Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ልናገር“የመረጃ ነፃነት በኢትዮጵያ” ምርቃትና እርግማን

  “የመረጃ ነፃነት በኢትዮጵያ” ምርቃትና እርግማን

  ቀን:

  በሪያድ አብዱል ወኪል

  እንደ መንደርደሪያ. . .

  ዕለተ ማክሰኞ ጥር 21 ቀን 2011 የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል አህመድ ሃምዛ ጋር ያደረገውን ቆይታ ባስነበበበት ጽሑፉ፣ ‹‹መረጃ አልባው ሜቴክ›› በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ቢሊዮኖች ተመድበውለት ክትትል የተነፈገው የመንግሥት የልማት ድርጅት ለአዲስ አደረጃጀትና ስያሜ ለውጡ የመረጃ አለመኖር ትልቁ ዕንቅፋት እንደሆነበት ዋና ዳይሬክተሩ መናገራቸውን ዘግቦ ነበር፡፡

  የመረጃ አለመኖር ወይም በደኅንነት እየተመካኘ ኦዲት አለመደረጉና በተደራጀ ሁኔታም አለመገኘቱ ያስከተለው መዘዝ፣ እስካሁንም ተመዝዞ ያላለቀ ስለመሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ዓለም አቀፉ የመረጃ ነፃነት ቀን በዓለም ለሦስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ባሳለፍነው መስከረም 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ቀዳሚ አስተባባሪነት ተከብሮ ነበር፡፡ ‹‹መረጃ ለምክንያታዊ ብያኔ›› በሚል መሪ ቃል ዕለቱ በፓናል ውይይት ሲከበር፣ የመረጃ ነፃነት ሐሳብን ከመግለጽ ነፃነት ጋር ተዛንቆ ምልከታ ተደርጎበትም ነበር፡፡

  ሆኖም ሰው ያመነበትን በመናገሩና በመጻፉ ብቻ ሲታሰርና ሲገፋባት በኖረችው አገራችን ለውጥ መጣ ተብሎ ሳያባራ፣ እዚህም እዚያም ‹‹በእርግጥ ለውጥ አለ ወይ?›› የሚያስብሉ ክስተቶችን ዓይተናል፣ ሰምተናልም፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ በወረዳ 01 ወሳኝ ኩነት ጽሕፈት ቤት በመረጃ ሠራተኝነት ስትሠራ የነበረች ባለሙያ፣ ከሙያ አንፃር ሚስጥር እንዲሆን የማይጠበቅን ሕገወጥ አሠራር በማጋለጧ ብቻ ከሕግ ከለላ ርቃ ከሥራዋ ታገደች፣ ተባረረች፣ ወደ ሥራዋ ተመለሰች መባልን የሰማነው እንደ ቀላል ነገር ነበር፡፡ በእዚሁ ክስተት ገፋፊነት ይኼንን ጽሑፍ እስከ ማሰናዳበት ጊዜ ድረስ በጉዳዩ ላይ ትክክለኛው “መረጃ” የማንኛው ወገን እንደሆነ በመደበኛው ሚዲያ በኩል ግልጽ አለመደረጉ ለአጠራጣሪ የሐሰት ዘመቻዎች፣ ለጥላቻ ንግግሮች፣ ለሚዛናዊ የዘገባ ዕጦትና መሰል ተያያዥ ችግሮች እንዳጋለጠን ዕሙን ነው፡፡ የመንግሥት አሠራር ላይ ግልጽነት እንዲሠፍን በሕገ መንገሥቱ ሳይቀር የተደገፈ ሆኖ ሳለ፣ መደበኛዎቹ የብዙኃን መገናኛ ጋዜጠኞች ላይ የሚፈጠሩ የመረጃ ክፍተቶች ለተቀራራቢ ዘገባ ዕጦት መበራከት የበኩሉን አዋጥቷል፡፡

  ምሁራዊው ምርቃት. . .

  ዕለተ ሐሙስ ጥር 23 ቀን 2011 ዓ.ም. ‹‹ኦንላይን መልቲ ሚዲያ ፕሮዳክሽን›› ባሰናዳውና ‹‹የመረጃ ነፃነት በኢትዮጵያ›› በተሰኘችው የመጽሐፍ ምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉትን የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ ታዋቂ ጋዜጠኞች፣ የጥበብ ሰዎችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መሰናዶውን ለመታደም የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን መሰብሰቢያ አዳራሽ ተገኝተው ነበር፡፡

  ከአንጋፋ የኢቢሲ ጋዜጠኞች አንዱ የሆነውና በዕለቱ መድረኩን ያጋፈረው ጋዜጠኛ ጳውሎስ ቦንሳ እጅግ ባማረ ሁኔታ መድረኩን በመራበት በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ፣ የአንድ ዘመን የሙያ ቀረቤታ የነበራቸው ሰዎች በርክተው የታዩበትም ነበር፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ አቶ አማኑኤል አብርሃም ጋዜጠኛና የሕግ ምሩቅ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የዋልታ ቴሌቪዥን መሥራችም ከነበሩት ውስጥ አንዱ ነው፡፡

  የመድረኩ ቀዳሚ አስተያየት ሰጪና የደራሲው የቀድሞ መምህር የነበሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ተሻገር በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚነሱ ሮሮዎች ሁሉ ሲጠቀለሉ፣ “የመረጃ ዕጦት” የሚፈጥራቸው ችግሮች መሆናቸውን በመጥቀስ የመረጃ ነፃነት ጉዳይን ከዕውቀት ምልከታ ረገድ ለታዳሚው ያስመለከቱት ሲሆን፣ ‹‹የሰው ልጅ የመረጃ ነፃነቱን ሲያጣ መፀዳጃ ቤት ገብቶ ይጥፋል፤›› በማለት፣ የሚጻፉትን ነገሮች ግን ለአገርና ወገን አይበጄ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

  የጋዜጠኝነት ትልቁ ፈተና የመረጃ ዕጦት መሆኑን የጠቀሱት መምህሩ፣ ስለሚሠራው ሥራ መረጃን አምርቶ ለሕዝብ ማድረስ ግዴታነቱን ባለመነ አሠራር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃኑ ጥራት መመዘኛነቱንም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹መረጃው ጥሩ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ሕዝቡ ይፍረደው፡፡ መረጃን ማግኘቱ ግን የሕዝብ መሠረታዊ መብት (Natural Right) ነው፤›› በማለት የቀድሞ ተማሪያቸው ለመጀመርያ ዲግሪ በመመረቂያነት ያዘጋጀውን ጽሑፍ በሒደት አዳብሮና ተመራምሮ በመጽሐፍ መልክ የማምጣቱን መልካም ጅማሮ አወድሰዋል፡፡

  ምሁሩ ይኼንን ይበሉ እንጂ የመረጃ ነፃነት የመሠረታዊ ሰብዓዊ መብት ወይስ ከዴሞክራሲያዊ መብቶች አንዱ ሆኖ የሚታይ ነው የሚለው፣ በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ቁርጥ ያለ ምላሽ ያገኘ አይመስልም፡፡ በሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 26 ሁለት ሥር ከሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ሥር ስናገኘው በአንቀጽ 29 (2/4) ሥር ደግሞ ይኸው መብት በዴሞክራሲያዊ መብትነት ሰፍሯል፡፡

  የሆነው ሆኖ አንጋፋው ጋዜጠኛ ዓለምነህ ዋሴ ‹‹ጋዜጠኛ ‘ለምን ይኼን አላልክም?’ ተብሎ ችግር አይመጣበትም፡፡ ‘ለምን ይኼንን አልክ?’ ተብሎ ግን ጣጣ ይከተለዋል፤›› በማለት በተለያዩ ወቅቶች ከገጠሙት ፈተናዎች እየቆነጠረ ለታዳሚው አካፍሏል፡፡ ዓለምነህ ቃለ ምልልሶቹ ያመጡበትን ጣጣ አስታውሶም፣ ‹‹እኔ የምታወቀው በውጭ ዜና ነው፡፡ ይህ ያለ ምክንያት የሆነ አይደለም፡፡ የአገር ውስጥ ዜናና ዘገባ ፈተናው ብዙ ስለሆነ ነው፤›› በማለት ለመጨረሻ ጊዜ ሌላው አንጋፋ የሬዲዮ ጋዜጠኛና ወዳጁ የሆነው ዳሪዎስ ሞዲ፣ “የፕሬስ ሕግ” ላይ በሰጠው አስተያየት ሳቢያ የከፈለውን መራር ዋጋ ከመረጃ ነፃነት ጋር በማሰናሰል አስታውሶ መድረኩን ለተከታዮቹ ተናጋሪዎች አውሷል፡፡

  ፖለቲካዊው እርግማን. . .

  ከዶ/ር ተሻገርና ከዓለምነህ ዋሴ በመቀጠል አቶ ግርማ ሰይፉ ምልከታቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ በንጉሡ ዘመን ተሻሽሎ የነበረው ሕገ መንግሥት አለመፅደቁ ችግር እንደሆነና የ1980 ዓ.ም. ሕገ መንግሥትም ቢሆን በአንቀጽ 47 (1) ሥር ጥሩ ነገሮች እንደነበሩት አውስተው ደራሲው የንጉሡንና የደርጉን ሕግጋተ መንግሥታት ‹‹ከወረቀት አልፈው በተግባር አልተገለጹም፤›› ማለቱን ‘ፖለቲካ ነው!’ ይሉትና ‹‹ኢሕአዴግ ዓለም አቀፎቹን የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብት ሰነዶችን ‘ተቀብያለሁ’ እያለ እንኳን፣ በማኅበራትና በፀረ ሽብር አዋጅ የለጎማቸው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን እንደማያግዙ በማመንና ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር ንቅንቅ ላለማለት ነው፤›› በማለት፣ የመጽሐፉ ደራሲ ኢሕአዴግን “ምሉዕ በኩልሔ” ማድረጉን ተችተዋል፡፡

  ከዚህም ባሻገር በመጽሐፉ “የአፈጻጸም ችግር” ተብሎ የተገለጸውም ቢሆን፣ ደራሲው ‘የአፈጻጸም ችግሮች’ ቢሏቸውና የአዋጁን ሸንጋይ መግቢያ እንድናምን ብሎም እኛም “ችግሩ የአፈጻጸም ነው” እንድንል ቢሞክሩም፣ ይህ አገላለጻቸው አንድም ‹‹የመረጃ ቡዳውን በደንብ እንዳላወቁት ያሳያል አልያም እያወቁት ለመግለጽ ተሽኮርምመዋል፤›› ብለዋል አቶ ግርማ፡፡

  የመጽሐፉ የሽፋን ምሥልን ገላጭነት አድንቀውና የቀን አቆጣጠሮቹ በአውሮጳውያን የዘመን ቀመር መሆኑ፣ ጥናቱ ወደ መጽሐፍነት ሲቀየር ካልታሰቡባቸውና እርምት ከሚሹ ጉዳዮች ውስጥ ተካታች መሆኑን በመጥቀስ ‹‹ለኢትዮጵያ አንባቢ ‘1966’ ሲባል ነው ወይስ ‘1974’ ሲባል ነው ቀልቡን የሚይዘው? ‘1983’ ሲባል ነው ወይስ ‘1991’ በማለት አጣይቀው፣ ከሰባቱ ምዕራፎች ውስጥ “ጉዳይ ያለኝ ከመጨረሻዎቹ ሁለቱ ምዕራፎች ጋር ነው፤›› በማለት በምዕራፍ 6 እና 7 ላይ ዕይታቸውን አቅርበዋል፡፡

  ደራሲው ‘የቁርጠኝነት አለመኖር’ ብለው እንደችግር የጠቀሱት ቢሆንም፣ ‹‹ለኢሕአዴግ ፕሮግራምማ ቁርጠኝነት ስላለ ነው ሕገ መንግሥት ወደ ጎን ተገፍቶ የድርጅት ፕሮግራም ሲፈጸም የኖረው፤›› በማለት፣ በዘጠናዎቹ መጨረሻ ላይ በኢሕአዴግ ከተዘጋጀ አንድ ሰነድ ሚዲያውን ማስታወቂያ እንዳያገኝ የማዳከም፣ በአስተዳደር፣ ፖለቲካና ሕጋዊ ዕርምጃዎች የማጥፋት ትልምም እንደነበረው በንባብ ጭምር በመጥቀስ፣ ኢሕአዴግ ቁርጠኝነት ያጠረው ለሕገ መንግሥቱ ነው እንጂ ለፕሮግራሙማ ቁርጠኛ ነበር ብለዋል፡፡

  ደራሲው የመረጃ ነፃነት ሕጉ በደባልነት መታወጁ፣ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ይኼንን አጀንዳ በተደራቢነት መሥራቱ፣ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችም የግንዛቤ ደረጃ ዝቅተኝነት ተደራርበው ለመረጃ ነፃነት ተግዳሮት ሆነዋል ማለታቸውን በመጥቀስ አቶ ግርማ ሲተቹ፣ ‹‹የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች›› እየተባሉ በየመንግሥት መሥርያ ቤቱ የተቀመጡ ግለሰቦች በብቃት ሳይሆን ለኢሕአዴግ ባላቸው ታማኝነት የተመረጡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ከቀድሞ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ጋር ስንጨዋወት እነዚሁ ባለሙያዎች ‹‹መረጃ ለተቃዋሚዎች ይሰጣል እንዴ?›› ብለው ዋና ዕንባ ጠባቂውን/ዋን ስለመጠየቃቸው አዋዝተው ተናግረዋል፡፡ በደራሲው በኩል እንደ መፍትሔ የቀረበውን ‹‹የመረጃ ኮሚሽነር ቢቋቋምስ?›› የሚለውን ሐሳብም አቶ ግርማ ሞግተዋል ‹‹ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምን ፈየደ?›› ብለው በመጠየቅ፡፡ ደራሲው የሚያውቁትንና ለረጅም ጊዜ የኖሩበትን “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” በጨረፍታ እንኳን ለማሳየት አለመድፈራቸውን እንደ ፖለቲካዊ ውግንና ያነሱት አቶ ግርማ፣ ይኼንን ዓይነት የፖለቲካ “ማዳላት” ታሪካዊ ሰነዶች ላይ ማስቀረትና ከግላዊ ስሜት መውጣት እንደሚኖርብን በመጠቆም፣ ‹‹በኢሕአዴግ ዘመን የመረጃ ነፃነትን የበላው ቡዳ እስካሁን ድረስ አልታወቀም፤›› በማለት ነበር መድረኩን ለተረኛ ያስረከቡት፡፡

  ሙያዊው ዕይታ. . .

  ከአቶ ግርማ በመቀጠል መጽሑፉን በሙያ መነጽር እንዲመለከተው የተጋበዘው አንጋፋው ጋዜጠኛና የፎርቹን ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ታምራት ገብረ ጊዮርጊስ ነበር፡፡ የመጽሐፉን ደራሲ “ፅናቱን ይስጥህ!’’ ብሎ ሳቅ በማጫር ንግግሩን የጀመረው ጋዜጠኛ ታምራት፣ ኅብረተሰባችን የመረጃ ነፃነት ሕግን “የጋዜጠኞች ሕግ” አድርጎ ስለሚመለከተው ተከራካሪ የታጣለት መብት/ሕግ” ስለመሆኑ፣ ጋዜጠኞችም የመረጃ ነፃነትን ከሐሳብ ነፃነት ጋር ማዛነቃቸው (ጥብቅ ቁርኝታቸው እንዳለ ሆኖ)፣ መረጃን ለማግኘት ከመሞከርና ከመጠየቅ ባህል ደካማነት ጋር ተዳምሮ ችግሩን እንዳባባሰው ገልጸዋል፡፡

  የመረጃ ነፃነትን ጅማሮ ከአገረ ስዊድን እስከ አሜሪካ በማስቃኘትና ታሪካዊ ዳራውን በማውሳት የጀመረው ታምራት፣ በአሜሪካ ጋዜጠኞች ከመንግሥት መረጃ ጠይቀው ሲከለከሉ ጉዳዩን ፍርድ ቤት ድረስ በመውሰድ መንግሥት ላይ መረጃን የመስጠት ግዴታ እንዲጣልበት የወሰነባቸውን “የኒክሰን/የፔንታጎን ወረቀቶች” በማውሳት፣ በእኛ አገር የመረጃ ነፃነት ጉዳይ ያልተሞከረ ስለመሆኑና ባልሞከርነውና ባልተሸነፍንበት ጉዳይ ላይ ማማረሩ አይጠቅመንም ብሏል፡፡ በኢትዮጵያ የመረጃ ነፃነት ሕግ የታወጀው በዓለም ላይ ለመረጃ ነፃነት ሕግ “ወርቃማው ዘመን” የተባለውና በብዙ የዓለማችን አገሮች ይኼው ሕግ ከተጧጧፈበት 2006 ከሁለት ዓመታት በኋላ በ2008 እንደነበር፣ ስለመረጃ ነፃነት ሕግም ኢሕአዴግን የጠየቀ ማንም ባልነበረበት የታወጀ ሕግ ነው ብሏል፡፡ ይኼንን ሕግ በማበልፀጉ ረገድ መረጃ ማግኘትን የሚመለከተው “The Law of Freedom” እና መረጃን መጠቀምን የሚመለከተው “The Culture of Freedom” ለይተን መመልከትና ሕዝባችንን ማሳወቅ፣ ባህሉም ላይ መበርታት ይኖርብናል ብሏል፡፡

  ስለመረጃ ስናወራ ስለስነዳ (Documentation) ነው የምናወራው፡፡ ጋዜጠኞች ዋነኞቹ ተጠቃሚዎች ብንሆንም ጠቅላላ ሕዝቡን የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ አጥኚዎች ማንኛውንም ዓይነት ሰነዶች የማግኘት መብት አላቸው፡፡ ‹‹መንግሥት ቁጥጥር በማድረጉ (Regulation) መተቸት ይኖርበታል ብዬ አላምንም፤›› ያለው ታምራት፣ እንዲያውም የኢሕአዴግ ሰዎች ባይመሠገኑ እንኳን ሊወቀሱባቸው ከማይገቡ ጉዳዮች ቀዳሚው የመረጃ ነፃነት ሕግን ማምጣታቸው ነው ብሎ፣ መረጃን የመጠየቅና የመጠቀም ባህላችንን ግን ተችቷል፡፡ በመረጃ ነፃነት አዋጁ ላይ “Exemptions” ተብለው የተቀመጡት “ክልከላዎች” ተብለው መተርጎማቸው ተገቢ እንዳልሆነ፣ ተቀራራቢው ትርጉምም “ዕገዳ” ሊሆን እንደሚገባ ጠቁሞ የአሜሪካ የመረጃ ሕግ ዘጠኝ፣ የእንግሊዝ 23፣ የኢትዮጵያ ደግሞ 11 ቢመስሉም ሲዘረዘሩ ወደ 64 ያህል ዕገዳዎች እንዳሉትና መሻሻሎች እንደሚያስፈልጉት ተናግሯል፡፡

  የመጽሐፉን ደራሲ እያመሠገንኩና በመስመሮች መካከል ያነበቡትንም ዕይታቸውን እንዲያካፍሉን እየጋበዝኩ አንድ ትምህርቱን እንጂ ማንነቱን ለጊዜው የዘነጋሁት ጠቢብ፣ በዓለም ላይ የሚታዩ ችግሮች እንዲፈቱ ባስቀመጠው መፍትሔ ልሰናበታችሁ ወደድኩ፡፡ ዓለማችን ላይ የሚታዩ ችግሮች እንዲፈቱ አንድም አሳቢዎች የጥበብ ወዳጆች የፖለቲካ ሥልጣኑን መያዝ ይኖርባቸዋል፣ አልያም የፖለቲካውን ሥልጣን የያዙት ሰዎች ጥበበኛ ሊሆኑ ይገባል ይላል ጠቢቡ፡፡ በቅርቡ ከዓለማችን አሰላሳዮች (ጠቢቦች) አንዱ ሆነው የተመረጡት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የኢትዮጵያን ክምቹ ችግሮች ለመፍታት እየጣሩ እነሆ ዓመት ሊሆናቸው ነው፡፡ ከካቢኔያቸው እስከ ታችኛው ዕርከን ያሉትን ውስን ሹማምንት ግን ዛሬም “እጃችሁ ከምን?” እንላችኋለን፡፡ ሰላም ለእናንተ ይሁን!

  ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው ibnalhabeshi@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...