Tuesday, August 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ልናገርኢትዮጵያ ከሙስና ተጋላጭነት ዓለም አቀፍ ደረጃ ለምን ተንሸራተተች?

  ኢትዮጵያ ከሙስና ተጋላጭነት ዓለም አቀፍ ደረጃ ለምን ተንሸራተተች?

  ቀን:

  በተስፋዬ ኢ.

  ለሰዎች የራስ ያልሆነውንና የሌላቸውን ነገር መፈለግና መጣር ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ከአሥርቱ ትዕዛዛት ውስጥ አትስረቅ የሚለው ቃል የተቀመጠው፣ የሰው ልጅ የራስ ያልሆነውን ነገር ከሌላ ሰው በግልጽ ወይም በሥውር መውሰድ ስለሚፈልግ ፈጠሪ የሰው ልጅ ከድርጊቱ እንዲታቀብ በማሰብ ሙሴ እንደ ሕግ በመቀበል እንዲያከብር አዞታል፡፡ የራስ ያልሆነውን የመፈለግ አስተሳሰብ እያደገ የመጣው ደግሞ ሰዎች ሳይለፉ የራስ ያልሆነውን ገንዘብና ንብረት ከሌለ ሰው ወይም ከመንግሥት የሕገወጥ ድርጊትን ተጠቅመው እየወሰዱ ሀብታም መሆን ሲጀምሩ፣ አንዱ ከሌለው እያየና እየተማረ የመጣ ተግባር ነው ማለት ይቻላል፡፡ አገራችን በመንግሥት በተመራችባቸው ዘመናት በሙሉ የራስ ያልሆነውን የሌለውን ሰው ወይም የመንግሥትን ገንዘብና ንብረት በግልጽና በሥውር በመውሰድ ሰዎች ሲጠቀሙበት ኖረዋል፡፡ በግልጽ የተባለው አንድ ሰው የሚፈልገውን ለማግኘት ሲል ተመጣጣኝ ወይም ባነሰ የሚሰጠው ጉቦ ለማለት ነው፡፡

  ይህ ተግባር ዛሬ ላይ መጠኑ አድጎ በሚሊዮኖች በሚቆጠር ገንዘብና ንብረት በሥውርና በግልጽ መወሰድ ተጀምሯል፡፡ የሰው ልጅ ይህን ተግባር ሲተገብር በፈጠሪ ዘንድ የሚያስቀስፍ አስነዋሪ ተግባር እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ግን በሥውር ይሰርቃል፡፡ ወይም ለሚሰጠው አገልግሎት የማይገበውን ጥቅም በግልጽ ጠይቆ ይቀበላል፡፡ በእርግጥ በአሁኑ ዘመን በግልጽ አምጣ እየተባለ የሚወሰድበት፣ የሚሰረቅበት፣ ወይም በሥውር የሚወሰድበት ሁኔታ በስፋት ቢኖርም የተጠየቀውና የተወሰደው ለመንግሥት ጆሮ ከደረሰ በሕግ ይቀጣል፡፡ መንግሥትም ለዚህ ሲል ግልጽ ጉቦና ሥውር ሌብነትን ለመከላከል የሚያስችል ጠንካራ ሕግ አወጥቷል፡፡ ነገር ግን መንግሥት ያወጣው ሕግ ይህን ያህል በሰዎች የሚፈራ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ሌብነት ሙያ ሆኗል፡፡

  ከመንግሥት የሚሰርቁ በስርቆት ሙያ በቂ ዕውቀትና ክህሎት የተላበሱ ሰዎች ናቸው፡፡ በሌብነት ሙያ በጣም የተካኑ ሰዎች ያላቸውን ክህሎትና ዕውቀት ተጠቅመው ሌብነትን በስፋት እየፈጸሙ ናቸው፡፡ በዕቃና አገልግሎት ግዥዎች፣ በጥገናዎች አፈጻጸም፣ በፕሮጀክቶች ትግበራና በመሳሰሉት ከፍተኛ ሌብነት አለ፡፡ በሌብነት ሙያ ክህሎትና ዕውቀት በተላበሱ ሰዎች የተፈጸመው ስርቆት በሕግ ሊቀጣ እየቻለ አይደለም፡፡ ሰዎች በሌብነት ባገኙት ገንዘብና ንብረት ተጠቅመው ዘንጠው እየኖሩ ናቸው፡፡ የወር ገቢያቸው ደመወዝ ብቻ ሆኖ ሳለ ከፍተኛ ሀብት ማከበታቸው በሕዝብ በግልጽ እየታወቀ አይከሰሱም፣ በሌብነት ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቢሄዱም በዋስ እየወጡ ናቸው፡፡ በፍርድ ቤት ተፈርዶባቸው በማረፊያ ቤት ከትንሽ ዓመታት ቆይታ በኋላ የዘረፉትን ሀብትና ንብረት በጠራራ ፀሐይ እየተጠቀሙ ናቸው፡፡ ሰዎች የመጽሑፍ ቅዱስ ቃልና የመንግሥት ጠንካራ የሌባ መቅጫ ሕግ እያለ ሌብነትን ሥራዬ ብለው ተያይዘውታል፡፡ አሁንም እየሰረቁ ናቸው፣ ወደፊትም ይሠርቃሉ፡፡ እንዲያውም የዜግነት ድርሻዬን ልውሰድ የተባለ እየመሰለ ነው፡፡

  ደሃው ግን በጣም እየተሰቀየ ነው፡፡ የቤት ኪራይ አሳሩን እያሰየው ነው፡፡ ትራንስፖርት ችግር ሲባበስ እንጂ ሲቀንስ አይታይም፡፡ ዜጎች በሕገወጥና ስግብግብ ነጋዴዎች እየተገፈፉ ናቸው፡፡ ኑሮ ጣሪያ ነክቷል፡፡ የሚቀመስ ነገር መግዛት እየተቻለ አይደለም፡፡ የአብዛኛው የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ መብራት ኃይል አገልግሎት አሰጣጥን ሳያሻሽል የፍጆታ ዋጋ ጣሪያ ላይ አውጥቷል፡፡ ሕዝቡ ለመክፈልም ሥቃዩን እያየ ነው፡፡  ደሃ አባቱ ማን ነው? ደሃ አባት የለውም፡፡ በደሃ ሕዝብ ስም የሚምለው ብዙ ነው፣ ግን ለደሃ አያስብም፡፡

  ለመነሻ ያህል ይህን ላቅርብ እንጂ አገራችን ውስጥ በንጉሡ ዘመን ሁሉም ነገር የሚጨረሰው የእጅ መንሻ ተብሎ በሚከፈል ጉቦ ነበር፡፡ በሥርዓቱ ጉቦ መቀበልና መስጠት ሕጋዊ ነው ባይባልም ባህል ተደርጎ በጣም ይተገበር ነበር፡፡ የደርግ መንግሥት ዘመንም በተመሳሳይ ጉቦ መስጠትና መቀበል እምብዛም ቁጥጥር የሚደረግበት አልነበረም፡፡ ጉዳይ የሚገደለው በጉቦ ነበር፡፡ ልጅ ብሔራዊ ውትድርና እንዳይሄድ ወላጆች ለአብዮት ጠበቂዎች ጉቦ ይሰጡ ነበር፡፡ በእርግጥ ከመንግሥት ለሚወሰደው ስርቆት ሥርዓቱ የሠርቶ አደር ቁጥጥር ኮሚቴም ሰይሞ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን የመረሸን አዝማሚያም ነበር፡፡ በዘመኑ ደግሞ የገንዘብ እንቅስቃሴ መጠን ውስን ስለነበር ከመንግሥት ካዝና ብዙ መጠን ያለው ገንዘብና ንብረት ስርቆት እየተፈጸመ ነው ለማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ በእርግጥ ጉዳዮች ግን በጉቦ ይገደላሉ፡፡ ሥርዓቱ አሁን ካለው የሌብነት መጠን ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ አልነበረም፡፡ ሌብነት ግን በብዛት ነበር፡፡ መጠቃቀምም በብዛት ነበር፡፡

  በኢሕአዴግ መንግሥት ዘመን ደግሞ የስርቆት ዓይነት መልኩን ቀይሮ መጣ፡፡ የሌብነት ተግባር ከፍተኛ ዕድገት አሳየ፡፡ የሕዝብ ቁጥርም በጣም ጨመረ፡፡ የገንዘብ እንቅስቃሴ መጠንም አደገ፡፡ ስርቆት የሚፈጸምባቸው ዘርፎች በጣም ተበራከቱ፡፡ ይህ ስርቆት በአገራችን ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ መልኩ እየቀየረ ስለመጣ የዓለም አቀፍ አጀንዳም ሆነ፡፡ አንዳንድ አገሮች የራሳቸውን የስርቆት መከላከያ ሕግ እያወጡ ትግሉን ጀምረው ውጤታማም ነበሩ፡፡  ሆንግ ኮንግና ሲንጋፖር የፖሊስ ሥራ ለሌብነት በከፍተኛ ሁኔታ እየተጋለጠ በመምጣቱ ስትራቴጂና ሥልት በመቀየስ ጭምር የፀረ ሙስና አጧጧፉት፡፡ ችግሩ የዓለም አቀፍ በአጀንዳ መሆን ሲጀምር በተባባሩት መንግሥታት ደረጃ ትግሉን ዓለም አቀፋዊ የሚያደርግ ኮንቬሽን ወጥቷል፡፡ ኢትዮጵያም የተባባሩት መንግሥታት ኮንቬሽን መውጣቱን ተከትላ የራሷን የትግል ሕግ አጠናክራ አወጣች፡፡ ኮንቬሽኑንም ፈረመች፡፡ በአፍሪካም በተመሳሳይ አከናወነች፡፡ የወጣውን ሕግ ተከትሎ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽንን አቋቋማች፡፡ ተቋሙም በሰው ኃይልና በበጀት ተደራጅቶ ሥራውን ጀመረ፡፡ ተቋሙ ሥራውን ከጀመረ 18 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ተቋሙ በቆይታው ሁለት ጊዜ ሕጉን አሻሽሏል፡፡ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ሕግ፣ እንዲሁም የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍል ማቋቋሚያ ደንብ እንዲወጣና እንዲተገበር ተደርጓል፡፡ በዘጠኙም ክልሎች የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች እንዲቋቋሙ ተደርጓል፡፡

  የፌዴራልና የክልል የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች ምን ሠሩ? ከሠሩስ ውጤታማ ናቸው ወይ? ውጤታማ ለምን አልሆኑም? እነዚህንና ሌሎችን በዝርዝር ማየት ያስፈልጋል፡፡ አገራችን የፀረ ሙስና ኮሚሽን ያቋቋማችው በግንቦት 1993 ዓ.ም. ሲሆን በወቅቱ የሕወሓት መካከፈል ወቅት ስለነበር፣ የተቋሙ መቋቋም ከሕወሓት ያፈነገጡትን ሰዎች ለማጥቃት ታስቦ ነው፡፡ የሚል አስተያየት እስከ ዛሬ ድረስ ይሰማል፡፡ እንደዚህ ከሆነ ከሕወሓት ያፈነገጡ ሰዎችን ለማጥቃት ሲባል ኮንቬሽኑ ተፈርሟል ሊባል ነው፡፡ ይህ ልክ አይደለም፡፡ ኮንቬሽኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተፈረመ ኢትዮጵያ ተቀብላ የፈረመችው ከአንድ ዓመት በኋላ ስለሆነ፣ የኮሚሽኑ መቋቋምና የሕወሓት አባላት መፈንገጥ ግጥጥሞሽ ይመስላል፡፡ ሆነም ቀረ ኮሚሽኑ ሥራውን የጀመረው ከሕወሓት ካፈነገጡት ሰዎች ውስጥ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ስዬ አብረሃ፣ የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩትን አቶ አባተ ኪሾንና ከእነሱ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሌሎች ሰዎችን በሙስና ወንጀል በመጠርጠርና በመክሰስ ነበር፡፡ ይህም በወቅቱ ኮሚሽኑ የሥርዓቱ ተላላኪና ጉዳይ ገዳይ እንዲባል አድርጎታል፡፡ ቀጥሎም የወቅቱ የምርጫ ቦርድ ጸሐፊ የነበሩትን ለሁለት ቀናት አስሮ በመልቀቁም፣ ይህም ኮሚሽኑ ለሌላ ዓለማ ሲባል እንደተቋቋመ ተደርጎ እንዲወሰድ አድርጎታል፡፡

  ኢትዮጵያ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ያቋቋማችው በወቅቱ ከኢኮኖሚ ድቀት ማገገም ላይ ስለነበረች፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የሚሰጡትን ብድርና ዕርዳታ ከማግኘት ከፈለገች በመንግሥት እጅ የሚገኙ ድርጅቶችን ወደ ግል ዘርፍ እንዲታዞርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ትግል የተጀመረበትን ሙስና ኮሚሽን ማቋቋም እንዳለበት በቅድመ ሁኔታ በማስቀመጣቸው ነበር፡፡ አሁንም የተጠቀሱት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለሚሰጡት ብድርና ዕርዳታ ኮሚሽኑን እንደ ቅድመ ሁኔታ እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡ የተጠቀሱት ድርጅቶችና የቻይና መንግሥት ጭምር አሁንም ከኮሚሽኑ ጋር የጠበቀ ግንኙት ያላቸው ናቸው፡፡ የሚሰጡት ብድርና ዕርዳታ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል በሚል ዕሳቤ፣ የኮሚሽኑን አቅም የሚገነቡ ተግባራት ቅድሚያ ሰጥተው በማከናወን ላይ ናቸው፡፡

  ኢትዮጵያ የፀረ ሙስና ኮሚሽንን ታቋቁም እንጂ ተቋሙ በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነትና ተግባር በአግባቡ እንዳይወጣ በሩን ቆልፋ ነበር የምታንቀሳቅሰው፡፡ ተቋሙ ነፃና ገላልተኛ እንዲሆን አልተደረገም፡፡ ሥራውን በቅልጥፍና እንዲያከናውን አልተፈቀደም፡፡ ከኅብረተሰቡ በሚቀርበው በአብዛኛው ጥቃቅን የሙስና ወንጀል ጥቆማ ላይ ብቻ ላይ ተመሥርቶ እንዲቀንቀሳቀሰ ብቻ ዕግድ ተደርጎበታል፡፡ የራሱ ኢንተለጀንስና ሰርቪላንስ የለውም፡፡ የመንግሥት ተቋማት በኃላፊነት እንዲመሩ የተሰየሙት ሹመኞች የትግሉ ተባባሪ አይደሉም፡፡ ሚዲያዎች ፀረ ሙስና ትግሉን በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲዘግቡ ዕቀባ ተደርጎበቸዋል፡፡ ኮሚሽኑን በበላይነት የሚመሩትና የሥራ ትዕዛዝ የሚሰጡት የአንድ ብሔር ኃላፊዎች ነበሩ፡፡ በቴሌቪዥን ስፖርቶችና ድራማዎች የሚተላለፉትና የሚቋረጡት በእነዚህ ሰዎች ትዕዛዝ ነበር፡፡ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ሕግ በተሿሚው ዙሪያ ያሉትን ቤተሰቦችን ያላከተተ ነው፡፡ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ መረጃ አውቶሜሽን ልማት ሥራ ክትትልና ድጋፍ የሚደረገው፣ በኢንሳ ስለነበር የእነዚህ ሰዎች የእጅ አዙር ቁጥጥር ነበር፡፡

  ስለሆነም የፀረ ሙስና ኮሚሽን ነፃና ገላልተኛ መሆኑ ቀርቶ በኤሌትሪክ ሽቦ አጥር ታጥሮ፣ ለዓለም አቀፍ ተቋማት ማሳያ እንዲሆን ብቻ አለ እየተባለ የኖረ ተቋም በመሆኑ ውጤታማ አልነበረም፡፡ ለዜጎች መስጠት የነበረበትን አገልግሎት አልሰጠም፡፡  የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ወደ ኃላፊነት ሲመጡ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ብሔር በብዛት ያለበትን የመንግሥት ኃላፊዎችንና የተወሰኑ ባለሀብቶችን በሙስና ወንጀል በመጠርጠር እንዲከሰሱ ሲያደርጉ፣ ከላይ የተጠቀሱት የአንድ ብሔር መሪዎች ኮሚሽኑ ከእጃቸው እየፈነገጠ መሆኑን ተረዱ፡፡ ጥቂት ጭፍራዎች ወደ ኮሚሽኑ ልከው በወቅቱ የነበሩትን አመራሮች እያሸማቀቁና እያስፈራሩ ሳሉ፣ የምርምራና የዓቃቤ ሕግ ሥራ ባልታሰበና ባልተጠበቀ ሁኔታ ከኮሚሽኑ እንዲወጠ ተደረገ፡፡ እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ ዘመን የታሰሩ ሰዎች ኮሚሽኑ ከዜጎች በደረሰው የሙስና ወንጀል ጥቆማ ላይ ተመሥርቶ ሳይሆን፣ በመንግሥት ቀጭን ትዕዛዝ ነው የታሰሩት በመቀጠልም ኮሚሽኑ በቆይታው ብዛት ያላቸውን የአንድ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ሰዎች ላይ የምርመራና ክስ ሥራዎችን በስፋት በመሥራቱ፣ በአሻጥር ከሕንፃው ጭምር በማስወጣት የማይሆን ቦታ ላይ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ተደረገ፡፡ አጃኢብ ነው፡፡

  ሌለው ኅብረተሰቡ በፀረ ሙስና ኮሚሽን ላይ ያለው ዕይታ ነው፡፡ ከቆይታ ልምድ ሦስት ዓይነት የኅብረተሰብ ዕይታዎች እንዳሉ ይገመታል፡፡ የመጀመሪያው የአገሪቱን የሙስና ችግር መፍታት ያለበት ኮሚሽኑ ሆኖ እያለ ምንም አልሠራም የሚሉ ኅብረተሰብ አካላት ሲሆኑ፣ ይህ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው በጣም ብዙ ሰዎች ናቸው፡፡ በመሠረቱ ኮሚሽኑ ብቻውን የትም አይደርስም፡፡ ሊደርስም አይችልም፡፡ ኅብረተሰቡ መጀመሪያ ሙስናን መጥላትና መታገል አለበት፡፡ ሙስናን አለመፈጸም፣ የሚፈጽሙትን ሲያይ ለሚመለከተው የሕግ አካል ጥቆማ በማቅረብ በምርመራ ሒደት መረጃ በመስጠትና በፍርድ ቤት ምስክር በመሆን በፅናት መታገል ከሁሉም አገር ወዳድ ዜጎች ይጠበቃል፡፡ ፍርድ ቤቶችም በተመሳሳይ ለሙስና ወንጀል ክስ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት በትክክለኛ ሕግ ላይ ተመሥርተው የኅሊና ፍርድ መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡ ኮሚሽኑ ደግሞ ራሱን ከሙስና ወንጀል በማራቅ የማስተባበሩን ሥራ በትጋት እንዲሠራ መንግሥት ሥራውን በአግባቡ መከታተል፣ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ላይ ወቅታዊ መፍትሔ መስጠት መቻል አለበት፡፡ 

  በተለይ ኅብረተሰቡንና ኮሚሽኑን በአገናኝነት ሚናውን መወጣት ያለበት ሚዲያው ነው፡፡ ኅብረተሰብ፣ መንግሥት፣ ሚዲያውና ኮሚሽኑ ሥራዎቻቸውን በአግባቡ ካከናወኑ በእርግጥ የአገራችን ሙስና ችግር ባይጠፋም ቢያንስ ይቀንሳል፡፡ ሌላው ኮሚሽኑ ራሱ ሌባ ነው የሚል ታፔላ የሚለጥፉ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ በሁለት ይከፋላሉ፡፡ የመጀመሪያው የሙስና ወንጀል ጥቆማ አቅርበው በአንድ ሌሊት ውጤት የሚጠብቁ ዜጎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች የሙስና ወንጀል ጥቆማ የሚያቀርቡት የማይፈልጉትን ሰዎች ለማጥቃትም ጭምር ነው፡፡ ወይም በአንድ ወቅት ራሳቸው የሙስና ወንጀል ሲፈጽሙ ቆይተው ቦታውን እንዲለቁ ሲደረግ፣ በሚያወቁት ጉዳይ ላይ በቀጥታ የሙስና ወንጀል ጥቆማዎችን ያቀርባሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ እነሱ ማግኘት እንደማይችሉ ሲረዱ ይሰርቃሉ በሚሉዋቸው ላይ የሙስና ወንጀል ጥቆማዎችን ያቀርባሉ፡፡ ወይም አንድ የሚፈልጉት ነገር ኖሮአቸው ሳይሰከላቸው ሲቀርም የሙስና ወንጀል ጥቆማ ያቀርባሉ፡፡

  እነዚህ ሰዎች የሙስና ወንጀል ጥቆማውን ከራሳቸው ፍላጎት አኳያም ቢሆን ጥቆማ በማቅረባቸው ብቻ የሚመሠገኑ ቢሆኑም፣ እነሱ የሚፈልጉት ባለመሳካቱ ብቻ ኮሚሽኑ ሌባ ነው የሚል ታፔላ ይለጥፋሉ፡፡ ነገር ግን ኮሚሽኑ ውስጥ የሚሠሩት ሰዎች መልዓክ ስላልሆኑ በጭራሽ አይሰርቁም የሚል ድምዳሜ የለኝም፡፡ በኮሚሽኑ ሥራ ምንም ዓይነት ግንዛቤ የሌላቸው ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች መንግሥት የሙስና ወንጀል መፈጸሙን በሚዲያ ሲገልጽ ብቻ አገሪቱ ተዘርፋለች የሚል ድምዳሜ ይደርሳሉ፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽንንም ከዚህ አንፃር ይፈርጁታል፡፡ በፀረ ሙስና ትግል ላይ ለመሳተፍም ፍላጎቱ የላቸውም፡፡ በጥቅሉ ገዥውን መንግሥት ሌባ ነው ብለው የሚፈርጁ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በአገሪቱም ምንም ይሠራ አይሠራ አይዋጥላቸውም፡፡ አቃቂር ያወጣሉ፡፡

  ከላይ የተገለጹት በኅብረተሰቡ ውስጥ ይኑሩ እንጂ መንግሥትም ለፀረ ሙስና ትግል ያለው ተነሳሽነት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በኮንቬሽኑ ላይ ፀረ ሙስና  ኮሚሽን ነፃና ገለልተኛ መሆን እንዳለበት፣ እንዲሁም የበጀት ዓመቱ በጀት አስተቃቀዱ በአስፈጻሚ በኩል ሳይሆን በፓርላማ በኩል ጥያቄ ቀርቦ በቂ በጀት እንዲመደብ ይደነግጋል፡፡ የአገራችን ፀረ ሙስና ኮሚሽን ነፃና ገለልተኛ አይደለም፡፡ ጠልቃ ገብነት በስፋት ነበር፡፡ በተለይም ኮሚሽኑ የምርመራና የዓቃቤ ሕግ ሥራ ሲሠራ በነበረበት ወቅት እከሌን እሰርና ክሰስ ማለት እንደነበር መረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ከፈለገም መንግሥት በራሱ ሰዎችን እስር ቤት በማስገባት ኮሚሽኑ የመመርመርና የመክሰስ ሥራ እንዲሠራ የሚያደርግበት ሁኔታም ነበር፡፡

  አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ፀረ ሙስና ኮሚሽንን ለማጠናከር ያላቸው አቋም ግልጽ አይደለም፡፡ ከእሳቸው በፊት ለነበረው ሥርዓት ተላላኪና ጉዳይ ገዳይ ነው ብለው ፈርጀው፣ በተቋሙ ላይ ምንም ላለማለት የራሳቸውን አቋም የያዙ ይመስላል፡፡ አንድም ቀን የፀረ ሙስና ኮሚሽን ስም ሲጠሩ ሰምቼ አላውቅም፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽን በጣም ከፍተኛ ጥቃት የደረሰበት ተቋም  ነው፡፡ ሽባ እንዲሆን የተደረገ ተቋምም ነው፡፡ ዶ/ር ዓብይ ግን ተቋሙን በቅርበት ዓይተውና ገምግመው ማጠናከር አለባቸው ባይ ነኝ፡፡ ቢያንስ የሕዝብ ችግር የሚደመጥበት ተቋም ስለሆነ፡፡ የአመራር ችግር ካለበት ፈትሸው ለሕዝቡ በቂ አገልግሎት የሚሰጥበት ተቋም አድርገው አጠንክረው ማዋቀር አለባቸው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት እ.ኤ.አ. በ2018 ሙስናን መታገል አለብን የሚል መሪ ቃል ይዞ በቅርቡ በተካሄደው ጉባዔ ምን ያህል ውጤት እንደተመዘገበ እንኳን ሳይገመግም ቢያልፍም፣ አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች ውስጥ የኬንያ፣ የላይቤሪያ፣ የአንጎላና የጋና መሪዎች በአገሪቱ ያለውን ሌብነት እንዴት መታገል እንደሚችል ለሕዝባቸው ቃል ገብተው በቃላቸው መሠረት ሲተገብሩ ይታያሉ፡፡

  ዶ/ር ዓብይ ግን ሌብነትን ከመጠየፍ ውጪ ትግሉን በምን አግባብ እንደሚመሩ አቋማቸውን በግልጽ አላስቀመጡም፡፡ በእርግጥ በጣም ጥቂት ሰዎች እስር ቤት እንዲገቡ ማድረጋቸው ጥሩ ነው፡፡ ለምሳሌ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በቅርቡ ፖሊሶች በሌብነት ሲያስቸግሯቸው ያደረጉት በጣም አስቂኝ ነው፡፡ የፖሊስ ልብስ ላይ ኪስ እንዳይኖር መወሰናቸው፡፡ ፖሊሶች ግን ኪስ የሌለውን ልብስ አንለብስም ብለዋቸዋል፡፡ ሌላም ነገር አድርገዋል፡፡ የመንግሥት ኃላፊዎች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡና ምንጩ ያልተወቀ ሀብት እንዲመልሱ በማድረግ፣ ለዜጎች አምቡላንስ እንዲገዛ ማድረጋቸው፣ እንዲሁም በሕገወጥ መንገድ የተፈጸሙ ከፍተኛ ግንባታዎችን በማፍረስ ሕዝብ ባለቤት እንዲሆን ማድረጋቸው በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው፡፡

  ሌለው አራተኛ መንግሥት የሚባለው ሚዲያ ነው፡፡ ሚዲያ ውስጥ ያሉት ባለሙያዎች ጉዳዮችን በትክክል ተረድተው ለሕዝብ ትክክለኛ መልዕክት እንዲያስተላልፉ ለማድረግ፣ ያላቸው የብቃትና የክህሎት ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ ሌብነትን ከመዋጋት ይልቅ ራሳቸው የሚሠሩበትን ሚዲያ ተጠቅመው ሌብነት መፈጸመቸው በጣም አሳፈሪ ነው፡፡ እንዲህ ሲባል ግን ብቃትና ክህሎት ያላቸውን የሚዲያ ባለሙያዎችን ሳንዘነጋ ነው፡፡ የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን በአገሪቱ የፀረ ሙስና ትግል በአገሪቱ መኖሩን የሚያወቁት፣ ሰዎች በሙስና ተጠርጥረው ሲታሰሩ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ አይዘግቡም፡፡ ሙስናን በራሳቸው ተሯሩጠው ማጋለጥ አይፈልጉም፡፡ አንዳንድ የተወሰኑ የግል የኅትመትና ኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎች በጣም ሊመሠገኑ ይገባቸዋል፡፡ ይዘግባሉ፡፡ የሕዝብ ሚዲያዎች ግን ሌብነትን በፅኑ ለመታገል ያለቸው ዝግጁነት ከጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው፡፡ ይታሰብበት፡፡

  ስለሆነም በኅብረተሰቡ፣ በመንግሥትና በሚዲያ ዘንድ ሌብነትን ለመታገል ያላቸው ዝግጁነት እዚህ ግባ የሚባል ስለሆነ፣ በአገሪቱ ሌብነት መልኩን እየቀረ ሲንሰራፋ እንጂ እየቀነሰ አይደለም፡፡ ሌቦች የልብ ልብ እያገኙ ሀብት እያካበቱ ናቸው፡፡ የፍትሕ ዘርፎችም በሌብነት ላይ እየተገበሩ ያለው ሥራ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ዱሮ ዱሮየበሙስና ተጠርጣሪዎች ተፈረደባቸው ሲባል ስንሰመው የነበረው አሁን አሁን ጠፍቷል፡፡ ስለሆነም አገራችን በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽል ደረጃ አሰጣጥ በ1997 ዓ.ም. ከ170 አገሮች ውስጥ 132ኛ ነበረች፡፡ በ2008 ዓ.ም. ከ180 አገሮች ወደ 104ኛ ደርሳ ነበር፡፡ በ2010 ዓ.ም. ከነበረችበት ከ107ኛ ደረጃ በ2011 ዓ.ም. ከ180 አገሮች ወደ 114ኛ ተንሸራታለች፡፡ በጣም ያሳዝናል፡፡

  ይህ የሆነው አገሪቱ ለፀረ ሙስና ትግል የሰጠችው ምላሽ አነስተኛ ስለሆነ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የብድርና የዕርዳታ መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል፣ ኢንቨስተሮችን ወደ አገራችን እንዳይመጡ መሰናክል ይሆናል፡፡ ብቻል በአፍሪካ የሩዋንዳ፣ የቦስትዋናና የሺሴልስ የፀረ ሙስና ትግል ውጤታማነት ተሞክሮ ተወስዶ ከወዲሁ መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ አገሮች በትራንስፓራንሲ ኢንተርናሽናል በተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኙ አገሮች ናቸው፡፡ አገራችን የፀረ ሙስና ትግሉን የአንድ ወቅት የዜጎች አመለካከት መቀየሪያና የፖለቲካ መሣሪያ ከማድረግ ይልቅ፣ የዜጎችን ዕንባ የሚያብስ ተግባር እንዲሆን ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ስለሆነም የለውጥ ኃይሉ የዶ/ር ዓብይ መንግሥት ለፀረ ሙስና ለትግሉ ያለውን ቁርጠኝነት በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር ሊያሳይ ይገባል፡፡ ሙስናን መዋጋት የሁሉም ዜጎች ግዴታ ነው፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻችን enuabidile@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡      

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የአገሪቱ ባንኮች ካፒታል 199.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ

  ከታክስ በኋላ 50 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ የአገሪቱ...

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...