Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

  የሳምንቱ ገጠመኝ

  ቀን:

  ከወቅቱ ትኩሳት ጋር የተያያዘ ገጠመኝ ነው፡፡ ባሳለፍነው ወር በአንዱ የሥራ ቀን ጠዋት በፐብሊክ ባስ የትራንስፖርት አገልግሎት ዓለም ባንክ ከሚባል ሠፈር ወደ ሜክሲኮ ተሳፍረን ትንሽ እንደተጓዝን፣ ከኋላዬ ካለ ወንበር አንድ ግለሰብ ከድምፁ እንደተረዳሁት ከሆነ በዕድሜ ወጣት ይመስለኛል በሞባይል ስልክ መነጋገር ጀመረ፡፡ ድምፁ ጎልቶ ይሰማ ነበር፡፡ ‹‹ምን አድርግ ነው የምትለኝ? የራስህን ምርጫ ውሰድ፡፡ አገሪቱ ሰላም ካጣች አሥር ወራት አለፋት እኮ! ሰው በየአቅጣጫው እያለቀ ነው፡፡ እንዲያው መሪያችን እንደመር እያለ እየቀነሰን ነው፡፡ ይኼ የሒሳብ አስተማሪ . . .›› እያለ ከወዲያኛው አቅጣጫ ከሚያነጋግረው ግለሰብ (በእርግጥም የሚያነጋግረው ሰው መኖሩን በሚያጠራጥር ሁኔታ) መልስ ሳይጠብቅ፣ የመተንፈሻ ጊዜ ሳይኖረው ያዥጎደጉደው ጀመር፡፡

  በመሀል ከተሳፋሪዎች አንድ አንድ እያሉ የተቃውሞ ንግግሮች መሰማት ጀመሩ፡፡ የተከፈለው ነው! ይላል ከአንዱ አቅጣጫ፣ ክፍያው የተቋረጠበት ነው! ይላል ደግሞ ሌላው፣ ተልኮ ነው!” ሌላው ደግሞ ‹‹አገራችን ሰላም ነው ምን ሟርተኛው ነው! መሪያችን የሰላም አባት ነው!›› እና ወዘተ. የመሳሰሉት አንዳንዱም ኃይለ ቃልና ማስፈራሪያ የተቀላቀለበት በሚመስል ከተለያየ አቅጣጫ መሰንዘር ጀመሩ፡፡ በእውነት ነው የምላችሁ ሁኔታው ወዴት ያመራ ይሆን በሚል በግሌ ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ መግባቴን መደበቅ አይቻለኝም፡፡ ከተሳፋሪዎች መሀል አንዳንዶች ሥጋቴን ይጋሩኝ ይመስለኛል፡፡

  ብቻ ደቂቃዎች ሰዓታት ሆነውብኝ መድረሻችን ርቆብኝ በሰላም ለመውረድ እየናፈቀኝ፣ ተናጋሪው ወጣት ግን ከተሳፋሪዎች የሚሰነዘርበትን ተቃውሞ፣ ትችትና ዛቻ ከቁብ ሳይቆጥር፣ መልስም ሳይሰጥ በመቅረቱ ምክንያት ይመስለኛል ሁኔታው ቀስ በቀስ እየበረደ በመሄዱ ሁሉም እንደየ እምነቱ ፈጣሪውን ሳያመሠግን አይቀርም፡፡ ያም ሆነ ይህ አይደረስ የለ መድረሻችን ደረሰና ከአውቶቡሱ ወረድን እላችኋለሁ፡፡ የሌላውን ባላውቅም እኔ በበኩሌ የቤት ሥራ ይዤ ወረድኩ፡፡ በዚያች ቀን ጠዋት ከተሳፋሪዎች ያላዳመጥኩትና ያልተመለከትኩት ነገር ቢኖር ሁኔታውን ለማረጋጋት የሞከረ፣ አልያም የወጣቱን ሐሳብ በድፍረት የደገፈ ወይም መብቱ መሆኑን የገለጸ አንድም ሰው አለመኖሩ ነበር፡፡

  በፍርኃት የታጀበ ጉዞ ማድረጋችን እንዴት ነው ነገሩ? ይህ ‘ዴሞክራሲ’ የሚባል ቃል እንዴት ነው እያስተናገድነው ያለነው? ንግግራችን በሌሎች ዘንድ ምን ያመጣል አለማለታችን፣ በጭፍን መደገፋችን፣ በጭፍን መቃወማችን፣ ሚዛናዊ መሆን አለመቻላችን እስከ መቼ ነው? የሐሳብ ነፃነት ለራሳችን እንደ ምንፈልገው ሁሉ፣ ሌላውም እንዲኖረው መፍቀድ እንዳለብን በማመን በተግባር መግለጽ መጀመርና መለማመድ አይኖርብንም ትላላችሁ? አሁን በአገራችን እየታየ ያለው አለመቻቻል ከፍ እያለ በመምጣቱ ለማኅበራዊ ትስስሩ ሳንካ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡

  የመደመር ጽንሰ ሐሳብና ዕይታችን የተለያየ ሊሆን እንደሚችል በማመን በፍልስፍናው ላይ በዜጎች መካከል ውይይትና ክርክር (Debate) ቢደረግበት፣ በአገር ጉዳይ ላይ በእርግጠኝነት በስተመጨረሻ ዕይታዎቻችን ተደምረው ወደሚያግባባ አረዳድ መምጣታችን የማይቀር ይሆናል፡፡ ነገር ግን እኛ እንደምንፈልገው የተናገረ፣ የተደመረ፣ የተቀደሰ፣ የሐሳብ ልዩነት ያለው ያልተደመረ የተረገመ እያልን ከፈረጅን ጉዳዩ የአገር ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ ፍፃሜዎች ሁሉ ሃይማኖታዊ አንድምታ እንዳላቸው በመቁጠር፣ ተቀበል ካልተቀበልክ ውግዝ ከመአርዮስ እንደ ማለት ነው፡፡ አገራዊና ፖለቲካዊ ዕይታችን ከፍ እያለ ከመጣው ስሜታዊነታችን ጋር አያይዘን እንፈትሸው፣ በማስተዋል እንጓዝ፣ ያገኘውን መልካም አጋጣሚ በገዛ እጃችን ለማጣት አንቸኩል እላለሁ፡፡ ሰላም ለአገራችን!

  (ምግባሩ ታየ፣ ከአዲስ አበባ)

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...