክል ሰፊ አገር ላኪነት ላይ ያተኮሩ የኢንዱስትሪ ክምችቶቿን በደቡብ ምሥራቃዊ ዳር አገሯ አካባቢ እንድትገጠግጥ ያደረጋትም ይኼው ጥቅም እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህንን ምዕራባዊና ሰሜናዊ ክፍሏን ከደቡብ ምሥራቃዊ ወደ ኋላ ያስቀረ አካሄድ ለማስተካከል የተያዘው፣ ወደ ምዕራብና ወደ ሰሜን ልማትን የማስፋት ፖሊሲ በቅርብ ጊዜ የመጣና አሁንም ያልተጠናቀቀ ሥራ ነው፡፡

  ለዚህም ቢሆን የልማት ሞተሩ አዋጪነት ነው፡፡ ለባህር ዳርቻ ቅርብ የሆኑት የቻይና ምሥራቃዊ የኢንዱትሪ ማዕከላት በሕዝብ ክምችት እየተጨናነቁና በኑሮና በሠራተኛ ዋጋ እየተወደዱ ሄዱ፡፡ ይህ ለውስጥም ሆነ ለድንበር ዘለል ባለሀብቶች ማነቆ ነበር፡፡ የምዕራባዊ ሰሜናዊ የቻይና ምድር ከደቡባዊ ምሥራቁ ጋር ሲተያይ የድህነት ቀጣና መሆን፣ ለቻይና መንግሥትም መሳጫ ከመሆን ባለፈ የፖለቲካ ቀውስ መፈንጃ እንዳይሆን አሳሳቢ ነበር፡፡ ከምሥራቅ ዳር አገር ወደ ምዕራብ በሺሕ ቤት በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቆ ሲኬድ የሚገኘው የፋብሪካ ሠራተኛ ዋጋ ሻንጋይና ጉዋንግዙ ውስጥ ከሚከፈለው በግማሽ ያህል ቅናሽ ሊገኝ መቻሉ፣ ኢንዱስትሪ ነክ ሥራ ከፋቾችን የሚስብ ማትጊያ ሆነ፡፡ ያልተነካ የሕዝብ ገዥነት ዕድልን ማነፍነፍ ራሱ ወደዚያ ይገፋ ነበር፡፡ በዚያ ላይ የመሬት በቀላል መገኘት፣ ያልተጨናነቀ መሠረተ ልማት በፍጥነትም ሆነ ሻል ባለ ዋጋ ለመገኘት መቻሉ ሁሉ መሳቢያ ሆኖ አገልግሏል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ሥራ ከፋቾችን ለመሳብ ሲባል አስተዳደሮች የሚሰጡት የግብር፣ ወዘተ እንክብካቤ፣ የሙስና ወጪና የኑሮ ወጪ መቅለል ሁሉ ከባህር ዳርቻ ርቆ የኢንዱስትሪዎችን ወደ ውስጥ መጥለቅን ጠቅመዋል፡፡

  የጨራረፍናቸው የአገሮች ልምዶች ከሌላው ጥፋትና ልማት መማር እንደሚያሻ ሁሉ፣ ዘመንንና የየአገርን ዓይነተኛ ባህርያት ለይቶ አውቆ ልማትን መቀየስ እንደሚገባ ለመገንዘብ ይጠቅማሉ፡፡ ኢትዮጵያን ከቻይና ጋር ካስተያየናትም ለወደብ አገልግሎት ከመክፈሏ በቀር፣ ለባህር በርና ለባህር የንግድ መስመር ሩቅ ነኝ የሚል ሰበብ ልታበጅ አትችልም፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡባዊ ምሥራቅ የድንበር አካባቢ ድረስ ለባህር በራፎች ቅርብ ነች፡፡ እናም ይህንን ቅርበት ተመርኩዛ ቻይና በተጓዘችበት መንገድ ትጓዝ? ወይስ የአሁኑ ዘመን ለኢትዮጵያ የከፈተላት ሌሎች አማራጮች አሉ?

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...