ዝሆኖች አጥቢ ከሆኑትና ምድር ላይ ከሚኖሩት እንስሳት በትልቅነቱ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛሉ፡፡ ክብደታቸው እስከ ስድስት ሺሕ ኪሎ ግራም የሚመዝን ሲሆን፣ እስከ 3.3 ሜትር ርዝማኔም አላቸው፡፡ ዝሆኖች እንደተወለዱ እስከ 91 ኪሎ ግራም ይመዝናሉ፡፡ ቁመታቸውም አንድ ሜትር ይደርሳል፡፡ ረዥም ጥርስ፣ ጠንካራና እንደ ፈለገ የሚታዘዝ ኩምቢ፣ እንዲሁም ትልቅ ጆሮ አላቸው፡፡ የላይኛው ከንፈራቸውና አፍንጫቸውም የተያያዘ ነው፡፡
ጄደብሊው ዶት ኦርግ በድረ ገጹ እንደገለጸው፣ ዝሆኖች ከሚጠራሩባቸው ደምፆች አንዳንዶቹ ለሰው ጆሮ የማይሰሙ ይሁኑ እንጂ በርካታ ኪሎ ሜትሮች ርቆ ለሚገኝ ዝሆን ሊሰማ የሚችል ከፍተኛ ኃይል ያላቸው ናቸው የሚለው ነው፡፡
የእንስሳትን ባህርይ የሚያጠኑ ሊቃውንት ዝሆኖች በጣም አስፈላጊ የሆኑ መልዕክቶችን በሚያስተላልፉባቸው የረቀቁ ዘዴዎች በጣም ተደንቀዋል። ጆይስ ፑል የአፍሪካ ዝሆኖች እርስ በርሳቸው የሚነጋገሩባቸውን ዘዴዎች ለ20 ዓመታት ያህል አጥንተዋል። እነዚህ በጣም ተፈላጊ በሆነው ጥርሳቸው ምክንያት በሠፊው ሊታወቁ የቻሉት ግዙፍ እንስሳት በጥቂት እንስሳት ላይ ብቻ የሚታይ ስሜት እንደሚታይባቸው ተገንዝበዋል።