Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ይድረስ ለሪፖርተርስላገለገሉ ተሽከርካሪዎች የቀረበ ሐሳብ

  ስላገለገሉ ተሽከርካሪዎች የቀረበ ሐሳብ

  ቀን:

  ከሰሞኑ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡበትን ሁኔታ በሚመለከት እየተሰራጩ ያሉ ዜናዎች ስላሳሰቡኝ ሕግ ከመውጣቱ በፊት የበኩሌን አስተያየት ለመስጠት ተገድጃለሁ፡፡

  በአገራችን የሚገኙትንና ወደፊት እንዲገቡ የሚታሰቡትን ማንኛውንም ዓይነት ተሽከርካሪዎች (የሥራም ሆነ የቤት አውቶሞቢል) በሚመለከት ጥናት አካሒደዋል የተባሉት ወገኖች፣ አገራችን የምትገኝበትን የመኪና ጥገናና የጥገና ወጪ እንዲሁም መኪኖቹ የተፈበረኩበትን ዘመን የሚያሳየውን የልዩነት ሁኔታ እንዲሁም እየቀረበ ያለውን የነዳጅ ዓይነት በተመለከተ ዕውቀቱ የሚያንሳቸው ወይም ሆን ተብሎ የዘለሉት መስሎ ይታየኛል፡፡ የቀረቡትን ምክንያቶች ስንመለከት የአካባቢ ብክለትን፣ አደጋን ለመቀነስ እንዲሁም በአገር ውስጥ የሚገኙ አምራቾችን ለማገዝና የመለዋወጫና የጥገና ወጪን ለመቀነስ የሚሉ ናቸው፡፡ የመፍትሔ ሐሳብ የተባለውም ከአምስት ዓመት በላይ የሆናቸው ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ የሚል ነው፡፡

  የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ እንዲቻል ለተባለው፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አጥንተው ባቀረቡት መሠረት፣ በባንክ ልዩ ድጋፍ ጭምር ወደ አገራችን ገብተውና እዚሁ ተገጣጠሙ የተባሉትን፣ አምስት ዓመታት እንኳ በቅጡ ያልሞላቸውን ቻይና ሠራሽ መኪኖች በየመንገዱ ያሉበትን ሁኔታና የሚወጣቸውን ጭስ መመልከቱ በቂ መልስ የሚሰጠን ይመስለኛል፡፡

   

  አደጋን ለመቀነስ ለተባለው አሁንም የቻይናውን ሲኖ ትራክን የተሰኘውን ከባድ ተሽከርካሪ ማየቱ በቂ ነው፡፡

  በአገር ውስጥ የሚገኙ አምራቾችን ለማገዝ የተባለውም ቢሆን፣ በአገር ውስጥ አምራቾች ተገጣጥመው ገና ሁለት ዓመት እንኳ ሳይሞላቸው በምን ደረጃ የሚገኙ የከተማ አውቶቡሶች እንዳሉ፣ የአንበሳ አውቶቡስ ሜካኒኮች በቅርቡ በቴሌቪዥን ቀርበው የሰጡትን አስተያየት መመልከቱ በቂ መረጃ የሚሰጠን ይመስለኛል፡፡

  የመለዋወጫና የጥገና ወጪን በሚመለከት የቀረበውም ቢሆን እኔ እስከማውቀው ድረስ፣ የጥገናም ሆነ የመለዋወጫ ወጪ ከዕድሜ ጠገቦቹ ይልቅ ለአዲሶቹ የሚቀርበው እንደሚበልጥ ነው፡፡ ምክንያቱም አዳዲሶቹን መኪናዎች ለመጠገን በየጊዜው ለመፈተሽ ዘመኑ የሚጠይቃቸው ቴክኖሎጂዎች፣ መመርመርያና ሌሎችም አቅርቦቶች ላይ ከሚታይባቸው ውስንነት በተጨማሪ የሚታይባቸውን ችግር የሚጠቁም መሣሪያ ስለሚፈልጉና በተወሳሰበው የጉምሩክ አሠራር ምክንያት አብዛኛዎቹ ጋራዦች እነዚህን መሣሪያዎች ስለማያገኙ፣ ሜካኒኮችም ስለማያውቋቸው፣ ከተገኙም በተወሰኑ ጋራዦች ውስጥ ብቻ ስለሚኖሩ ችግሩ በአዲሶቹ ላይ ይበረታል፡፡ በተጨማሪም በነዳጅ ቦቴዎች ከነጭ ጋዝና ከሌሎች ምንነታቸውን ከማናውቃቸው ነገሮች ጋር ተዋህዶ የሚቀርብልንና ደረጃው ያልታወቀውን ነዳጅ ሞተራቸው ሊቋቋመው የሚችለው የቆዩት መኪናዎች ስለመሆናቸው አያጠያይቅም፡፡

  የአገልግሎት ዘመናቸው አምስት ዓመት ብቻ እንዲሆን የተመረጠበት ምክንያትም ለእኔ ግልጽ አይደለም፡፡ ከዚህ በመነሳት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አንድ ዓመት እንኳ ሳይሞላቸውና በአሁኑ ጊዜ አገራችን ውስጥ በጣም አጣዳፊ ውሳኔ የሚጠይቁ ጉዳዮች እንዳሉባቸው ስለሚታወቅ፣ በእሳቸው የተሾሙት ባለሥልጣናትም ወንበራቸውን ሳያደላድሉና ነገሮችን በአግባቡ ሳይረዱ፣ ከአስመጪውም ሆነ ከባለጋራዦች ጋር ግልጽ ውይይት ሳይደረግበት ረቂቅ ሕጉን አጣድፎ ለማጸደቅ የተጀመረው ሩጫ ዓላማው ለአገርና ለሕዝብ ታስቦ ሳይሆን በግርግር ጥቂት ቡድኖችን ለመጥቀም ያለመ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

  ስለሆነም በእኔ እምነት አጥኚ ቡድን የተባላችሁት ሰዎች ሲፈበረኩ ቀኝ መሪ ሆነው ከተመረቱትና ወደ አገራችን ለማስገባት ሲባል ወደ ግራ መሪ ዞረው ከሚመጡት መኪናዎች በስተቀር ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡበትን አግባብ ለጊዜውም ቢሆን ተወት አድርጉ፡፡

  ይልቁንም በከተማው የትራፊክ ሕግና ሥርዓትን ሳንከተል የምንተራመሰውን የመኪና አሽከርካሪዎችና እግረኞች የመንገድ አጠቃቀማችን የሚሻሻልበትን ሕግና ሥርዓት መሥራቱ ላይ ማተኮር ይገባ ነበር፡፡ የትራፊክ ፖሊሶቻችን ሕግና ሥርዓት በአግባቡ የሚያስከብሩበትን፣ ከጉምሩክ ጋር በመነጋገር ሜካኒኮቻችን ከዘመናዊው የመኪና መመርመሪያ መሣሪያ ጋር የሚተዋወቁበትንና ጋራዦቻችን የተሟሉና ዘመናዊ የሚሆኑበትን፣ በጉምሩክ የተሳሳተ የዋጋ መረጃ ሰጪነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እየተጠቀመበት ያለውን፣ መንግሥትንም ለተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ብክነት የዳረገውን የተጋነነ የመኪናዎች የማስገቢያ ዋጋ ለማስቀረት ይረዳ ዘንድ በዓለም የሚሠራበትን ተቀራራቢ የመኪናዎች ዋጋ አጥንታችሁ ለሚመለከታቸው አካላት ብታቀርቡ የተሻለ ይሆናል፡፡

  ***

  ችግራችን ዘመናዊ የፓርላማ አዳራሽ ይሆን?

  አንድ ነገር ላውጋችሁ፡፡ ዛሬ ዓለማችንን ከወታደራዊ ጡንቻቸውም በተጨማሪ በጠንካራ ኢኮኖሚ እያንቀጠቀጡ ያሉት የምዕራብ አገሮች የፓርላማ አባላት ተሰባስበው የሚመክሩበት፣ በአገራቸው ጉዳይ ወይም የዓለምን ዕቅድ ከዕለት የሕይወት አዙሪት የሚያሽከረክሩበት የመሰብሰቢያ ወይም የፓርላማ አዳራሻቸውን ከድረገጽ ለማየት እንሞክር፡፡ ለምሳሌ የሥልጣኔ በር ከፋች የሆነችው የአውሮፓዊቷን የግሪክ የፓርላማ አዳራሽ፣ አልያም የታላቋ ብሪታኒያን የፓርላማ አዳራሽ እናስተውል፡፡ ሌላም ብዙ ዋቢ መጥቀስ ይቻላል፡፡

  እንግሊዞች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ቱባ ሚኒስትሮችና ሌሎቹም የፓርላማ አባላት እግር ለእግር ገጥመው ዱላ ቀረሽ የሐሳብ ፍጭት አድርገው ግሩምና በሚገባ የተመከረባቸውን የውሳኔ ሐሳቦች የሚያቀርቡትና የሚያጸድቁት፣ በጠባቧ የፓርላማ አዳራሽ ነው፡፡ ከዚህ ፓርላማ አዳራሽ የሚወጡትን አንቃናቂ ውሳኔዎችና ሕጎችን ስናይ ከመደነቅ በቀር ምን ማለት ይቻለናል? እነዚያን ድንቅ አዳራሾች በ18ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ገንብተው ያወረሷቸው የቀደሙ ትውልዶች ታሪካዊ ሀብቶች ናቸው፡፡ የእንግሊዝ ፓርላማ ምናልባትም የዘመኑን ድንቅ ቴክኖሎጂዎች ከማካተት በቀር፣ የሕንፃው መገልገያዎች፣ ሌላው ቀርቶ የመቀመጫ ወንበሮቹን እንኳ በነበሩበት አግባብ ታሪካዊ ማንነታቸውን ሳይቀይሩና ሳይቀንሱ ይጠቀሙባቸዋል፡፡

  ካላቸው ሀብት፣ ካለቸው የሠለጠነ የሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ ልቀት አኳያ አዲስና ዘመናዊ ሕንፃ መደንቀር ተስኗቸው አይመስለኝም፡፡ በአዲስ አስተሳሰብ መገንባት የፈለጉት የመንግሥት የሥራ ዘመናቸውን ለመከወን በየወቅቱ የሚሰባሰቡትን የፓርላማ አባላትን እንጂ፣ ዕድሜ ለቀደመው ትውልድ መሰብሰቢያው አይጨንቃቸውም፡፡ ኢትዮጵያ በእኔ ዕይታ ለመጪው ትውልድ ጭምር ለምክክር፣ ሕግ ለማውጣት፣ በሐሳብ ለመፋጨት የሚያስችል በቂ የፓርላማ አዳራሽ አካቶ እንዳስፈላጊነቱ ዘመኑ የፈበረካቸውን ዘመናዊ የሚዲያ ቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ማከል ብቻ ላለን የሕዝብ እንደራሴዎች ሕንጻ በቂ ነው፡፡ በሕንጻ ላይ ሌላ ሕንጻ ለመገንባት መሯሯጥ የበጀት ማሟያ ዳርጎት በሚሰጡን ምዕራባውያን ፊት መሳለቂያ መሆን ነው፡፡ ከ40 በመቶ በላይ ሕዝብ ንፁህ የመጠጥ ውኃ እያጣ በጥም በሚቃጠልባት አገር ውስጥ የቱ መቅደም እንዳለበት ማሰብ ከቸገረን መቼም አስገራሚ ነው፡፡

  (ቧዘ ነኝ ከአዲስ አበባ)

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...