Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊከሽንት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ ሊውል ነው

  ከሽንት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ ሊውል ነው

  ቀን:

  በሔለን ተስፋዬ

  ከሽንት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተሠርቶ ሥራ ላይ ሊውል መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ማይክሮቢስ ሴንተርና ሞኖኪውላር ባዮሎጂ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር አደይ ፈለቀ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

  ትምህርት ክፍሉ ከሽንት ማዳበሪያ ለመሥራት ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ ሲያጠና መቆየቱን የገለጹት ዶ/ር አደይ፣ ከዚህ ቀደም ዓርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሠራ ቢሆንም በስፋት መሬት ላይ አልዋለም ብለዋል፡፡

  ሽንት ለምን ተመረጠ የሚለው ሲታይም፣ ናይትሮጅንና ፎስፈረስ ንጥረ ነገሮችን የሚያዝ በመሆኑ፣ ለአትክልት ወይም ለእርሻ እንደ ግብዓትነት ጥቅም ላይ የሚውለው ማዳበሪያ ከናይትሮጅን፣ ከፎስፈረስና ከፓታሽየም የተዘጋጁ በመሆናቸው፣ እነዚህ ንጥረ ነገሮች ደግሞ የሰው ልጅና የከብት ሽንት ውስጥ በብዛት ስለሚገኙና የሰውን ልጅ ሽንት በቀላሉ ማጠራቀም ስለሚቻል በምርምሩ ለማዳበሪያው ግብዓትነት ሊውል እንደቻለ ተናግረዋል፡፡  

  ለምርምር ግብዓትነት የሚውለው ሽንት ፒያሳና መስቀል አደባባይ አካባቢ ወጣቶች ተደራጅተው የመፀዳጃ አገልግሎት ከሚሰጡባቸው ሥፍራዎች በክፍያ የሚሰበሰብ መሆኑን፣ የተሰበሰበውን ሽንት ከባክቴሪያ ለማፅዳት ሽንቱን ለተወሰኑ ቀናት ማስቀመጥ ብቻ በቂ እንደሆነ አክለዋል፡፡

  ዶ/ር አደይ እንደገለጹት፣ ማዳበሪያው ለጊዜው ከሦስት ሔክታር በታች መሬት ላላቸው አርሶ አደሮች እንደታሰበ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያው ጥራቱን ጠብቆ ከተሠራ ለሁሉም የግብርና ምርት እንደሚውልና የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ፖሊሲ መሠረት ለአንድ ወር የሚቀመጥ ሽንት ከሆነ በስለው እስከ ስድስት ወር ከተቀመጠ በጥሬ ለሚበሉ ምግቦች መዋል ይችላል፡፡ ይኼ ግኝት ሥራ ላይ ሲውል ከውጭ የሚገባው ማዳበሪያ የሚያስከትለውን የአፈር አሲዳማነት ሊቀንስ ይችላል፡፡

  ይህ ፕሮጀክት ሲቀረጽ የማይክሮባዮሎጂ፣ የሲቪል ኢንጂነሪንግ፣ የመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል፣ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል፡፡ የምርምር ውጤቱን በመጀመርያ አዲስ አበባ ዙሪያ ላሉ አትክልት አምራቾች የሚሠራጭ ሲሆን፣  ከሥርጭት በፊት የአመለካከትና የዝግጅቱን ሒደት አስመልክቶ ለአርሶ አደሩ አብሮ በመሥራት ለውጡን እንዲረዱት ይደረጋል፡፡

  አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከምታወጣባቸው ግዥዎች መካከል ማዳበሪያ አንዱ መሆኑን ዶ/ር አደይ ገልጸው፣ አሁን የተሠራው የተፈጥሮ ማዳበሪያው ሙሉ ለሙሉ የውጭ ምንዛሪ እንዳይወጣ ባያደርግም፣ እጥረት ሲያጋጥምና በሰዓቱ ሳይደርስ ሲቀር የሚኖረውን ክፍተት ይሞላል ብለዋል፡፡

  በጥናት የተረጋገጡ የተፈጥሮ ማዳበሪያዎች ለምሳሌ የሰው ልጅ ሰገራም ለማዳበሪያ ግብዓትነት ቢውልም፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ከባህል አንፃር ይኼንን መተግበር ከባድ እንደሆነና ሰገራ ውስጥ የሚገኙትን የተለያዩ ባክቴሪያዎች ለማስወገድ እንደ ሽንት ቀላል እንዳልሆነ አብራርተዋል፡፡

  ማሊ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ በጥናት ደረጃና በትናንሽ ሠርቶ ማሳያ በተወሰነ መልኩ ከሰገራ የተዘጋጀ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ይጠቀማሉ፡፡

  ከሰው ሽንት የተፈጥሮ ማዳበሪያ መሥራት ስዊድንና ቻይና ከጥንት ጀምሮ ሲገለገሉት የነበረ ባህላቸው መሆኑንና ናይትሶይል (Nightsoil) በመባል እንደሚታወቅ ረዳት ፕሮፌሰሯ ገልጸዋል፡፡

  አጠቃቀሙም በቀጥታ ከአፈር ጋር በመቀላቀል እንደነበር ገልጸው፣ ይኼንን ወደ ዘመናዊ መንገድ በመቀየርና ፖሊሲ በማውጣት ለጤና በማይጎዳ መልኩ እንደሚጠቀሙም አክለዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...