Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ይድረስ ለሪፖርተርበ40/60 ቤቶች ጉዳይ ለሚመለከታችሁ አቤት እንላለን

  በ40/60 ቤቶች ጉዳይ ለሚመለከታችሁ አቤት እንላለን

  ቀን:

  በመጀመርያ በአገሪቱ እየተካሄዱ ላሉት ለውጦች ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እንዲሁም ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) እና ሌሎችም በየደረጃው ያላችሁ መሪዎች መልካም ጅምሮችን በእናንተ በማየታችን ከሚደሰቱ ብዙኃን መካከል መሆናችንን በመግለጽ ወደ ጉዳያችን እንግባ፡፡

  እንደሚታወቀው መንግሥት የነዋሪዎችን የቤት እጥረት ለመቅረፍ ከጀመራቸው የቤት ፕሮጀክቶች አንዱ 40/60 የቁጠባ ቤቶች ፕሮግራም ነው፡፡ ፕሮግራሙ ሲጀመር ቀድሞ የከፈለ ቀድሞ የቤት ባለቤት ይሆናል በሚለው ውል መሠረት አብዛኛዎቻችን በተቻለን አቅም ከቤተሰብ፣ ከዘመድ አዝማድ ለሌላ አንገብጋቢ ጉዳይ የሚያውሉትን ገንዘብ በልመናም በብድርወስደን ለቤት ቁጠባ ከፍለናል፡፡ እርግጥ ነው አብዛኛው በውጭ አገር የሚኖሩ ወገኖቻችንም በስንት መከራ ያገኙት ገንዘብ ለዚህ ዓላማ የከፈሉ ይመስለናል፡፡

  ይህ ፕሮግራም በአብዛኞቻችን ቤት ፈላጊዎች ዘንድ ተመራጭ ሆኖ መቶ በመቶ የቆጠብንበት ምክንያት፣ በሪል ስቴት ገንቢዎች ዘንድ በ40/60 ዋጋ ቤት መጠን ቤት እንደማይገኝ ስለተረዳንም ነው፡፡ ለዓመታት ስንጠብቅ ቆይተን በሠንጋ ተራና በክራውን በተደረገው የዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓትም መሥፈርቱ መቶ በመቶ ቀድመው ለከፈሉ በሚለው አሠራር መሠረት ቤቶች መተላለፋቸው ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳ በዕጣ አወጣጡ ሲስተም ላይ ዕጣ ውስጥ የገቡ ዕድለኞች ዝርዝር መጀመሪያ ለሕዝብ ይፋ መደረግ እንደነበረበት ብናምንም፣ ይህ ሳይደረግ ቀርቶ ለእነ እገሌ ዕጣው ወጥቷል ተብሏል፡፡ በእኛ እምነት ዕጣ ውስጥ የገቡ ተመዝጋቢዎች ስም ዝርዝር መጀመሪያውኑ ተለይቶ ለሕዝብ ይፋ መደረግ ነበረበት፡፡ ይህ ሁሉ አልፎ ባለፈው የተፈጠሩት ስህተቶች ታርመው ዕጣውም በነበረው አሠራር መሠረት ይከናወናል ብለን ስንጠብቅ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ከ40 በመቶ በላይ የቆጠቡ ሁሉ ዕጣው ይወጣላቸዋል መባሉ፣ የሚከተሉትን ሥጋቶች የሚያጭርና አሁን ያለው አመራርም ነገሩን በውል አልተረዳውም፣ ያልተገነዘበው ጉዳይ ይኖራል ብለን እንድናምን አስገድዶናል፡፡

   ስለሆነም በመጀመርያ ደረጃ መንግሥት መቶ በመቶ የከፈልነው ተርፎንና ኖሮን ሳይሆን፣ አሥርም ሃያም ዓመታት ስንቆጥበው የኖረ ገንዘብ መሆኑ ግምት ውስጥ እንዲገባልን እንጠይቃለን፡፡ አንዳንዶቻችን ከዘመድ አዝማድ በብድር የወሰድነውን ገንዘብ ለቤት ቁጠባው መክፈላችንን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡ በዚህ ገንዘብ ከሪል ስቴት ቤት መግዛት የማይታሰብ መሆኑን፣ ወደዚህ መርሐ ግብር በድፍረት የገባነውም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ደንበኞቹ በተመዘገቡበት የ40/60 ቤት፣ እንደቤቶቹ ክፍል ብዛት ቀድሞ በመቆጠብ ክፍያውን ላጠናቀቀ ቅድሚያ ዕጣ አውጥቼ እሰጣለሁ በማለት በተዋዋለው መሠረት፤ እንዲሁም በተደጋጋሚ በሰጠው መግለጫ መሠረት እምነት አድሮብን መሆኑ ታውቆ ክቡራን መሪዎቻችን እባካችሁ፡

  1. የሕግ የበላይነት በሚከበርበት አገር፣ ባንኩም እንደ ማንኛውም የንግድ ተቋም ከደንበኞቹ ጋር የተዋዋለውን ውል ጥሶ የባንኮችንም አመኔታ እንዳያሳጣ፣
  2. በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ በወቅቱ በተገባው ውል መሠረት ክፍያ መፈጸማቸው እየታወቀ የቀደመው ስምምነት እንዲህ ሲለወጥ፣ በመንግሥትና በባንኩ ላይ ወደፊት እምነት ኖሮት በልማትና በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚያደርገው ተነሳሽነትና ተሳትፎ ሊቀንስ ስለሚችል፣
  3. ባንኮች የሚከተሉት ዓለም አቀፍ የንግድ ሕግ ስላለ፣ የተዋዋሉበትን ስምምነት በመጣሱ በንግድ ባንክ ላይ የሚፈጥረው ትልቅ የእምነት መጓደልና የሕግ መፋለስ ባንኩን በብርቱ ሊጎዳው ስለሚችል፣
  4. በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ የበላይነት ሊከበር አይችልም የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ስለሚችል፣
  5. ሕግን ያለ ጥልቅ ጥናት ተርጉሞ በተፈለገ ጊዜ የባንክና የደንበኞችን ውል ማፍረስ ከተጀመረ፣ በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነትን እንዴት ማምጣት ይቻላል የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ስለሚችል፣
  6. ቀድሞ የተደረገውን ውል ያውም በተዋዋዮች አለመግባባት ሳይሆን፣ በሦስተኛ ወገን በኩል ውሉን ባለቀ ሰዓት መቀየር ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓት አካሄድ ስላልሆነ እርምት ቢወሰድ፣
  7. በባንኩ የውል ስምምነት ውስጥ ከተቀመጡት አንቀጾች መካከል፣ ‹‹የቤት ድልድል ቅደም ተከተሉ በደንበኞች የቁጠባ ልክ፣ በምዝገባ ጊዜና በዕጣ ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት ለብድር ብቁ የሆኑና ከፍተኛ ገንዘብ የቆጠቡ ቅድሚያ ዕድል ይኖራቸዋል›› የሚለው አንቀጽ የተጣሰ በመሆኑ፣ ግዴለም ተቸግረን ከዛሬ ነገ ቅድሚያ እንገኛለን ብለን በቆጠብነው ገንዘብ የመብት ተጠቃሚነታችንን የሚነካ ውሳኔ ምክትል ከንቲባው ስለወሰኑ በድጋሚ እንዲያጤኑት እየጠየቅን፣ ጥያቄያችንን በአንክሮ እንድትመለከቱልን እንጠይቃለን፡፡

  (ከ40/60 ቤት ተመዝጋቢዎች)

  ***

  ትኩረት ለወጣቶች

  የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም፣ ‹‹ወጣቶች ዛሬ ላይ የት እንደሚውሉ ንገረኝና የነገውን የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ እነግርሃለሁ›› ይላል፡፡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አብዛኛው እጅ ወጣት ነው፡፡ ይኼንን ኃይል በአግባቡ ከተጠቀምንበት ጥንካሬም ሀብትም ነው፡፡ ካልተጠቀምንበት ግን ሥጋት ነው፡፡

  ዘኢኮኖሚስት መጽሔት ባደረገው ጥናት መሠረት፣ የአፍሪካ ወጣቶች ሦስት ነገሮች ይፈልጋሉ፡፡ እነዚም የትምህርት ዕድል፣ ነፃነትና የሥራ ዕድል ናቸው፡፡

  ኢትዮጵያ የትምህርት ተደራሽነትን በማስፈን በኩል ያከናወነቻቸው ሥራዎች አበረታች ናቸው፡፡ ይሁንና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ ያሉት ክፍተቶች መደፈን አለባቸው፡፡ ወጣቱ በአገሪቱ ለውጥ እንዲመጣ ከፍተኛ መስዋዕትነትን ከፍሏል፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የሥራ አጥ ቁጥር ወጣት አብዛኛው ድርሻውን ይይዛል፡፡ ስለዚህ አዳዲስ ሥልቶችን በመንደፍ ወጣቱ የሥራ ዕድል እንዲያገኝ ምቹ ነገር ሊፈጠርለት ይገባል፡፡ ለምሳሌ አሁን ካሉት የመንግሥት ሠራተኞች ውስጥ 25 ወይም 30 ዓመታት ያገለገሉት እንደሙያቸው ደረጃ 55 እና ከዚያ በላይ ዕድሜ ልክ ላይ የሚገኙትን የጡረታ መብታቸውን ሰጥቶ በእነሱ ቦታ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ማመቻቸት ይቻላል፡፡

  የመገናኛ ብዙኃንም በአገሪቱ የሚታዩ ግጭቶችን ከማጋነንና ኢትዮጵያ ተስፋ እንደሌላት አስመስሎ ማቅረባቸውን በመቀነስ፣ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታዎችና ዕድሎችን ማሳየት ይገባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ወጣቱን ስለነገ ተስፋ እንዲኖረው ማድረግ አለባቸው፡፡ ተስፋ የሁሉም ነገር መሠረት ነው፡፡ ሁሉም ወጣት በአንዴ ሥራ እንዲያገኝ ማድረግ ባይቻልም፣ ዛሬ ያላገኘውን ነገ ሊያገኘው የሚችልበት ዕድል እንዳለና ተስፋ እንዲያድርበት ማድረግ ይገባል፡፡ ታዋቂው ጸሐፊ ቢል ኮክሲ፣ በሚያነቃቃው መጽሐፉ ስለተስፋ የሚከተለውን ብሏል፡፡ ‹‹ራዕይ ካለህና ለራዕይ ቁርጠኛ ከሆንህ፣ ተስፋ መገንባት ይኖርብሃል፡፡ ተስፋ አንድን ነገር የማድረግ ቁርጠኝነት ነው፡፡ አመንክም አላመንክም ተስፋ ዓለምን ይቆጣጠራል፡፡››

  ‹‹ወደ ጦርነት የሚገቡ ሰዎች እንደሚያሸንፉ ተስፋ ስላላቸው ነው፡፡ ሰዎች ትዳር የሚመሠርቱት በትዳር ላይ ተስፋ ስላላቸው ነው፡፡ በዓለም እንደ ተስፋ የሚያነሳሳ ኃይል የለም፡፡ ተስፋ ወደ ድርጊት ለመግባት ያነሳሳል፡፡ ተስፋ በሌለበት ግን ሰላም ይጠፋል፡፡ አንተን የህሊና ቁስለኛ በማድረግ የሕይወትህን ጤናማነት ጥቅም ያሳጣል፡፡ የሰው ልጅ ውጤታማነት ከተስፋ ጋር በቀጥታ ተያያዥነት አለው፡፡ በራዕይህ ላይ እምነት ካለህና በመጪው ጊዜ ላይ ተስፋ ካደረክ፣ ካሰብከው መንገድ በላይ ብዙ ተጨማሪ ማይሎችን መጓዝ ትችላለህ፡፡››

  ስለዚህ ኢትዮጵያም ተስፋ ያላት አገር እንደሆነችና ሕዝቧም በተስፋ እንደሚጓዝ ማሳየት የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡

  (ስንታየሁ ግርማ፣ ከአዲስ አበባ)

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...