Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ኪንና ባህልሕፃናት እንዲያነቡ

  ሕፃናት እንዲያነቡ

  ቀን:

  በሔለን ተስፋዬና በተመስገን ተጋፋው

  ኢትዮጵያ ሪድስ ሚያዝያ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ዓመታዊ የሕፃናት ንባብ ጉባዔን በሳፍየር አዲስ ሆቴል አካሂዷል፡፡ በጉባዔው ላይ አራት ዋና ዋና ሐሳቦች የተነሱ ሲሆን እነዚህም የማንበብ ባህልን ማሳደግ፣ ሙያዊ ትምህርት ለቤተ መጻሕፍት ዕድገት፣ አገራዊ መጽሐፎችን ውጤታማነታቸውና ፈተናዎቻቸው፣ የኢትዮጵያን የንባብ ባህል ለማስተዋወቅ ጥረቶችና ፈተናዎቻቸው በሚል ለታዳሚዎች ቀርቧል፡፡

  ከቀረቡት ጽሑፎች መካከል ምዕራባውያን ልጆቻቸውን የማንበብ ክህሎታቸው በምን መልኩ እንደሚያስተምሩአቸው ደራሲ ጄን ካርትስ ያላትን ተሞክሮ ለተሳታፊ አስረድታለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሚስስ ከሮል ሴትጋስትና አቶ ይታገሱ ጌትነት በጥምረት ለተሳታፊዎች በድርጅቱ የተሠሩትን ሥራዎች አቅርበዋል፡፡

  የኢትዮጵያ ሪድስ ሕፃናትን ከትምህርት መጻሕፍት ውጭ ያሉ መጽሐፎች እንዲያነቡ ለማድረግ ዕውቀትን የመፈለግ ጥበብ ሥራ እየተሠራ መሆኑን በመድረኩ ተነስቷል፡፡ የድርጅቱ ዳይሬክተር ወ/ሪት የምሥራች ወርቁ፣ የሕፃናት የንባብ ባህልን ለማሳደግ ከ70 በላይ ለሚሆኑ በሁሉም አካባቢ በሚገኙ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ቤተ መጻሕፍት መገንባታቸው ገልጸው፣ ቤተ መጻሕፍት ብቻ መክፈት በቂ ስላልሆነ ለቤተ መጻሕፍት ባለሙያዎች፣ ለመምህራን፣ ለትምህርት ቤቶች ኃላፊዎች ሥልጠና መስጠቱንም ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በ100 ሺሕ የሚቆጠሩ በ22 ርዕሰ ጉዳዮች በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ መጽሐፎች ለ300 ትምህርት ቤቶች ማከፋፈላቸውን ተናግረዋል፡፡

  ኢትዮጵያ ሪድስ እስካሁን ጥሩ የሚባል ሥራ የሠራ ቢሆንም በአገሪቱ በሚገኙ ሕፃናት ላይ ለመሥራት ድርጅቱ ብቻ በቂ ስላልሆነ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ማለትም ከትምህርት ሚኒስቴርና ከሚመለከተው ሁሉ ጋር ለመሥራት የተዘጋጀ መድረክ እንደሆነ ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡

  የኢትዮጵያ ሪድስ የቀድሞ ባልደረባ አቶ ይታገሱ ጌትነት የንባብ ጉባዔ በአብዛኛው ሲካሄድ የነበረው ለአዋቂዎች ያመዘነ እንደነበር አስታውሰው ለሕፃናት ዕውቀትን የመፈለግ ጥበብ የማሳወቅ ጉባዔ መካሄዱ ጥሩ ጅማሬ መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

  የትምህርት ሥርዓቱ እስካሁን እየሄደ ያለው መንገድ ፊደልን አውቆ ማንበብ፣ መጻፍን የሚችል መፍጠር እንጂ ዕውቀት የመፈለግ ጥበብ ላይ ትኩረት እየሰጠ አለመሆኑ አቶ ጌትነት ተናግረዋል፡፡

  ‹‹ፊደልን ማሳወቅ ልጆች ሲፈልጉ ያነባሉ ሳይፈልጉ ይተዋሉ፤ ነገር ግን ዕውቀትን የመፈለጊያ ዘዴ ማስተማር ግን ሁልጊዜም መጽሐፍን ፈላጊዎች እንዲሆኑ ያደርጋል፤ የማንበብ ባህል ስንል የማወቅ ፍላጎት ማዳበር ማለት ነው፤›› ሲሉም አክለውበታል፡፡

  ከተሳታፊዎች መካከል ‹‹ቴዎድሮስ›› በሚባለው የሕፃናት መጽሐፍ የሚታወቀው አቶ ዳንኤል ወርቁ የተለያዩ የሕፃናት መጽሐፎችን የፃፈ ሲሆን አብዛኛው ትምህርት ቤቶች ላይ ለሕፃናት ከሚማሩበት መጽሐፎች ውጪ ሌሎች እንደ ተረት፣ ልብ ወለድ ዓይነት መጽሐፎች በቤተ መጻሕፍት እንደማይገኙ ገልጿል፡፡

  ይህንን ችግር በመፍታት መንግሥት፣ የግል ድርጅቶች፣ ማኅበረሰብ፣ ደራስያን ሁሉም በጋራ መሥራት መፍትሔ እንደሆነ አቶ ዳንኤል ተናግሯል፡፡

  ኢትዮጵያ ሪድስ እ.ኤ.አ. 2002 በኢትዮጵያ ውስጥ የተቋቋመ የውጭ አገር የበጎ አድራጎት ተቋም ሲሆን ራዕዩም ሁሉም ሕፃናት በአካልና በሥነ ልቦና የማደግ ዕድል እንዲኖራቸውና በትምህርታቸውም ጠንካራና በራስ የመተማመን ስሜት ኖሯቸው እንዲያድጉ ነው፡፡

  ከዚህም ባሻገር የንባብ ባህልን፣ ትምህርትን በማስፋፋትና በማሳደግ ወላጆች ልጆቻቸውን በትምህርታቸው በመደገፍ ብርቱ ሚና እንዲጫወቱ ያደርጋል፡፡ ለተማሪዎቹም ምቹና ደኅንነቱ የተጠበቀና የማንበብ ፍላጎትን የሚጨምር ሥፍራን በመፍጠር እንዲሁም ደረጃውን የጠበቀ የልጆች መጻሕፍትን ማሳተምን ዋነኛ ዓላማው አድርጎ ላለፉት አሥራ ስድስት ዓመት ሲሠራ ቆይቷል፡፡

  ዋናው መሥሪያ ቤቱም በአሜሪካ ሚኒአፓሊስ ሜኒሶታ ስቴት ሲሆን የተለያዩ የውጭ አገር በጎ ፈቃደኞች ድርጅቱን በገንዘብና በዕውቀት ይደግፉታል፡፡ በኢትዮጵያ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ትምህርትና ቤተ መጻሕፍት ተኮር ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ በዘጠኙ ክልሎች፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች በመሥራትም ላይ ይገኛል፡፡

  የ‹‹ኢትዮጵያ ታንብብ›› ሥራዎች

  ኢትዮጵያ ሪድስ [ኢትዮጵያ ታንብብ] ካከናወናቸውና እያከናወናቸው ካሉ ሥራዎች መካከል በዋነኛነት የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ ትምህርት ቤት ባልተከፈተባቸው ራቅ ያሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክፍሎች እንዲሁም በሱሉልታ ኤኮዳጋ በሚባል ቀበሌ ውስጥ የራሱን ትምህርት ቤት በመክፈት ችግረኛ ለሆኑ ቤተሰቦች ለልጆቻቸው የትምህርት አገልግሎት በመስጠት፣ የትምህርት ቤት ወጪያቸውን በመሸፈን፣ ለተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት በመስጠት፣ ለመምህራን ሙያዊና ሌሎች የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች በመስጠት እንዲሁም መምህራን የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ በማመቻቸትና የትምህርት ወጪያቸውን በመሸፈን፣ ሌሎች በተለያዩ ምክንያት ትምህርት ቤት መግባት ያልቻሉና በንባብ አገልግሎት ተደራሽነት ለሌላቸው አንዳንድ በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች ለሚገኙና ከአምስት ሺሕ ለሚበልጡ ሕፃናት በፈረስና በሰው ኃይል በመታገዝ በየመንደራቸው በመግባት መጻሕፍትን ይዞ የንባብ አገልግሎት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ በሐዋሳና በአዲስ አበባ ከተሞች የሕፃናትና የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት በመክፈት በአካባቢ ላሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የንባብ አገልግሎት በመስጠት እያገለገለ ሲሆን ድርጅቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በሁሉም ክልሎች ከ70 በላይ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ቤተ መጻሕፍትን በማቋቋም ከመንግሥትና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር አብሮ ይሠራል፡፡

  በዚህም እስካሁን ድረስ ከ130,000 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች፣ መምህራንና ሌሎች የትምህርት ቤት ማኅበረሰብ በተለያዩ ትምህርትና ንባብ ተኮር በሆኑ ፕሮግራሞች ድጋፍ አድርጓል፡፡

  ድርጅቱ በተለይም ሕፃናትን ገና ከጅምሩ በንባብ እየኮተኮቱ በማሳደግ ረገድ ብዙ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ የድርጅቱም አብዛኛው የፕሮጀክት ትኩረት ሕፃናት ላይ ያተኮረ ሲሆን ይህንንም ለማድረግ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ከ300,000 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ አገር መጻሕፍትን በተለያየ መንገድ ለሕፃናትና ለተማሪዎች ተደራሽ አድርጓል፡፡

  ከመጽሐፍ ኅትመት ጋርም ተያይዞ ድርጅቱ ከዚህ በፊት ያሳተማቸው መጽሐፍ እንደ ማሞ ቂሎ፣ ተክሌ፣ የሾላ ዛፍ፣ የፋፊ በግ፣ ዝሆን እና ዶሮ፣ የላሊበላዋ ንብ አርቢ የሚገኝበት ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜም “Ready Set – Go” በሚል መጠሪያ ስም 100,000 የሕፃናት መጻሕፍትን (Story Books) በእንግሊዝኛ፣ በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ሲዳሞኛና ዲዚኛ በ22 ርዕሶች በማዘጋጀትና በማሳተም በአዲስ አበባ፣ በሐዋሳ፣ በሲዳማ በባህር ዳር፣ በጎንደር፣ በደሴ፣ በድሬዳዋና በሐረሪ ክልሎች ለሚገኙ 300 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በተለይም በ1ኛ እስከ 4ኛ ላሉ ተማሪዎች በቤተ መጻሕፍት ውስጥ እንዲጠቀሙ በማሰብ በነፃ አሠራጭቷል፡፡ ወደፊትም የመጻሕፍትን ጠቀሜታ በሚገባ በማጥናትና በመገምገም የኅትመትና የሥርጭት ሥራውን እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

  ኢትዮጵያ ሪድስ በሕፃናት የንባብ ልማድ ዙሪያ ያተኮረ ጉባዔውን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቀጣይነት እንደ አንድ ፕሮግራም በመያዝ ለማስቀጠልም ማቀዱንም ይፋ አድርጓል፡፡

  በዚህም ፕሮግራም ከተለያዩ ተቋማት የሚወከሉ ኃላፊዎች፣ የፖሊሲ አውጪዎችና ተግባሪዎች፣ የትምህርት ዘርፍ የጥናት ባለሙያዎች፣ መምህራን ደራሲያን፣ አሳታሚዎች፣ እንዲሁም ትምህርትና ንባብን ለማሳደግ ከመንግሥት ጋር አብረው የሚሠሩ ድርጅቶች ይገኙበታል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የአገሪቱ ባንኮች ካፒታል 199.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ

  ከታክስ በኋላ 50 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ የአገሪቱ...

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...