Monday, August 15, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ሕዝብን አፈናቅሎ ሜዳ ላይ መበተን ተቀባይነት የለውም!

  ሰሞኑን የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር ሕገወጥ ናቸው ያላቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ማፍረሱ፣ እንዲሁም ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ለማፍረስ መዘጋጀቱ የበርካቶችን ሕይወት በማመሳቀል አሳሳቢ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ እየተወሰደ ባለው ዕርምጃ ምክንያት እናቶች፣ ሕፃናት፣ አዛውንትና አቅመ ደካሞች ሳይቀሩ ለዓመታት ከኖሩበት ቀዬ እየተፈናቀሉ ነው፡፡ መንግሥት ለእነዚህ ወገኖች ተለዋጭ ወይም አማራጭ መኖሪያ ሳያዘጋጅ በደፈናው በሕገወጥነት ፈርጆ ሲያፈናቅል፣ የራሱ ሹማምንት ከዚህ ቀደም የፈጸሙት አሉታዊ ድርጊት ውጤት መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ የከተማ አስተዳደሩ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሥር የዛሬ 11 ዓመት ከመዋቀሩ በፊት ጀምሮና ከዚያም በኋላ፣ ከአርሶ አደሮች መሬት በይፋ እየገዙ ጎጆአቸውን የቀለሱ ዜጎች አሁን ሲፈናቀሉ በወቅቱ ሹማምንቱ የመሬት ግብር እየተቀበሉዋቸው እስካሁን መዝለቃቸውን ይናገራሉ፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ ለውኃ፣ ለኤሌክትሪክ፣ ለአስተዳደሩ አገልግሎቶችና ለመሳሰሉት ክፍያ ሲፈጽሙ የነበሩት በሹማምንቱ ዕውቅና ነው፡፡ የይዞታ ማረጋገጫና የቤት ቁጥር የሰጧቸውም እነሱ ናቸው፡፡ የከተማው አዲሱ አስተዳደር ከዚህ ቀደም ተፈጸሙ ያላቸውን ሕገወጥ አሠራሮች መስመር ለማስያዝ ሲነሳ፣ የሰባት ቀናት ማሳሰቢያ ብቻ በመስጠት አፍራሽ ግብረ ኃይል መላክ ነበረበት? ወይስ ለሚፈናቀሉት ዜጎች የወደፊት ዕጣ ፈንታ በመጨነቅ ሌሎች አማራጮችን ማየት ነበረበት? ሕግ ማስከበር የዜጎችን ደኅንነት ከመጠበቅ ይጀምራል እንጂ፣ ዜጎችን እንደ አሮጌ ቁና አውጥቶ መጣል በፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡ ከሰብዓዊነት ጋርም ይቃረናል፡፡

  እንደሚታወቀው የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም እንኳ አገር ለመንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ ሥልጣን የሚሰጠው፣ መንግሥት የሰው ኃይልና የበጀት እጥረት ሳይገጥመው ሰዎችን ለማዳን መረባረብ እንዲችል ነው፡፡ በየትም ሥፍራ ለመንግሥት ሰዎችን የማፈናቀልና ከይዞታ የማናጋት የአስቸኳይ ጊዜ ሥልጣን ተሰጥቶ አያውቅም፡፡ ከአገራቸው በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ፣ መግቢያና መጠለያ ያጡ ስደተኞችን በሰብዓዊነት ምክንያት ከኢትዮጵያውያን ያልተናነሰ የዜግነት መብት አከል ሰብዓዊ አያያዝ ለማድረግ ሕግ ያወጣ መንግሥት፣ የራሱን ዜጎች በገዛ ራሱ አፍራሽ ግብረ ኃይል በጅምላ ሲያፈናቅል ያስደነግጣል፡፡ የውጭ ስደትን ለማባባስ ምክንያት ሊሆን የሚችል የአገር ውስጥ ማፈናቀል ሕገወጥ መሆኑ አይታወቅም ወይ? ወይስ ዛሬም አድራጊ ፈጣሪነት የበለጠ እየሰፋ ሕዝብ መፍራት አልተጀመረም ወይ? አሁን በለገዳዲ ለገጣፎ ከተማ እየተፈጸመ ያለውን ድርጊት ክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥቱ ዕውቅና የቸሩት ነው? ወይስ የለውጡ እርጥበት የማያርሳቸው ሰዎች አሉ? እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት ከሌሎች አደገኛ የሆኑ ጥቃቶችና ማፈናቀሎች የሚለየው ምንድነው? አገር እያንገሸገሸ ያለውን ማፈናቀል ማስቆም ማለት ይኼንን አይጨምርም ወይ? ሕዝብ እየጮኸ ያለው ሰዎችን ከገዛ መኖሪያቸው በኃይል ማፈናቀል ሰብዓዊ መብትን የሚፃረር ድርጊት በመሆኑ ነው፡፡

  በአሁኑ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ቅድሚያ የሚሰጠው ሰላምና መረጋጋት ነው፡፡ የአገሪቱ ሰላም አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ለዓመታት ሙዚየም ውስጥ ያለችው ጥንታዊ ቅሪተ አካል ሉሲ ሳትቀር የሰላም ጉዞ ስትጀምር፣ በሌላ በኩል ለተቃውሞ የሚያነሳሳ ድርጊት መፈጸም ግራ ያጋባል፡፡ መንግሥት ሕገወጥነትን በሕጋዊነት መስመር የማስያዝ ፍላጎት ካለው፣ ከምንም ነገር በፊት ለሕዝብ ደኅንነት ቅድሚያ መስጠት አለበት፡፡ የተባለው ቦታ ለአረንጓዴ ሥፍራ ይፈለጋል ሲባልም መጀመርያ መቅደም ያለበት ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ነው፡፡ ሕፃናት ሳይቀሩ ሜዳ ላይ ፈሰው አረንጓዴ ሥፍራን ማለም መራር ቀልድ ይፈጥራል፡፡ ‹‹መጀመርያ የመቀመጫዬን›› እንዳለችው እንስሳ፣ የዜጎች መኖሪያና ደኅንነት የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከዚህ ውጪ ልማትም ሆነ ማስተር ፕላን ከሰው አይበልጡም፡፡ ትናንት ባለጊዜ የነበሩ ሹማምንት ዓይናቸው እያየ የመሬት ግዥና ሽያጭ አፅንተው፣ ዛሬ የመጡ ሹማምንት በቡልዶዘር ቤቶችን ሲያፈርሱ የደሃ ዕንባ ይፋረዳል፡፡ ‹‹መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው›› የሚለው አባባል ሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሠፈረ ቢሆንም፣ በመሬት ላይ የሚታወቀው ዕውነታ ግን በጠራራ ፀሐይ በግልጽ ሲቸበቸብ እንደነበረ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ መሬቶች በሹማምንትና በደላሎች ትብብር እየተቸበቸቡ የከበሩት እነ ማን እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ሕገወጥነትን በሕጋዊነት መስመር ማስያዝ ከተፈለገ ሚዛናዊ መሆን የግድ ነው፡፡ ሕዝብ ማፈናቀል አገርን ሰላም ይነሳል እንጂ ለማንም አይበጅም፡፡

  የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር ያፈናቀላቸውንና እያፈናቀላቸው ያሉ ወገኖችን መልሶ በማቋቋም፣ ለዘለቄታው ሕጋዊ መኖሪያ የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡ ሕግ አስከብራለሁ ሲልም ሕግ አለመጣሱን ማረጋገጥ አለበት፡፡ በተለይ መንግሥት በዚህ ወቅት የመፈናቀል ጣጣዎችን ማስቆም፣ ግራ የተጋባውን ኢኮኖሚ ማነቃቃት፣ ለወጣቶች በፍጥነት ሥራ መፍጠር፣ የተጀመረውን የዴሞክራሲ ግንባታ ማፋጠንና ለሕዝብ ቅሬታ ምንጭ የሆነ አጓጉል ድርጊቶችን መግታት ይጠበቅበታል፡፡ ሰዎች በሕገወጥ ድርጊት ውስጥ ሲገኙ እንኳን ማን ከሰሰ? ማን ፈረደ? ማን አስፈጸመ? ለሚለው ጥያቄ ግልጽ መልስ እንደሚያስፈልግ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ መንግሥት በራሱ ጉዳይ ራሱ ከሳሽ፣ ራሱ ዳኛ፣ ራሱ አስፈጻሚ መሆን አይችልም፡፡ ፍርድ ቤት መሄድ አለበት፡፡ ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ፣ ‹‹…እግዚአብሔርና ታሪክ ይፈርዳሉ…›› የሚለው ታሪካዊ ጥቅስ እኛ ተበድለንና ተጠቅተን የያኔው ሊግ ኦፍ ኔሽንስ (የመንግሥታቱ ማኅበር) ዘንድ ሄደን አቤቱታ ስናሰማ ብቻ ሳይሆን፣ የሌሎችን በደልና ግፍ ጭምር ስናስተጋባ እንደሆነ ያስታውሰናል፡፡ መንግሥት ከላይ እስከ ታች ያሉ መዋቅሮቹ በደልና ግፍ የሚከናወኑባቸው ከሆኑ ከሕዝብ ጋር ሆድና ጀርባ ይሆናል፡፡ ሕዝብና መንግሥት ሲቀያየሙ ደግሞ ሌላ ዙር ግጭትና ውድመት ነው የሚከተለው፡፡ የመንግሥት ዕርምጃዎች የሕዝብን የልብ ትርታ የሚያዳምጡና የሰከኑ መሆን አለባቸው፡፡ አንዳንዶች ሕግ በማስከበር ስም የሚፈጽሙት ድርጊትና የሚያስተላልፉት መልዕክት፣ ከሰብዓዊ መብት ጋር የሚጣረስ ከሆነ ውጤቱ ለሰላም ጠንቅ ይሆናል፡፡ ‹አንዴ ጀምረናል ወደኋላ አንመለስም› እያሉ ከሕዝብ ጋር መጋጨት ለአገር አይጠቅምም፡፡ ዘለቄታዊ መፍትሔ ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ ለአመፅና ለብጥብጥ የሚጋብዝ  ዕርምጃ ውስጥ መግባት ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ በተወሰደው ዕርምጃ አማካይነት ለነዋሪዎች የተመቸ ከተማ ለመፍጠር ታስቧል ቢባል እንኳ፣ ሕዝብን ሜዳ ላይ እየበተኑ መሆን የለበትም፡፡

  ‹‹አንድ ጊዜ ለመቁረጥ ሰባት ጊዜ ለካ›› የሚለው አባባል ለዚህ ጊዜ ጠቃሚ ነው፡፡ አንድ ዕርምጃ ለመውሰድ ሲታሰብ መጀመርያ ከሚመለከተው ነዋሪ ጋር በቂ የሚባል ውይይት መደረግ አለበት፡፡ በሚወሰደው ዕርምጃ ላይ በቂ የሆነ ግንዛቤ ተፈጠረ የሚባለው፣ ጉዳዩ የሚመለከተው ነዋሪ በሚገባ ተደራድሮ በቀጣይ ሊያገኝ የሚችለው ነገር ላይ ሲስማማ ነው፡፡ ቀጥሎ ሕጋዊ ማዕቀፎች ይታያሉ፡፡ በዕርምጃ አወሳሰድ ወቅት ቅሬታዎች ቢፈጠሩ እንዴት ይስተናገዳሉ ለሚለው ምላሽ ለማበጀትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን መልክ ለማስያዝ ስለሚያግዙ ነው፡፡ በሌሎች ወገኖች ጥያቄ ሲቀርብም ባለጉዳዮቹ ተመሳሳይ ገጽ ላይ ሆነው ማስረዳት የሚችሉበት የጋራ ግንዛቤ መኖሩን ለማሳየት ይጠቅማል፡፡ እርግጥ ነው ይህ ሁሉ በአንዴ ተሟልቶ ላይገኝ ይችላል፡፡ ነገር ግን ለውጥ ላይ ባለች አገር ውስጥ ሕዝብና መንግሥት በተቻለ መጠን እየተናበቡ ቢሄዱ ጠቀሜታው ለአገር ነው፡፡ አለበለዚያ ጽንፍ የረገጡ ኃይሎች ያላወራረዱትን የቁርሾና የጥላቻ ፖለቲካ ሕዝብ ውስጥ እያሠራጩ፣ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋቱን የበለጠ በማደፍረስ ችግር ይፈጥራሉ፡፡ የብሔር ካርታ እየተመዘዘ ሒሳብ ማወራረድ ሲጀመር ደግሞ ለግጭትና ለውድመት ይዳርጋል፡፡ ይህም በማኅበራዊ ሚዲያ በግልጽ እየተሰማ ነው፡፡ ሕግ በማስከበር ስም እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ ‹‹ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል›› እየሆነ ሕዝብ እንዳይበደል መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ሕግ ማስከበር ተገቢ ቢሆንም፣ የሰውን መብት ማክበር የግድ ይሆናል፡፡ በሥርዓት መምራትና መመራት የሚቻለው የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማክበር ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ሕዝብ እየተበደለ መንግሥት አይረጋጋም፣ አገርም ሰላም አታገኝም፡፡ ስለዚህ ሕዝብን አፈናቅሎ ሜዳ ላይ መበተን ተቀባይነት እንደሌለው መገንዘብ ይገባል!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  ለኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸጥበት ታሪፍ ማሻሻያ ተደረገበት

  በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ስምምነቱ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያና የኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል...

  አዲስ አበባ እንዳይገቡ በተከለከሉ ዜጎች ጉዳይ የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ተወያይተው ችግሩ እንዲፈታ አደረጉ

  ለሳምንታት በርካታ ቅሬታ ሲነሳበት የነበረውና ከአማራ ክልል በደብረ ብርሃን...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...

  ለኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸጥበት ታሪፍ ማሻሻያ ተደረገበት

  በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ስምምነቱ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያና የኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ሁለተኛው ተርባይን ሥራ መጀመሩ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈጠረው ደስታ ቃላት ከሚገልጹት...

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን ነፃነትም ተምሳሌት ናት፡፡ የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የሚያኮራ ተግባር ፈጽመው ያለፉት፣ ከአገራቸው በፊት የሚቀድም...