Saturday, August 13, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ልናገርለውጡን አለመደገፍ መብት ቢሆንም ለውጡን ማደናቀፍ ግን…

  ለውጡን አለመደገፍ መብት ቢሆንም ለውጡን ማደናቀፍ ግን…

  ቀን:

  በሰለሞን መለሰ ታምራት

  ሐሙስ የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢሕአዴግ ሊቀመንበር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ኢትዮጵያን ወደፈለጉት አቅጣጫ ሊመሩበት የሚያስችሏቸውን ሁለት ቁልፍ ሥልጣኖች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደማይፈልጓቸው አስታወቁ፡፡ ፓርቲያቸው ተተኪያቸውን ባስታወቀ ማግሥት ሥራ አስረክበው ተራ ሕይወታቸውን ለመቀጠል መወሰናቸው በተሰማ ጊዜ ያልደነገጠ ኢትዮጵያዊ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ያሉት፣ አሊያም ፈጣሪ ለነቢይነት የቀባው መሆን ነበረበት፡፡ ከእርሳቸው ቀደም ብለው ተመሳሳዩን ሥልጣን ለ17 ዓመታት ጨብጠው የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ በተደጋጋሚ ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ሲገልጹ እንደሰማናቸው የመንግሥት ሥልጣን ቢለቁም የፓርቲያቸውን ሊቀመንበርነት ይዘው እንደሚቀጥሉ ያስታውቁ ስለነበር፣ ተተኪያቸው አቶ ኃይለ ማርያም በምን ምክንያት ለአንድ የምርጫ ዘመን እንኳን በወጉ ያላጣጣሙትን ሁለቱንም ሥልጣን ለመልቀቅ እንደፈለጉ ማወቅ በወቅቱ የሚሊዮን ብር ጥያቄ ሆኖ ነበር፡፡ ሰንበትበት ብሎም ኢሕአዴግ የማይቀረውን የሥልጣን ተተኪ ይዞ ብቅ አለ፡፡ ብዙዎች የሥልጣን ሽግሽጉን በአንድ ፓርቲ ውስጥ የተከናወነ የጉልቻ መለዋወጥ አድርገው ለማየት/ለማሳየት ቢሞክሩም፣  እየዋለ ሲያድር ጉዳዩ ተመሳሳይ ዓላማና ርዕዮተ ዓለም ባላቸው የአንድ ግንባር አባላት መካከል ሊታሰብ የማይችል የአስተሳሰብ ክፍተትና አተካሮ እያስከተለ መጣ፡፡ ሁኔታውን ላስተዋለው ሰው፣ በምርጫ እንኳን ሥልጣን በተነጣጠቁ ባላንጣዎች መካከል ሊከሰት የማይችል ጣት መቀሳሰር በውስጡ በርካታ ጉዶችን አዝሎ እንደመጣ የሚያሳብቅ ነበር፡፡

  እነሆ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ምትክ የኢሕአዴግን ሊቀመንበርነትና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ከተረከቡ አንደኛ ዓመታቸውን ሊደፍኑ ጥቂት ሳምንታት ቀርቷቸዋል፡፡ አገሪቱም ከዚህ ቀደም እንደተከሰቱት ሥር ነቀል ለውጦች በአስቸጋሪ ማዕበል እየተገፋች የጭንቅ ጉዞዋን ተያይዛዋለች፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት መቶ ዓመታት ገደማ የተከናወኑት ሥር ነቀል ለውጦች እንዲህ እንዳሁኑ ዜጎችን በዳዴ ያስኬዱ የነበሩ ቢሆኑም ቅሉ፣ ሁሉም አልፈው ኢትዮጵያ ዛሬም በሌላ የምጥ ወቅት ላይ እንደምትገኝ ካሰብነው ‹‹ይኼም ያልፋል›› የምንልበት ዕድል ይታየኛል፡፡ ነገሩንም ሰፋ አድርገን ካየነው በተለይ ከሰብዓዊ ቀውስ አንፃር የንጉሡን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴንም ሆነ የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ሥልጣን ለማስጠበቅ ሲባል ከተከፈለው መስዋዕትነት አንፃር፣ እስካሁን አንድም ቢሆን የጠፋ የሰው ሕይወት መኖሩን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ የሰማናቸው በመቶዎች የሚቆጠሩት የሞትና በዓለማችን ውስጥ ከተከናወኑት የአገር ውስጥ መፈናቀሎች (internal displacement) መደዳ የተቆጠረው ሥደት የተከሰተበትን ምክንያት ሁላችንም እንደምንረዳው ጎሳን ማዕከል አድርጎ የተዘራው ክፉ የዘር ፍሬ መሆኑን ነው፡፡ ዛሬም በአገሪቷ ውስጥ በሚፈጠሩት ብሔር ተኮር ግጭቶች የሚጠፋው የሰዎች ሕይወት በእጅጉ አሳሳቢ ቢሆንም፣ ከመስከረም 2008 እስከ የካቲት 2010 ዓ.ም. በዘለቀው የሕዝባዊ አመፅ ወቅት በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች (የማን እንደሆነ በግልጽ ያልታወቀ ሥልጣንን ለማስጠበቅ) በቀጥታ በተወሰደ ዕርምጃ ከጠፋው ጋር ብናስተያየው እንኳን፣ በእርግጥም የፈጣሪ ጥበቃ በዝቶልናል ለማለት የሚያስችል ነው፡፡ በበርካታ አገሮች የሚነሱ ዘርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች በቀላሉ በቁጥጥር ሥር የማይውሉ ሲሆኑ፣ በጣም በአጭር ጊዜያት ውስጥም በቀውሱ የሚጠፋው ሕይወት የትየለሌ ነው፡፡ ለምሳሌም በምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ካሉ አገሮች በአንፃራዊ ሰላሟ የምትመሠገነው ጎረቤታችን ኬንያ ከምርጫ ጋር ተያይዞ በተነሳ የሁለት ጎሳዎች ግጭት፣ ከአንድ ሺሕ በላይ የሆኑ ሰዎችን ሕይወት ለመቅጠፍ የአንድ ወር ጊዜ እንኳን እንዳልፈጀባት የቅርብ ጊዜ ታሪክ ስለሆነ አስታዋሽ አያስፈልገንም፡፡

  እንግዲህ ላለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያን በፍፁም አምባገነንነትና ፈላጭ ቆራጭነት ሲገዛ የነበረው ኢሕአዴግ ተነስቶ (ተወግዶ)፣ አይደለም በዕውናችን በህልማችንም እንኳን የማንጠብቀው ለስላሳና ገደብ በሌለው ትዕግሥቱ ታሪክ ሲያስታውሰው የሚኖረው ኢሕአዴግ ተተክቷል፡፡ የሥልጣን ሽግግሩ በአንድ ፓርቲ ውስጥ የተደረገ የጉልቻ መለዋወጥ ሳይሆን፣ እንደ ሰማይና ምድር የተራራቁ ሁለት በአንድ ግንባር ውስጥ የሚገኙ ቡድኖች ከብዙ መፈታተግ በኋላ ያደረጉት የሥልጣን ርክክብ መሆኑን ለመረዳት የተለየ እውቀትን አይጠይቅም፡፡ ሰሞኑን ከሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ተሰጠ  የተባለው መግለጫና የድርጅቱም ሊቀመንበር ሰጡት በተባለው ቃለ ምልልስ ላይ የታዩት ከረር ያሉ ቃላት ከዛቻም አልፎ ‘ዕርምጃን’ እንደ አማራጭ የሚያነሳ መሆኑን በመስማታችን ተረብሸናል፡፡ ለዛሬው መጣጥፌ መነሻ የሆነውም ይኸው አቅጣጫው ያልታወቀው የሁለት ወገኖች የገመድ ጉተታ አዝማሚያን በመቃኘት፣ መፍትሔ ሊሆን ይችላል ያልኩትን ምልከታ ለማሳየት ነው፡፡

  በግንቦት ወር 1983 ዓ.ም. የ17 ዓመታት የትጥቅ ትግሉን በድል ደምድሞ የመንግሥትን ሥልጣን የተቆጣጠረውና ኢሕአዴግ በማለት ራሱን የሰየመው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ‘ፋሺስት’ ብሎ የጠራውን የቀድሞውን መንግሥትና ጠቅላላ መዋቅሮቹን በማፈራረስ፣ ለሚያቋቁመው የሽግግር መንግሥት በግብዣ የጠራቸው የፖለቲካ ድርጅቶችና ሕዝባዊ ማኅበራት ወዳጆቼ ያላቸውንና ሁሉንም ሊባሉ በሚያስችል ሁኔታ ዘርን መሠረት አድርገው የተዋቀሩትን ነበር፡፡ እናም ደመኛ ጠላቶቼ ናቸው ያላቸውን ኢሕአፓና መኢሶንን የመሳሰሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በተለይም ዛሬ ዛሬ ዳያስፖራ ብለን የምንጠራቸውን፣ ወታደራዊውን ሥርዓት ሸሽተው በመላው ዓለም የተበተኑ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ያገለለ እንደነበር የቅርብ ዘመን ታሪካችን ነው፡፡ ከዚያን ወቅት አንስቶ ጥርሱን የነከሰው የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ከዶ/ር ዓብይ አህመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በፊት የአገሩ ጉዳይ ‹‹ላም እሳት ወለደች …›› ዓይነት ሆኖበት ቆይቷል፡፡ እንዳይተዋት የእትብቱ መቀበሪያና እናቴ የሚላት አገሩ ሆናበት፣ እንዳያያት ደግሞ ባላሰበውና ባልጠበቀው ሁኔታ እንደ ጠላት የሚመለከተው መንግሥት ተደንቅሮበት ኖሯል፡፡ አስገራሚው እንቆቅልሽ በሕወሓት የአገር አፍራሽነት ታርጋ ተለጥፎበት ከጦርነት ያልተናነሰ አዋጅ የታወጀበት አዲሱ የዶ/ር ዓብይ አስተዳደር የቅድሚያ አጀንዳው የሆኑት፣ እነዚሁ እስከ 40 ዓመትና ከዚያም በላይ ለሆነ ጊዜ አገራቸውን አገራችን ብለው ለመጥራት የተቸገሩት ኢትዮጵያውያን ሆነዋል፡፡ ሁለተኛው አስገራሚው እንቆቅልሽ ደግሞ ሕወሓት ለመፈጠሩና ወደ ሥልጣን ይመጣ ዘንድ ትልቁን ድርሻ ያበረከተለትን በኤርትራ ሥልጣንን ከተቆጣጠረው ሕግሃኤ ጋር ከተደረገው ዘግናኝ (barbaric) ጦርነት በኋላ፣ መቼም እንደማይታረቁ ሆነው ተለያይተው የነበሩት ኢትዮጵያና ኤርትራን የታረቁበት የለውጥ ዕርምጃ ነው፡፡

  በበኩሌ ሕወሓትን ያላካተተው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሥልጣንን ከተቆናጠጠ ገና አንደኛ ዓመቱን ሊያከብር በዝግጅት ላይ ይገኛል ብዬ ነው የማስበው (ሕወሓት ለ27 ዓመታት ሥልጣን ላይ የነበረው፣ አጋር ብሎ ከሚጠራቸው ፓርቲዎች ያልተሻለ ብቃትና ሥልጣን ከነበራቸው ብአዴንና ኦሕዴድ ጋር መሆኑን ታሳቢ በማድረግ)፡፡ እናም ከዚህ በኋላ ኢሕአዴግ በምልበት ወቅት ከዶ/ር ዓብይ አህመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ ያለውንና ሕወሓት የሌለበትን ገዥውን ፓርቲ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

  ከላይ የጠቀስናቸው ሁለት ዓበይት ጉዳዮች ባለፉት ጥቂት የለውጥ ወራት ከተከናወኑት በርካታ ኹነቶች መካከል ሲሆኑ፣ የፖለቲካ እስረኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት፣ በመላው ዓለም ለሚገኙ ሁሉንም ዓይነት ተቃዋሚ ኃይሎች የተደረገው የሰላም ጥሪ፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ አንድም ጋዜጠኛ በእስር ቤት የሌለባት አገር መሆኗ (በነገራችን ላይ የሪፖርተር ጋዜጣ ቀዳሚ ገጽ ላይ የሚገኘው የ‹‹ፕሬስ ነፃነትን ከስቅላት ያድኑ›› ጥሪ የሚያበቃው መቼ ነው?) እና ሌሎችም የምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ ውሳኔዎች ተወስነውና በተግባር ላይ ውለውም ለመመልከት በቅተናል፡፡ ፍትሕ፣ ልማትና ዴሞክራሲን ለማስፈን የሥልጣን ዘመኑን ሀ ብሎ የጀመረው የሕወሓት መንግሥት ለ27 ዓመታት አጋር ይሆኑኛል ካላቸውና በአምሳሉ ከቀረፃቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ቢያደርግም፣ መጨረሻው ግን ፈጽሞ እንዳላመረ ግልጽ ሆኗል፡፡ ለ15 ዓመታት ያህል በሁለት ዲጂት አድጓል የተባለው ኢኮኖሚም አገሪቷን ከዓለም የደሃ ደሃ አገሮች መካከል ሊያላቅቃት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰትም ከዓለማችን ፈላጭ ቆራጭ መንግሥታት ጋር ስሟ ከዓመት ዓመት የሚብጠለጠል ሆናለች፡፡ የዴሞክራሲ ተስፋችን እየጨለመ መምጣቱን ማስተባበል ያልቻሉት መሪዎቻችን ዴሞክራሲና ልማትን የሚያገናኛቸው ጉዳይ እንደሌለ በማስረዳት፣ አርፈን ‘ልማታችንን’ እንድናጣጥም በግልጽ ሊነግሩን ሞክረውም ነበር፡፡

  ባለፉት 11 ወራት እነዚህንና ሌሎች በርካታ የዴሞክራሲና የልማት በጎ ጅምሮችን ማጣጣም በመቻላችን ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ደስታውን መሸሸግ ባልቻለበትና ደስታውንም ገልጾ ባልጨረሰበት ወቅት፣ በቅፅበት ተንሸራተን የእርስ በርስ መፋተግ ውስጥ ልንገባ የቻልንበትን ምክንያት ማወቁ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታችንም ይሆናል፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ‘በሽታው ታወቀ ማለት የፈውሱ ግማሽ ተገኝቷል’ ማለት ነውና፡፡ ሁለቱም መንገዶች ፈጽሞ ልንሰማቸው የሚከብዱን አማራጮች ቢሆኑም ቅሉ፣ ዛሬ ላይ ያለው ወቅታዊው ሁኔታ የሚያሳየን ኢትዮጵያ ዳግም ወደ አምባገነንና የአንድ ዘር የበላይነት ወደ ነገሠበት ሥርዓት ከምትመለስ ተበታትና እንደ አገር የመቀጠሏ ጉዳይ ቢያበቃላት የሚቀል መሆኑን ነው፡፡  ዛሬ ላይ የታየውን ይኼንን ለውጥ በግልጽ የሚቃወሙት ወገኖችም በትክክል የትኛውን አማራጭ እንደሚፈልጉት ለመናገር አቅም ቢያንሳቸውም፣ ሌላ ሦስተኛ አማራጭ ያለ መኖሩን እውነታ ግን ሊያስተባብሉት የሚቻላቸው አይሆንም፡፡ ሁላችንንም እንደሚያስማማን ኢትዮጵያ ዳግም ወደኋላ ልትመለስበት የማትችለውን የለውጥ ጉዞ ጀምራለች፡፡ ይህ ጉዞ አገሪቱን ወዴት ያደርሳታል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በዋነኛነት ለውጡን በኃላፊነት እየመራ የሚገኘውን ቲም ለማንና በዙሪያው የተሰበሰቡ አማካሪዎቹን የሚመለከት ቢሆንም፣ ሌሎች በተለያየ ጠርዝ ላይ የምንገኝ ዜጎችም የሚኖረን ድርሻ ቀላል እንዳልሆነ ይገባኛል፡፡ በዚህም መሠረት ሰሞኑን ከተሰሙት የዛቻና የፉከራ መግለጫዎች ባሻገር ሕወሓት ይኼንን ለአገራችን የመጣውን ሦስተኛም አልነው አራተኛ፣ ወይም አምስተኛ የለውጥ ዕድል ለማደናቀፍ ከፍተኛውን ድርሻ ሊያበረክት ይችላል ያልኩበትን ምክንያቶች በማቅረብ እንዴት እንቅፋቱን ልናስወግደው እንደሚሻል የግል ምልከታዬን አሰፍራለሁ፡፡

  የትግራይ ልሂቃን ፈተና

  ብዙዎቻችን ከምናስታውሳቸው የተረትና ምሳሌ ወጎች መካከል እናት ልጇ ከእንቁላል ጀምሮ ዶሮ፣ በግና የፍየል ሙክት ሰርቆ ሲያመጣላት ከየት ነው ያመጣኸው እንኳን ብላ ሳትጠይቅ፣ በመጨረሻ በሬ ሰርቆ መያዙን ስትሰማ እንዴት ልትቋቋመው ያልቻለቸው ሐዘን እንዳጋጠማት የሚተርከውንና የልጇንም ምላሽ በዚህ አጋጣሚ ማስታወሱ ለማለት የፈለግኩትን ጉዳይ በመጠኑ የሚገልጸው ይመስለኛል፡፡ ከላይ በተደጋጋሚ ላብራራው እንደሞከርኩት የዛሬው የለውጥ ዕርምጃ በዋነኛነት ከመንገድ ጠርጎ ያስወጣው፣ ላለፉት 27 ዓመታት ያለማንም ተቆጪ አገሪቱን በብቸኝነት ሲያነሳና ሲጥላት የነበረውን የሕወሓትን አገዛዝ ነው፡፡ ማንም እንደሚረዳው የትግራይን ሕዝብ ከጨቋኙ የ‘አማራ ገዥ መደብ’ ነፃ ለማውጣት የትጥቅ ትግል የጀመረው ቡድን እንዳሰበው ትግራይን ነፃ በማውጣት ብቻ ውጥኑ እንደማይሳካ ሲገባው፣ ሌሎች በአምሳሉ የቀረፃቸውን ቡድኖች በማደራጀትና ከኤርትራው የነፃ አውጪ ግንባርም ጋር በመተጋገዝ ራሱን በራሱ እየበላ ለመፈራረስ አንድ ሐሙስ ብቻ የቀረውን ወታደራዊ አገዛዝ ያስጨንቀው ጀመር፡፡ ዕድል ቀንቶት ኢትዮጵያ የምትባለውን ግዛት ከጫፍ እስከ ጫፍ ተቆጣጥሮ ሲያበቃ ሊሆኑ ይገባቸዋል ያላቸውን ዕርምጃዎች አንድ በአንድ ተግባራዊ ለማድረግ ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ በበርካታ አገሮች በተግባር ላይ ሊውል አይደለም እንደ ሕገወጥነት የሚታውን በዘርና በቋንቋ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካና የፌዴራሊዝም ሥርዓት እነሆ በማለት ሲያበረክትልን፣ ይመጥናችኋል ያለውን ሕገ መንግሥትም ለማፀደቅና ኢትዮጵያን በተሳሳተ ሐዲድ ላይ አስቀምጦ ለመምራት የፈጀበት አጠቃላይ ጊዜ ቢቆጠር ሦስት ዓመት እንኳን አልሞላም፡፡ በወቅቱ አገሪቱ ለዘመናት የገነባቻቸው የሲቪልና የወታደራዊ ተቋማት ከመፈራረሳቸውም በላይ፣ እንደ የኢትዮጵያ ባህር ኃይልን የመሳሰሉ ከፍተኛ የሰውና የቁሳቁስ ሀብት የነበራቸውም ዳግም እንዳያንሰራሩ ተደርገው ግብዓተ መሬታቸው ተፈጸመ፡፡ ጥቂት ሰነባብቶም በመጠኑም ቢሆን ሕወሓትን ሊገዳደረው የሚችለውን የኦሮሞ ነፃነት ግንባርን ከጨዋታ ውጪ በማድረግ አገሪቷን ሙሉ በሙሉ ያለ ማንም ከልካይ ሊቆጣጠራትና ያሻውን ሲሾምባትና ሲሽርባት፣ ገፍቶ የሚመጣም ጠያቂ ሲኖር በማስፈራራት ለጥቆም በማሰርና ከፍ ካለም በማስወገድ የሥልጣን ዘመኑን ይገፋበት ጀመር፡፡

  በእነዚህ አስቸጋሪ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናት ከፍተኛውን የኢኮኖሚና የፖለቲካ አመራርና የማማከር ሥራውን ጠቅልለው የሚመሩት ኤርትራውያንና የሻዕቢያ ደጋፊዎች ሲሆኑ፣ የትግራይ ተወላጅ የሕወሓት አባላት ደግሞ የታዘዙትን በመፈጸምና በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኘውን የአስፈጻሚ መዋቅር በመምራት ተወስነው ነበር፡፡ ለጥቂት ዓመታት የዘለቀው ይኸው የአዛዥና ታዛዥ ግንኙነት የፈጠረው እልህና ቁጭት ለ1990 ዓ.ም. የኢትዮጵያና የኤርትራ አሳዛኝ ጦርነት መነሻ ምክንያት መሆኑ በግልጽ የታወቀ ነው፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ ሁለቱ አገሮች ወደ ጦርነት ሊገቡ የቻሉት ባድመ ለምትል ጠባብ መሬት ነው የሚል ምሁርም ሆነ መሐይም አላጋጠመኝም፡፡ ባይሆን የኢኮኖሚ ጥቅም ግጭቶችንና ሌሎች ማኅበራዊ ግንኙነቶች ናቸው የግጭቱ መንስዔዎች በማለት ለማለባበስ ሲሞከር በተደጋጋሚ ተሰምቷል፡፡ ችግሩንም በፍትሕ አደባባይ ይሁን በድርድር ለመፍታት ያስቸገረበት አንዱና ዋነኛው ምክንያት፣ ይኸው በግልጽ ለመነገር ድፍረት የታጣበት የጦርነት መነሻ ሰበብ ነበር፡፡ ሻዕቢያ ዕርቅ የሚፈጸመው በሕወሓት መቃብር ላይ ነው ቢልም፣ በአንፃሩም ሕወሓት ለሻዕቢያ ከዙፋን መውረድ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አቅሙ የቻለውን ሁሉ ቢሞክርም ያለ አሸናፊና ተሸናፊ ፍትጊያው ለ18 ዓመታት ቀጥሎ መቋጫውን አግኝቷል፣ ዓለምን ባስደነቀ መልኩ፡፡

  እንደሚታወቀው ባለፉት 20 ዓመታት የሻዕቢያ ደጋፊዎችና አባላት የተውትን የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነት ጠቅለው የተረከቡት የትግራይ ልሂቃን ናቸው፡፡ ከራሷም ተርፎ ለማንም ሊበቃ የሚችለው የአገሪቱ አጠቃላይ የኢኮኖሚ መዋቅር፡፡ የአንድ ፓርቲ ድርጅቶችና ለሕወሓት ፍፁም ታማኝነታቸውን ለሚገልጹ በተለይ ከአንድ ክልል ለሚመጡ ተወላጆች በትልቅ መሶብ ቀርቦ፣ ሌሎች በሁለተኛ ደረጃ የተመደቡ ኢትዮጵያውያን ግን ከሞሰቡ በሚንጠባጠበው ፍርፋሪ ላይ እንዲራኮቱ ባልተጻፈ መመርያ ተፈረደባቸው፡፡ ቀሪው አቅመቢስ የብዙኃን ስብስብ ግን አይደለም ወደ መሶቡ ወደ ፍርፋሪውም እንዳይጠጋ በሽቦ አጥርና በቀይ መስመር ተከልሎ የበይ ተመልካች እንዲሆን ተፈርዶበት እንደነበር የትናንት ትዝታችን ነው፡፡ እሱም አልበቃ ብሎ በሽሚያው ከፍ ያለ ጉርሻን ያነሱ ከተገኙም ከሞሰቡ ላይ ለሚጎርሱት ልሂቃን ወይም እነሱ ላዘዙለት የጥቅም ተጋሪያቸው ማጉረስ ይጠበቅባቸው ነበር፣ ‹‹ሙስና›› የሚል የሚያምር የዳቦ ስም ወጥቶለት፡፡ በመከላከያው፣ በፖሊስ ኃይሉ፣ በደኅንነት ክፍሉና በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሚገኙትን የውሳኔ ሰጪነት ሥልጣኖች ለእነዚሁ ጥቂት የትግራይ ልሂቃን ብቻ ተከፋፍለው በመሰጠታቸው ሌላው ፍርፋሪ ለቃሚ ሁሉ አርፎ የታዘዘውን በመፈጸም የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ተፈርዶበታል፡፡ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ይኼ የአንድ ቡድን የበላይነት እንደማያዋጣና መዘዙም የከፋ እንደሚሆን የተነገራቸው፣ ዛሬ በአንድ አካባቢ መሽገው የሚገኙት አብዛኛዎቹ የሕወሓት አመራሮች የሚሰጡት ‘ምን እናድርግ ለቦታው የሚሆን ብቁ ሰው አጣን’ ዓይነት የፌዝ ምላሽ ነበር፡፡

  ኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫ ከድጡ ወደማጡ እየዘቀጠች በምትገኝባቸው የሕወሓት የመጨረሻ ጊዜያት ሳይቀር መሪዎቻችን ‘አይዞአችሁ ይኼ የምታዩት ቀውስ ሁሉ የመጣው በተፈጠረው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ምክንያት ነው’ በማለት ሊያሞኙን ሞክረዋል፡፡ አቅመቢስ የነበረው የኔብጤ የብዙኃን ስብስብም (The silent majority) ፅዋው ሲሞላ (በደሉ ከልክ በላይ ሲሆን) ይሞከር የማይመስለውን ተራራ ለማነቃነቅ ችሎ ዛሬ ለመጣው ለውጥ ትልቁን ድርሻ አበርክቷል፡፡ ለውጡ ዛሬ ላይ እንደምናየው ሰላማዊና በከፍተኛ ጥንቃቄ የተደረገ ባይሆን ኖሮ፣ ትልቁ በትር ሊያርፍ የሚችለው መሶቡን ከበው ሲቦጠቡጡ በከረሙት ከፍተኛ አመራሮችና ዙሪያውን ከበው ፍርፋሪ ሲለቅሙ በነበሩት አነስተኛ ከበርቴዎች ላይ ይሆን ነበር፡፡ በአንፃሩም ይኼው ጥቅሙን የሚያጣ ቡድን የሞት ሞቱን በሚወስደው ዕርምጃ ሊፈጠር ይችል የነበረውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመገንዘብ በዙሪያችን የሚገኙ የፈራረሱ አገሮችን መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡ የዶ/ር ዓብይ ትልቁ ሥራ የታየውና  ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሳይፈልግ በግድ ለዶ/ር ዓብይ ትልቁን አክብሮት እንዲቸራቸው ያበቃው ጉዳይ፣ በቀላሉ ሊቀጣጠል የነበረውንና ያስቀሩትን የጥፋት መንገድ በአግባቡ ለመረዳት በመቻሉ ነው፡፡

  ይኼንኑ ገደብ የሌለውን ትዕግሥት ያልተረዳው ወይም እንደ አቅመ ቢስነት የተመለከተው፣ ራሱንም እንደተሸናፊ የቆጠረው ቡድን (በእውነቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አሸናፊ ነው ሊባልበት የሚገባ ለውጥ ነበር) ሊያጠፋ በሚችልበት አቅሙ ሁሉ አገሪቱን ለመከፋፈል ሲታትር ከርሞ በጠበቀው ፍጥነት አልሳካ ሲለው፣ አሁን ግልጽ ያላደረገውን ዕርምጃ እንደሚወስድ በመዛት መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡ ወደ አንድ ዓመት ገደማ በዘለቀው የለውጥ ሒደት እስካሁን እንደታየው ካሉት ዘጠኝ ክልሎችና ሁለት የከተማ መስተዳድር መዋቅሮች መካከል ለውጡን በጥብቅ የማውገዝና የመቃወም ድምፅ የሚሰማውም ከዚሁ ሕወሓት ከሚመራው ክልል ብቻ በመሆኑ፣ አያድርገውና ችግር ቢፈጠር ማን በማን ላይ እንደሚነሳ ለመገመት የፖለቲካ ጠቢብ መሆን አያስፈልግም፡፡ 

  እንግዲህ የትግራይ ልሂቃን ትልቁ ፈተና የተጋረጠው እዚህ ላይ ነው፡፡ ምንም እንኳን ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት እንዳሻው ሲሰጥና ሲነሳ የቆየው የጥቅም ሸሪካቸው ሕወሓት ጥቅሙ እንደተነካበት ግልጽ ቢሆንም፣ የትኛውም ስህተት ሊታረም የሚገባበት ጊዜ መምጣቱ አይቀሬ ነውና (በሌላ አነጋገርም ያበጠ ጎማ ሁሉ መተንፈሱ አይቀርምና) ይኼው ዛሬ የመጣውን አጠቃላይ ለውጥ በፀጋ ሊቀበለው እንደሚገባ በሚግባቡበት ቋንቋ ሊነግሩት የሚችሉት እነሱ ብቻ ናቸው፡፡ ገና የለውጡ አቅጣጫ እንኳን ሳይታወቅ ሥልጣኑን ያጣ የመሰለው ይኼ ቡድን ዛሬም ለኢትዮጵያ የወደፊት ዕርምጃ የሚያበረክተው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ደግሞም ከወደቁ በኋላ መንፈራገጥ እንደማያዋጣ በማስረዳት አቋሙን ለዘብ አድርጎ የለውጡን ጎዳና እንዲቀላቀል፣ ካልሆነም በጨዋ ተቃዋሚነት ሰላማዊ ትግሉን ቢቀጥል የተሻለ እንደሚሆንለት ከእነርሱ ሌላ ማን መካሪ ሊመጣለት ይችላል?

  ከዚህ ውጪ ግን የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማደናቀፍ መሞከር የሚያስከትለው ጥፋት እጅግ ከፍተኛ መሆኑን በማስገንዘብ፣ ከታሪክም አንፃር ከፍተኛ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ብቻም ሳይሆን ያለፉትን 44 ዓመታት ድካምና ልፋት (ልማትም ሊሆን ይችላል) በዜሮ የሚያባዛ በመሆኑ ከአሁኑ እንዲታረም እነዚሁ የትግራይ ልሂቃን ትልቁን ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡ ዛሬ አገር በምጥ ጣር ላይ የምትገኝበት ወቅት ነው፡፡ አሁን አገራችንን እንዴት እናድን በሚለው ጥያቄ ላይ መምከር እንጂ፣ ነገ በድንገት ጥለነው የምንሄደውን ቁሳዊ ጥቅምን ታሳቢ ያደረገ እሰጥ አገባ የሞኝ ለቅሶ ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ የጥፋት መንገድም መቀጠል ጥቂት የማይባሉ የዋህ ተከታዮችን ለከፍተኛ ኪሳራ የሚዳርግ በመሆኑ ሊቀጣጠል በጀመረው እሳት ላይ ቤንዚን ከማርከፍከፍ መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ለማደናቀፍ መሞከር በእሳት የመጫወትን ያህል አደገኛ ነው፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው sol.tamerat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ

  ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ...

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...