Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

  የሳምንቱ ገጠመኝ

  ቀን:

  የዚህ ዘመን አሳሳቢ ነገሮች ከመብዛታቸው የተነሳ የቱን አንስቼ የቱን ልተወው ያሰኛል፡፡ ያም ሆነ ይህ ከብዙዎቹ ጉዳዮች መካከል እኔ አንዱን ላነሳ ተገድጃለሁ፡፡ በተለይ ይኼንን የረጋና ለዘመናት በመከባበርና በመተሳሰብ አብሮ የኖረን ሕዝብ የማይወክሉ፣ ነገር ግን ቆም ተብሎ ካልታሰበባቸው እያደር ሥር እየሰደዱ የሚሄዱ አደገኛ አዝማሚያዎች እያታዩ ነው፡፡ ሕዝባችን ውስጥ የሚታዩት ጨዋነት፣ ይሉኝታ፣ ታጋሽነት፣ ደግነትና የተለያዩ ዓይነት የፍቅር መገለጫዎችን የሚያነጥፉ ክፋቶች የገጠመኜ መነሻ ሆነዋል፡፡ ሕዝብን በተለያዩ ጉዳዮች ማጣላትና ማጋጨት፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ የንፁኃንን ደም ማፍሰስ ተለመደ፡፡ አሁን ደግሞ ይኼንን አሳዛኝ ድርጊት ወደ ሃይማኖት ለመቀየር ሙከራዎች እየታዩ ነው፡፡ ይህ ችግር ግን በጣም መሠረታዊ የሆነ መነሻ አለው፡፡ እስኪ በገጠመኞች እንየው፡፡

  በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሐሳብ ልውውጥ ሲደረግ፣ ሐሳቡ ላይ ተመርኩዞ አስተያየት መስጠት ሲገባ ያልተገባ አተካራ ውስጥ ይገባል፡፡ አንድ ሰው የሚያምንበትን ነገር በነፃነት ሲናገር ወይም ሐሳቡን በጽሑፍ ሲያሰፍር፣ ከሐሳቡ ጋር ሊኖር የሚገባው ሙግት ይቀርና ግለሰቡ ላይ ዘመቻ ይጀመራል፡፡ የግለሰቡ ዘር፣ ሃይማኖት፣ የፖለቲካ አቋምና የአኗኗር ዘይቤው ላይ ትኩረት ይደረጋል፡፡ ግለሰቡ የሚመዘነው ይዞ በቀረበው ሐሳብ ወይም አመለካከት ሳይሆን፣ ሌሎች እሱ ላይ በለጠፉት ምልከታ ብቻ ነው፡፡ ይዘቱ ሳይሆን ቅርፁ ላይ ይተኮራል፡፡ ይኼ ደግሞ በአብዛኛው የሚንፀባረቀው ፊደል በቆጠረውና የተሻለ ትምህርት አለው በሚባለው የኅብረተሰብ ክፍል ነው፡፡

  ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ተግባራዊ መሆን የሚችለው፣ ሰዎች የፈለጉትን አቋም በመሰላቸው መንገድ ማንሸራሸር ሲችሉ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የዴሞክራሲ አንዱ መገለጫ ነው፡፡ አንድን ጉዳይ መደገፍም ሆነ መቃወም የግለሰቡ መብት ሲሆን፣ የመቀበል ወይም ያለመቀበል መብት ደግሞ የአዳማጩ ወይም የአንባቢው ነው፡፡ ከዚያ ውጪ እኔ የምደግፈውን ካልደገፍክ፣ እኔ የማቀነቅነውን ካላስተጋባህ፣ ወይም የእኔ ዓይነት ማልያ ካልለበስክ ማለት ይኼንን ሥልጡን ዘመን የማይወክል አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡ አንድ ሰው የፈለገውን የሙዚቃ ሥልት የማዳመጥ፣ የሚወደውን የቀለም ዓይነት የመጠቀም ወይም ውበትን በራሱ መንገድ የማድነቅ መብቱ እንደሚከበርለት ሁሉ፣ በፖለቲካም ሆነ በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የፈለገውን የመቀበልና ያለመቀበል መብቱ ሊከበርለት ይገባል፡፡

  አንዲት የሥራ ጓደኛዬ በቅርቡ ምሣ እየበላን ሳለ አንድ ጉዳይ ለውይይት ታቀርባለች፡፡ እሷ የምትለው በአገር ጉዳይ ባለቤት ማን ነው? እንግዳስ ማን ነው? የሚለው አከራካሪ ነገር ብዙዎችን እያደናቆረ መሆኑን ነው፡፡ አንዱ ከአገር በፊት ማንነቴ ይቀድምብኛል ሲል፣ ሌላው የምን ማንነት ነው አገር እያለችልህ ይላል፡፡ ይህ ጭቅጭቅ በተለይ በፌስቡክ መንደር ብዙዎችን ያናጀሰ ነው፡፡ ማናጀሱ ብቻ ሳይሆን ለስድብ፣ ለዘለፋና ለማስፈራራት ጭምር የተጋለጠ አጀንዳ ሆኗል፡፡ ሰዎች በቅጡ መነጋገር ቢችሉ ኖሮ ጭቅጭቃቸውስልቻቀልቀሎቀልቀሎስልቻከሚለው አባባል አይዘልም ነበር፡፡ አንዱ ማንነት ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ አገርን ከሚያብጠለጥል፣ ሌላውአገር አገር. . .› እያለ ማንነትን ከሚያበሻቅጥ ግማሽ መንገድ ላይ ተገናኝቶ መነጋገር ቀላል ነው፡፡ አሁን ግን ዛቻና ድንፋታው ሥልጣኔ ይመስል፣ የብዙዎችን አለመብሰል እያጋለጠ ነው፡፡ ከእነሱ አልፎ ተርፎም ሌሎችን እያጋደለ ነው፡፡

  ሌላው ጓደኛዬ የገጠመው ደግሞ ይኼንን ይመስላል፡፡ አንድ በአካባቢው የሚኖር ሰው በወንጀል ይጠረጠርና ይታሰራል፡፡ የታሰረበት ቦታ ሊጠይቀው ሄዶ ምን እንዳጋጠመው ይጠይቀዋል፡፡ ሰውየው ስለታሰረበት ምክንያት ምንም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ይነግረዋል፡፡ ከጎረቤቶቹ ጋር ስለታሰረው ግለሰብ ጉዳይ ሲወያዩ፣ ጓደኛዬ ሰውየው ለምን እንደታሰረ እንደማያውቅ እንደነገረው ይነግራቸዋል፡፡ አንደኛዋ ጎረቤት ግን ሰውየው የታሰረበትን ምክንያት እንደሚያውቀው፣ ጉዳዩም ከዘረፋ ጋር የተያያዘ መሆኑን፣ ፖሊስ ባደረገው ብርበራም የዘረፋቸውን በርካታ ገንዘቦችና ጌጣጌጦች መያዙን ትዘረዝራለች፡፡ ፖሊስ ምርመራውን ጨርሶ ዓቃቤ ሕግ ጥፋቱን ዘርዝሮ ክስ መመሥረቱን ታክላለች፡፡ በዚህ መሀል አንዱ፣ ‹‹እንዴት በሰው ፊት ይኼንን ትናገሪያለሽ?›› ብሎ ሴትየዋን ካልገደልኩ ይላል፡፡ በስንት መከራ እንዲረጋጋ ተደርጎ ምክንያቱን ሲጠየቅ፣ ታሳሪው የእሱ ብሔረሰብ ሰው በመሆኑ ገመናው በአደባባይ ሊነገርበት አይገባም ብሎ ደነፋ፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ ሰውየው የሚያከላክለው ፍርድ ቤት በግልጽ የሚቀርብን የወንጀል ክስ ነው፡፡ ይህ ሰው ሴትዮዋ ለምን ይኼንን ተናገረች ብሎ በሌላ ጊዜ ድብደባ ስለፈጸመባት ፖሊስ እየመረመረው እንደሆነ ሰማን፡፡ ሊገድላትም ይችል ነበር፡፡

  በአንድ ወቅት የፌስቡክ ገጼን ከፍቼ የተለያዩ ሰዎች የጻፉዋቸውን ስቃርም፣ ብዙዎቹ ከሥር የሚሰጡዋቸው አስተያየቶች በብልግና ቃላት የታጀቡና የሚያሳፍሩ ነበሩ፡፡ አንዳንዱ ጽሑፍ ሳያነብኮሜንትያደርጋል፡፡ ይኼንን በቀላሉ ማወቅ የሚቻለው የተጻፈው ጉዳይና የሚሰጠውኮሜንትምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም፡፡ አንዳንዱ ደግሞ አንብቦ መረዳት ሲያቅተው ይሳደባል፡፡ የዕውቀት ድሃ ማለት እንዲህ ዓይነቱን ነው፡፡ ገብቶዋቸው ነገር ግን ከዕውነታው ጋር ጠብ ያላቸው ደግሞ ማንነትን፣ ሃይማኖትን፣ የፖለቲካ አመለካከትን ወይም ሌላ ልዩነትን መሠረት አድርገው ሰውን ያንቋሽሻሉ፡፡ ልዩነትን ተቀብሎ ጉዳዩን ከመተቸት ይልቅ፣ ተሳዳቢውና ደንፊው በዝቷል፡፡ በዚህ ዓይነት ማን ነው ዴሞክራቱ? ዴሞክራት ለመሆን እኮ ማንበብ፣ ማሰላሰል፣ መወያየት. . . የግድ ነው፡፡ ያለበለዚያ ግንበኛ የፖለቲካ ሳይንቲስቱን፣ የታክሲ ሾፌር የማክሮ ኢኮኖሚ ሊቁን ሲሳደቡ ሊኖሩ ነው፡፡ ችግሩ ግን ሁሉም የሚሳደበው የእኔ ወገን አይደለም የሚለውን መሆኑ ነው፡፡

  በዚህ ጉዳይ በጣም የተመረረ አንድ ደራሲ ወዳጄ፣ ‹‹ከመጻፍ ይልቅ ዝም የሚባልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ የአደባባይ ሰው ስትሆን ትችትንና ወቀሳን መቀበል የአባት ነው፡፡ ነገር ግን በማንም የዕውቀት ድሃ ባለጌ መሰደብ ያሳምማል፡፡ አንዳንዶቹ ከምን ዓይነት ፍጡር እንደተወለዱ አይገባኝም፡፡ ነገረ ሥራቸው በሙሉ ሰይጣናዊ ነው፡፡ አንዳንዴ ለማረም ወይም ነገር ለማብረድ አስተያየትህን ጣል ስታደርግ ትሰደባለህ፡፡ ስድብ የብልግና እንጂ የዕውቀት መገለጫ አይደለም፡፡ ይልቁንም በትርፍ ጊዜና በምሽት ጭምር ከአስረሽ ምቺው በቀር ምንም ከማያውቁ ሱሰኞች ጋር እንዴት መነጋገር ይቻላል? ከዕውቀት አልባና ከባለጌ ጋር አፍ ከመካፈት ዝም ማለት ይሻላል፤›› ነበር ያለኝ፡፡ እንግዲህ በፖለቲካ አመለካከት፣ በብሔር፣ በጥቅም ጉድኝትና በመሳሰሉት ጎራ እየለዩ መናጀስ ከቀጠለ፣ ተረኛው ሃይማኖት የሆነ ጊዜ ምን ይደረጋል? ወዴትስ ይደረሳል?

  (.. ከአዲስ አበባ)

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...